ከእኛ የተለየ ቋንቋ የሚናገር ሰው ሲያጋጥመን
1. ክልል ስንሠራ የትብብር መንፈስ ማሳየታችን ይበልጥ አስፈላጊ እየሆነ የመጣው ለምንድን ነው?
1 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች፣ ጉባኤያቸው ከሚመራበት የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችን የማግኘታቸው አጋጣሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ብዙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች እነዚህን ሰዎች በመንፈሳዊ ለመርዳት በተለያዩ ቋንቋዎች የሚመሩ ቡድኖችንና ጉባኤዎችን ማቋቋሙ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል። በአንድ አካባቢ ውስጥ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚመሩ በርካታ ጉባኤዎች በአንድ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ለማገልገል ይገደዱ ይሆናል። ታዲያ፣ የስብከቱን ሥራ ሥርዓት ባለው መንገድ ለማከናወን ጉባኤዎች ተባብረው ሊሠሩ የሚችሉት እንዴት ነው?—1 ቆሮ. 14:33
2. ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል በሌላ ቋንቋ ከሚመሩ ቡድኖች ወይም ጉባኤዎች ጋር ተባብረን መሥራት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ጥሩ የትብብር መንፈስ:- አንድ አስፋፊ በመንገድ ላይ ሲያገለግልም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሲመሠክር ከእሱ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ጨምሮ ማንኛውንም ግለሰብ የማነጋገር እንዲሁም ሰዎቹ በሚፈልጉት ቋንቋ ጽሑፎችን የማበርከት ነፃነት እንዳለው ሊሰማው ይገባል። ሆኖም አስፋፊው በሌላ ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች በሚሠሩበት ክልል ውስጥ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል የእሱ ጉባኤ የሚመራበትን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ያሉባቸው ቤቶች ላይ ብቻ ማተኮር ይኖርበታል። የተለያዩ ጉባኤዎች በአንድ አካባቢ የሚያገለግሉ ከሆነ ጥሩ የሆነ የመዝገብ አያያዝ እንዲኖር ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። የየጉባኤዎቹ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቾች እርስ በርስ መነጋገር እንዲሁም ሁሉንም ሊጠቅም በሚችል መንገድ ነገሮችን ማቀናጀት ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 11:14) ይሁንና አንድ አስፋፊ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ከእሱ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ቢያጋጥሙትና በዚያ ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ በአቅራቢያው ባይኖርስ? አስፋፊው ለእነዚህ ሰዎች ለመመሥከርም ሆነ ግለሰቦቹን ተከታትሎ ለመርዳት ጥረት ማድረግ ይገባዋል።
3. በሌላ ቋንቋ በሚመራ ቡድን ወይም ጉባኤ ውስጥ ያሉ አስፋፊዎች እኛ እየሠራነው ባለነው ክልል ውስጥ እያገለገሉ እንደሆነ ካስተዋልን ምን ዓይነት መንፈስ ማሳየት ይገባናል?
3 አንድ ዓይነት ሥራ:- ከተለያዩ ጉባኤዎች የመጡ አስፋፊዎች አንድን ክልል በተመሳሳይ ቀን የሚሸፍኑበት አጋጣሚ ቢፈጠር ምን ማድረግ ይገባል? እርግጥ ነው፣ የቋንቋ ልዩነት ክርስቲያናዊ ፍቅር ላለማሳየት እንቅፋት ሊሆን አይገባም፤ ሁሉንም አስፋፊዎች በዋነኝነት ሊያሳስባቸው የሚገባው በክልሉ ውስጥ ያሉ ሰዎች ፍላጎት ነው። (ዮሐ. 13:34, 35) በመሆኑም ኃላፊነት ያለባቸው ወንድሞች፣ አንደኛው ቡድን ለጊዜው ወደ ሌላ የአገልግሎት ክልል መሄድ ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ ምክንያታዊ የሆነና ፍቅር የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል።—ያዕ. 3:17, 18
4. በዛሬው ጊዜ ፍጻሜ እያገኘ ያለው የትኛው ትንቢት ነው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ምሥራቹን እንደሚሰሙ ትንቢት ተናግሯል። (ራእይ 14:6, 7) በሁሉም አስፋፊዎች መካከል ጥሩ የትብብር መንፈስ መኖሩ አንድ ቤት በተደጋጋሚ ጊዜ እንዳይንኳኳ ከማድረጉም በላይ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ግለሰቦችን ጨምሮ ብዙ አዳዲስ ሰዎች ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ መንገድ ይከፍታል።—ኤፌ. 4:16