‘የተሟላ ምሥክርነት ስጡ’
1. ሐዋርያው ጳውሎስ በአገልግሎት ረገድ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?
1 “አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።” (2 ጢሞ. 4:5) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ማሳሰቢያ ለጢሞቴዎስ ሲሰጥ ጉዳዩን በተመለከተ ሕሊናውን የሚወቅሰው ነገር እንዳልነበረ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ጳውሎስ ከ47 እስከ 56 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ ሦስት የሚስዮናዊ ጉዞዎችን አድርጓል። ጳውሎስ “የተሟላ ምሥክርነት” ይሰጥ እንደነበረ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ተገልጿል። (ሥራ 23:11፤ 28:23) እኛስ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
2. ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል የተሟላ ምሥክርነት መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ከቤት ወደ ቤት፦ ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ ያላገኙ ሰዎችን ቤታቸው ለማግኘት ወደ እነሱ የምንሄድበትን ሰዓት መቀያየር ይኖርብናል። የቤቱ አባወራ ምሽት ላይ ወይም ቅዳሜና እሁድ ቤት ይገኝ ይሆናል። ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎች ጋር በተደጋጋሚ በመሄድ በእያንዳንዱ ቤት የሚገኙ ሰዎችን ለማናገር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ሰዎችን ቤታቸው ለማግኘት የምናደርገው ጥረት ባይሳካስ? በደብዳቤ ወይም በስልክ ለመመሥከር ጥረት ካደረግን ጥሩ ውጤት ልናገኝ እንችላለን።
3. በአደባባይ ወይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ምን አጋጣሚዎች አሉን?
3 በአደባባይና መደበኛ ባልሆነ መንገድ፦ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች ለሚሰማ ሁሉ እውነተኛ “ጥበብ” ያዘለ መልእክት ያውጃሉ። ይህን የሚያደርጉት አንዳንድ ጊዜ “በጐዳና ላይ” አሊያም ‘በአደባባይ’ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 1:20, 21) የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን ስናከናውንስ ለመመሥከር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በንቃት እንከታተላለን? ‘ቃሉን በመስበኩ ሥራ በእጅጉ ተጠምደናል’ ሊባል ይችላል? (ሥራ 18:5) ከሆነ “የተሟላ ምሥክርነት እንድንሰጥ” የተጣለብንን ግዴታ በሚገባ እየተወጣን ነው ማለት ነው።—ሥራ 10:42፤ 17:17፤ 20:20, 21, 24
4. ጸሎትና ማሰላሰል የተሟላ ምሥክርነት በመስጠት ረገድ የሚረዱን እንዴት ነው?
4 አንዳንድ ጊዜ ግን ከራሳችን ድክመት የተነሳ ወይም ዓይናፋር በመሆናችን ምክንያት ከመመሥከር ወደኋላ ልንል እንችላለን። ይሖዋ ያሉብንን የአቅም ገደቦች እንደሚረዳ ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 103:14) ያም ቢሆን እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ለመናገር የሚያስችል ድፍረት እንዲሰጠን ይሖዋን በጸሎት ልንጠይቀው እንችላለን። (ሥራ 4:29, 31) በተጨማሪም የግል ጥናት ስናደርግና በአምላክ ቃል ላይ ስናሰላስል ምሥራቹ ላለው የላቀ ዋጋ ያለንን አድናቆት ለማሳደግ ጥረት ማድረግ እንችላለን። (ፊልጵ. 3:8) ይህ ደግሞ ምሥራቹን በቅንዓት ለማወጅ ያስችለናል!
5. የኢዩኤል ትንቢት እንዲፈጸም የበኩላችንን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
5 ኢዩኤል፣ ታላቁና አስፈሪው የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት የአምላክ ሕዝቦች ‘መሄዳቸውን’ እንደሚቀጥሉ ማለትም በስብከቱ ሥራ እንደሚገፉ ደግሞም ይህን ከማድረግ ምንም የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለ በትንቢት ተናግሯል። (ኢዩ. 2:2, 7-9) እንግዲያው ፈጽሞ በማይደገመው በዚህ የስብከት ሥራ የተሟላ ተሳትፎ እናድርግ!