የጥያቄ ሣጥን
◼ በሌሎች አገሮች ለሚገኙ ችግር ላይ ለወደቁ ወንድሞች የገንዘብ መዋጮ የምናደርግበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምን ሊሆን ይችላል?
አንዳንድ ጊዜ በሌሎች አገሮች ያሉ ወንድሞች በስደት፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ምክንያት ቁሳዊ እርዳታ እንዳስፈለጋቸው እንሰማለን። በእነዚህ ወቅቶች አንዳንድ ወንድሞች ችግሩ በተከሰተባቸው አገሮች ውስጥ ወዳሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎች የገንዘብ መዋጮ ለመላክ ይገፋፋሉ። የላኩት ገንዘብ አንድን ግለሰብ ወይም ጉባኤ ለመርዳት አሊያም ደግሞ አንድን የግንባታ ፕሮጀክት ለማገዝ እንዲውል ይጠይቁ ይሆናል።—2 ቆሮ. 8:1-4
ለእምነት ባልንጀሮቻችን እንዲህ ዓይነት ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየቱ የሚያስመሰግን ቢሆንም፣ ብዙውን ጊዜ መዋጮ አድራጊው ካሰበው ይበልጥ አፋጣኝ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ይኖራሉ። እንዲያውም እርዳታው የተላከላቸው ወገኖች ቀድሞውኑ ተረድተው ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው ዓለም አቀፉን ሥራ ለመደገፍ፣ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታዎችን ለማገዝ ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የተጎዱትን ለመርዳት ታስበው ወደ ቅርንጫፍ ቢሯችን የሚላኩት መዋጮዎች ለጋሹ ላሰበው ዓላማ እንደሚውሉ ልንተማመን እንችላለን።
ያልታሰበ ችግር ሲያጋጥም አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዲቻል በሁሉም ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወንድሞች በቂ ሥልጠና አግኝተዋል። ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ሁሉ ቅርንጫፍ ቢሮው ጉዳዩን ለአስተዳደር አካል ያሳውቃል። ምናልባት ተጨማሪ እርዳታ ካስፈለገ የአስተዳደር አካሉ በአቅራቢያው ያሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዲረዱ ይጠይቃል፤ ወይም በቀጥታ ከዋናው መሥሪያ ቤት የገንዘብ እርዳታ ይላካል።—2 ቆሮ. 8:14, 15
ስለዚህ ዓለም አቀፉን ሥራ ለመደገፍ፣ በሌሎች አገሮች የሚሠሩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማገዝ ወይም በአደጋዎች የተጎዱትን ለመርዳት ታስበው የሚላኩ መዋጮዎች በምንኖርበት አካባቢ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በቀጥታ ወይም በጉባኤያችን አማካኝነት መላክ ይኖርበታል። በዚህ መንገድ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በአስተዳደር አካሉ አማካኝነት ባዘጋጀው ድርጅታዊ መዋቅር መሠረት ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር የሚያጋጥመውን ችግር ሥርዓት ባለው ሁኔታ ይፈታል።—ማቴ. 24:45-47 የ1954 ትርጉም፤ 1 ቆሮ. 14:33, 40