ጨዋና ሰው አክባሪ በመሆን ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
1 ይሖዋ የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ ቢሆንም ፍጹማን ላልሆኑት የሰው ልጆች ደግነት፣ አሳቢነትና አክብሮት ያሳያቸዋል። (ዘፍ. 13:14፤ 19:18-21, 29) እነዚህን የመሳሰሉ ግሩም ባሕርያት ያሉትን አምላካችንን ምሳሌ በመኮረጅ ምሥራቹን የምንሰብክበትን መንገድ ይበልጥ ማሻሻል እንችላለን። (ቈላ. 4:6) ይህ ደግሞ በጨዋነትና በአክብሮት መንፈስ ከመናገር የበለጠ ነገር ይጠይቃል።
2 ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል:- ወደ ሰዎቹ ቤት የሄድነው አመቺ ባልሆነ ጊዜ ወይም በሥራ ከመወጠራቸው የተነሳ ሊያነጋግሩን በማይችሉበት ሰዓት ላይ ቢሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ችግራቸውን ተገንዝበንላቸው ንግግራችንን ለማሳጠር ወይም ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ለመያዝ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ሰዎቹ ጽሑፎቻችንን እስካልፈለጉ ድረስ ወስደው እንዲያነቡ ባለመጫን ደግነት እናሳያቸዋለን። በተጨማሪም ለሌሎች ያለን አሳቢነት ንብረቶቻቸውን በአግባቡ እንድንይዝ ግድ ይለናል። ለምሳሌ የውስጥም ሆነ የውጪ በሮችን በጥንቃቄ በመዝጋትና ልጆቻችንም እንዲህ እንዲያደርጉ ሥልጠና በመስጠት እንደምናስብላቸው እናሳያለን። ሰዎቹ ቤታቸው በማይኖሩበት ጊዜ የሚነበቡ ጽሑፎች ለመተው ስናስብ አላፊ አግዳሚ በሚያይበት ቦታ አስቀምጠን እንዳንሄድ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። በእርግጥም ጨዋና ሰው አክባሪ መሆን ሰዎች እኛን እንዲይዙን በምንፈልግበት መንገድ ሌሎችን እንድንይዝ ያነሳሳናል።—ሉቃስ 6:31
3 በመንገድ ላይ ስንመሠክር:- በመንገድ ላይ ስናገለግል ሰዎች የሚተላለፉበትን መንገድ ባለመዝጋት እንዲሁም ከንግድ ቤቶች ፊት ለፊት እጅብ ብለን ባለመቆም አክብሮት ማሳየት እንችላለን። ሌሎች ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ በማስተዋል ረገድ ፈጣን ልንሆን ይገባል። በጣም ቸኩለው የሚሄዱትን ከማስቆም ይልቅ ጥቂት ደቂቃ ሊሰጡን ከሚችሉ ሰዎች ጋር ብቻ ለመነጋገር ጥረት እናድርግ። አንዳንድ ጊዜ አካባቢው ውካታ የበዛበት ከመሆኑ የተነሳ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለመናገር እንገደድ ይሆናል። ሆኖም ይህን የምናደርገው በአክብሮትና የሌሎችን ትኩረት ወደ እኛ በማይስብ መንገድ መሆን ይኖርበታል።—ማቴ. 12:19
4 በስልክ ስንመሠክር:- በስልክ በምንመሠክርበት ጊዜ ጫጫታ በሌለበት ቦታ ሆነን በመደወል ለሰዎች አሳቢነት ማሳየት እንችላለን። ቶሎ ብለን ራሳችንን በማስተዋወቅና የደወልንበትን ምክንያት በመጥቀስ ጥሩ ምግባር እናሳያለን። የስልኩን መነጋገሪያ ወደ አፋችን አስጠግተን ደስ በሚል የድምፅ ቃና መናገራችን ከሌሎች ጋር ገንቢ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት እንድናደርግ ያስችለናል። (1 ቆሮ. 14:8, 9) በእነዚህ መንገዶች ለሰዎች ደግነት፣ አሳቢነትና አክብሮት በማሳየት የአምላካችንን የይሖዋን ግሩም ባሕርያት እንኮርጃለን።