ክርስቲያናዊ ሕይወት
የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩበት ክልል ውስጥ ተባብረን መስበክ የምንችለው እንዴት ነው?
ሰዎች የመንግሥቱ መልእክት በቋንቋቸው ሲሰበክላቸው ብዙውን ጊዜ ለመስማት ይበልጥ ፈቃደኞች ይሆናሉ። በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ የተገኙት “በምድር ዙሪያ ካለ አገር ሁሉ የመጡ ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን” እንደ ዕብራይስጥና ግሪክኛ ያሉ ቋንቋዎችን ቢችሉም፣ ምሥራቹን ‘በአገራቸው ቋንቋ’ እንዲሰሙ ይሖዋ ዝግጅት ያደረገው ለዚህ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 2:5, 8) በዛሬው ጊዜ፣ በተለያየ ቋንቋ በሚመሩ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ አስፋፊዎች በተመሳሳይ አካባቢ ያገለግሉ ይሆናል። እንዲህ ያሉት ጉባኤዎች እያንዳንዱ ሰው ምሥራቹን እንዲሰማ ለመርዳት ጥረት የሚያደርጉ ቢሆንም አንድን ቤት በተደጋጋሚ በማንኳኳት የቤቱን ባለቤቶች እንዳያስቆጡ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፤ ታዲያ እነዚህ ጉባኤዎች ተባብረው መሥራት የሚችሉት እንዴት ነው?
መመካከር (ምሳሌ 15:22)፦ የየጉባኤዎቹ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቾች፣ የጉባኤዎቻቸውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ምሥራቹን ተባብረው ለመስበክ የሚያስችላቸው ዘዴ ለማግኘት መመካከራቸው አስፈላጊ ነው። በሌሎች ቋንቋዎች የሚመሩት ጉባኤዎች ክልላቸው ሰፊ ካልሆነ በክልላችሁ ውስጥ ያሉ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ መኖሪያ ቤቶችን እያለፋችሁ እንድትሄዱ ሊፈልጉ ይችላሉ። አሊያም ደግሞ ክልላቸው በጣም ሰፊ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ መሸፈን ስለሚከብዳቸው የትኛውንም ቤት ሳታልፉ እንድትሰብኩ ይጠይቋችሁ ይሆናል፤ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ፍላጎት ያሳየ ሰው ካገኛችሁ ግን ልትጠቁሟቸው ትችላላችሁ። (od 93 አን. 37) በሌላ በኩል ደግሞ ጉባኤያቸው የሚመራበትን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን በመፈለግ ረገድ እንድታግዟቸውና ይህን ቋንቋ የሚናገር ሰው ካገኛችሁ አድራሻውን እንድትሰጧቸው ሊጠይቋችሁ ይችላሉ። (km 7/12 5 ሣጥን) አንዳንድ ጊዜ፣ በአንድ ቤት ውስጥ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ክልሎችን ለመሸፈን የሚደረጉት ዝግጅቶች፣ ከግለሰቦች የግል መረጃ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ሕጎችን የሚጥሱ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
መተባበር (ኤፌ 4:16)፦ የጉባኤያችሁ የአገልግሎት የበላይ ተመልካች የሚሰጣችሁን ማንኛውንም መመሪያ በጥብቅ ተከተሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠኑት ሰው ጉባኤያችሁ በሚመራበት ቋንቋ ሳይሆን በሌላ ቋንቋ መወያየት ይቀለው ይሆን? ግለሰቡን ለእሱ በሚቀለው ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ወይም ቡድን የሚገኙ አስፋፊዎች እንዲያስጠኑት ብታደርጉ እድገቱ ሊፋጠን ይችላል።
መዘጋጀት (ምሳሌ 15:28፤ 16:1)፦ በክልላችሁ ውስጥ ከቤት ወደ ቤት ስታገለግሉ ሌላ ቋንቋ የሚናገር ሰው ቢያጋጥማችሁ ምሥራቹን ለማካፈል የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ። በክልላችሁ የሚገኙ ሰዎች በሚናገሯቸው ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችንና ቪዲዮዎችን ስልካችሁ ላይ በማውረድ አስቀድማችሁ ዝግጅት ማድረግ ትችላላችሁ። በተጨማሪም በእነዚህ ቋንቋዎች ሰላምታ የሚሰጥበትን መንገድ ለማወቅ ጄ ደብልዩ ላንግዌጅ (JW Language) የተባለውን አፕሊኬሽን መጠቀም ትችላላችሁ።