የሰላም ማስከበር ጥረቶች ለዓለም ሰላም ያመጡ ይሆን?
ዓለማችን ማባሪያ በሌላቸው ጦርነቶችና የትጥቅ ግጭቶች እየታመሰች ነው። በዚህም የተነሳ የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ድርጅቶች የሰላም ማስከበርa ተልእኮዎችን ያከናውናሉ፤ ለዚህም ሲባል ችግር ወዳለባቸው አካባቢዎች ሰዎች ይልካሉ። ዓላማቸው ግጭት የተፈጠረባቸውን አካባቢዎች ማረጋጋት ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዲህ ብለዋል፦ “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ሰላም ለማምጣት ለያዝነው ግብ የልብ ምት ናቸው።”
ባለፉት ዓመታት የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች መጠነኛ ስኬት አስገኝተዋል። ለምሳሌ ለንጹሐን ዜጎች ከለላ አድርገዋል፣ ስደተኞችን ወደ አገራቸው መልሰዋል፣ ሰብዓዊ እርዳታ አድርሰዋል እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸውን መሠረተ ልማቶች ጠግነዋል። ይሁንና የሰላም ማስከበር ጥረቶች የታለመላቸውን ያህል ስኬት እንዳያስገኙ እንቅፋት የሚሆኑባቸው ከባድ ተግዳሮቶች አሉ። ታዲያ ለዓለም እውነተኛ ሰላም የሚያስገኝ ዘላቂ መፍትሔ የለም ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምን መልስ ይሰጣል?
የሰላም ማስከበር ተግዳሮቶችና የመጽሐፍ ቅዱስ መፍትሔዎች
ተግዳሮት፦ የትብብር ማነስ። የሰላም ማስከበር ሥራ በአብዛኛው ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ብዙ ተቋማትን ትብብር የሚጠይቅ ነው፤ ይሁንና እነዚህ ወታደራዊም ሆኑ የሲቪል ተቋማት እንዲተባበሩ ማድረግ ቀላል አይደለም። አንዳቸው ሌላውን በተሳሳተ መንገድ በመረዳታቸው ወይም ቅድሚያ የሚሰጡት ነገር በመለያየቱ የተነሳ አብረው መሥራት የሚቸገሩባቸው ጊዜያት አሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መፍትሔ፦ “የሰማይ አምላክ . . . መንግሥት ያቋቁማል። . . . እነዚህን [የሰዎች] መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።”—ዳንኤል 2:44
በቅርቡ አምላክ ጦርነትን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል፤ እንዲሁም በመላው ዓለም ላይ ሰላም ያሰፍናል። (መዝሙር 46:8, 9) ምድር ላይ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ አጥፍቶ በአንድ መንግሥት ይኸውም በአምላክ መንግሥት ይተካቸዋል። ከጦርነት የጸዳችውን ምድራችንን የሚያስተዳድረው በሰማይ ያለው ይህ ፍጹም መንግሥት ብቻ ይሆናል፤ በመሆኑም ያን ጊዜ ሰዎች ያቋቋሟቸው ሰላም አስከባሪ ተቋማት አያስፈልጉም።
ተግዳሮት፦ የግብዓትና የሰው ኃይል ማነስ። የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች የሰው ኃይል፣ የገንዘብ እንዲሁም የሌሎች ግብዓቶች እጥረት የሚያጋጥማቸው ጊዜ አለ፤ ይህም የሥራቸውን ውጤታማነት ይቀንሰዋል። ሰላም አስከባሪ ልዑካን በሚሄዱባቸው ቦታዎች ደግሞ ሁኔታዎቹ ይበልጥ ውስብስብና አደገኛ እየሆኑ መጥተዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መፍትሔ፦ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ . . . ክርስቶስን ከሞት [አስነስቶ] በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ [አስቀምጦታል]፤ . . . ከየትኛውም መስተዳድር፣ ሥልጣን፣ ኃይልና ጌትነት . . . በላይ እጅግ የላቀ ቦታ ሰጥቶታል።”—ኤፌሶን 1:17, 20, 21
ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋb የመንግሥቱ ንጉሥ አድርጎ ለሾመው ለኢየሱስ ለሥራው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ ሰጥቶታል። (ዳንኤል 7:13, 14c) አምላክ ለኢየሱስ የሰጠው ሥልጣን፣ እውቀት፣ ጥበብና ማስተዋል ከየትኛውም ሰብዓዊ መንግሥት ወይም ድርጅት የላቀ ነው። (ኢሳይያስ 11:2) በተጨማሪም ኢየሱስ ትእዛዙን የሚፈጽሙ ኃያላን መላእክትን ያቀፈ ሠራዊት አለው። (ራእይ 19:14) እሱን ሊፈታተን የሚችል አንድም ውስብስብ ወይም ከባድ ችግር የለም።
ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠውን አቅምና ግብዓት ተጠቅሞ የሚያከናውነው ሥራ ግጭቶችን በማስወገድ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከዚህም ባለፈ በእሱ አገዛዝ ሥር ሁሉም ሰው እውነተኛ ጸጥታ፣ ደህንነትና ሰላም እንዲያገኝ ያደርጋል።—ኢሳይያስ 32:17, 18
ተግዳሮት፦ ሕግ ነክ ገደቦች። ሰላም አስከባሪ ልዑካን ተልእኳቸውን በግልጽ የሚያስቀምጥ መመሪያ የማያገኙበት ጊዜ አለ፤ ወይም ደግሞ እንቅስቃሴያቸውንና ተግባራቸውን በነፃነት እንዳያከናውኑ የሚያደርጉ ሕጋዊ ገደቦች ይገጥሟቸው ይሆናል። ሕጉ ላይ ባሉት በእነዚህ ገደቦች የተነሳ የሚያስቡትን ያህል ለንጹሐን ዜጎች ከለላ ማድረግ ወይም ተልእኳቸውን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ይቸገራሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መፍትሔ፦ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል።”—ማቴዎስ 28:18
አምላክ፣ ተልእኮው ዓለም አቀፍ ሰላም ማምጣት እንደሆነ ለኢየሱስ በግልጽ አስቀምጦለታል፤ ይህን ለማሳካት የሚያስችለውን ሙሉ ሥልጣንም ሰጥቶታል። (ዮሐንስ 5:22) ኢየሱስ መቼም ቢሆን ፍርድ አያዛባም ወይም ሥልጣኑን አላግባብ አይጠቀምበትም። (ኢሳይያስ 11:3-5) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “የሰላም መስፍን” እንደሚባል፣ መንግሥቱም “በፍትሕና በጽድቅ” ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን መናገሩ በእርግጥም እውነት ነው።—ኢሳይያስ 9:6, 7
የአምላክ መንግሥት—እውነተኛ የሰላም ኃይል
ሰዎች የሚያቋቁሟቸው ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ተሳካላቸው ቢባል እንኳ የተወሰነ መረጋጋት ቢያመጡ ነው፤ ምናልባትም በአንዳንድ አካባቢዎች የትጥቅ ግጭት እንዲያቆም ማድረግ ይችሉ ይሆናል። ለጠቡ መነሻ የሆነውን ነገር ግን ማስወገድ አይችሉም፤ ይህም በብዙ ሰዎች ልብ ውስጥ የታመቀው ጥላቻ ነው።
“ዋነኛው ችግራችን ቀድሞውኑም ሰላም በሌለበት ሰላም ለማስከበር መሞከራችን ነው።”—ዴኒስ ጄት፣ የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ አምባሳደር
በሌላ በኩል ግን የአምላክ መንግሥት እውነተኛ ሰላም ማምጣት ይችላል፤ ምክንያቱም ሰዎች ጥላቻን ከልባቸው ነቅለው እንዲያወጡ ይረዳል። ለምሳሌ ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ያደረገውን አስታውስ፤ ተከታዮቹ ሰላም እንዲፈጥሩና ፍቅር እንዲያሳዩ በንግግርም ሆነ ምሳሌ በመሆን አስተምሯቸዋል፦
በተጨማሪም ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ለሌሎች በሚያሳዩት ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። የአምላክ መንግሥት ባልንጀራቸውን የሚጠሉ ሰዎችን እንደማይታገሥ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል፦
የሰውን ዘር የፈጠረው ይሖዋ ለዓለም ሰላም የሚያመጣው ከሁሉ የተሻለውና ብቸኛው መፍትሔ ምን እንደሆነ ያውቃል። የእሱ መንግሥት፣ የሰላም ማስከበር ጥረቶችን ጨምሮ ሰዎች ሞክረው ያላሳኳቸውን ነገሮች ሁሉ ያሳካል።
a የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ድርጅቶች የሚጠቀሙባቸው ሌሎች ተያያዥ አገላለጾችም አሉ፤ ለምሳሌ “ሰላም ግንባታ” እና “የሰላም ተልእኮ።”
b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c ዳንኤል 7:13, 14 ላይ “የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—ማቴዎስ 25:31፤ 26:63, 64