በመንገድ ላይ ውጤታማ ምሥክርነት መስጠት
1. የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?
1 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት መንገድ ላይም ሆነ ሕዝብ በሚበዛባቸው ሌሎች አካባቢዎች የሚያገኛቸውን ሰዎች ከማናገር ወደኋላ አላለም። (ሉቃስ 9:57-61፤ ዮሐ. 4:7) የያዘውን ጠቃሚ መልእክት በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማካፈል ይፈልግ ነበር። ዛሬም ሰዎች የአምላክን ጥበብ እንዲያገኙ መርዳት ከምንችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ መንገድ ላይ ማገልገል ነው። (ምሳሌ 1:20) ሰዎችን ቀርበን ለማናገር ጥረት ካደረግን ብሎም አስተዋዮች ከሆንን ይበልጥ ስኬታማ እንሆናለን።
2. መንገድ ላይ በምናገለግልበት ጊዜ ምን ጥረቶችን ማድረግ ይኖርብናል?
2 ሰዎችን ቀርቦ ለማናገር ጥረት ማድረግ፦ አንድ ቦታ ላይ በመቆም ወይም በመቀመጥ በዚያ የሚያልፍ ሰው መጥቶ እስኪያናግራችሁ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ሰዎችን ቀርባችሁ ማናገራችሁ በአብዛኛው የተሻለ ነው። ዓይን ዓይናቸውን በመመልከት ፈገግ ለማለት ሞክሩ፤ እንዲሁም በተረጋጋና ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ለመቅረብ ጥረት አድርጉ። ከሌሎች አስፋፊዎች ጋር አብራችሁ የምትሠሩ ከሆነ በተናጠል ሰዎችን ለማናገር መሞከራችሁ በጣም ጥሩ ነው። እንዲህ ማድረጋችን ጊዜውን የግል ጉዳዮቻችንን አንስተን በመጨዋወት ከማሳለፍ ይልቅ መልእክቱን ለሌሎች በማድረሱ ተግባር ላይ እንድናተኩር ይረዳናል። በተጨማሪም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በሌላ ጊዜ አግኝቶ ማናገር የሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። የሚቻል ከሆነ በውይይታችሁ መጨረሻ ላይ ግለሰቡን በሌላ ጊዜ እንዴት ልታገኙት እንደምትችሉ ጠይቁት። አንዳንድ አስፋፊዎች መንገድ ላይ በሚሠሩበት ጊዜ አንድ ቦታ ላይ አዘውትረው ያገለግላሉ፤ ይህም ቀደም ሲል ያነጋገሯቸውን ሰዎች በድጋሚ ለማግኘትና ፍላጎታቸውን ለማሳደግ አስችሏቸዋል።
3. መንገድ ላይ በምናገለግልበት ወቅት አስተዋይ መሆናችንን እንዴት ማሳየት እንችላለን?
3 አስተዋይ ሁኑ፦ መንገድ ላይ ከማገልገል ጋር በተያያዘ የት አካባቢ መቆም እንዲሁም ማንን ማናገር እንዳለብን ስንወስን ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ይኖርብናል። አላፊ አግዳሚውን በሙሉ ማናገር አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ሁኔታዎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ለምሳሌ ያህል፣ ግለሰቡ ቸኩሎ ከሆነ አለማናገሩ የተሻለ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎችን ለማናገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ንቁ ሁኑ። በንግድ አካባቢ ስንመሠክር የድርጅቱን ኃላፊ ላለማስቆጣት ጠንቃቃ መሆን ይገባናል። ሰዎች ወደ ድርጅቱ ሊገቡ ሲሉ ከመመሥከር ይልቅ ጉዳያቸውን ጨርሰው ሲወጡ ማናገሩ በአብዛኛው የተሻለ ይሆናል። ሰዎችን በምታናግሩበት ወቅት እንዲደነግጡ ወይም እንዲበረግጉ በሚያደርግ መንገድ ላለመቅረብ ጥንቃቄ አድርጉ። ጽሑፎችን ስታበረክቱም አስተዋዮች ሁኑ። ግለሰቡ ብዙም ፍላጎት እንደሌለው ካስተዋላችሁ መጽሔቶችን ከመስጠት ይልቅ ትራክት አበርክቱለት።
4. መንገድ ላይ መመሥከር አስደሳችና ውጤታማ የአገልግሎት ዘርፍ ሊሆንልን የሚችለው እንዴት ነው?
4 መንገድ ላይ ማገልገል በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ የእውነት ዘር ለመዝራት ያስችለናል። (መክ. 11:6) እንዲያውም መንገድ ላይ የምናገኛቸው አንዳንድ ሰዎች ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ቤታቸው ልናገኛቸው ያልቻልናቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለመመሥከር ትኩረት ሰጥተን የምንሠራ ከሆነ መንገድ ላይ መመሥከር አስደሳችና ውጤታማ የመስክ አገልግሎት ዘርፍ ይሆንልናል።