አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም
ይህ ዓለም አሁን ያለንበት ሁኔታ ለዘላለም ይቀጥላል ብለን እንድናምን ይፈልጋል። የአምላክ ቃል ግን ከዚህ የተለየ ሐሳብ ይነግረናል። (1 ዮሐ. 2:15-17) ከዚህም ባሻገር በምድር ላይ ሀብት ማከማቸት ከንቱ ልፋት መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። የ2007 የአገልግሎት ዓመት የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም “በሰማይ . . . ሀብት አከማቹ” የሚል ጭብጥ ያለው ሲሆን የአምላክ ሕዝቦች ያላቸውን አቋም ይበልጥ ያጠነክርላቸዋል።—ማቴ. 6:20
የመጀመሪያው ቀን:- በዚህ በችግር በተሞላ ዓለም ውስጥ የአምላክን መንግሥት ማስቀደም በእርግጥ ጠቃሚ ነው? የመጀመሪያው ተከታታይ ንግግር የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩብንም እንኳ እንዲህ እንድናደርግ ያበረታታናል። ቀጣዮቹ ሁለት ንግግሮች ደግሞ መንፈሳዊ ሀብት ያለውን ከፍተኛ ዋጋ የሚያጎሉ ከመሆናቸውም ሌላ አገልግሎታችንን ለመፈጸም በይሖዋ ላይ መታመናችን አስፈላጊ መሆኑን ያብራራሉ።
ሁለተኛው ቀን:- ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ቁሳዊ ሀብታችንን በምን መንገድ ልንጠቀምበት እንመርጣለን? ሁለተኛው ተከታታይ ንግግር እነዚህን ነገሮች በጥበብ ልንጠቀምባቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። የሕዝብ ንግግሩ አሁን ልንወስደው የሚገባንን እርምጃ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። የመደምደሚያ ንግግሮቹ ደግሞ ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ረገድ ማስተካከያ ማድረግ ይገባን እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ይረዱናል።
በመንፈሳዊ ገንቢ በሆነው በዚህ የሁለት ቀን ፕሮግራም ላይ ከተገኘን ‘በሰማይ ለራሳችን ሀብት እንድናከማች’ የሚያበረታታ ትምህርት እናገኛለን!