የአይሁዳውያን የዘመናት አቆጣጠር ምን ያህል ትክክለኛ ነው?
እንደ አይሁዳውያን አቆጣጠር መስከረም 16, 1993 ሮሽ ሐሸና (የአይሁዳውያን አዲስ ዓመት) ተከብሮ የዋለበት ቀን ነበር። በዚያን ቀን በባሕሉ መሠረት አዲሱ ዓመት መግባቱን ለማብሰር ሾፋር ወይም ከበግ ቀንድ የተሠራ መለከት ሲነፋ ተሰምቷል። ይህ ዓመት እንደ አይሁዳውያን አቆጣጠር 5754ኛው ዓመት ነው። ዓመቱ ከመስከረም 16, 1993 እስከ መስከረም 5, 1994 ድረስ ይቆያል።
በአሁኑ ጊዜ በሰፊው እየተሠራበት ባለው በምዕራባውያን ወይም በጎሮጎሮሳውያንና በአይሁዳውያን የጊዜ አቆጣጠር መካከል የ3,760 ዓመታት ልዩነት መኖሩን እንረዳለን። ይህ ልዩነት ሊመጣ የቻለው ለምንድን ነው? የአይሁዳውያኑ የዘመናት አቆጣጠርስ ምን ያህል ትክክለኛ ነው?
መነሻ ተደርጎ የሚወሰደውን ዓመት መወሰን
ማንኛውም የጊዜ አቆጣጠር ስልት መሠረት አድርጎ የሚነሣበት ወይም የሚጠቅሰው አንድ የተወሰነ የመነሻ ነጥብ የግድ ሊኖረው ይገባል። ለምሳሌ የሕዝበ ክርስትና የዘመን አቆጣጠር የተመሠረተው ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶበታል ተብሎ የታሰበውን ዓመት መነሻ በማድረግ ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያሉት ዘመናት የክርስትና ዘመናት እየተባሉ ይጠራሉ። ብዙውን ጊዜም “በጌታችን ዓመት” የሚል ትርጉም ባላቸው አኖ ዶሚኒ የሚሉትን የላቲን ቃላት በሚወክሉ ፊደላት በእንግሊዝኛ (A.D.) በአማርኛ ዓመተ ምሕረት በመባል ይጻፋሉ። ከዚያ ዓመት በፊት የነበሩት ዓመታት ደግሞ “ከክርስቶስ ልደት በፊት” የሚል ትርጉም ባላቸው ምኅጻረ ቃላት በእንግሊዝኛ (B.C.) ተብለው ይጻፋሉ።a ጥንታዊዎቹ ቻይናውያንም በተመሳሳይ የቢጫው ንጉሠ ነገሥት ነው ተብሎ በአፈ ታሪክ የሚነገርለት የዋንግ ዲይ ግዛት ከጀመረበት ዓመት ከ2698 ከዘአበ በመነሣት ይቆጥራሉ። በዚህ አቆጣጠር መሠረት የካቲት 10, 1994 የቻይናውያን 4692ኛ የጨረቃ ዓመት የጀመረበት መሆኑ ታውቋል። ይሁን እንጂ ስለ አይሁዳውያን የዘመናት አቆጣጠርስ ምን ማለት ይቻላል?
ዘ ጁዊሽ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ሲል ያትታል፦ “በአሁኑ ጊዜ በአይሁዳውያን አንድ ነገር የተከሰተበትን ዘመን ለመመዝገብ የሚጠቀሙበት የተለመደ ዘዴ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ ያለፉትን ዓመታት መቁጠር ነው።” በአይሁዳውያን ዘንድ የፍጥረት ዘመን ተብሎ በሚታወቀው በዚህ የአቆጣጠር ስልት በይበልጥ መጠቀም የተጀመረው በዘጠነኛው መቶ ዘመን እዘአ ጀምሮ ነው። በዚህ ምክንያት በአይሁዳውያን አቆጣጠር የሚጻፉ ዘመናት ኤ ኤም (A.M.) ወይም ዓመተ ዓለም ተብሎ ይጻፋሉ። ይህም “ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ” የሚል ትርጉም ካላቸው አብ ክርሪኦታዬኔ ሙንዲ የሚሉት የላቲን ቃላት በማሳጠር ሲጻፉ የሚወከሉባቸውን ፊደላት በመጠቀም ነው። በዚህ የጊዜ አቆጣጠር ስልት መሠረት አሁን ያለው ዓመት A.M. 5754 ስለሆነ “ዓለም ከተፈጠረ” 5753 ዓመት አልፎታል ማለት ነው። ይህ እንዴት ሊታወቅ እንደቻለ እስቲ እንመርምር።
“የፍጥረት ዘመን”
በ1971 የታተመው ኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ ቀጥሎ ያለውን ማብራሪያ ይሰጣል፦ “በልዩ ልዩ የረቢዎች ስሌት መሠረት ‘የፍጥረት ዘመን’ የጀመረው ከዘአበ በ3762 እና በ3758 ባሉት ዓመታት መካከል በአንደኛው ዓመት በበልግ ወራት ላይ ነው። ይሁን እንጂ ከ12ኛው መቶ ዘመን እዘአ አንሥቶ ‘የፍጥረት ዘመን’ የጀመረው በ3761 ከዘአበ (ትክክለኛውን ቀን ለመጥቅስ በዚያው ዓመት ጥቅምት 7) ነው የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት አገኘ። ይህ ስሌት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እና ከመጽሐፍ ቅዱስ በኋላ በተጻፉ ጥንታዊ የአይሁድ ጽሑፎች ላይ በተገኙት መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው።”
ከ“ዓለም ፍጥረት” ጀምሮ የሚሰላው የጊዜ ቀመር የአይሁድ ረቢዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ በተረዱበት መንገድ ላይ የተመሠረተ ነው። የአይሁድ ምሁራን እንደ ሕዝበ ክርስትና ምሁራን ሁሉ ዓለምና በውስጧ ያለው በሙሉ ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ ተፈጥረዋል የሚል እምነት ስላላቸው የመጀመሪያው ሰው አዳምና ዓለም የተፈጠሩት በአንድ ዓመት ውስጥ ነው የሚል ግምት አላቸው። ይሁን እንጂ ይህ በጭራሽ ትክክል አይደለም።
የዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ይጀምራል። ከዚያም አምላክ ምድርን በስድስት ተከታታይ “ቀኖች” ውስጥ ‘ቅርጽ የለሽና ባዶ ከነበረችበት ሁኔታ’ ለሰዎች የምትስማማ ምቹ መኖሪያ እንድትሆን አድርጎ ለመለወጥ ያደረጋቸውን ነገሮች ይዘረዝራል። (ዘፍጥረት 1:1, 2 የ1980 ትርጉም) በእነዚህ ሁለት ደረጃዎች ማለትም መሬት መጀመሪያ በነበረችበት መልክና ለሰው ተስማሚ ሆና እስክትሰናዳ ባሉት ጊዜያት መካከል በሚልዮን የሚቆጠሩ ዓመታት ሊያልፉ ይችላሉ። ከዚህም በላይ የፍጥረት ቀናት የ24 ሰዓት ርዝማኔ ያላቸው አልነበሩም። የፈጣሪ ሥራ እንዲህ ባሉት የጊዜ ገደቦች የሚገታ አይደለም። “ቀን” የሚለው አባባል ከ24 ሰዓት የበለጡ ጊዜያትን እንደሚያመለክት የሚያሳየው ዘፍጥረት 2:4 ሁሉንም የፍጥረት ጊዜያት እንደ አንድ “ቀን” አድርጎ መግለጹ ነው። በመጀመሪያው የፍጥረት ቀንና አዳም በተፈጠረበት በስድስተኛው የፍጥረት ቀን መካከል ብዙ ሺህ ዓመታት አልፈዋል። አዳምም ሆነ ግዑዙ ሰማይና ምድር የተፈጠሩት በአንድ ጊዜ እንደሆነ አድርጎ መቁጠር ቅዱስ ጽሑፋዊም ሆነ ሳይንሳዊ ድጋፍ የለውም። ታዲያ “የፍጥረት ዘመን” በ3761 ከዘአበ በፊት መጀመሩ የታወቀው እንዴት ነው?
ለአይሁዳውያን የጊዜ ቀመር መሠረት የሆነው ነገር
የሚያሳዝነው የጊዜ ቀመሩን ለማዘጋጀት መሠረት ተደርገው የተወሰዱት አብዛኞቹ የአይሁድ ጽሑፎች አሁን የሌሉ መሆናቸው ነው። አሁን ያለው መረጃ ቢኖር ሴዳር ኦላም (የዓለም ሥርዓት) ተብሎ ይጠራ የነበረው የጊዜ ስሌት ብቻ ነው። የተጻፈውም በሁለተኛው መቶ ዘመን የታልሙድ ሕግ ምሁር በሆኑት በዮሴ ቤን ሃላፍታ ነው። ይህ ጽሑፍ ከአዳም አንሥቶ አይሁዳውያን በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ በሐሰተኛው ነቢይ በባር ኮባ መሪነት በሮማውያን ላይ እስካመፁበት ጊዜ ድረስ ባሉት ዘመናት ውስጥ የተፈጸመውን ታሪክ በቅደም ተከተል ይዘረዝራል። (ይህን ጽሑፍ ሴዳር ኦላም ዙታ የሚል ርዕስ ካለው የመካከለኛው መቶ ዘመን ዜና መዋዕል ለመለየት ሲባል ሴዳር ኦላም ራባ ተብሎ ይጠራ ጀመር።) ጸሐፊው እንዲህ ያለውን መረጃ ሊያገኙ የቻሉት እንዴት ነው?
ዮሴ ቤን ሃላፍታ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊ ዘገባ ተከትለው ለመጻፍ ጥረት ቢያደርጉም እንኳ ጥቅሱ ዘመኑን ለይቶ በማያስቀምጥበት ቦታ ላይ የራሳቸውን ትርጓሜ ጨምረዋል። ዘ ጁዊሽ እንሳይክሎፒዲያ እንዳለው “ብዙ ቦታ ላይ . . . ያሰፈሯቸውን ቀኖች ያገኟቸው ሲወርድ ሲዋረድ በቆዩአቸው ወጎች ላይ ተመርኩዘው ነው። ከእሳቸው በፊትና በእሳቸው ዘመን ከነበሩት ረቢዎች ያገኟቸውን ሃላኮት [አፈ ታሪክ ማለት ነው] ጨምረው አስገብተዋል።” ሌሎች ጸሐፊዎች ለቆዩት ወጎችና ባሕሎች የሰጧቸው ግምቶች ግን አነስተኛ ናቸው። ዘ ቡክ ኦቭ ጁዊሽ ኖውሌጅ የተባለው መጽሐፍ ቀጥሎ ያለውን ማረጋገጫ ይሰጣል፦ “ዮሴ ቤን ሃላፍታ ያዘጋጁት የጊዜ ቀመር ከፍጥረት ጊዜ ጀምሮ በመቁጠር ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም አንሥቶ እስከ ታላቁ እስክንድር ድረስ አንዳንድ ሁኔታዎች ተከናውነውባቸዋል ተብለው በሚታመንባቸው መሠረተ ቢስ የዘመናት ግምቶች ላይ የተመሠረተ ነው።” እንዲህ ያሉት አተረጓጎሞችና ጭማሪዎች የአይሁዳውያንን የዘመናት ቀመር ትክክለኛነትና እውነተኝነት የነካው እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።
ወጎችና ትርጓሜዎች
ዮሴ ቤን ሃላፍታ ራቢዎች ሲተርኩት ከቆዩት ባሕላዊ ታሪክ ጋር በመስማማት በኢሩሳሌም የተሠራው ሁለተኛው ቤተ መቅደስ በጠቅላላው ለ420 ዓመታት ያህል እንደቆየ አስልተዋል። ይህም ረቢዎቹ ስለ “ሰባ ሱባዔ” ወይም 490 ዓመታት ለሚናገረው የዳንኤል ትንቢት በሚሰጡት ትርጓሜ ላይ በመንተራስ የተደረገ ስሌት ነው። (ዳንኤል 9:24) ይህ ጊዜ የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ከጠፋበት አንሥቶ ለሁለተኛ ጊዜ የተሠራው ቤተ መቅደስ እስከ ወደመበት ድረስ ያለውን የጊዜ ርዝመት የሚያመለክት ነው ይላሉ። ዮሴ ቤን ሃላፍታ እስራኤላውያን በባቢሎን በግዞት የቆዩበትን 70 ዓመት በመቀነስ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ የቆየው ለ420 ዓመታት ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ።
ሆኖም ይህ ማብራሪያ ትልቅ ስህተት አለው። የባቢሎን መንግሥት የተገረሰሰበትም (539 ከዘአበ) ሆነ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ የወደመበት (70 እዘአ) በታሪክ የታወቁ ዓመታት ናቸው። ስለዚህ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ የቆየው ለ420 ዓመት ሳይሆን ለ606 ዓመት ያህል ነው። ይህ ጊዜ 420 ዓመት ብቻ ነው በማለቱ የአይሁዳውያን የጊዜ ቀመር በ186 ዓመታት ልዩነት ተሳስቷል።
የዳንኤል ትንቢት በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ለማሳየት የተነገረ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መሢሑ መቼ እንደሚመጣ ለማመልከት የተነገረ ትንቢት ነው። ትንቢቱ “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል” በማለት ይህን ግልጽ ያደርግልናል። (ዳንኤል 9:25, 26) አይሁዳውያን ከግዞት በተመለሱ በሁለተኛው ዓመት ላይ የቤተ መቅደሱ መሠረት ሲጣል (በ536 ከዘአበ) የኢየሩሳሌም ከተማን ቅጥር ለመሥራት ያስቻለው ‘ትእዛዝ’ ግን እስከ ‘ንጉሥ አርጤክሰስ ሀያኛ ዓመት ድረስ’ ገና አልወጣም ነበር። (ነህምያ 2:1–8) ትክክለኛ ምንጭ ያለው የዓለም ታሪክ ያ ዓመት 455 ከዘአበ እንደሆነ ያረጋግጣል። ከዚህ ጊዜ በመነሳት 69 “ሱባዔ” ወይም 483 ዓመት ስንቆጥር 29 እዘአ ላይ ያደርሰናል። የመሢሑ መምጣት የታየው ኢየሱስ በተጠመቀበት በዚህ ጊዜ ላይ ነበር።b
በአይሁዳውያን የጊዜ ቀመር ላይ ትልቅ ልዩነት የሚፈጥረው ሌላው የረቢዎች አተረጓጎም ደግሞ አብርሃም የተወለደበትን ጊዜ አስመልክቶ የሚሰጡት ትንተና ነው። የአይሁድ ምሁራን ማለትም ረቢዎች በዘፍጥረት 11:10–26 [በ1980 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም] ላይ የተዘረዘሩትን ተከታታይ ትውልዶች ዕድሜ በመደመር ከጥፋት ውኃ አንሥቶ አብርሃም (አብራም) እስከ ተወለደበት ጊዜ ድረስ 292 ዓመታት ያለፉ መሆናቸውን ይናገራሉ። ሆኖም ትልቁ የረቢዎች ችግር “ታራ 70 ዓመት ከሆነው በኋላ አብራምን፣ ናኮርንና ሃራንን ወለደ” ለሚለው በቁጥር 26 ላይ ላለው ሐሳብ የሰጡት ትርጉም ነው። ከዚህ ጥቅስ በመነሣት የአይሁድ ባሕላዊ ታሪክ አብርሃም ሲለወለድ ታራ የ70 ዓመት ሰው ነበር ይላል። ይሁን እንጂ ጥቅሱ ታራ በ70 ዓመቱ አብርሃምን እንደወለደ ለይቶ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ጥቅሱ የሚናገረው ታራ 70 ዓመት ከሆነው በኋላ ሦስት ወንዶች ልጆችን መውለዱን ብቻ ነው።
አብርሃም ሲወለድ ትክክለኛው የታራ ዕድሜ ምን ያህል እንደነበር ለማወቅ የሚያስፈልገን የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ማንበብ ብቻ ነው። ከዘፍጥረት 11:32 እስከ 12:4 ካለው ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ታራ በ205 ዓመቱ ሲሞት አብርሃም ይሖዋ እንዳዘዘው ቤተሰቡን ይዞ ከካራን ወጣ። በዚያ ጊዜ አብርሃም የ75 ዓመት ሰው ነበር። ስለዚህ አብርሃም የተወለደው ታራ 70 ዓመት ሆኖት እያለ ሳይሆን የ130 ዓመት ሰው እያለ መሆን አለበት። እንግዲያው ከጥፋት ውኃ አንሥቶ አብርሃም እስከ ተወለደበት ያለው ጊዜ 292 ዓመት ሳይሆን 352 ዓመት ነው። እዚህ ላይ የአይሁዳውያን የጊዜ ቀመር በ60 ዓመት ልዩነት ተሳስቷል።
ሃይማኖታዊ ወግ
በሴዳር ኦላም ራባ እንዲሁም ታልሙድን መሠረት በማድረግ በተዘጋጁት ሌሎች የዘመናት ቀመር ውስጥ ያሉት እንዲህ ያሉ ስህተቶችና ልዩነቶች በአይሁዳውያኑ ምሁራን ዘንድ ብዙ ኃፍረትና ከፍተኛ ሙግት አምጥተዋል። ይህን የዘመን ቀመር በሰፊው ከሚታወቁ ታሪኮች ጋር ለማስታረቅ ብዙ ሙከራዎች ቢደረጉም እንኳ ፈጽሞ ሊሳኩ አልቻሉም። ለምን ይሆን? “ፍላጎታቸው ሃይማኖታዊ ምርምር ለማድረግ አልነበረም። በተለይ ተቃዋሚ የሃይማኖት ቡድኖችን ለመቋቋም ሲባል የተከፈለው መሥዋዕትነት ተከፍሎ ባሕል መጠበቅ አለበት የሚል ነው” በማለት ኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ የታዘበውን አስፍሯል። አንዳንድ የአይሁድ ምሁራን በወጎቻቸው ምክንያት የተፈጠረውን ግራ መጋባት ከማስወገድ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዘገባ ዋጋ ለማሳጣት ቃጥተዋል። ሌሎች ደግሞ ከባቢሎናውያን፣ ከግብጻውያንና ከሂንዱ አፈ ታሪኮችና ወጎች ድጋፍ ለማግኘት ሙከራ አድርገዋል።
በዚህ ምክንያት የታሪክ ምሁራን “የፍጥረት ዘመን” የተባለው የዘመናት ቀመር እምነት ሊጣልበት የሚችል የሥራ ውጤት አድርገው መመልከታቸውን አቁመዋል። ጥቂት የአይሁድ ምሁራን ስሌቱ ትክክል ነው ብለው ለመከራከር ጥረት አድርገው ነበር፤ ሆኖም እንደ ጁዊሽ ኢንሳይክሎፔዲያ እና ኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ ያሉት ተአማኒ መጻሕፍት እንኳ ለቀመሩ ያላቸው አመለካከት በአብዛኛው አሉታዊ ነው። ስለዚህ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ የሚጀምረው ባሕላዊው የአይሁዳውያን የጊዜ አቆጣጠር የይሖዋ አምላክ የማይሻሩ ትንቢቶች የጊዜ ሠሌዳ ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌትና አንጻር ሲታይ እንደ ትክክለኛ ስሌት ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው በ2 ከዘአበ ነው። ስለዚህ ብዙዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት እና በኋላ እየተባሉ የሚጠሩትን ጊዜያት ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ ሲሉ እዘአ (እንደ ዘመናችን አቆጣጠር) እና ከዘአበ (ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት) ማለትን ይመርጣሉ። በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ የሚጠቀሱት ቀናት የሚገለጹትም በዚህ መንገድ ነው።
b ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 614–16፣ 900–902 እንዲሁም ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው በተባለው መጽሐፍ ጥናት ቁጥር 3፣ አንቀጽ 18፤ በተጨማሪም መግ 92 10/1 ገጽ 11፣ ገጽ አንቀጽ 8–11 ተመልከት።