ሰዎችን በማመስገን ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
1 ሰዎችን ከልብ በመነጨ ስሜት ማመስገን እንዲበረታቱ፣ ለተግባር እንዲነሳሱና ደስተኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ከብዙ አስፋፊዎች ተሞክሮ እንደታየው በአገልግሎት ላይ አጠር ያለ ልባዊ ምስጋና ማቅረብ አብዛኛውን ጊዜ ሰሚ ጆሮ ለማግኘት ይረዳል። እኛም ምሥራቹን ለሰዎች በምናካፍልበት ጊዜ ሰሚ ጆሮ ማግኘት እንፈልጋለን። ታዲያ ሰዎችን ማመስገን የምንችለው በምን መንገድ ነው?
2 አስተዋይ ሁን:- ክብር የተላበሰው ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሿ እስያ የነበሩት ሰባት ጉባኤዎች የሚያደርጓቸውን መልካም ተግባሮች ከሰማይ ሆኖ ይከታተል ነበር። (ራእይ 2:2, 3, 13, 19፤ 3:8) እኛም በአገልግሎታችን ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ያለን ልባዊ አሳቢነት እንድናመሰግናቸው የሚያደርጉንን አጋጣሚዎች እንድንፈላልግ ያነሳሳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ግቢው በደንብ እንደተያዘ ወይም የቤቱ ባለቤት ለልጆቹ ጥልቅ ፍቅር እንዳለው የሚያሳይ ነገር ተመልክተሃል? ወይም ደግሞ ግለሰቡ ሰላም ያለህ ፈገግታ በተሞላበት ሁኔታ ነው? እነዚህ ሁሉ ሰዎቹን ለማመስገን የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ናቸው። እነዚህን ነገሮች ለማስተዋል ፈጣን ነህ? አጋጣሚዎቹንስ ትጠቀምባቸዋለህ?
3 በጥሞና አዳምጥ:- ለሰዎች በምትሰብክበት ጊዜ ተገቢ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሐሳባቸውን እንዲናገሩ መንገድ ክፈትላቸው። የሚናገሩትን ነገር በጥሞና በማዳመጥ አክብሮት እንዳለህ አሳያቸው። (ሮሜ 12:10) በዚህ ወቅት ምስጋና እንድትቸራቸው የሚያነሳሳህ አንድ ሐሳብ ማግኘትህ አይቀርም። ከዚያም በተስማማችሁበት የጋራ ነጥብ ላይ ውይይት መጀመር ትችላለህ።
4 በማመዛዘን ችሎታህ ተጠቀም:- አንድ የቤት ባለቤት ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የማይስማማ ነገር ቢናገር ምን ማድረግ ይኖርብናል? ስህተቱን ለማረም ከመጣር ይልቅ ግለሰቡ ስሜቱን በመግለጹ አመስግነነው “ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደሰጡ ማስተዋል ችያለሁ” ልንለው እንችላለን። (ቈላ. 4:6) ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው ተከራካሪ ቢሆን እንኳ ለተነሳው ጉዳይ ይህን ያህል ከልቡ ተቆርቁሮ ሐሳቡን በመግለጹ ልናመሰግነው እንችላለን። እንደዚህ ያለው ለስለስ ያለ አቀራረብ የምሥራቹን በጣም ይቃወማል ብለን የምናስበውን ሰው እንኳ ሊያለዝበው ይችላል።—ምሳሌ 25:15
5 ምስጋናችን አበረታች እንዲሆን ከፈለግን ልባዊ መሆን ይኖርበታል። እንዲህ ዓይነቱን የሚያንጽ ንግግር መናገራችን ይሖዋን የሚያስከብር ከመሆኑም ሌላ ሰዎችም በመንግሥቱ መልእክት እንዲሳቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።