ተገዶ መደፈር እውነተኛው ሁኔታ ምንድን ነው?
ይህን ገጽ አንብበህ ለመጨረስ በሚሰውድብህ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንዲት ሴት ተገዳ ትደፈራለች። ብቻዋን ሆና፣ ምናልባትም ከዚያ በፊት የምታውቀው ሰው በፈጸመባት ዓመፅና ባደረሰባት ውርደት በፍርሃት ትርበተበታለች። ተደብድባ ሊሆን ይችላል። የደረሰባትን ጥቃት ለመቃወም ጥረት አድርጋ ይሆናል። ለሕይወቷ እንደምትሰጋ አያጠራጥርም።
አስገድዶ መድፈር በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፍጥነት በመዛመት ላይ ያለ ወንጀል ነው። በመሆኑም በዓለም ላይ አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎች በከፍተኛ ደረጃ ከሚፈጸምባቸው አገሮች አንዷ ዩናይትድ ስቴትስ ሆናለች። በፖሊስ ዘገባ መሠረት በእያንዳንዱ ሰዓት በ16 ሴቶች ላይ አስገድዶ የመድፈር ሙከራ ሲፈጸም 10 ሴቶች ደግሞ ተገደው ይደፈራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሪፖርት የማይደረጉ አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎች ከዚህ በአሥር እጥፍ የሚበልጡ መሆናቸው ቁጥሩ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ለመገመት ያስችላል!
ይህ ወንጀል በዚህ አስደንጋጭ መጠን ተስፋፍቶ የሚገኘው በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ አይደለም። በፈረንሳይ ከ1985 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት ውስጥ ተገደው እንደ ተደፈሩ ሪፖርት ያደረጉ ሰዎች ቁጥር 62 በመቶ ከፍ ብሏል። በ1990 በካናዳ በስድስት ዓመታት ውስጥ ብቻ የፆታ ጥቃት እንደ ደረሰባቸው ሪፖርት ያደረጉት ሰዎች ቁጥር በእጥፍ በመጨመር ወደ 27,000 ከፍ ብሏል። ጀርመን በየሰባት ደቂቃው በሴቶች ላይ የፆታ ጥቃት እንደሚደርስ ሪፖርት አድርጋለች።ተገዶ መደፈር ወንዶችም ላይ የሚደርስ ጥቃት ነው።a የሥነ ልቦና ተመራማሪ የሆኑት ኤልሳቤጥ ፖዌል ወንዶች “ከጠቅላላው ማኅበረሰብ ግማሽ የሚሆኑት ከሌሎች ለመራቅ፣ ሌሎችን ለመጠራጠርና ለመፍራት በሚገደዱበት ኅብረተሰብ ውስጥ በመኖራቸው ችግር ደርሶባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ሚስቶቻቸው፣ እናቶቻቸው፣ እህቶቻቸው፣ ሴት ልጆቻቸውና ጓደኞቻቸው ተገደው እንዳይደፈሩ ይሰጋሉ። የሚወዷቸው ሴቶች ተገደው ሲደፈሩ የሚሰማቸውን የጥፋተኝነት ስሜትና ኀዘን ለመቋቋም ይገደዳሉ።
ይህን ያህል የተስፋፋው ለምን ይሆን?
አስገድዶ መድፈር እጅግ የተስፋፋው ዓመፅንና ልቅ የሆነ የፆታ ሥነ ምግባርን በዝምታ በሚመለከቱ ኅብረተሰቦች ውስጥ ነው። በብዙ አገሮች ወንዶችና ሴቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ከመገናኛ ብዙሐን፣ ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከእኩዮቻቸው ስለ ፆታ የሚነገሩ አፍራሽ መልእክቶችና የተሳሳቱ መረጃዎች ውርጅብኝ ይዘንብባቸዋል። ይህም ሴቶች የሚኖሩት ፈለጉም አልፈለጉም የወንዶችን የፆታ ስሜት ለማርካት ስለሆነ የፆታ ግንኙነት ማድረግና አስገድዶ መድፈር ልዩነት የላቸውም የሚል መርዘኛ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጓል።
በመዝገብ ያዥነት የሚሠራ ጄይ የተባለ የ23 ዓመት ወጣት ያለውን አመለካከት እንውሰድ። “እውነተኛ ወንድ ለመሆን ከተለያዩ ሴቶች ጋር ብዙ ጊዜ የፆታ ግንኙነት ማድረግ አለብህ በሚል ኅብረተሰብ ውስጥ እንደሚኖር” ገልጿል። አክሎም “እንደሚባለው ባታደርግስ? ታዲያ ወንድነትህ ምኑ ላይ ነው?” ብሏል። በደረሰበት ግፊት ምክንያት እንዲህ ያለ አመለካከት ስላዳበረ አንዲት ሴት ካናደደችው ወይም ካበሳጨችው አስገድዶ ይደፍራታል ማለት ነው።
አስገድዶ ስለ መድፈር ምርምር ያደረጉት ሊንዳ ሌድሬይ አስገድዶ መድፈር በተለመደባቸው ባሕሎች ለሴቶች እንዲህ ያለ የዓመፅና የጭካኔ ጠባይ ማሳየት በጣም የተስፋፋ እንደሆነ ያምናሉ። እርሳቸውም “አስገድዶ የመድፈር ወንጀል የሚፈጽመው ሰው በኅብረተሰቡ ውስጥ በብዛት ተስፋፍቶ የሚገኘውን ዝንበሌ ያንጸባርቃል” ብለዋል። ፊልሞችና ቴሌቪዥኖች ደግሞ ለዚህ ማኅበራዊ ዝንባሌ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። አስገድዶ መድፈር ብልግናን በገሃድ በሚያሳዩ መጻሕፍትና መጽሔቶች ውስጥ ተጋንኖ ይቀርባል። ይሁን እንጂ እንዲህ ላለው የወንጀል ድርጊት በምክንያትነት የሚጠቀሱት ብልግናን በግልጽ የሚያሳዩት የወሲብ ጽሑፎች ብቻ አይደሉም። ከዓመፅ ነፃ ሆነው ወሲባዊ ድርጊቶችን በግልጽ ከሚያሳዩት ፊልሞች ይልቅ የፆታን ጉዳይ በቀጥታ ሳይጠቅሱ ዓመፅ የሚያሳዩ ፊልሞች በሴቶች ላይ የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙ ወንዶችን የሚያበረታቱ ሆነው መገኘታቸውን የተደረጉት ጥናቶች አረጋግጠዋል። ቴሌቪዥንም “በየቦታው በጣም ተስፋፍቶ የሚገኘውን ልቅ የፆታ ሥነ ምግባር በማሳየት በድርጊቱ ተካፋይ ሆኗል” ሲሉ ፖዌል ተናግረዋል። መገናኛ ብዙሐንስ የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው? “ስትናደድ ብስጭትህን በሌላው ላይ ተወጣ” የሚል ነው።
እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በሰዎች መካከል በሚደረጉ ዕለታዊ ግንኙነቶች ላይ አሳዛኝ ውጤቶች እያስከተለ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን ይህን ዓመፅ ዝም ብሎ በሚመለከተው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ወንዶች ብዙውን ጊዜ ያላቸው አመለካከት በተለይ ወንድዬው ለሴቷ ገንዘብ ካወጣ ወይም መጀመሪያ ላይ ሴትየዋ የወንድዬውን ፍላጎት የምትደገፍ ትመስል ከነበረ ሴቶች የፆታ ስሜቶቻችንን የማርካት ግዴታ አለባቸው የሚል ነው።
ሮቢን ዋርሻው የተባሉ ጋዜጠኛ “የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ ‘አልፈልግም’ የሚለው ቃል የተነገረው በሴቷ ከሆነ ምንም ዋጋ አይኖረውም” ብለዋል። ብዙውን ጊዜ ተገዶ መደፈርን ያስከትላል።
“ሁለተኛው መደፈር”
ኬቲ ትማርበት በነበረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሆኪ ስፖርት ቡድን አባሎች የሆኑ ሦስቱ ልጆች አስገድደው በደፈሯት ጊዜ 15 ዓመቷ ነበር። ቤተሰቦቿ ክስ መመሥረታቸው ሲታወቅ ጓደኞቿ፣ ጎረቤቶቿና አላፊ አግዳሚው ሁሉ በማንቋሸሽና ከማኅበራዊ ጉዳዮች በማግለል አበሳጯት። “ወንዶች ምን ጊዜም ወንዶች ናቸው” እያሉ ለቤተሰቦቿ ይናገሩ ነበር። በትምህርት ቤትም ኬቲን ጸያፍ አነጋገር ይናገሯትና በዴስኳ ሥርም የዛቻና የማስፈራሪያ መልእክት እየጻፉ ያስቀምጡ ነበር። ኬቲን የደፈሯት ልጆች በአመክሮ እንዲቆዩና በሕዝባዊ አገልግሎት እንዲቀጡ ተደረጉ። ከዚያም የትምህርት ቤቱ ዝነኛ ስፖርተኞች የመሆን ጥረታቸውን ቀጠሉ። ኬቲ በደረሰባት ብስጭት ለብዙ ወራት ተሠቃየች። በመጨረሻም ራሷን ገደለች።
በኬቲ ላይ የደረሰው አሳዛኝ ሁኔታ ተገደው የተደፈሩ ሴቶች በመጀመሪያ አስገድዶ በደፈራቸው ሰው አካላዊ፣ ቀጥሎም በሌሎች ሰዎች ስሜታዊ ጥቃት እንዴት እንደሚደርስባቸው የሚያሳይ ምሳሌ ነው። አስገድዶ ስለ መድፈር የተሳሳተና ከእውነታው የራቀ አመለካከት በመኖሩ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ለድርጊቱ ተጠያቂ ናቸው የሚል አስተሳሰብ እንዳለ ብዙ ሴቶች ይሰማቸዋል። ጓደኞች፣ የቤተሰብ አባሎች፣ ፖሊሶች፣ ሐኪሞችና ዳኞች ጉዳት የደረሰባቸውን መርዳት የሚገባቸው ሆነው ሳሉ የሚወሩትን የተሳሳቱ አመለካከቶች በመያዝ አስገድዶ የደፈራቸው ሰው ካደረሰባቸው የአካል ጉዳት ባላነሰ ሁኔታ ተገደው በተደፈሩ ሴቶች ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳሉ። ተገደው በተደፈሩ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ወቀሳ የሚፈጥረው ችግር በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሣ አንዳንዶች “ሁለተኛው መደፈር” ብለውታል።
አስገድዶ ስለ መድፈር የሚነገሩት ወሬዎች የተሳሳተ ግምት ስለሚያሳድሩ ያዘናጋሉ። በሌላ አባባል አንዲት ሴት ተገዳ የተደፈረችው ሰውነቷን የሚያሳይ ጥብቅ ያለ ልብስ ስለ ለበሰች ወይም በማታ ብቻዋን ስለ ሄደች ወይም ራሷ የፆታ ግንኙነት ማድረግ ስለ ፈለገች ነው የሚሉና እነዚህን የመሳሰሉ ስሕተቶችን ማግኘት ከተቻለ አንቺ ወይም የምታፈቅሪያቸው ሴቶች እንዲህ ካላደረጋችሁ በፍጹም አትደፈሩም የሚል እምነት ያሳድራል። ተገድዶ መደፈር አንዲት ሴት ምንም ዓይነት ልብስ ብትለብስና ድርጊቱን ምንም ያህል ብትጠላ ሳትፈልግ በግድ የሚፈጸምና በማንም ላይ ሊደርስ የሚችል የዓመፅ ድርጊት መሆኑን መቀበል ያስፈራል።
“ደግና ጨዋ” ነው ብላ በገመተችው ሰው የተደፈረች አንዲት ሴት “በእኔ ላይ ሊደርስ አይችልም ብሎ ማሰብ ከሁሉ የከፋ ስሕተት ነው” ብላለች።
አስገድዶ ስለ መድፈር የሚታመኑ የተሳሳቱ ግምቶችና እውነታው
ጥቃቱ የደረሰበትን ሰው ጥፋተኛ በማድረግ ዓመፀኛውን በድርጊቱ እንዲቀጥል የሚያበረታቱ አስገድዶ ስለ መድፈር ለረጅም ጊዜ ሲታመኑ ከቆዩት የተሳሳቱ አመለካከቶች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው:-
የሚባለው:- አንዲት ሴት የምትደፈረው በማታውቀው ሰው ጥቃት ሲደርስባት ብቻ ነው።
እውነቱ:- በአብዛኞቹ ተገደው የተደፈሩ ሴቶች ላይ እንደታየው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በሚያውቁትና በሚተማመኑበት ሰው ነው። ይህን በተመለከተ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ተገደው ከተደፈሩ ሴቶች መካከል 84 በመቶ የሚሆኑት ጥቃት ያደረሱባቸውን ሰዎች እንደሚያውቋቸው ሲናገሩ 57 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የተደፈሩት አብረው ለመጫወት ቀጠሮ ባደረጉበት ቀን ነው። ከ7 ባለ ትዳር ሴቶች መካከልም አንዷ በራሷ ባል ትደፈራለች።b አንዲት ሴት ተገዳ የተደፈረችው ከዚያ በፊት በማታውቀው ሰው፣ በትዳር ጓደኛዋ ወይም አብራው ለመጫወት ቀጠሮ በሰጠችው ወዳጅዋ ይሁን ሁሉም ስሜታዊ ቁስለት የሚያስከትሉ የዓመፅ ድርጊቶች ናቸው።
የሚባለው:- አንዲት ሴት ተገዳ ተደፍራለች የሚባለው ድርጊቱ እንዳይፈጸምባት ተከላክላ የነበረ መሆኗን የሚያሳይ የመቀጥቀጥ ወይም የሰንበር ምልክት ካለባት ብቻ ነው።
እውነቱ:- አካላዊ ተቃውሞ ያድርጉ አያድርጉ እንደመቀጥቀጥ ወይም መድማት ወይም እንደ ሰንበር ያሉ የሚታዩ ምልክቶች የሚታይባቸው ጥቂቶቹ ሴቶች ብቻ ናቸው።
የሚባለው:- አንዲት ሴት መደፈሯን በድርጊት ካልተቃወመች በስተቀር ለመደፈሯ በከፊል ተጠያቂ ናት።
እውነቱ:- አስገድዶ መድፈር ማለት አንድን ሰው ከራሱ ፈቃድ ውጭ በኃይል ወይም በማስፈራራት ወይም በማንኛውም መንገድ ተጠቅሞ በግድ የፆታ ግንኙነት ለማድረግ የሚሰነዘር ጥቃት ማለት ነው። አንድን ሰው አስገድዶ ደፍሯል የሚያሰኘውም ድርጊቱ እንዲፈጸምበት ፈቃደኛ ያልሆነውን ሰው ማስገደዱ ነው። ስለዚህ ተገዳ የተደፈረች ሴት ዝሙት ፈጽማለች ተብላ መወቀስ ወይም እንደ ጥፋተኛ መታየት የለባትም። በቅርብ የሥጋ ዘመዷ እንደምትደፈር ሴት ሰውዬው ከእርሷ የበለጠ ኃይል ያለው መሆኑን ተመልክታ አለፈቃዷ ሳትከላከል ተደፍራ ይሆናል። አንዲት ሴት ሰውዬውን ስለፈራች ወይም ግራ ስለተጋባች ሳትከላከል ብትደፈር በድርጊቱ ተስማምታለች ማለት አይደለም። በድርጊቱ ተስማምታለች ሊባል የሚቻለው ያለምንም ማስፈራራት በውዴታና በሙሉ ፈቃድ ያደረገችው ሲሆን ብቻ ነው።
የሚባለው:- አስገድዶ መድፈር በከፍተኛ የፆታ ስሜት በመገፋፋት የሚደረግ ወንጀል ነው።
እውነቱ:- አስገድዶ መድፈር የዓመፅ ድርጊት ነው። ወንዶች አስገድደው የሚደፍሩት የፆታ ግንኙነት ለማድረግ ብቻ ብለው ሳይሆን ከሌላው ሰው የበለጠ ኃይል ያላቸው መሆኑን ለማሳየት ነው።c
የሚባለው:- አንዲት ሴት አንድን ወንድ የፆታ ስሜቱን ፈጽሞ መቆጣጠር እስኪያቅተው ድረስ ወይም አስገድዶ እንዲደፍራት በሚያደረግ መንገድ ስለምትቃለደው ነው።
እውነቱ:- ሴቶችን አስገድደው የሚደፍሩ ወንዶች ሌሎቹ ወንዶች ካላቸው የፆታ ስሜት የሚያይል ስሜት የላቸውም። እንዲያውም አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ከሚፈጽሙት ወንዶች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የተሟላ የፆታ ግንኙነት ማድረግ አልቻሉም። አብዛኛውን ጊዜ አስገድዶ የመድፈር ዓመፅ ሆን ተብሎ በእቅድ የሚደረግ እንጂ ድንገት በተፈጠረ ስሜት የሚፈጸም አይደለም። የማያውቋቸውን ሴቶች አስገድደው የሚደፍሩ ወንዶች የጥቃታቸው ሰለባ ያደረጓቸውን ሴቶች ተከታትለው ብቻቸውን ሲሆኑ አድብተው ሲይዙ የሚያውቋቸውን ሴቶች ደግሞ ብቻዋን የምትሆንበትን ሁኔታ አመቻችተው ይደፍራሉ።
የሚባለው:- ሴቶች የፆታ ግንኙነት ማድረጋቸው ስሕተት እንደሆነ ሲሰማቸው ወይም ሰውዬውን ለመወንጀል ሲሉ ተደፈርኩ ብለው ይዋሻሉ።
እውነቱ:- እንደ ማንኛውም የዓመፅ ወንጀል ሁሉ ተደፍረናል የሚሉ የሐሰት ሪፖርቶች ከመቶ 2 ይሆናሉ። በሌላ በኩል ግን አብዛኞቹ ተገደው የተደፈሩ ሴቶች ሪፖርት ሳያደርጉ እንደሚቀሩ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
የሚባለው:- አንዲት ሴት የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ልብስ በመልበስ፣ የአልኮል መጠጥ በመጠጣት፣ እንዲጋብዛት በመፍቀድ ወይም ቤቱ ድረስ በመሄድ አንድን ወንድ እንዲደፍራት “ልትጠይቅ” ትችላለች።
እውነቱ:- አንዲት ሴት ንዝህላል ወይም አላዋቂ በመሆኗ ምክንያት ብትደፈር ስለ ፈለገች ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ለወንጀሉ ብቸኛ ተጠያቂ አስገድዶ የደፈራት ሰው ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተገዶ የመደፈር ጥቃት ከሚደርስባቸው 10 ሰዎች መካከል አንዱ ወንድ ነው።
b ባለ ትዳር ሴቶች ተገደው የሚደፈሩት አንድ ባል ሚስቱን በጉልበት አሸንፎ አለፈቃዷ የፆታ ግንኙነት ሲፈጽም ነው። አንዳንድ ባሎች ሐዋርያው ጳውሎስ ባል በሚስቱ አካል ላይ አለው ብሎ የጠቀሰው “ሥልጣን” አንጻራዊ ሳይሆን ፍጹም ሥልጣን እንደሆነ አድርገው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ “እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል” ብሏል። ሐዋርያው ጴጥሮስም ባሎች ሚስቶቻቸውን “እንደ ደካማ ዕቃ አድርገው ለሴትነት ባሕርያቸው ሊጠነቀቁላቸው” እንደሚገባ ተናግሯል። አስገድዶ ወይም በኃይል ተጠቅሞ የፆታ ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችል አንድም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት የለም። — 1 ቆሮንቶስ 7:3–5፤ ኤፌሶን 5:25, 28, 29፤ 1 ጴጥሮስ 3:7 አዓት፤ ቆላስይስ 3:5, 6፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3–7
c በሜሪላንድ በቦልቲሞር ከተማ ሴክሹዋል ኦፌንስ ዩኒት ተብሎ ለሚታወቀው ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዋንዳ ኪይስ ሮቢንሰን “ወንጀሉ የሚፈጸመው ‘የፆታ ግንኙነት’ ለማድረግ ተብሎ አይደለም። ይህን የዓመፅ ወንጀል የሚፈጽመው ሰው ፆታን እንደ መሣሪያ አድርጎ ስለሚጠቀምበት ነው እንጂ” ብለዋል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ4 ሴቶች መካከል አንዷ ተገዳ የመደፈር ጥቃት ይፈጸምባታል ወይም አስገድዶ የመድፈር ሙከራ ይደረግባታል
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አስገድዶ የመድፈር ወንጀል እጅግ ተስፋፍቶ የሚገኘው ዓመፅንና ልቅ የፆታ ሥነ ምግባርን በዝምታ በሚመለከቱ ኅብረተሰቦች ውስጥ ነው