በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
የተባለውን ብሮሹር መጠቀም የሚቻልበት መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ወደ ድርጅቱ ለመምራት የሚረዳ አዲስ ብሮሹር
1. የይሖዋ ፈቃድ የተባለው ብሮሹር ያሉት ሦስት ዓላማዎች የትኞቹ ናቸው?
1 በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የተባለውን አዲስ ብሮሹር መጠቀም ጀምረሃል? የብሮሹሩ ዓላማ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (1) የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆንን እንዲያውቁ (2) እንቅስቃሴያችን ምን እንደሚመስል እንዲማሩና (3) ድርጅታችን ምን እንደሚያከናውን እንዲገነዘቡ መርዳት ነው። የይሖዋ ፈቃድ በተባለው ብሮሹር ላይ እያንዳንዱ ትምህርት የተቀመጠው በአንድ ገጽ ላይ ብቻ በመሆኑ ጥናቱ ካበቃ በኋላ በየጊዜው ለአምስት ወይም ለአሥር ደቂቃ በቀላሉ ትምህርቶቹ ላይ መወያየት ይቻላል።
2. ይህ ብሮሹር የተዘጋጀበትን መንገድና ያሉትን አንዳንድ ገጽታዎች ጥቀስ።
2 ብሮሹሩ የተዘጋጀበት መንገድ፦ ብሮሹሩ ሦስት ክፍሎች አሉት፤ እያንዳንዱ ክፍል ከላይ ከተገለጹት ነገሮች መካከል አንዱን ጉዳይ በማንሳት ስለ ይሖዋ ድርጅት ማብራሪያ ይሰጣል። ብሮሹሩ 28 ትምህርቶች ያሉት ሲሆን ሁሉም ርዕሶች በጥያቄ መልክ የቀረቡ ናቸው፤ ደመቅ ተደርገው የተጻፉት ንዑስ ርዕሶች ደግሞ ለጥያቄው መልስ ይሰጣሉ። ሥራችን ያለውን ዓለም አቀፋዊ ይዘት ለማሳየት ከ50 በላይ ከሆኑ አገሮች የተውጣጡ ፎቶግራፎች በብሮሹሩ ውስጥ ይገኛሉ። በብሮሹሩ ላይ ያሉ በርካታ ትምህርቶች “ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት” የሚል ሣጥን ይዘዋል፤ ጥናታችሁ ሣጥኖቹ ውስጥ ያሉትን ሐሳቦች እንዲሠራባቸው ልታበረታቱት ትችላላችሁ።
3. የይሖዋ ፈቃድ የተባለውን ብሮሹር እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?
3 ብሮሹሩን እንዴት መጠቀም ይቻላል? መጀመሪያ ላይ በጥያቄ መልክ የቀረበውን የትምህርቱን ርዕስ ለጥናታችሁ አሳዩት። ከዚያም በትምህርቱ ላይ ያለውን ሐሳብ ስታነብቡ ደመቅ ብለው የተጻፉትን ንዑስ ርዕሶች ጎላ አድርጋችሁ ግለጹለት። በመጨረሻም በገጹ ግርጌ ላይ የሚገኙትን የክለሳ ጥያቄዎች ጠይቁት። በትምህርቱ ውስጥ የሚገኙትን አንቀጾች በሙሉ በአንድ ጊዜ ልታነቡ አሊያም አንቀጽ በአንቀጽ ልትወያዩባቸው ትችላላችሁ። የትኞቹን ጥቅሶች አውጥታችሁ ማንበብ እንዳለባችሁ ለመወሰን የማመዛዘን ችሎታችሁን ተጠቀሙ። በሥዕሎቹና “ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት” በሚሉት ሣጥኖች ላይ መወያየታችሁን አትዘንጉ። አብዛኛውን ጊዜ ትምህርቶቹን በተቀመጡበት ቅደም ተከተል ብትወያዩባቸው የተሻለ ነው። ያም ቢሆን ከጥናታችሁ ጋር ልትወያዩበት የምትፈልጉት ርዕስ ካለ አልፋችሁ መሄድ ትችላላችሁ። ለምሳሌ በቅርቡ ትልቅ ስብሰባ የምታደርጉ ከሆነ ሌሎቹን ዘልላችሁ በትምህርት 11 ላይ መወያየት ትችላላችሁ።
4. ይህን አዲስ መሣሪያ ማግኘትህ የሚያስደስትህ ለምንድን ነው?
4 አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና በሰማይ ከሚገኘው አባታችን ጋር እንዲተዋወቅ እየረዳነው ነው። ይሁንና ስለ ይሖዋ ድርጅትም ልናስተምረው ይገባል። (ምሳሌ 6:20) ይህን ለማድረግ የሚረዳ አዲስ መሣሪያ በማግኘታችን ምንኛ ደስተኞች ነን!