የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 2/1 ገጽ 9-13
  • ‘እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ወዶናል’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ወዶናል’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “እግዚአብሔር ፍቅር ነው”
  • ቤዛ ያስፈለገው ለምንድን ነው?
  • ዋጋው ምን ያህል ከፍተኛ ነው?
  • ቤዛው ያስገኘው ነገር
  • ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • የክርስቶስ ቤዛ የአምላክ የመዳን መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • የይሖዋ ዓላማ ይፈጸማል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 2/1 ገጽ 9-13

‘እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ወዶናል’

“እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።”​— 1 ዮሐንስ 4:​11

1. መጋቢት 23 ቀን ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በምድር ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመንግሥት አዳራሾችና በሌሎች መሰብሰቢያ ቦታዎች የሚሰበሰቡት ለምንድን ነው?

መጋቢት 23, 1997 እሁድ ዕለት ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በዓለም ዙሪያ ከ13,000,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በመንግሥት አዳራሾችና የይሖዋ ምሥክሮች በሚጠቀሙባቸው ሌሎች የመሰብሰቢያ ቦታዎች እንደሚሰበሰቡ ጥርጥር የለውም። የሚሰበሰቡት ለምንድን ነው? አምላክ ለሰው ልጆች ባሳየው ከሁሉ የላቀ የፍቅር መግለጫ ልባቸው ስለተነካ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ በማለት በዚህ ታላቅ የአምላክ የፍቅር መግለጫ ላይ ትኩረት አድርጓል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”​— ዮሐንስ 3:​16

2. ለአምላክ ፍቅር የምንሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ሁላችንም ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች ብንጠይቅ ጥሩ ይሆናል?

2 አምላክ ያሳየውን ፍቅር ስንመረምር ‘አምላክ ያደረገውን ነገር በእርግጥ አደንቃለሁን? ሕይወቴን የምጠቀምበት መንገድ ይህ አድናቆት እንዳለኝ ያሳያልን?’ ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ ጥሩ ይሆናል።

“እግዚአብሔር ፍቅር ነው”

3. (ሀ) ፍቅር ማሳየት ለአምላክ እንግዳ ነገር ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ውስጥ ኃይልና ጥበብ የተንጸባረቁት እንዴት ነው?

3 “እግዚአብሔር ፍቅር” ስለሆነ ፍቅር ማሳየት ለእሱ እንግዳ ነገር አይደለም። (1 ዮሐንስ 4:​8) ፍቅር ከሁሉ የላቀ ባሕርይው ነው። ምድርን ለሰው መኖሪያነት ሲያዘጋጅ ተራሮችን ከፍ አድርጎ መሥራቱና ውኃን በሐይቆችና በውቅያኖሶች ውስጥ ማከማቸቱ እጅግ የሚያስደንቅ የኃይል መግለጫ ነው። (ዘፍጥረት 1:​9, 10) አምላክ የውኃን ዑደትና የኦክስጅንን ዑደት ሥራ ላይ ሲያውል፣ የሰው ልጆች ተመግበው ሕይወታቸውን ማቆየት እንዲችሉ የምድርን ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች ወደ ምግብነት የሚለውጡ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው በዓይን የማይታዩ ጥቃቅን ተሕዋሲያንና ልዩ ልዩ ዓይነት ዕፅዋት ሲፈጥር እንዲሁም ሰውነታችን ሥራውን የሚያከናውንበት የጊዜ ፕሮግራም በፕላኔቷ ምድር ላይ ካለው የቀኖችና የወራት ርዝመት ጋር እንዲጣጣም ሲያደርግ በሥራው ላይ ታላቅ ጥበብ ተንጸባርቋል። (መዝሙር 104:​24፤ ኤርምያስ 10:​12) ሆኖም በፍጥረታት ላይ ይበልጥ ጎላ ብሎ የተንጸባረቀው የአምላክ ፍቅር ነው።

4. ሁላችንም በሚታዩ ፍጥረታት ላይ የተንጸባረቀውንና አምላክ አፍቃሪ እንደሆነ የሚያሳየውን የትኛውን ማስረጃ ማስተዋልና ማድነቅ አለብን?

4 ብዙ ውኃ ያለው አንድ የበሰለ ፍሬ ስንገምጥ የመቅመስ ችሎታችን አምላክ አፍቃሪ እንደሆነ ያስገነዝበናል፤ ሕይወታችንን እንዲያቆይልን ብቻ ሳይሆን ደስታም እንዲሰጠን ጭምር የተዘጋጀ እንደሆነ ግልጽ ነው። ፀሐይ ስትጠልቅ የምትፈጥረው እጅግ አስደናቂ የሆነ ዕይታ፣ በጠራ ሌሊት የሚታዩት በከዋክብት የተሞሉ ሰማያት፣ በጣም ደማቅ የሆኑ ቀለማት ያሏቸው ልዩ ልዩ ዓይነት አበቦች፣ የግልገሎች ቡረቃና የጓደኞቻችን ሞቅ ያለ ፈገግታ አምላክ አፍቃሪ መሆኑን በግልጽ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። በጸደይ ወራት የሚፈነዱትን አበቦች ጣፋጭ መዓዛ ስናሸት አምላክ አፍቃሪ እንደሆነ እንረዳለን። የፏፏቴዎችን ድምፅ፣ የወፎችን ዝማሬና የምንወዳቸውን ሰዎች ድምፅ ስንሰማ የአምላክን ፍቅር እናስተውላለን። አንድ የምንወደው ሰው በጋለ የወዳጅነት ስሜት ሲያቅፈን አምላክ ለእኛ ያለው ፍቅር ይሰማናል። አንዳንድ እንስሳት ከሰዎች ችሎታ በላይ የሆኑ ነገሮችን የማየት፣ የመስማትና የማሽተት ችሎታ አላቸው። ሆኖም የሰው ልጆች የተፈጠሩት በአምላክ አምሳል በመሆኑ ማንኛውም እንስሳ ሊረዳው በማይችለው መንገድ የአምላክን ፍቅር የመረዳት ችሎታ አላቸው።​— ዘፍጥረት 1:​27

5. ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ይህ ነው የማይባል ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ማለትም አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥር ፍቅሩን የሚያንጸባርቁ ብዙ ነገሮች በዙሪያቸው አዘጋጅቶ ነበር። አንድ የአትክልት ሥፍራ ማለትም ገነት አዘጋጀና በውስጡ የተለያዩ ዛፎች አበቀለ። የአትክልት ሥፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ አዘጋጀ፤ እንዲሁም የአትክልት ሥፍራው እጅግ አስደናቂ በሆኑ አዕዋፍና እንስሳት እንዲሞላ አደረገ። ከዚያም ይህን ሁሉ ለአዳምና ለሔዋን መኖሪያ አድርጎ ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 2:​8-10, 19) ይሖዋ የጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰቡ አባል የሆኑ ልጆቹ አድርጎ ያዛቸው። (ሉቃስ 3:​38) የእነዚህ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ሰማያዊ አባት ኤደንን እንደ ናሙና አድርጎ በማቅረብ ገነትን አስፋፍተው ምድርን ሁሉ እንድትሸፍን የማድረግ አስደሳች ሥራ ሰጣቸው። መላዋ ምድር በዘሮቻቸው እንድትሞላ ዓላማው ነበር።​— ዘፍጥረት 1:​28

6. (ሀ) አዳምና ሔዋን ስለፈጸሙት የዓመፅ ድርጊት ምን ይሰማሃል? (ለ) በኤደን ከተፈጸመው ሁኔታ ትምህርት እንዳገኘንና ባገኘነው እውቀት እንደተጠቀምን ሊጠቁም የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

6 ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ አዳምና ሔዋን ታዛዥነታቸውን የሚፈትን የታማኝነት ፈተና አጋጠማቸው። በመጀመሪያ አንዳቸው ከዚያም ሌላኛው አምላክ ላሳያቸው ፍቅር አድናቆት ሳያሳዩ ቀሩ። ያደረጉት ነገር አሳፋሪ ነበር። ምንም የሚያመካኙት ነገር አልነበራቸውም! በዚህም ምክንያት ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ዝምድና አጡ፤ ከቤተሰቡ ተባረሩ፤ ከኤደንም እንዲወጡ ተደረገ። የፈጸሙት ኃጢአት ያስከተለው ውጤት በዛሬው ጊዜ በእኛም ላይ ደርሷል። (ዘፍጥረት 2:​16, 17፤ 3:​1-6, 16-19, 24፤ ሮሜ 5:​12) ሆኖም ከዚህ ከደረሰው ሁኔታ ትምህርት አግኝተናልን? ለአምላክ ፍቅር ምን ዓይነት ምላሽ እየሰጠን ነው? በየዕለቱ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ፍቅሩን እንደምናደንቅ ያሳያሉን?​— 1 ዮሐንስ 5:​3

7. አዳምና ሔዋን ቢያምፁም እንኳ ይሖዋ ለዘሮቻቸው ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?

7 የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ወላጆቻችን አምላክ ላደረገላቸው ነገር ሁሉ ምንም ዓይነት አድናቆት አለማሳየታቸው እንኳ አምላክ ፍቅሩን ለሌሎች እንዳያሳይ አላደረገውም። አምላክ በዛሬው ጊዜ የምንኖረውን ሰዎች ጨምሮ በዚያን ጊዜ ገና ላልተወለዱት የሰው ልጆች በመራራት አዳምና ሔዋን ከመሞታቸው በፊት ልጆች ወልደው እንዲያሳድጉ ፈቀደላቸው። (ዘፍጥረት 5:​1-5፤ ማቴዎስ 5:​44, 45) እንደዚያ ባያደርግ ኖሮ ማንኛችንም ባልተወለድን ነበር። ይሖዋ ቀስ በቀስ በተገለጠው ፈቃዱ አማካኝነት እምነት የሚያሳዩ የአዳም ዘሮች ሁሉ ተስፋ ማድረግ የሚችሉበት መሠረት አዘጋጀ። (ዘፍጥረት 3:​15፤ 22:​18፤ ኢሳይያስ 9:​6, 7) ዝግጅቱ አሕዛብ በሙሉ አዳም ያጣውን ነገር ማለትም ተቀባይነት ያገኙ የአምላክ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባል ሆኖ ፍጹም ሕይወት የመኖር መብት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ የሚያካትት ነው። ይህን ያደረገው ቤዛ በመስጠት ነው።

ቤዛ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

8. አዳምና ሔዋን መሞት ያለባቸው ቢሆንም እንኳ ታዛዥ የሆኑ ዘሮቻቸው በሙሉ እንዳይሞቱ አምላክ ሊደነግግ ያልቻለው ለምንድን ነው?

8 አንድን ሰብዓዊ ሕይወት ዋጋ አድርጎ በመስጠት ቤዛ መክፈል አስፈላጊ ነበርን? አዳምና ሔዋን ለፈጸሙት የዓመፅ ድርጊት መሞት ያለባቸው ቢሆንም እንኳ አምላክ እሱን የሚታዘዙ ዘሮቻቸው በሙሉ ለዘላለም መኖር እንዲችሉ መደንገግ አይችልም ነበርን? አርቆ አሳቢነት ከጎደለው ሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ይህ ምክንያታዊ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ “ጽድቅንና ፍትሕህን ይወድዳል።” (መዝሙር 33:​5 NW) አዳምና ሔዋን ልጆች የወለዱት ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ነበር፤ ስለዚህ ከልጆቻቸው መካከል ፍጹም ሆኖ የተወለደ የለም። (መዝሙር 51:​5) ሁሉም ኃጢአት ወረሱ፤ የኃጢአት ደመወዝ ደግሞ ሞት ነው። ይሖዋ ይህን ችላ ብሎ አልፎት ቢሆን ኖሮ ይህ ሁኔታ ለአጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰቡ አባላት ምን ዓይነት ምሳሌ ይሆን ነበር? የራሱን የጽድቅ መስፈርቶች ችላ ሊል አይችልም። የፍትሕ ደንቦችን አክብሯል። ማንም ሰው ለተነሱት አከራካሪ ጉዳዮች አምላክ መልስ የሰጠበትን መንገድ ለመተቸት የሚያስችል በቂ ምክንያት ሊያገኝ አይችልም።​— ሮሜ 3:​21-23

9. በመለኮታዊው የፍትሕ መሥፈርት መሠረት ምን ዓይነት ቤዛ ያስፈልግ ነበር?

9 እንግዲያው ለይሖዋ ፍቅራዊ ታዛዥነት ያሳዩ የአዳም ዘሮችን ለማዳን ተስማሚ የሆነ መሠረት መጣል የሚቻለው እንዴት ነው? አንድ ፍጹም ሰው መሥዋዕታዊ ሞት ቢሞት በፍትሕ መሠረት የዚህ ፍጹም ሕይወት ዋጋ ቤዛውን አምነው የሚቀበሉ ሰዎችን ኃጢአት ሊሸፍን ይችላል። መላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ኃጢአተኛ እንዲሆን ያደረገው የአንድ ሰው ማለትም የአዳም ኃጢአት ስለሆነ ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው የሌላ ፍጹም ሰው ደም መፍሰስ የፍትሕ ሚዛኑ እኩል እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​5, 6) ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ሰው ከየት ሊገኝ ይችላል?

ዋጋው ምን ያህል ከፍተኛ ነው?

10. የአዳም ዘሮች የሚያስፈልገውን ቤዛ ማቅረብ ያልቻሉት ለምንድን ነው?

10 ከኃጢአተኛው አዳም ዘሮች መካከል አዳም ያጣውን የሕይወት ተስፋ መልሶ ለማግኘት መከፈል ያለበትን ዋጋ መክፈል የሚችል ሰው አልነበረም። “ወንድም ወንድሙን አያድንም፣ ሰውም አያድንም፤ ቤዛውን ለእግዚአብሔር አይሰጥም፣ ለዘላለም እንዲኖር፣ ጥፋትንም እንዳያይ፤ የነፍሳቸው ለውጥ ከብሮአልና [“ነፍሳቸውን ለማዳን የሚከፈለው ዋጋ በጣም ውድ ስለሆነ” NW] ለዘላለምም ቀርቶአልና።” (መዝሙር 49:​7-9) ይሖዋ የሰውን ዘር ያላንዳች ተስፋ እንዲኖር አልተወውም፤ ከዚህ ይልቅ በምሕረት ተገፋፍቶ ራሱ ዝግጅት አደረገ።

11. ይሖዋ ተስማሚ የሆነ ቤዛ ለመክፈል የሚያስፈልገውን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ያቀረበው በምን መንገድ ነው?

11 ይሖዋ አንድ መልአክ ወደ ምድር እንዲመጣና ሥጋዊ አካሉን አሳልፎ በመስጠት የሞተ አስመስሎ በመንፈሳዊ አካል በሕይወት መኖሩን እንዲቀጥል አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ፈጣሪ የሆነው አምላክ ብቻ ሊፈጽመው የሚችለውን ተአምር በመሥራት የአንድን ሰማያዊ ልጅ የሕይወት ኃይልና ስብዕና ከይሁዳ ነገድ ወደሆነችው የኤሊ ልጅ ወደ ማርያም ማኅፀን አዛወረው። የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነው ቅዱስ መንፈሱ ልጁ በእናቱ ማኅፀን ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተጠብቆ እንዲያድግ በማድረጉ ፍጹም ሰው ሆኖ ተወለደ። (ሉቃስ 1:​35፤ 1 ጴጥሮስ 2:​22) ይህ ሰው መለኮታዊ ፍትሕ የሚጠይቃቸውን ብቃቶች ሙሉ በሙሉ የሚያሟላ ቤዛ ለማቅረብ የሚያስፈልገው ዋጋ ነበረው።​— ዕብራውያን 10:​5

12. (ሀ) ኢየሱስ የአምላክ “አንድያ ልጅ” የሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) አምላክ ቤዛውን ለማቅረብ ይህን አንድያ ልጁን መላኩ ለእኛ ያለውን ፍቅር ጎላ አድርጎ የሚያሳየው እንዴት ነው?

12 ይሖዋ ቁጥር ሥፍር ከሌላቸው ሰማያዊ ልጆቹ መካከል ይህን ሥራ የሰጠው ለማን ነው? በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “አንድ ልጁ” ተብሎ ለተጠራው ነው። (1 ዮሐንስ 4:​9) ይህ አገላለጽ የሚያመለክተው ሰው ሆኖ ከተወለደ በኋላ የነበረውን ሁኔታ ሳይሆን ከዚያ በፊት በሰማይ እያለ የነበረበትን ሁኔታ ነው። ይሖዋ ያለማንም እገዛ በቀጥታ የፈጠረው እሱን ብቻ ነው። የፍጥረታት ሁሉ በኩር ነው። አምላክ ሌሎቹን ፍጥረታት በሙሉ ወደ መኖር ያመጣው በእሱ አማካኝነት ነው። አዳም የአምላክ ልጅ እንደነበረ ሁሉ መላእክትም የአምላክ ልጆች ናቸው። ኢየሱስ ግን ‘አባት ለአንድያ ልጁ የሚሰጠው ዓይነት’ ክብር እንዳለው ተገልጿል። “በአባቱ እቅፍ” እንደሚኖር ተነግሯል። (ዮሐንስ 1:​14, 18) ከአባቱ ጋር ያለው ዝምድና የተቀራረበ፣ የምሥጢር ወዳጅነትና ፍቅር የተሞላበት ነው። ኢየሱስ አባቱ ለእሱ ያለውን ዓይነት ፍቅር ለሰው ዘር ያሳያል። ምሳሌ 8:​30, 31 አባቱ ስለዚህ ልጅ ምን እንደሚሰማውና ልጁ ለሰው ዘር ምን እንደሚሰማው እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “[ይሖዋን] ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፣ በፊቱም ሁል ጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፣ . . . ተድላዬም [የይሖዋ ዋነኛ ሠራተኛ የሆነውና የጥበብ ፍጹም ምሳሌ የሆነው ኢየሱስ ተድላው] በሰው ልጆች ነበረ።” አምላክ ቤዛውን ለመስጠት ወደ ምድር የላከው ይህን ከሁሉ በላይ ውድ የሆነ ልጅ ነበር። “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት በእርግጥም ትልቅ ትርጉም ያዘሉ ናቸው!​— ዮሐንስ 3:​16

13, 14. አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው እንደነበረ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ ስላደረገው ነገር ምን እንድንገነዘብ ሊረዳን ይገባል? (1 ዮሐንስ 4:​10)

13 አምላክ ይህ ምን ማለት እንደሆነ በተወሰነ መጠን መረዳት እንድንችል ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ማለትም ከዛሬ 3,890 ዓመት ገደማ በፊት አብርሃምን እንዲህ ሲል አዝዞት ነበር:- “የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው።” (ዘፍጥረት 22:​1, 2) አብርሃም በእምነት ታዘዘ። እስቲ ራስህን በአብርሃም ቦታ አስቀምጥ። ልጁ በጣም የምትወደው አንድያ ልጅህ ቢሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን እንጨት ስትሰነጣጥቅ፣ ወደ ሞሪያም ምድር ለመድረስ ለበርካታ ቀናት ስትጓዝና ልጅህን በመሠዊያ ላይ ስታጋድመው ምን ይሰማህ ነበር?

14 አንድ ሩኅሩኅ ወላጅ እንዲህ ዓይነት ስሜቶች የሚሰሙት ለምንድን ነው? ዘፍጥረት 1:​27 አምላክ ሰውን በአምሳሉ እንደፈጠረው ይናገራል። የፍቅርና የርኅራኄ ስሜቶቻችን የራሱን የይሖዋን ፍቅርና ርኅራኄ በጣም በተወሰነ ደረጃ ያንጸባርቃሉ። አብርሃምን በተመለከተ አምላክ ጣልቃ በመግባት ይስሐቅ እንዳይሠዋ አድርጓል። (ዘፍጥረት 22:​12, 13፤ ዕብራውያን 11:​17-19) ይሁን እንጂ ይሖዋ የራሱን ሁኔታ በተመለከተ ምንም እንኳ ቤዛው እሱም ሆነ ልጁ ከፍተኛ ዋጋ እንዲከፍሉ የጠየቀባቸው ቢሆንም ቤዛውን ከማቅረብ ወደ ኋላ አላለም። አምላክ ይህን ያደረገው ግዴታ ሆኖበት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይገባናል የማንለው ታላቅ ደግነት መግለጫ ነው። ይህን ከልባችን እናደንቃለንን?​— ዕብራውያን 2:​9

ቤዛው ያስገኘው ነገር

15. ቤዛው በአሁኑ የነገሮች ሥርዓትም እንኳ ሳይቀር የሰዎችን ሕይወት የነካው እንዴት ነው?

15 ይህ የአምላክ ፍቅራዊ ዝግጅት በእምነት በሚቀበሉት ሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያሳድራል። ቀደም ሲል በኃጢአት ምክንያት ከአምላክ የራቁ ሰዎች ነበሩ። ቃሉ እንደሚለው ‘ክፉ ሥራ በመሥራት በአሳባቸው ጠላቶች የነበሩ’ ናቸው። (ቆላስይስ 1:​21-23) ሆኖም ‘በልጁ ሞት ከአምላክ ጋር ታርቀዋል።’ (ሮሜ 5:​8-10) የአኗኗር መንገዳቸውን በመለወጥና አምላክ በክርስቶስ መሥዋዕት ለሚያምኑ ሰዎች የሚሰጠውን የኃጢአት ይቅርታ በመቀበል ንጹሕ ሕሊና አግኝተዋል።​— ዕብራውያን 9:​14፤ 1 ጴጥሮስ 3:​21

16. የታናሹ መንጋ አባላት በቤዛው ላይ ባላቸው እምነት የተነሣ ምን በረከቶች አግኝተዋል?

16 ይሖዋ ከእነዚህ መካከል የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የታናሹ መንጋ አባላት በሰማያዊ መንግሥት ከልጁ ጋር አብረው በመሆን መጀመሪያ ለምድር ያወጣውን ዓላማ እንዲፈጽሙ ይገባናል የማይሉትን መብት ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 12:​32) እነዚህ ሰዎች ‘ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ የተዋጁ ሲሆኑ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ሆነው በምድር ላይ የሚነግሡ’ ናቸው። (ራእይ 5:​9, 10) ሐዋርያው ጳውሎስ ለእነዚህ ሰዎች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ . . . የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፣ . . . ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” (ሮሜ 8:​15-17) አምላክ ልጆቹ አድርጎ ስለተቀበላቸው አዳም ያጣውን ውድ ዝምድና አግኝተዋል፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ልጆች አዳም ፈጽሞ ያላገኛቸውን የሰማያዊ አገልግሎት ተጨማሪ መብቶችም ያገኛሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ” ማለቱ ምንም አያስደንቅም! (1 ዮሐንስ 3:​1) አምላክ ለእነዚህ ሰዎች በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራውን ፍቅር (አጋፔ) ብቻ ሳይሆን በእውነተኛ ጓደኞች መካከል የሚንጸባረቀውንም ከአንጀት የመውደድ ስሜት (ፊሊያ) ያሳያቸዋል።​— ዮሐንስ 16:​27

17. (ሀ) በቤዛው የሚያምኑ ሁሉ ምን አጋጣሚ ተሰጥቷቸዋል? (ለ) “የእግዚአብሔር ልጆች ክብራማ ነፃነት” ለእነርሱ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

17 ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሕይወት ባዘጋጀው የልግስና ዝግጅት የሚያምኑ ሌሎች ሰዎችም አዳም ያጣውን ውድ ዝምድና ማግኘት የሚችሉበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የፍጥረት [የአዳም ዘሮች የሆኑት ሰብዓዊ ፍጥረታት] ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና [ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥት ወራሾች የሆኑት የአምላክ ልጆች ለሰው ዘር ጠቃሚ የሆኑ እርምጃዎች መውሰድ መጀመራቸው በግልጽ የሚታወቅበትን ጊዜ ይጠባበቃሉ ማለት ነው]። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና [ሲወለዱ ሞት የሚያስከትል ኃጢአት ወርሰዋል፤ ራሳቸውን ነፃ ማውጣት የሚችሉበት ምንም መንገድ አልነበራቸውም]፣ በተስፋ [አምላክ በሰጠው ተስፋ] ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።” (ሮሜ 8:​19-21) ይህ ነፃነት ምን ትርጉም ይኖረዋል? ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ወጥተዋል። የአእምሮና የአካል ፍጽምና ያገኛሉ፤ መኖሪያቸው ገነት ይሆናል፤ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት አግኝተው በፍጽምናቸው እየተደሰቱና እርሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ አድናቆታቸውን እየገለጹ ይኖራሉ። ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በአምላክ አንድያ ልጅ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ነው።

18. መጋቢት 23 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ምን እናደርጋለን? ለምንስ?

18 ኒሳን 14, 33 እዘአ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም አንድ ደርብ ላይ በሚገኝ ክፍል ውስጥ የሞቱን መታሰቢያ በዓል አቋቋመ። በየዓመቱ የሚከበረው የሞቱ መታሰቢያ በዓል በሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል ነው። ኢየሱስ ራሱ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ አዟል። (ሉቃስ 22:​19) በ1997 የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው መጋቢት 23 ቀን ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ (ኒሳን 14 ሲጀምር ማለት ነው) ይሆናል። በዚያ ቀን በዚህ የመታሰቢያ በዓል ላይ ከመገኘት የሚበልጥ ነገር ፈጽሞ ሊኖር አይችልም።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ አምላክ ለሰው ልጆች ይህ ነው የማይባል ፍቅር ያሳየው በምን መንገዶች ነው?

◻ የአዳምን ዘሮች ለመቤዠት ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

◻ ይሖዋ ቤዛውን ለማቅረብ ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል?

◻ ቤዛው ምን አስገኝቷል?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ አንድያ ልጁን ሰጥቷል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ