ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 33–34
የይሖዋ ማራኪ ባሕርያት
ሙሴ የይሖዋን ባሕርያት መረዳቱ እስራኤላውያንን በትዕግሥት እንዲይዛቸው ረድቶታል። እኛም በተመሳሳይ ስለ ይሖዋ ባሕርያት ያለንን እውቀት ባሳደግን መጠን የእምነት ባልንጀሮቻችንን በምሕረት መያዝ እንችላለን።
“መሐሪና ሩኅሩኅ”፦ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥልቅ ፍቅር እና ልባዊ አሳቢነት እንደሚያሳዩአቸው ሁሉ ይሖዋም አምላኪዎቹን በዚህ መንገድ ይንከባከባቸዋል
“ለቁጣ የዘገየ”፦ ይሖዋ አገልጋዮቹን በትዕግሥት ይይዛቸዋል፤ ይኸውም ድክመታቸውን ይታገሣል እንዲሁም ለውጥ የሚያደርጉበት ጊዜ ይሰጣቸዋል
“ታማኝ ፍቅሩ . . . እጅግ ብዙ የሆነ”፦ ይሖዋ ታማኝ ፍቅር ስላለው ከሕዝቦቹ ጋር ምንጊዜም የማይለወጥ ትስስር ይመሠርታል
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ምሕረትና ርኅራኄ በማሳየት ረገድ ይሖዋን መምሰል የምችለው እንዴት ነው?’