የአንድን አስፋፊ የማያምን የትዳር ጓደኛ መርዳት ትችላላችሁ?
1. አንድ የማያምን የትዳር ጓደኛ እውነትን እንዲቀበል የመርዳት ፍላጎት ያላቸው አማኝ የሆኑት የትዳር አጋሮች ብቻ አይደሉም የምንለው ለምንድን ነው?
1 በጉባኤያችሁ ውስጥ የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው አስፋፊዎች አሉ? ከሆነ እነዚህ አስፋፊዎች የትዳር ጓደኛቸው እውነተኛውን አምልኮ ቢቀበል ደስ እንደሚላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና ደስ የሚላቸው እነሱ ብቻ አይደሉም። መላው ጉባኤ የአምላክ ዓይነት አመለካከት አለው፤ አምላክ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ይፈልጋል። (1 ጢሞ. 2:4) ታዲያ በጉባኤያችን ውስጥ ያለን አስፋፊ የማያምን የትዳር ጓደኛ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
2. አንድ የማያምን የትዳር ጓደኛ ምን ስሜት እንዳለው መገንዘባችን እሱን ለመርዳት የሚያስችለን እንዴት ነው?
2 በመጀመሪያ ደረጃ የማያምነውን ግለሰብ ስሜት ለመረዳት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ብዙ የማያምኑ የትዳር ጓደኞች ቤተሰባቸውን የሚወዱ ሲሆን ጥሩ የትዳር አጋርና ወላጅ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ። ምናልባት ከልብ የሚያምኑባቸው ከእኛ የተለዩ ሃይማኖታዊ እምነቶች ይኖሯቸዋል። ስለ እኛ ብዙም የማያውቁ ወይም ጭፍን ጥላቻ ያላቸው ሰዎች ከነገሯቸው በስተቀር ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እምብዛም የሚያውቁት ነገር ላይኖር ይችላል። አንዳንዶች ደግሞ የሚያምነው የትዳር ጓደኛ ከዚህ በፊት ከቤተሰቡ ጋር የሚያሳልፈውን ጊዜ ለአምልኮ የሚጠቀምበት መሆኑ ቅር ያሰኛቸው ይሆናል። ስለ አንድ የማያምን የትዳር አጋር አንዳንድ ነገሮችን ማወቃችን በደግነትና በአክብሮት እንድንይዘው እንዲሁም አብረነው ስንሆን ከሚገባው በላይ እንዳንጨነቅ ይረዳናል።—ምሳሌ 16:20-23
3. አንድን የማያምን የትዳር ጓደኛ ለመርዳት የተሻለው ዘዴ ምንድን ነው?
3 ትኩረት ስጡ፦ አንድ የማያምን የትዳር ጓደኛ ለእውነት ፍላጎት እንዲያድርበት ለማድረግ የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለው ዘዴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ሳይሆን ተግባር ነው። (1 ጴጥ. 3:1, 2) ተግባራዊ የሆነ ነገር ለማድረግ ትኩረት መስጠት በጣም አስፈላጊ ነው። በጉባኤ ውስጥ ያሉ እህቶች ለአንዲት የማታምን ሚስት፣ ወንድሞች ደግሞ ለአንድ የማያምን ባል ትኩረት መስጠት ይችላሉ። ይህንን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
4. ለማያምኑ የትዳር ጓደኞች ትኩረት መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
4 የማያምነውን የትዳር ጓደኛ ከዚህ በፊት የማታውቁት ከሆነ ክርስቲያን ከሆነው የትዳር ጓደኛ ጋር ከተነጋገራችሁ በኋላ መተዋወቅ ትችላላችሁ። ግለሰቡ መጀመሪያ ላይ ስሜቱ ቀዝቀዝ ቢልባችሁ ተስፋ አትቁረጡ። ወዳጃዊ ስሜት ማሳየታችንና ትኩረት መስጠታችን ለይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት እንዲኖረው ሊያደርግ ይችላል። (ሮም 12:20) አንዳንድ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከማያምኑ የትዳር ጓደኞች ጋር የበለጠ ለመተዋወቅ ብሎም ጭፍን ጥላቻ ቢኖርባቸው እንኳ ያንን ለማስወገድ እነሱንና ቤተሰባቸውን ምግብ የመጋበዝ ልማድ አላቸው። ከዚያም ውይይታቸውን ወደ መንፈሳዊ ነገሮች ከማዞር ይልቅ የማያምነው ሰው ስለሚወደው ርዕሰ ጉዳይ አንስተው ይጫወታሉ። በኋላም ከግለሰቡ ጋር ይበልጥ ሲግባቡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ማድረግ ይችሉ ይሆናል። ወይም ደግሞ ከአንዳንድ የጉባኤው አባላት ጋር ስለተዋወቀ ባለቤቱ በስብሰባዎች ላይ ስትገኝ ምን እንደምትማር ተገኝቶ እንዲመለከት የምናቀርብለትን ግብዣ ይቀበል ይሆናል። ግለሰቡ እውነትን ለመመርመር ባይነሳሳ እንኳ አማኝ ለሆነችው የትዳር ጓደኛው ለሚያደርግላት ድጋፍ ሊመሰገን ይገባዋል።
5. ሽማግሌዎች የአንድን አስፋፊ የማያምን የትዳር ጓደኛ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
5 በተለይ ሽማግሌዎች የአንድን አስፋፊ የማያምን የትዳር ጓደኛ ለመርዳት ጥረት ማድረግ እንዲሁም ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ንቁ መሆን ይኖርባቸዋል። ከዚህ ቀደም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ ያልነበረ የማያምን የትዳር ጓደኛ ሆስፒታል ሲገባ ወይም ከፍተኛ የጤና መታወክ ሲያጋጥመው የሚሰጠውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ ለመስማት ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ሞትን የመሰለ መከራ ሲያጋጥም ሽማግሌዎች ቤተሰቡን ሲያጽናኑ የማያምነው ግለሰብም አብሯቸው እንዲሆን ሊጋብዙት ይችላሉ።
6. የአንድን አስፋፊ የማያምን የትዳር ጓደኛ ለመርዳት እንድንነሳሳ የሚያደርገን ምክንያት ምንድን ነው?
6 አንድ ክርስቲያን የማያምን የትዳር ጓደኛው እውነትን ቢቀበል ምን ያህል ሊደሰት እንደሚችል ገምት! ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ያለው ሁኔታ ለይሖዋ፣ ለመላእክትና ለሌሎች የጉባኤው አባላት ከፍተኛ የሆነ ደስታ ያስገኛል። (ሉቃስ 15:7, 10) መጀመሪያ ላይ የማያምነው የትዳር ጓደኛ ለምናደርገው ጥረት በጎ ምላሽ ባይሰጥም እንኳ ጥረታችንን መቀጠላችን “ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ [የሚታገሠውን]” ይሖዋን ደስ ያሰኘዋል፤ እኛም ይሖዋን እያስደሰትን እንደሆነ ማወቃችን ደስታ ያስገኝልናል።—2 ጴጥ. 3:9
[ከገጽ 6 የተቀነጨበ ሐሳብ ]
አንድ የማያምን የትዳር ጓደኛ ለእውነት ፍላጎት እንዲያድርበት ለማድረግ የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለው ዘዴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ሳይሆን ተግባር ነው