የጦርነት ሰቆቃ
የጦርነትንና የግጭትን ያህል በሰዎች ሕይወት ላይ የከፋ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነገር የለም ማለት ይቻላል። በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ወታደሮችና ንጹሐን ዜጎች የጦርነትን ሰቆቃ በዓይናቸው ተመልክተዋል።
ወታደሮች
“በዙሪያችን ሰዎች ሲገደሉና ሲቆስሉ እናያለን። ቀን ከሌት በስጋት ነው የምንኖረው።”—ጌሪ፣ ብሪታንያ
“ጀርባዬና ፊቴ ላይ በጥይት ተመትቻለሁ፤ ልጆችንና አረጋውያንን ጨምሮ ብዙዎች ሲገደሉ አይቻለሁ። ጦርነት ልብ ያደነድናል።”—ዊልማር፣ ኮሎምቢያ
“ከፊት ለፊትህ አንድ ሰው ተተኩሶበት ሲገደል ስታይ ትዕይንቱ ከአእምሮህ አይጠፋም። ያሰማው ጩኸትና ሲቃ ያቃጭልብሃል። ግለሰቡን ፈጽሞ አትረሳውም።”—ዘፊራ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ንጹሐን ዜጎች
“መልሼ ደስተኛ መሆን የምችል አልመሰለኝም ነበር። ለሕይወትህ ትሰጋለህ፤ ከዚህም በላይ ደግሞ ለቤተሰቦችህና ለጓደኞችህ ሕይወት ትሰጋለህ።”—ኦሌክሳንድራ፣ ዩክሬን
“ከአሁን አሁን ተባራሪ ጥይት መታኝ ብለው እየተሳቀቁ ከሌሊቱ 8 ሰዓት እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ ለምግብ መሰለፍ በጣም ያስፈራል።”—ዴለር፣ ታጂኪስታን
“ጦርነት ወላጆቼን ነጥቆኛል። ብቻዬን ስለቀረሁ የሚያጽናናኝም ሆነ የሚንከባከበኝ ማንም ሰው አልነበረም።”—ማሪ፣ ሩዋንዳ
ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች የጦርነትን ሰቆቃ ያዩ ቢሆንም ሰላም ማግኘት ችለዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ማንኛውም ዓይነት ጦርነትና ግጭት በቅርቡ እንደሚያበቃ እርግጠኞች ናቸው። ይህ የሚሆነው እንዴት እንደሆነ ይህ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሞ ያብራራል።