የጥድፊያ ስሜታችሁን አታጥፉ!
1 ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረው ቆይታ አባቱ የሰጠውን ሥራ ለመፈጸም ያለው ጊዜ አጭር መሆኑን ያውቅ ነበር። (ዮሐ. 9:4) ከዚህም የተነሳ አገልግሎቱን በጥድፊያ ስሜት ከማከናወኑም ባሻገር ደቀ መዛሙርቱንም እንዲሁ እንዲያደርጉ አሰልጥኗቸዋል። (ሉቃስ 4:42–44፤ 8:1፤ 10:2-4) ቅድሚያ የሚሰጠው ለራሱ ምቾትና ድሎት አልነበረም። (ማቴ. 8:20) በመሆኑም ይሖዋ እንዲሠራ የሰጠውን ሥራ በብቃት ሊፈጽም ችሏል።—ዮሐ. 17:4
2 ጊዜው አጭር ነው፦ ምሥራቹን “በዓለም ሁሉ” ለመስበክም የቀረው ጊዜ አጭር ነው። (ማቴ. 24:14) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ወደ መጨረሻው ዘመን በጣም ጠልቀን እንደገባን ያሳያሉ። በቅርቡ ‘እግዚአብሔርን የማያውቁትና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙት በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።’ (2 ተሰ. 1:6-9) ይህ የጥፋት ቀን በድንገት ከተፍ ይላል። (ሉቃስ 21:34, 35፤ 1 ተሰ. 5:2, 3) ስለሆነም ሰዎች ካሉበት አደገኛ ሁኔታ መንቃት ይኖርባቸዋል። ጊዜው ሳያልፍ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት እንዲጥሩ መርዳት ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ነው።—ሶፎ. 2:2, 3
3 የተቻለንን ሁሉ እናድርግ፦ የአምላክ አገልጋዮች “ዘመኑ አጭር” መሆኑን ስለተገነዘቡ ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ ይሰጣሉ። (1 ቆሮ. 7:29-31፤ ማቴ. 6:33) አንዳንዶች በስብከቱ ሥራ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ከፍ ለማድረግ ሲሉ ኑሮን ለማደላደል መሯሯጥን ወይም ገንዘብ የሚያስገኙ አጋጣሚዎችን በፈቃደኝነት ትተዋል። (ማር. 10:29, 30) ሌሎች ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር በመጽናት ‘በጌታ ሥራ ዘወትር ትጉ’ ሆነው ቀጥለዋል። (1 ቆሮ. 15:58) ብዙዎች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ምሥራቹን ሰብከዋል። (ዕብ. 10:23) የመንግሥቱን ዓላማ ለማራመድ ሲባል የሚደረጉትን እነዚህን መሰል መሥዋዕቶች ይሖዋ አቅልሎ እንደማይመለከታቸው ግልጽ ነው።—ዕብ. 6:10
4 ሕይወታችን የስብከቱን ሥራ ጨምሮ በይሖዋ አምልኮ ዙሪያ እንዲያተኩር ማድረግ የይሖዋን ቀን አቅርበን እንድንመለከት ይረዳናል። ይህም የሰይጣን ዓለም በሚያቀርባቸው ነገሮች እንዳንታለል የሚጠብቀን ከመሆኑም በላይ በቅድስና ለመመላለስ በወሰድነው አቋም እንድንጸና ያስችለናል። (2 ጴጥ. 3:11-14) በእርግጥም አገልግሎታችንን በጥድፊያ ስሜት የምናከናውን ከሆነ የራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን ሰዎች ሕይወት ከጥፋት እንታደጋለን።—1 ጢሞ. 4:16