አእምሮህን ጠብቅ
1. በ2013 የአገልግሎት ዓመት የሚካሄደው የወረዳ ስብሰባ ጭብጥ ምንድን ነው? ይህ ስብሰባ የተዘጋጀበት ዓላማስ ምንድን ነው?
1 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ይሖዋን በሙሉ ልባቸው፣ ነፍሳቸውና አእምሯቸው እንዲወዱ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 22:37, 38) ቀጣዮቹ የአውራጃ፣ የወረዳና የልዩ ስብሰባዎች የተዘጋጁት ውስጣዊ ማንነታችንን እንድናሻሽል እኛን ለመርዳት ታስበው ነው። እንደምታውቁት የአውራጃ ስብሰባችን ጭብጥ “ልብህን ጠብቅ!” የሚል ነው። በ2013 የአገልግሎት ዓመት የሚካሄደው የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም “ሕሊናህን ጠብቅ” የሚል ጭብጥ አለው። ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በተከታታይ የሚደረገው የወረዳ ስብሰባ ደግሞ “አእምሮህን ጠብቅ” የሚል ጭብጥ ያለው ሲሆን የተመሠረተው በማቴዎስ 22:37 ላይ ነው። ይህ ስብሰባ የተዘጋጀው አስተሳሰባችንን እንድንመረምር እኛን ለመርዳት ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን ደግሞ የምናስባቸው ነገሮች ይበልጥ ይሖዋን የሚያስደስቱ እንዲሆኑ ያስችላል።
2. በስብሰባው ወቅት ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት መጣር ይኖርብናል?
2 በስብሰባው ላይ የሚብራሩት ነጥቦች፦ የወረዳ ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ዋና ዋና ነጥቦቹን አጉልተው ለሚያሳዩት ለሚከተሉት ጥያቄዎች የሚሰጡትን መልሶች በትኩረት መከታተል ይኖርብናል፦
• ‘የሰውን ሐሳብ’ ከማሰብ መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?
• የማያምኑ ሰዎችን አእምሮ ያሳወረውን መሸፈኛ መግለጥ የምንችለው እንዴት ነው?
• ምን ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል?
• ተገቢ የሆነ ማሰላሰል ምን ጥቅሞች አሉት?
• ይሖዋ አስተሳሰባችንን እንዲቀርጽልን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
• ባሎች፣ ሚስቶች፣ ወላጆችና ልጆች ለቤተሰባቸው ደስታ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?
• ለይሖዋ ቀን ዝግጁ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
• አእምሮን ዝግጁ በማድረግ ለሥራ መታጠቅ ሲባል ምን ማለት ነው?
• የተማሩትን ተግባራዊ የሚያደርጉ ሁሉ ምን ጥቅም ያገኛሉ?
3. በሁለቱም የስብሰባ ቀናት መገኘት፣ ስብሰባውን በትኩረት መከታተልና የተማርነውን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
3 ሰይጣን አእምሯችንን ለማበላሸት ከፍተኛ ተጋድሎ ያደርጋል። (2 ቆሮ. 11:3) በመሆኑም አስተሳሰባችንን በመቆጣጠር አእምሯችንን መጠበቅ ይኖርብናል። የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማንጸባረቃችንን መቀጠልና ዓመፀኛ የሆነው ይህ ዓለም የሚያሳድርብንን ተጽዕኖ መቋቋም ያስፈልገናል። (1 ቆሮ. 2:16) እንግዲያው በሁለቱም የስብሰባ ቀናት ለመገኘት ዝግጅት አድርጉ። እንዲሁም ስብሰባውን በትኩረት ተከታተሉ። በስብሰባው ላይ የምናገኛቸውን አስፈላጊ ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረጋችን አእምሯችንን ዝግጁ በማድረግ አገልግሎታችንን በቅንዓት እንድናከናውን ያስችለናል።—1 ጴጥ. 1:13