ክፍል 5—የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ምን ያህል ትምህርት እንደምንሸፍን መወሰን
1 ኢየሱስ በሚያስተምርበት ወቅት የደቀ መዛሙርቱን አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት “መረዳት በሚችሉበት መጠን” ይነግራቸው ነበር። (ማር. 4:33፤ ዮሐ. 16:12) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉት የአምላክ ቃል አስተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያስጠኑ አንድን ትምህርት በምን ያህል ጊዜ መሸፈን እንደሚችሉ መገመት አለባቸው። እርግጥ የሚሸፈነው ትምህርት መጠን በአስጠኚውም ሆነ በጥናቱ ችሎታና ሁኔታ ላይ የተመካ ነው።
2 ጠንካራ እምነት ገንቡ፦ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በአንድ የጥናት ክፍለ ጊዜ በቀላሉ ሊረዱ የሚችሉትን ትምህርት ለሌሎች ጥናቶች በሁለት ወይም በሦስት ክፍለ ጊዜ ማስጠናት ሊኖርብን ይችላል። አሳሳቢው ነገር ተማሪው ትምህርቱን በግልጽ መረዳቱ እንጂ በፍጥነት መጨረሱ አይደለም። እያንዳንዱ ተማሪ ከአምላክ ቃል ያገኘው አዲስ እምነት በጠንካራ መሠረት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል።—ምሳሌ 4:7፤ ሮሜ 12:2
3 በየሳምንቱ ጥናት በምንመራበት ጊዜ ተማሪው ከአምላክ ቃል የተማረው እንዲገባውና እንዲቀበለው ለማድረግ የሚያስፈልገውን ያህል ጊዜ መመደብ ይኖርብናል። ስለሆነም ትምህርቱን በሩጫ በመሸፈን ተማሪው ከሚማራቸው እውነቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንዳይሆን ማድረግ የለብንም። በዋና ዋና ነጥቦቹ ላይ ለማተኮርና ለትምህርቱ መሠረት በሆኑት ቁልፍ ጥቅሶች ላይ ለመወያየት በቂ ጊዜ መድብ።—2 ጢሞ.3:16,17
4 ትኩረታችሁን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ነገሮችን አስወግዱ፦ ጥናቱን በጥድፊያ መምራት እንደሌለብን ሁሉ ትኩረታችንን የሚከፋፍሉ ነገሮች እንዲፈጠሩም አንፈልግም። ተማሪው ስለ ግል ጉዳዮቹ ሊነግረን የሚፈልገው ብዙ ነገር ካለ ጥናቱን ስናበቃ ለመወያየት ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል።—መክ. 3:1
5 በሌላ በኩል ደግሞ ለእውነት ያለን አድናቆት በጥናቱ ወቅት ብዙ እንድንናገር ሊፈትነን ይችላል። (መዝ. 145:6, 7) እርግጥ አንዳንድ ጊዜ በጥናቱ መሃል ተጨማሪ ሐሳብ ወይም ተሞክሮ መናገራችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እንደነዚህ ያሉት ሐሳቦች ረጅም ወይም የተንዛዙ ሆነው ተማሪው መሠረታዊ ስለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ትክክለኛ እውቀት ሳይቀስም እንዲቀር አንፈልግም።
6 በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንን እንደ አቅማቸው በማስጠናት ‘በእግዚአብሔር ብርሃን እንዲመላለሱ’ ልንረዳቸው እንችላለን።—ኢሳ. 2:5