ነቢያትን አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው—ሶፎንያስ
1. ሶፎንያስ ነቢይ እንዲሆን በተሾመበት ወቅት በጊዜው የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? ለእኛ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነንስ እንዴት ነው?
1 ጊዜው ሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. አጋማሽ ሲሆን በወቅቱ ይሁዳ ውስጥ የበኣል አምልኮ በይፋ ይከናወን ነበር። መጥፎ ንጉሥ የነበረው አሞን ከተገደለ ብዙም አልቆየም፤ እሱን ተክቶ በመግዛት ላይ ያለው ወጣቱ ኢዮስያስ ነው። (2 ዜና 33:21 እስከ 34:1) ይሖዋ የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ ሶፎንያስን ያስነሳው በዚህ ጊዜ ላይ ነበር። ሶፎንያስ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ሊሆን ቢችልም እንኳ ይሖዋ ለይሁዳ መሪዎች ያስተላለፈውን ውግዘት ያዘለ መልእክት ለማለሳለስ አልሞከረም። (ሶፎ. 1:1፤ 3:1-4) እኛም ሶፎንያስን በድፍረቱ ለመምሰል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ ቤተሰቦቻችንና ዘመዶቻችን ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ መፍቀድ የለብንም። (ማቴ. 10:34-37) ለመሆኑ ሶፎንያስ ያወጀው መልእክት ምንድን ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?
2. ከይሖዋ የቁጣ ቀን ለመሰወር ምን እርምጃ መውሰድ አለብን?
2 ይሖዋን ፈልጉ፦ ሰዎች ከይሖዋ የቁጣ ቀን ሊተርፉ የሚችሉት እሱ ጥበቃ ካደረገላቸው ብቻ ነው። በመሆኑም ሶፎንያስ የይሁዳ ሕዝቦች ጊዜው ሳያልቅ ይሖዋን፣ ጽድቅንና ትሕትናን እንዲፈልጉ አሳስቧቸዋል። (ሶፎ. 2:2, 3) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እኛም እንደ ሶፎንያስ፣ ሰዎች ይሖዋን እንዲፈልጉ እናበረታታለን፤ ይሁን እንጂ እኛም ራሳችን ‘ይሖዋን ከመከተል ወደ ኋላ እንዳንመለስ’ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። (ሶፎ. 1:6) የአምላክን ቃል በሚገባ በማጥናትና አምላክ እንዲመራን በመጸለይ ይሖዋን እንፈልጋለን። በሕይወታችን ንጹሕ ሥነ ምግባር በመያዝ ጽድቅን እንፈልጋለን። እንዲሁም የታዛዥነት መንፈስ በማዳበርና ከይሖዋ ድርጅት ለምናገኘው መመሪያ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ትሕትናን እንፈልጋለን።
3. ለአገልግሎት አዎንታዊ አመለካከት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
3 መልካም ውጤቶች፦ የሶፎንያስ የፍርድ መልእክት ቢያንስ አንዳንድ የይሁዳ ነዋሪዎች እርምጃ እንዲወስዱ አነሳስቷቸዋል፤ በተለይ ደግሞ ገና በልጅነቱ ይሖዋን መፈለግ በጀመረው በወጣቱ ኢዮስያስ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሳያሳድር አልቀረም። ከጊዜ በኋላ ኢዮስያስ በአገሪቱ የተስፋፋውን የጣዖት አምልኮ ለማስወገድ መጠነ ሰፊ እርምጃ ወስዷል። (2 ዜና 34:2-5) በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱ ዘር በመንገድ ዳር፣ በድንጋያማ ቦታ ወይም በእሾህ መካከል ሊወድቅ ቢችልም የተወሰነው ግን በጥሩ አፈር ላይ ወድቆ ፍሬ ማፍራቱ አይቀርም። (ማቴ. 13:18-23) የመንግሥቱን ዘር በመዝራቱ ሥራ ከተጠመድን ይሖዋ የምናደርገውን ጥረት እንደሚባርክልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝ. 126:6
4. ይሖዋን ‘መጠባበቅ’ ያለብን ለምንድን ነው?
4 በይሁዳ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ይሖዋ እርምጃ እንደማይወስድ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ታላቁ ቀኑ እንደቀረበ ማረጋገጫ ሰጥቷል። (ሶፎ. 1:12, 14) መዳን የሚያገኙት በይሖዋ የሚታመኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። (ሶፎ. 3:12, 17) ይሖዋን ‘ስንጠባበቅ’ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር አንድ ላይ ሆነን ታላቁን አምላክ በማገልገል ደስታ እንጨድ።—ሶፎ. 3:8, 9