ክርስቲያናዊ ሕይወት
ወጣቶች—‘ለመልካም ሥራ የምትቀኑ’ ሁኑ
ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ቲቶን ጨምሮ ወጣት ወንዶች “በማንኛውም ሁኔታ መልካም ሥራ በመሥራት አርዓያ [ለመሆን]” መጣር እንዳለባቸው ገልጿል። (ቲቶ 2:6, 7) በዚሁ ምዕራፍ ላይ ትንሽ ወረድ ብሎ ደግሞ ኢየሱስ የይሖዋን ሕዝብ ያነጻው “ለመልካም ሥራ የሚቀና” እንዲሆን ለማድረግ መሆኑን ጽፏል። (ቲቶ 2:14) “መልካም ሥራ” የሚለው አገላለጽ ስለ አምላክ መንግሥት መስበክንና ማስተማርን ይጨምራል። አንተም ወጣት ከሆንክ የወጣትነት ጉልበትህን ረዳት አቅኚ ወይም የዘወትር አቅኚ ሆነህ ለማገልገል ልትጠቀምበት ትችላለህ?—ምሳሌ 20:29
አቅኚ ሆነህ ማገልገል የምትፈልግ ከሆነ ሁኔታህን ያገናዘበ እቅድ አውጣ። (ሉቃስ 14:28-30) ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስካፈል ራሴን የማስተዳድረው እንዴት ነው? የሰዓት ግቤን የማሟላውስ እንዴት ነው? ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ጸልይ። (መዝ 37:5) ስለ እቅድህ ወላጆችህንና ውጤታማ የሆኑ አቅኚዎችን አማክራቸው። ከዚያም ግብህ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ውሰድ። ይሖዋ በእሱ አገልግሎት በቅንዓት ለመካፈል የምታደርገውን ጥረት እንደሚባርከው አትጠራጠር!
ይሖዋን እያከበሩ ያሉ ወጣቶች የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
አንዳንዶች በአቅኚነት ለመካፈል የትኞቹን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት አስፈልጓቸዋል? ይህን ያደረጉትስ እንዴት ነው?
ወላጆች ልጆቻቸው የዘወትር አቅኚ እንዲሆኑ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
የአገልግሎት ፕሮግራም ማውጣት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
የጉባኤው አባላት አቅኚዎችን መርዳትና ማበረታታት የሚችሉት እንዴት ነው?
አቅኚዎች ምን በረከቶች ያገኛሉ?
አቅኚ ለመሆን ያወጣሁት ግብ ላይ መድረስ የምችለው እንዴት ነው?