ጸሎትና ማሰላሰል—ቀናተኛ ለሆኑ አገልጋዮች አስፈላጊ ናቸው
1. ኢየሱስ ዋነኛ ከሆነው ተግባሩ የሚያዘናጉትን ነገሮች ማስወገድ እንዲችል የረዳው ምንድን ነው?
1 ኢየሱስ ምሽቱን ያሳለፈው በሽተኞችን በመፈወስና አጋንንትን በማስወጣት ነበር። በማግስቱ ደቀ መዛመርቱ ሲያገኙት “ሰው ሁሉ እየፈለገህ ነው” በማለት ተአምር መሥራቱን እንዲቀጥል መገፋፋት ጀመሩ። ኢየሱስ ግን ዋነኛ ተግባሩ ከነበረው የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ሥራ ምንም ነገር እንዲያዘናጋው አልፈቀደም። “በዚያም እንድሰብክ በአቅራቢያ ወዳሉት ትንንሽ ከተሞች እንሂድ፤ የመጣሁትም ለዚሁ ዓላማ ነው” አላቸው። ኢየሱስ ለአገልግሎቱ ቅድሚያ መስጠቱን እንዲቀጥል የረዳው ምንድን ነው? ኢየሱስ በዚያኑ ዕለት ለመጸለይና ለማሰላሰል በማለዳ ተነስቶ ነበር። (ማር. 1:32-39) እኛንስ ጸሎትና ማሰላሰል ቀናተኛ ሰባኪዎች ለመሆን የሚረዱን እንዴት ነው?
2. ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ በምን ነገሮች ላይ ማሰላሰል እንችላለን?
2 ስለ ምን ነገሮች ማሰላሰል እንችላለን? ኢየሱስ ሕዝቡ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው” እንደነበር አስተውሏል። (ማቴ. 9:36) እኛም ብንሆን የመንግሥቱ ምሥራች ለሰዎች ምን ያህል እንደሚያስፈልግ ማሰላሰል እንችላለን። በጊዜው አጣዳፊነት ላይም ማሰላሰል እንችል ይሆናል። (1 ቆሮ. 7:29) የይሖዋ ሥራዎችና ባሕርያት፣ የይሖዋ ምሥክር የመሆን መብታችን እንዲሁም በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ፈጽሞ የማያውቁት ከአምላክ ቃል ያገኘነው ውድ መንፈሳዊ ሀብት ልናሰላስልባቸው የሚገቡ ነገሮች ናቸው።—መዝ. 77:11-13፤ ኢሳ. 43:10-12፤ ማቴ. 13:52
3. መቼ ማሰላሰል እንችላለን?
3 ማሰላሰል የምንችለው መቼ ነው? አንዳንዶች ኢየሱስ እንዳደረገው ጸጥ ባለው የማለዳ ጊዜ ተነስተው ያሰላስላሉ። ሌሎች ደግሞ ማታ ከመተኛታቸው በፊት ያለውን ጊዜ ለማሰላሰል አመቺ ሆኖ አግኝተውታል። (ዘፍ. 24:63) ፕሮግራማችን የተጣበበ ቢሆን እንኳ ለማሰላሰል የሚሆን ጊዜ ማግኘት እንችላለን። አንዳንዶች በሕዝብ መጓጓዣ ላይ እያሉ ጊዜውን ለማሰላሰል ይጠቀሙበታል። ሌሎች ደግሞ ከምሳ እረፍታቸው ላይ የተወሰነውን ጊዜ በጸጥታ ለማሰላሰል ይጠቀሙበታል። ብዙዎች አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት ጥቂት ማሰላሰላቸው በቅንዓትና በድፍረት ለመስበክ እንደሚረዳቸው ተገንዝበዋል።
4. ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው?
4 ጸሎትና ማሰላሰል ይሖዋን ለማገልገል ያለንን ፍላጎት ያሳድግልናል፣ በሕይወታችን ውስጥ ለአምልኮታችን ቅድሚያውን እንድንሰጥ ያስችለናል እንዲሁም መስበካችንን ለመቀጠል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። ማሰላሰል የአምላክ ዋነኛ አገልጋይ የሆነውን ኢየሱስን እንደጠቀመው ሁሉ እኛንም ሊጠቅመን ይችላል።