የጥናት ርዕስ 45
መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች
ሌሎችን ስታስታምሙ ደስታችሁን ጠብቁ
“በእንባ የሚዘሩ፣ በእልልታ ያጭዳሉ።”—መዝ. 126:5
ዓላማ
አረጋውያንን የሚንከባከቡና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን የሚያስታምሙ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ለየት ያሉ ችግሮች መቋቋምና ደስታቸውን ጠብቀው መኖር የሚችሉት እንዴት ነው?
1-2. ሌሎችን የሚንከባከቡ ሰዎችን ይሖዋ እንዴት ይመለከታቸዋል? (ምሳሌ 19:17) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
በኮሪያ የሚኖር ጂን-ዮል የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ለ32 ዓመታት በትዳር ቆይተናል። ላለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ ሳስታምማት ቆይቻለሁ። ፓርኪንሰንስ የተባለ ሕመም ስላለባት መንቀሳቀስ ይከብዳታል። ባለቤቴን በጣም እወዳታለሁ፤ እሷን መንከባከብም ያስደስተኛል። የምትተኛው ቤታችን ውስጥ ባለ የሆስፒታል አልጋ ላይ ነው። እኔም እሷ አጠገብ እተኛለሁ፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን ነው የምንተኛው።”
2 አንተስ የምትወደውን ሰው ለምሳሌ ወላጆችህን፣ የትዳር አጋርህን፣ ልጅህን ወይም ጓደኛህን እያስታመምክ ነው? ከሆነ፣ እነሱን ልዩ በሆነ መንገድ የመርዳት አጋጣሚ በማግኘትህ እንደምትደሰት ጥርጥር የለውም። የምትወዳቸውን ሰዎች ስትንከባከብ ለይሖዋ ያደርክ መሆንህንም እያሳየህ ነው። (1 ጢሞ. 5:4, 8፤ ያዕ. 1:27) ሆኖም ሌሎች ሰዎች የማያስተውሏቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እነዚህን ችግሮች ብቻህን እየተጋፈጥክ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ከሰዎች ጋር ስትሆን ደስተኛ ትመስላለህ፤ ብቻህን ስትሆን ግን እንባህን መቆጣጠር ሊያቅትህ ይችላል። (መዝ. 6:6) ያለብህን ትግል ሌሎች ባያስተውሉትም እንኳ ይሖዋ ሁልጊዜ ስሜትህን ይረዳልሃል። (ከዘፀአት 3:7 ጋር አወዳድር።) እንባህንና የምትከፍለውን መሥዋዕት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (መዝ. 56:8፤ 126:5) የምትወዳቸውን ሰዎች ለመንከባከብ የምታደርገውን እያንዳንዱን ነገር ይመለከታል። ለእነሱ የምታደርገውን ነገር ለእሱ እንዳበደርክ አድርጎ ይቆጥረዋል፤ ደግሞም ወሮታህን እንደሚከፍልህ ቃል ገብቷል።—ምሳሌ 19:17ን አንብብ።
የምትወደውን ሰው እያስታመምክ ነው? (አንቀጽ 2ን ተመልከት)
3. አብርሃምና ሣራ ታራን ሲንከባከቡ ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው ሊሆን ይችላል?
3 መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎችን ስለተንከባከቡ ወንዶችና ሴቶች የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎችን ይዟል። የአብርሃምንና የሣራን ምሳሌ እንመልከት። ዑርን ለቀው ሲወጡ አባታቸው ታራ ዕድሜው 200 ዓመት ነበር። ያም ቢሆን አብሯቸው ሄዷል። ወደ ካራን ለመሄድ 960 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዘዋል። (ዘፍ. 11:31, 32) አብርሃምና ሣራ ታራን ይወዱት እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም፤ ሆኖም በተለይ በጉዞ ወቅት እሱን መንከባከብ ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል አስበው። ይጓዙ የነበረው በግመል ወይም በአህያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ደግሞ በዕድሜ ለገፋው ለታራ በጣም አስቸጋሪ መሆን አለበት። በዚህ ወቅት ከባድ ድካም ቢሰማቸው ወይም ቢዝሉ የሚያስገርም አይደለም። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ጥንካሬ እንደሰጣቸው ጥርጥር የለውም። ይሖዋ አብርሃምንና ሣራን እንደደገፋቸው ሁሉ አንተንም ይደግፍሃል፤ እንዲሁም ያጠነክርሃል።—መዝ. 55:22
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
4 ደስተኛ መሆንህ ሌሎችን ስትንከባከብ እንድትጸና ሊረዳህ ይችላል። (ምሳሌ 15:13) ያለህበት ሁኔታ ከባድ ቢሆንም ደስተኛ ሆነህ መቀጠል ትችላለህ። (ያዕ. 1:2, 3) ታዲያ እንዲህ ያለውን ደስታ ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ወደ ይሖዋ መጸለይና አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ እንዲረዳህ መጠየቅ ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ አስታማሚዎች ደስታቸውን ለመጠበቅ ማድረግ የሚችሏቸውን ሌሎች ነገሮች እንመለከታለን። በተጨማሪም ሌሎች እነሱን መርዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እናያለን። በመጀመሪያ ግን አስታማሚዎች ደስታቸውን መጠበቅ የሚያስፈልጋቸው ለምን እንደሆነና ደስታቸውን ሊሰርቋቸው የሚችሉት ተፈታታኝ ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ እንመልከት።
ሌሎችን ማስታመም ደስታህን ሊያሳጣህ የሚችለው እንዴት ነው?
5. አስታማሚዎች ደስታቸውን መጠበቅ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
5 አስታማሚዎች ደስታቸውን ካጡ በቀላሉ ሊታክቱ ይችላሉ። (ምሳሌ 24:10) ከታከቱ ደግሞ ደግነት ማሳየትና በአግባቡ ማስታመም ሊከብዳቸው ይችላል። ታዲያ አስታማሚዎች ደስታቸውን እንዲያጡ ሊያደርጓቸው የሚችሉት ተፈታታኝ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?
6. አንዳንድ አስታማሚዎች እንዲዝሉ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
6 አስታማሚዎች ሊዝሉ ይችላሉ። ሊያ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “የተለየ ችግር ባይኖርም እንኳ ሌሎችን ማስታመም በራሱ ስሜትን የሚያዝል ነገር ነው። ብዙውን ጊዜ በቀኑ መጨረሻ ላይ አቅሜ ሙሉ በሙሉ እንደተሟጠጠ ይሰማኛል። አንዳንዴ የጽሑፍ መልእክት ለመመለስ እንኳ አቅም አጣለሁ።” ሌሎች ደግሞ በቂ እረፍት ማግኘት እንዲሁም ለራሳቸው ጊዜ መስጠት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ኢኔስ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በቂ እንቅልፍ ለማግኘት እቸገራለሁ። ብዙውን ጊዜ ሌሊት ላይ አማቴን ለመንከባከብ በየሁለት ሰዓቱ መነሳት ያስፈልገኛል። እኔና ባለቤቴ ወጣ ብለን ከተዝናናን ብዙ ዓመት ሆኖናል።” አንዳንድ አስታማሚዎች የሚያስታምሙት ሰው የሙሉ ጊዜ እንክብካቤ ስለሚያስፈልገው ማኅበራዊ ግብዣዎችን ብሎም ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን መቀበል አይችሉም። በዚህም የተነሳ በብቸኝነት ስሜት ሊሠቃዩና እስረኞች እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል።
7. አንዳንድ አስታማሚዎች በጥፋተኝነት ስሜትና በሐዘን የሚዋጡት ለምንድን ነው?
7 አስታማሚዎች በከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜትና በሐዘን ሊዋጡ ይችላሉ። ጄሲካ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ካሉብኝ የአቅም ገደቦች ጋር እታገላለሁ። ለራሴ ጊዜ ስሰጥ በጥፋተኝነት ስሜት እዋጣለሁ፤ እንዲሁም ራስ ወዳድ እንደሆንኩ ይሰማኛል።” አንዳንድ አስታማሚዎች ባሉበት ሁኔታ በመማረራቸው ምክንያት የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ ለሚያስታምሙት ሰው በቂ እንክብካቤ እንዳላደረጉ ይሰማቸዋል። ውጥረት ውስጥ በገቡበት ወቅት የሚንከባከቡትን ሰው የሚጎዳ ነገር በመናገራቸው የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማቸውም አሉ። (ያዕ. 3:2) አንዳንዶች በአንድ ወቅት ጤናማና ጠንካራ ሆኖ የሚያውቁት ሰው እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሱ በሐዘን ይዋጣሉ። ባርባራ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በጣም የከበደኝ የምወዳት ጓደኛዬ ሁኔታ ዕለት ዕለት እያሽቆለቆለ ሲሄድ መመልከት ነው።”
8. ጥቂት የምስጋና ቃላት በአስታማሚዎች ስሜት ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
8 አንዳንድ አስታማሚዎች ሌሎች ጥረታቸውን እንደማያደንቁ ሊሰማቸው ይችላል። ለምን? ለልፋታቸውና ለሚከፍሉት መሥዋዕትነት ብዙ ጊዜ ስለማይመሰገኑ ነው። ጥቂት የምስጋና ቃላት እንኳ መስማታቸው በስሜታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። (1 ተሰ. 5:18) ሜሊሳ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ተስፋ ቆርጬ የማለቅስባቸው ጊዜያት አሉ። ሆኖም የምንከባከባቸው ሰዎች ‘ለምታደርጊልኝ ነገር ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ’ ሲሉኝ መንፈሴ ይታደሳል። እንዲህ ያለው ምስጋና በቀጣዩ ቀን እነሱን በድጋሚ ለመንከባከብ እንድነሳሳ ያደርገኛል።” አማዱ የተባለ ወንድም የምስጋና ቃላት መስማቱ በስሜቱ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ ተናግሯል። እሱና ባለቤቱ አብራቸው የምትኖረውን የባለቤቱን የእህቷን ልጅ ይንከባከባሉ፤ ልጅቷ በሚጥል በሽታ ትሠቃያለች። አማዱ እንዲህ ብሏል፦ “ምንም እንኳ እሷን ለመንከባከብ ስንል ምን ያህል መሥዋዕትነት እየከፈልን እንዳለ ሙሉ በሙሉ ባይገባትም አድናቆቷን ስትገልጽልን ወይም ‘እወዳችኋለሁ’ ብላ ስትጽፍልን ልቤ በደስታ ይሞላል።”
ደስተኛ ሆነህ መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው?
9. አስታማሚዎች ልካቸውን እንደሚያውቁ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
9 ልክህን የምታውቅ ሁን። (ምሳሌ 11:2) ሁላችንም ጊዜያችንና ጉልበታችን ውስን ነው። በመሆኑም ማድረግ ስለምትችለውና ስለማትችለው ነገር ገደብ ማበጀት ይኖርብሃል። አልፎ አልፎ ደግሞ “አልችልም” ማለት ያስፈልግሃል። ደግሞም እንዲህ ማድረግህ ምንም ችግር የለውም! እንዲያውም ልክህን የምታውቅ መሆንህን ያሳያል። ሌሎች ሊያግዙህ ከፈለጉ እርዳታቸውን በደስታ ተቀበል። ጄይ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ጊዜ ማድረግ የምንችለው ነገር የተወሰነ ነው። ያለብህን ገደብ አምነህ በመቀበልና ከዚያ አልፈህ ባለመሄድ ደስታህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ።”
10. አስታማሚዎች አስተዋይ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 19:11)
10 አስተዋይ ሁን። (ምሳሌ 19:11ን አንብብ።) አስተዋይ ከሆንክ የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥምህ መረጋጋት ቀላል ይሆንልሃል። አስተዋይ ሰው፣ አንድ ሰው ከሚያሳየው ምግባር በስተ ጀርባ ያለው ምክንያት ምን እንደሆነ ለማስተዋል ጥረት ያደርጋል። አንዳንድ ሥር የሰደዱ በሽታዎች አንድ ሰው ያልተገባ ባሕርይ እንዲያሳይ ሊያደርጉ ይችላሉ። (መክ. 7:7) ለምሳሌ ደግና አሳቢ የነበረ ሰው ተጨቃጫቂና ጠብ አጫሪ ሊሆን ይችላል። ወይም አጉረምራሚ፣ ተቺ እንዲሁም በቀላሉ የማይደሰት ሊሆን ይችላል። ከባድ ሕመም ያለበትን ሰው እያስታመምክ ከሆነ ስለ በሽታው ይበልጥ ለማወቅ ጥረት ማድረግህ ሊጠቅምህ ይችላል። ስለ በሽታው የበለጠ ስታውቅ የግለሰቡ ምግባር የባሕርይ ችግር ሳይሆን ከበሽታው ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነ ልትገነዘብ ትችላለህ።—ምሳሌ 14:29
11. አስታማሚዎች በየቀኑ ለየትኞቹ አስፈላጊ ነገሮች ጊዜ መመደብ አለባቸው? (መዝሙር 132:4, 5)
11 ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ለማጠናከር ጊዜ መድብ። አንዳንድ ጊዜ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ለማድረግ ስንል አንዳንድ ነገሮችን መተው ያስፈልገናል። (ፊልጵ. 1:10) ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ማጠናከር ነው። ንጉሥ ዳዊት ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። (መዝሙር 132:4, 5ን አንብብ።) አንተም በቀን ውስጥ የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለማንበብና ለመጸለይ ጊዜ መመደብህ አስፈላጊ ነው። ኤሊሻ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “መጸለዬና መዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ባሉ አጽናኝ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰሌ ደስታዬን ጠብቄ እንድኖር አስችሎኛል። ቆሜ የምሄደው በጸሎት ነው። መረጋጋት እንድችል በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ።”
12. አስታማሚዎች ጤናቸውን ለመንከባከብ ጊዜ መመደብ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
12 አካላዊ ጤንነትህን ለመንከባከብ ጊዜ መድብ። አስታማሚዎች ብዙ ሥራ ስላለባቸው ጤናማ አመጋገብ መከተል ከባድ ይሆንባቸዋል። ምክንያቱም አስቤዛ ለመሸመትና ገንቢ ምግብ ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ አይኖራቸውም። ጤናማ ምግብ መመገብና አዘውትሮ እንቅስቃሴ ማድረግ ለአካላዊም ሆነ ለአእምሯዊ ጤንነትህ በጣም አስፈላጊ ናቸው። በመሆኑም ያለህ ጊዜ የተጣበበ ቢሆንም እንኳ ጤናማ ምግብ ለመመገብና አዘውትረህ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት አድርግ። (ኤፌ. 5:15, 16) በተጨማሪም በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ሞክር። (መክ. 4:6) አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንቅልፍ ከአንጎላችን መርዛማ ነገሮችን ለማስወገድ ይረዳል። አንድ የጤና ድርጅት “እንቅልፍ በውጥረት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። እዚያ ላይ እንደተገለጸው በቂ እንቅልፍ ማግኘት ጭንቀትን ለመቀነስ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ውጥረትን የመቋቋም ችሎታችንን ያሳድግልናል። ለመዝናኛም የተወሰነ ጊዜ መመደብ ይኖርብሃል። (መክ. 8:15) አንዲት አስታማሚ ደስተኛ ሆና ለመቀጠል የረዳትን ነገር ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “አየሩ ጥሩ ሲሆን ወደ ውጭ ወጥቼ ፀሐይ እሞቃለሁ። በተጨማሪም በወር አንዴ ከጓደኛዬ ጋር ለመዝናናት ጊዜ እመድባለሁ።”
13. መሳቅ ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 17:22)
13 አጋጣሚዎች ፈልገህ ሳቅ። (ምሳሌ 17:22ን አንብብ፤ መክ. 3:1, 4) መሳቅ ለአካላዊም ሆነ ለአእምሯዊ ጤንነትህ ጠቃሚ ነው። አንድን ሰው ስትንከባከብ ብዙውን ጊዜ ነገሮች በጠበቅከው መንገድ አይሄዱም። ሆኖም በሚያበሳጩ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ የሚያስቅ ነገር ከፈለግክ ሁኔታውን መቋቋም ቀላል ይሆንልሃል። ከምታስታምመው ሰው ጋር አብረህ መሳቅህ ደግሞ ዝምድናችሁን ያጠናክረዋል።
14. ለምታምነው ወዳጅህ የልብህን አውጥተህ መናገርህ የሚረዳህ እንዴት ነው?
14 ለምታምነው ጓደኛህ የልብህን ንገረው። ደስተኛ ለመሆን ጥረት ብታደርግም አልፎ አልፎ ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ለምታምነው ጓደኛህ ስሜትህን አውጥተህ መናገርህ ሊረዳህ ይችላል። እንዲህ ያለው ወዳጅ ስሜትህን ስትገልጽ አይታዘብህም ወይም አይኮንንህም። (ምሳሌ 17:17) ጓደኛህ በጥሞና ሲያዳምጥህ እንዲሁም በሚያጽናኑ ቃላት ሲያበረታታህ ደስታህን ለመጠበቅ ቀላል ይሆንልሃል።—ምሳሌ 12:25
15. በተስፋው ላይ ማተኮርህ ደስታ የሚያስገኝልህ እንዴት ነው?
15 በገነት ውስጥ አብራችሁ የሚኖራችሁን ሕይወት በዓይነ ሕሊናህ ሣል። የአስታማሚነት ኃላፊነትህ ጊዜያዊ እንደሆነ ለማስታወስ ሞክር። ሌሎችን ማስታመም በይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማ ውስጥ አልነበረም። (2 ቆሮ. 4:16-18) ‘እውነተኛ የሆነው ሕይወት’ ወደፊት እየጠበቀህ ነው። (1 ጢሞ. 6:19) ከምትንከባከበው ሰው ጋር በገነት ውስጥ አብራችሁ ምን እንደምታከናውኑ ማውራትህ ትልቅ ደስታ ሊያስገኝልህ ይችላል። (ኢሳ. 33:24፤ 65:21) ሄዘር የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ለምንከባከባቸው ሰዎች በቅርቡ አብረን ልብስ እንደምንሰፋ፣ አብረን እንደምንሮጥ እንዲሁም አብረን ብስክሌት እንደምንነዳ እነግራቸዋለሁ። ከሞት ለሚነሱት ወዳጆቻችን ዳቦ እንደምንጋግር እንዲሁም ምግብ እንደምናበስል እናወራለን። ከዚያም ይሖዋ እንዲህ ያለ ተስፋ ስለሰጠን አብረን እናመሰግነዋለን።”
ሌሎች እርዳታ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?
16. በጉባኤያችን ያለን አስታማሚ ልንረዳ የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
16 አስታማሚዎች ለራሳቸው ጊዜ እንዲያገኙ እርዷቸው። በጉባኤ ውስጥ ያለን ወንድሞችና እህቶች ታማሚውን በመንከባከብ አስታማሚውን መርዳት እንችላለን። ይህም አስታማሚዎች አእምሯቸው እንዲያርፍና ለግል ጉዳዮቻቸው ጊዜ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። (ገላ. 6:2) አንዳንድ አስፋፊዎች እንዲህ ለማድረግ ሳምንታዊ ፕሮግራም አውጥተዋል። መራመድ የማይችለውን ባለቤቷን የምትንከባከብ ናታሊያ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በጉባኤያችን ያለ አንድ ወንድም በሳምንት አንዴ ወይም ሁለቴ ቤታችን እየመጣ ከባለቤቴ ጋር ጊዜ ያሳልፋል። አብረው ያገለግላሉ፣ አብረው ያወራሉ እንዲሁም አብረው ፊልም ያያሉ። ባለቤቴ ከእሱ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ በጣም ያስደስተዋል። እኔም ወክ ለማድረግ እንዲሁም ሌሎች የግል ጉዳዮቼን ለማከናወን ጊዜ አገኛለሁ።” አንዳንዴ ደግሞ ታማሚውን እየተንከባከባችሁ ለማደር ራሳችሁን ልታቀርቡ ትችላላችሁ። ይህም አስታማሚው በቂ እንቅልፍ እንዲያገኝ ያስችላል።
በጉባኤያችሁ ውስጥ ያለን አንድ አስታማሚ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? (አንቀጽ 16ን ተመልከት)a
17. በጉባኤ ስብሰባ ወቅት አስታማሚዎችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
17 በጉባኤ ስብሰባዎች ወቅት አስታማሚዎችን አግዙ። አስታማሚዎች በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ወቅት ታማሚውን ስለሚንከባከቡ ከስብሰባው የተሟላ ጥቅም ማግኘት አይችሉም። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች በእነዚህ ስብሰባዎች ወቅት ቢያንስ ለተወሰነ ሰዓት ከታማሚው ጋር አብረው በመቀመጥ እርዳታ ማበርከት ይችላሉ። ታማሚው ከቤት መውጣት የማይችል ከሆነ ደግሞ ቤቱ ሄዳችሁ በስልክ ወይም በቪዲዮ ስብሰባውን አብራችሁ ለመከታተል ልታመቻቹ ትችላላችሁ። ይህም አስታማሚው በስብሰባ ላይ በአካል እንዲገኝ ሊረዳው ይችላል።
18. አስታማሚዎችን ለመርዳት ሌላስ ምን ማድረግ እንችላለን?
18 አስታማሚዎችን አመስግኗቸው እንዲሁም ጸልዩላቸው። ሽማግሌዎች ለአስታማሚዎች አዘውትረው እረኝነት ማድረጋቸው ጠቃሚ ነው። (ምሳሌ 27:23) ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን፣ በጉባኤ ውስጥ ያለን ሁላችንም አስታማሚዎችን አዘውትረን ማመስገን እንችላለን። በተጨማሪም ይሖዋ እንዲያጠነክራቸውና ደስታቸውን ለመጠበቅ እንዲረዳቸው መጸለይ እንችላለን።—2 ቆሮ. 1:11
19. ወደፊት ምን ይጠብቀናል?
19 በቅርቡ ይሖዋ ከሁሉም ሰው ፊት ላይ እንባን ያብሳል። ሕመምና ሞት ፈጽሞ አይኖርም። (ራእይ 21:3, 4) “አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል።” (ኢሳ. 35:5, 6) በእርጅና ምክንያት የሚመጣው መከራና የሚወዱትን ሰው ማስታመም የሚያስከትለው ሥቃይ ‘ከማይታወሱት የቀድሞዎቹ ነገሮች’ ውስጥ ይካተታሉ። (ኢሳ. 65:17 ግርጌ) የዚህን አስደናቂ ተስፋ ፍጻሜ በምንጠባበቅበት በአሁኑ ጊዜም ይሖዋ ፈጽሞ አይተወንም። ብርታት እንዲሰጠን በእሱ መታመናችንን ከቀጠልን “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት [እንድንቋቋም]” ይረዳናል።—ቆላ. 1:11
መዝሙር 155 የዘላለም ደስታ
a የሥዕሉ መግለጫ፦ ሁለት ወጣት እህቶች አንዲትን አረጋዊት እህት ሄደው ሲጠይቁ፤ ይህም አስታማሚዋ ወክ ለማድረግ ጊዜ እንድታገኝ አስችሏታል።