ነቢያትን አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው—ዮናስ
1. ዮናስ ምን ግሩም ባሕርያትን አሳይቷል?
1 ስለ ነቢዩ ዮናስ ስታስቡ ወደ አእምሯችሁ የሚመጣው ነገር ምንድን ነው? አንዳንዶች ዮናስን የሚመለከቱት ፈሪ ወይም ግትር እንደሆነ አድርገው ነው። ዮናስ ግን ትሑት፣ ደፋርና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ያለው ሰው መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። ታዲያ ግሩም በሆኑት የዮናስ ባሕርያት ላይ በማተኮር ይህን ነቢይ እንደ ‘አርዓያ አድርገን ልንመለከተው’ የምንችለው እንዴት ነው?—ያዕ. 5:10
2. ትሕትና በማሳየት ረገድ የዮናስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
2 ትሕትና፦ በመጀመሪያ ዮናስ የተመደበበትን ክልል በመሸሽ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ሄዶ ነበር። እንዲህ ማድረጉ የሚገርም አይደለም፤ ምክንያቱም አሦራውያን በጭካኔያቸው የታወቁ ሲሆኑ ከተማቸው ነነዌም ‘የደም ከተማ’ ተብላ ትጠራ ነበር። (ናሆም 3:1-3) ያም ቢሆን ይሖዋ ለዮናስ ተግሣጽ ሰጥቶታል፤ ዮናስም ሌላ ዕድል ሲያገኝ የተሰጠውን ተልዕኮ በመቀበል ትሑት መሆኑን አሳይቷል። (ምሳሌ 24:32፤ ዮናስ 3:1-3) መጀመሪያ ላይ ጥሎ ቢሸሽም በኋላ ላይ የይሖዋን ፈቃድ ፈጽሟል። (ማቴ. 21:28-31) እኛስ፣ ተግሣጽ ወይም ፈታኝ የሆነ ክልል ቢሰጠንም እንኳ ምሥራቹን ለመስበክ ቁርጥ ውሳኔ እናደርጋለን?
3. አገልግሎትህን ለማከናወን ድፍረትና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየት የሚያስፈልግህ ጊዜ አለ?
3 ድፍረትና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ፦ ዮናስ ያደረገው መጥፎ ውሳኔ የመርከበኞቹን ሕይወት አደጋ ላይ እንደጣለ ሲገነዘብ የራሱን ሕይወት መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል። (ዮናስ 1:3, 4, 12) በኋላም በነነዌ የተሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም በሄደበት ጊዜ የይሖዋን የፍርድ መልእክት ለማወጅ የሚያስችለውን ተስማሚ ቦታ ለመፈለግ ሳይሆን አይቀርም ወደ ከተማዋ መሀል ዘልቆ ገብቷል። ደፋር የአምላክ ነቢይ ካልሆነ በስተቀር ፈሪ ሰው ይህን አያደርግም! (ዮናስ 3:3, 4) ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? እኛም ተቃውሞ ሲያጋጥም በድፍረት ለመመሥከር እንድንችል ከአምላክ የሚገኘው ድፍረት ያስፈልገናል። (ሥራ 4:29, 31) ጊዜያችንንና ገንዘባችንን በአገልግሎቱ ላይ ለማዋል የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማዳበር ያስፈልገናል።—ሥራ 20:24
4. የይሖዋ ነቢያት በተዉት ግሩም አርዓያ ላይ ጊዜ ወስደን ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው?
4 ስለ አንድ የይሖዋ ነቢይ ባነበብክ ቁጥር ራስህን በእሱ ቦታ የምታስቀምጥ ከሆነ ብዙ ትጠቀማለህ። እንግዲያው ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘እኔ ብሆን ኖሮ ምን አደርግ ነበር? የእሱን ግሩም ባሕርይ በሕይወቴ ማንጸባረቅ የምችለው እንዴት ነው?’ (ዕብ. 6:11, 12) ከሌሎቹም የይሖዋ ነቢያት ምን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንደምንችል የሚገልጹ ርዕሶች ወደፊት በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ይወጣሉ።