በዘመቻ የሚሰራጭ የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም
1 ሁሉም ሰው ለማለት ይቻላል የወፎችን ዝማሬ መስማትና ጀንበር ስትጠልቅ ማየት ያስደስተዋል። ይሁንና ብዙዎች እነዚህን ነገሮች የፈጠረው በሰማይ የሚኖር አፍቃሪ አባት መሆኑን አያምኑም። በመሆኑም የንቁ! መጽሔትን ልዩ እትም በማሰራጨት ይሖዋ ፈጣሪ ስለመሆኑ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ተከፍቶልናል። (ኢሳ. 40:28፤ 43:10) የመስከረም ንቁ! መጽሔት ሙሉ በሙሉ “በእርግጥ ፈጣሪ አለ?” በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው።
2 በክልላችን ውስጥ:- የምትችሉ ከሆነ፣ በሁሉም ቅዳሜዎች ከጉባኤያችሁ ጋር ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ለመካፈል ዝግጅት አድርጉ። እርግጥ ነው፣ በሌሎች ቀናትም ቢሆን ይህን ልዩ እትም ማበርከት ትችላላችሁ። ይህ መጽሔት በተለይ የአስተማሪዎችንና ከትምህርት ጋር ተያያዥነት ያለው ሙያ ያላቸውን ሰዎች ትኩረት መሳቡ አይቀርም። ስለሆነም በክልላችሁ ውስጥ የሚገኙ እነዚህን የመሰሉ ሰዎችን ለማነጋገር ልዩ ዝግጅት ልታደርጉ ትችላላችሁ።
3 አንድ ሰው ፍላጎት እንዳለው ካሳየ በሌላ ጊዜ መልስ የምትሰጡበት ጥያቄ ማንሳት ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል፣ ‘አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ ይህ ሁሉ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?’ ለማለት ትችሉ ይሆናል። ከዚያም በድጋሚ ስትሄዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ወይም ምዕራፍ 11 ላይ ያለውን ሐሳብ ማስተዋወቅ ይቻላል። ወይም ደግሞ ፈጣሪ ለምድር ካለው ዓላማ ጋር የተያያዘ ጥያቄ በመጠየቅ ተመልሳችሁ ስትሄዱ በምዕራፍ 3 ላይ ለመወያየት ትመርጡ ይሆናል።
4 በትምህርት ቤት:- ተማሪዎች ከሆናችሁ ይህን የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም ለአስተማሪዎቻችሁ ወይም አብረዋችሁ ለሚማሩ ልጆች ለምን በስጦታ መልክ አትሰጧቸውም? መጽሔቱን ዴስካችሁ ላይ ማስቀመጥ ብቻ እምነታችንን የሚመለከቱ ጥያቄዎች እንዲነሱ መንገድ ሊከፍት ይችላል። በክፍላችሁ ውስጥ እምነታችሁን ለሌሎች ማስረዳት የምትችሉባቸው አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ እንዲሁም ሪፖርት አዘጋጅታችሁ እንድታቀርቡ ስትጠየቁ በዚህ መጽሔት ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች ልትጠቀሙባቸው ትችላላችሁ። በዚህ ረገድ መጽሔቱ “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው አምድ ሥር እናንተን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ “በፍጥረት እንደማምን በደንብ ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ይዞ ይወጣል።
5 ይሖዋ ሁሉን በመፍጠሩ ክብርና ውዳሴ ይገባዋል። (ራእይ 4:11) የመስከረም ወር የንቁ! መጽሔትን ልዩ እትም በቅንዓት በማሰራጨት ፈጣሪያችንን ማክበርና ሌሎች ይህን እንዲያደርጉ መርዳት እንችላለን።