ጦርነት እና ግጭት ቢኖርም ሰላም ማግኘት
ቀደም ሲል በጦር ሠራዊት ውስጥ ያገለግል የነበረው ጌሪ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናቴ በፊት በዓለም ላይ ጭካኔ፣ ግፍና መከራ ይህን ያህል የበዛው ለምን እንደሆነ ግራ ይገባኝ ነበር። አሁን ግን የአእምሮ ሰላም አለኝ። ይሖዋ አምላክ ዓለማችንን ሰላማዊ ቦታ እንደሚያደርጋት እተማመናለሁ።”
እንዲህ የሚሰማው ጌሪ ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ሰዎችን የረዳቸው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ።”—መዝሙር 86:5
ይህን ማወቅ ምን ጥቅም አለው? “ይህ ጥቅስ ይሖዋ መሐሪ እንደሆነ ያረጋግጥልኛል። በጦርነት እካፈል በነበረበት ጊዜ ያደረግኩትን ነገር ሁሉ ይቅር ሊለኝ ፈቃደኛ እንደሆነ አውቃለሁ።”—ዊልማር፣ ኮሎምቢያ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እየፈጠርኩ ነውና፤ የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታወሱም፤ ወደ ልብም አይገቡም።”—ኢሳይያስ 65:17 የግርጌ ማስታወሻ
ይህን ማወቅ ምን ጥቅም አለው? “ወታደር ሳለሁ ባሳለፍኩት አሰቃቂ ነገር የተነሳ በኃይለኛ ጭንቀትና በድባቴ እሠቃያለሁ። ሆኖም ይህ ጥቅስ ይሖዋ በቅርቡ የሚረብሹኝን ሐሳቦች ጸጥ እንደሚያሰኝልኝና ቅዠቶቼን እንደሚያስወግድልኝ ያስታውሰኛል። እነዚህ ነገሮች ከልቤና ከአእምሮዬ ይጠፋሉ። ይህ እንዴት ያለ ግሩም ስጦታ ነው!”—ዘፊራ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በእሱ ዘመን ጻድቅ ይለመልማል፤ ጨረቃም በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሰላም ይበዛል።”—መዝሙር 72:7
ይህን ማወቅ ምን ጥቅም አለው? “ይህን ጥቅስ ብዙ ጊዜ አስታውሰዋለሁ። በቅርቡ የጦርነት ሰቆቃ ይወገዳል፤ ያኔ ስለ ቤተሰቦቻችንና ስለ ጓደኞቻችን ደህንነት መጨነቅ አያስፈልገንም።”—ኦሌክሳንድራ፣ ዩክሬን
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ። . . . እናንተ በአፈር ውስጥ የምትኖሩ፣ ተነሱ፤ በደስታም እልል በሉ!”—ኢሳይያስ 26:19
ይህን ማወቅ ምን ጥቅም አለው? “በቱትሲዎች ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በተካሄደበት ወቅት ሁሉም ቤተሰቦቼ ተገድለዋል። ሆኖም ይህ ጥቅስ ቤተሰቦቼን ዳግመኛ እንደማገኛቸው ዋስትና ይሰጠኛል። ከሞት ተነስተው በደስታ እልል ሲሉ ለመስማት እጓጓለሁ።”—ማሪ፣ ሩዋንዳ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም። . . . የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:10, 11
ይህን ማወቅ ምን ጥቅም አለው? “ጦርነቱ ያበቃ ቢሆንም ኢፍትሐዊ ድርጊቶችና ክፉ ሰዎች አሁንም አሉ። ይህ ጥቅስ በጣም ረድቶኛል። ይሖዋ ሁሉንም ነገር ያያል፤ ያለሁበትን ሁኔታም ያስተውላል። በቅርቡ ይህ ሁሉ መከራ እንደሚወገድና እንደሚረሳ ቃል ገብቷል።”—ዴለር፣ ታጂኪስታን
በዚህ መጽሔት ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሰላም እንዲያገኙ ከረዳቸው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች የዘር፣ የብሔርና የጎሣን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ጥላቻ ማሸነፍ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ተምረዋል። (ኤፌሶን 4:31, 32) በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኞች ናቸው፤ እንዲሁም በማንኛውም የዓመፅ ድርጊት ለመካፈል ፈቃደኞች አይደሉም።—ዮሐንስ 18:36
በተጨማሪም በመላው ዓለም ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንድ አፍቃሪ ቤተሰብ እርስ በርስ ይደጋገፋሉ። (ዮሐንስ 13:35) ለምሳሌ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኦሌክሳንድራ በጦርነት ምክንያት ከእህቷ ጋር ወደ ሌላ አገር ለመሰደድ ተገዳ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ልክ ድንበሩን እንደተሻገርን እኛን ሊቀበሉ የመጡ የይሖዋ ምሥክሮችን አገኘን። የእነሱ ድጋፍ፣ ተሰደን በመጣንበት አገር የጀመርነውን አዲስ ሕይወት እንድንለምድ ረድቶናል።”
በስብሰባዎቻችን ላይ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ሰላም የሚያስገኝ መልእክት እንዲሁም ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ የምንችልበትን መንገድ እንማራለን። አንተንም በስብሰባዎቻችን ላይ እንድትገኝ እንጋብዝሃለን። በምትኖርበት አካባቢ ስብሰባ የሚካሄድበትን ቦታ ለማወቅ ወይም ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኝተህ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመን በነፃ የምንሰጠውን አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስ ለመውሰድ jw.orgን ተመልከት።