በትዳር ውስጥ አዲሱን ሰውነት ማዳበር
“አእምሮአችሁን በሚያንቀሳቅሰው ኃይል ታደሱ፣ . . . አዲሱን ሰውነት ልበሱ።” — ኤፌሶን 4:23, 24 አዓት
1. ጋብቻ እንደ ቀላል ነገር ተደርጎ መታየት የሌለበት ለምንድን ነው?
ጋብቻ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ከሚወስዳቸው ከባድ እርምጃዎች አንዱ ነው። በመሆኑም እንደ ቀላል ነገር ተደርጎ መታየት አይኖርበትም። ለምን? ምክንያቱም ጋብቻ ከሌላ ሰው ጋር ተሳስሮ ለመኖር የዕድሜ ልክ ግዴታ መግባት ማለት ነው። ሕይወትን በሙሉ ከዚያ ሰው ጋር መካፈል ማለት ነው። ይህ ውል ጽኑ እንዲሆን ከተፈለገ ብስለትና አመዛዛኝ መሆንን ይጠይቃል። ‘አዲሱን ሰውነት ለመቅረጽ አእምሮን የሚያንቀሳቅስ አዎንታዊ የውስጥ ግፊትም ያስፈልጋል። — ኤፌሶን 4:23, 24፤ ከዘፍጥረት 24:10–58ና ከማቴዎስ 19:5, 6 ጋር አወዳድር።
2, 3. (ሀ) የትዳር ጓደኛን በጥበብ ለመምረጥ የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ትዳር ምን ማድረግን የሚጠይቅ ነው?
2 በኃይለኛ የሥጋ ፍላጎት በመገፋፋት በጋብቻ ውስጥ ዘው ብሎ ከመግባት ለመገታት ጥሩ ምክንያት አለ። የጎልማሳነትን ባሕርይ ለማዳበር ጊዜ ያስፈልጋል። ከዚህም ሌላ ጊዜ የሕይወትን ተሞክሮና ዕውቀትን ይጨምራል። ይህም ነገሮችን በትክክል የማመዛዘን ችሎታን ለማዳበር ጥሩ መሠረት ይሆናል። ይህ ከሆነም ተስማሚ የሕይወት ጓደኛ ለመምረጥ የተሻለ ሁኔታ ይኖራል። “ከማይሆን ጋብቻ በነጠላነት መኖር ይሻላል” የሚል አንድ የስፓንኛ ምሳሌ ነገሩን ግልጽ አድርጎ ያስቀምጠዋል። — ምሳሌ 21:9፤ መክብብ 5:2
3 ትክክለኛ የትዳር ጓደኛ መምረጥ ለተሳካ ትዳር መሠረት እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ እንዲሆንም አንድ ክርስቲያን በአካላዊ አቋም፣ ተገቢ ባልሆነ የስሜትና የፍቅር ግፊት ከመመራት ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል አለበት። ጋብቻ የሁለት አካላት ጥምረት ማለት ብቻ አይደለም። ሁለት የተለያዩ ባሕርያት፣ ከሁለት ቤተሰቦች የመጡና በትምህርት፣ በባሕል፣ ምናልባትም በቋንቋ የሚለያዩ የሁለት ሰዎች ጥምረትም ሊሆን ይችላል። የሁለት ሰዎች በጋብቻ መጣመር ምላስን በተገቢ መንገድ መጠቀምን ይጠይቃል። በንግግር ችሎታችን ሰውን እናፈርሳለን አለዚያም እንገነባለን። “በጌታ ብቻ” ማለትም አማኝ ብቻ አግቡ የሚለው የጳውሎስ ምክር ጥበብ የተሞላ መሆኑን ከዚህ ሁሉ ለመረዳት እንችላለን። — 1 ቆሮንቶስ 7:39፤ ዘፍጥረት 24:1–4፤ ምሳሌ 12:18፤ 16:24
በትዳር ውስጥ የሚያጋጥሙ ውጥረቶችን መቀበልና መቋቋም
4. አንዳንድ ጊዜ በትዳር ውስጥ ግጭትና ውጥረት የሚፈጠሩት ለምንድን ነው?
4 ጥሩ የጋብቻ መሠረት ቢኖርም እንኳን ግጭት፣ ተፅዕኖና ውጥረት የሚያጋጥምባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ያገቡም ሆነ ያላገቡ ሰዎች የሚያጋጥሟቸው የተለመዱ ነገሮች ናቸው። የኢኮኖሚና የጤና ችግሮች በማንኛውም ግንኙነት ላይ ውጥረት ሊፈጥሩ ይችላሉ። የስሜት መለዋወጥ በጣም ጥሩ በሆኑ ትዳሮችም ውስጥ ግጭት ሊያመጡ ይችላሉ። ሌላው ጉዳይ ደግሞ ያዕቆብ እንደጠቀሰው ማንም ሰው አንደበቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አለመቻሉ ነው። “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው። . . . እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፣ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል!” — ያዕቆብ 3:2, 5
5, 6. (ሀ) አለመግባባቶች ሲነሱ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? (ለ) አለመግባባቱ እንዲሽር ምን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል?
5 በጋብቻ ውስጥ ውጥረቶች ከተነሱ ሁኔታውን እንዴት ልንቆጣጠረው እንችላለን? አለመግባባት ወደ ጥል፣ ጥልም ግንኙነትን ወደማቋረጥ እንዳይደርስ ለመከላከል የምንችለው እንዴት ነው? አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል በነገሩ ላይ ድርሻ የሚኖረው በዚህ ጊዜ ነው። ይህ የሚገፋፋ መንፈስ ቀና ወይም አፍራሽ ሊሆን፣ ገንቢና ወደ መንፈሳዊነት የሚያደላ አለዚያም በሥጋዊ ዝንባሌዎች በመመራቱ ከደረጃ ዝቅ የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። ገንቢ ከሆነ ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ትዳራቸው ጉዞውን እንዲቀጥል ለማድረግ የተሰበረውን ለመጠገን ይሞክራሉ። ክርክርና በአንዳንድ ነገሮች አለመስማማት ጋብቻውን ወደ ፍጻሜ ሊያመጡት አይገባም። አለመግባባቱን ለማስወገድና የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ በማዋል የጋራ መከባበርና መግባባት እንዲመለስ ለማድረግ ይቻላል። — ሮሜ 14:19፤ ኤፌሶን 4:23, 26, 27
6 በእነዚህ ሁኔታዎች ሥር ቀጥሎ ያሉት የጳውሎስ ቃላት በጣም ተገቢ ናቸው:- “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ [ይሖዋ በነፃ አዓት] ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ [የአንድነት አዓት] ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።” — ቆላስይስ 3:12–14
7. አንዳንዶች በጋብቻቸው ውስጥ ምን ችግር ሊኖርባቸው ይችላል?
7 ይህን ጥቅስ ማንበብ ቀላል ነው፤ ነገር ግን ተጽዕኖ በበዛበት በዘመናዊው ኑሮ ምክሩን በሥራ ላይ ማዋሉ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። መሠረታዊ ችግሩ ምን ይሆን? አንዳንድ ጊዜ አንድ ክርስቲያን ሳይታወቀው ሁለት ዓይነት የአቋም መረጃዎችን ይዞ ይኖር ይሆናል። በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በወንድሞች መካከል ስለሆነ የደግነትና የአሳቢነት ነገሮችን ያደርግ ይሆናል። ከዚያም ወደ ቤት ሲመለስ በተለመደው የቤት ውስጥ ኑሮው መንፈሳዊ ግንኙነቱን ወደ መርሳት ያዘነብል ይሆናል። እቤት ሲሆኑ “እሱ” እና “እሷ” ተባብለው የሚጠራሩ ወንድና ሴት ናቸው። የስሜት መረበሽ ሲገጥማቸው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በፍጹም የማያወጧቸውን መጥፎ ቃላት ሊናገሩ ይችሉ ይሆናል። ምን ተፈጠረ? ለጊዜው የክርስትና ጉዳይ በንኗል። የአምላክ አገልጋይ እቤትም ክርስቲያን ወንድም (እህት) መሆኑን (መሆኗን) ረስቶታል (ረስታዋለች)። አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል ገንቢ በመሆን ፈንታ አፍራሽ ሆኗል። — ያዕቆብ 1:22–25
8. አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል አፍራሽ ሲሆን ምን ውጤት ሊከተል ይችላል?
8 ውጤቱስ ምንድን ነው? ባልየው ‘ሚስቱን እንደ ደካማ ዕቃ አድርጎ እያከበራት ከእርስዋ ጋር በማስተዋል አብሮ መኖሩን’ ያቆም ይሆናል። ሚስትም “የዋህና ዝግተኛ መንፈስዋ” ጠፍቶ ባሏን ማክበሯን ትተው ይሆናል። አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል መንፈሳዊ ከመሆን ይልቅ ሥጋዊ ሆኗል። “ሥጋዊ አእምሮ” አሸንፏል። እንግዲያው አእምሮን የሚገፋፋውን ኃይል መንፈሳዊና ገንቢ ለማድረግ ምን ሊደረግ ይችላል? መንፈሳዊነታችንን ማጠናከር አለብን። — 1 ጴጥሮስ 3:1–4, 7፤ ቆላስይስ 2:18
ይህን ኃይል አጠናክሩት
9. በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ውስጥ ምን ምርጫዎች ይቀርቡልናል?
9 አንቀሳቃሹ ኃይል ውሳኔዎችንና ምርጫዎችን ማድረግ በሚኖርብን ጊዜ አእምሮአችንን የሚገፋፋው ዝንባሌ ነው። ሕይወት ጥሩ ወይም መጥፎ፣ ራስ ወዳድ ወይም ራስ ወዳድ ያልሆኑ፣ ሥነ ምግባራዊ ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ምርጫዎችን በተከታታይ ያቀርብልናል። ትክክለኛውን ውሳኔ እንድናደርግ የሚረዳን ምንድን ነው? የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ላይ ያተኮረ ከሆነ አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል ሊረዳን ይችላል። መዝሙራዊው “አቤቱ ይሖዋ፣ የሥርዓትህን መንገድ አስተምረኝ ሁልጊዜም እፈልገዋለሁ” ሲል ጸልዮአል። — መዝሙር 119:33፤ ሕዝቅኤል 18:31፤ ሮሜ 12:2
10. አእምሮአችንን የሚያንቀሳቅሰውን ኃይል መልካምና ቀና በሆነ መንገድ ልናጠናክረው የምንችለው እንዴት ነው?
10 ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና ካለን እሱን ለማስደሰት እንድንችልና ለትዳር ታማኝ አለመሆንን ከሚጨምረው ክፋት እንድንሸሽ ይረዳናል። እስራኤላውያን ‘በአምላካቸው በይሖዋ ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ’ ተበረታተዋል። ይሁን እንጂ አምላክ “እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] የምትወድዱ፣ ክፋትን ጥሉ” በማለትም መክሯቸዋል። ከአሥርቱ ትእዛዛት ሰባተኛው “አታመንዝር” ይል ስለነበረ እስራኤላውያን ምንዝርን መጥላት ነበረባቸው። ያ ትዕዛዝ አምላክ በጋብቻ ውስጥ ታማኝነት መኖር እንዳለበት የሚፈልግ መሆኑን ያሳያል። — ዘዳግም 12:28፤ መዝሙር 97:10፤ ዘጸአት 20:14፤ ዘሌዋውያን 20:10
11. አእምሮአችንን የሚያንቀሳቅሰውን መንፈስ ይበልጥ ልናጠነክረው የምንችው እንዴት ነው?
11 አእምሮን የሚያንቀሳቅሰውን ኃይል ከዚህ የበለጠ ልናጠነክረው የምንችለው እንዴት ነው? መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችንና አቋሞችን ከፍ አድርገን በማየት ነው። ይህም ማለት የአምላክን ቃል አዘውትረን የማጥናትን አስፈላጊነት በተግባር በማሳየትና የይሖዋን ትምህርቶችና ምክሮች በተመለከተ በአንድነት በምናደርገው ውይይት መደሰትን መማር ማለት ነው። ውስጣዊ የልብ ስሜታችን እንደሚከተለው እንዳለው መዝሙራዊ መሆን ይኖርበታል:- “በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፣ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ [ይሖዋ፣ አዓት] የሥርዓትህን መንገድ አስተምረኝ፣ ሁልጊዜም እፈልገዋለሁ። እንዳስተውል አድርገኝ፣ ሕግህንም እፈልጋለሁ።” — መዝሙር 119:10, 11, 33, 34
12. የክርስቶስን አስተሳሰብ በማንፀባረቅ በኩል አንድ ሊያደርጉን የሚችሉት ምን ነገሮች ናቸው?
12 ለይሖዋ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይህን ዓይነት አድናቆት እንደያዝን ለመቀጠል የምንችለው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ብቻ ሳይሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አዘውትረን በመካፈልና በክርስቲያን አገልግሎት አብረን በመሥራትም ጭምር ነው። እነዚህ ኃይለኛ ግፊት የሚሰጡ ሁለት ነገሮች የክርስቶስን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁ ራስ ወዳድነት የሌለባቸው ውሳኔዎችን ለመወሰን እንችል ዘንድ አእምሮን የሚያንቀሳቅሰውን ኃይል ያለማቋረጥ ሊያጠነክሩት ይችላሉ። — ሮሜ 15:5፤ 1 ቆሮንቶስ 2:16
13. (ሀ) አእምሮን የሚያንቀሳቅሰውን ኃይል ለማጠንከር ጸሎት በጣም ጠቃሚ ነገር የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
13 ሌላው ነገር ደግሞ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ” ሲል ያጎላው ነገር ነው። (ኤፌሶን 6:18) ባልና ሚስት አንድ ላይ መጸለይ ያስፈልጋቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ጸሎቶች ልብን ይከፍቱና ማንኛውንም ዓይነት ቅሬታ ለማስወገድ ወደሚረዱ ግልጽ የሆኑ ውይይቶች ይመራሉ። በፈተና ጊዜ እርዳታ ለማግኘትና ከክርስቶስ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ ነገር ለማድረግ የሚያስችለንን መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲሰጠን በመጠየቅ በጸሎት ወደ አምላክ ዘወር ማለት ያስፈልገናል። ፍጹሙ ኢየሱስ እንኳን በብዙ አጋጣሚዎች ወደ አባቱ በጸሎት በመቅረብ እርዳታና መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲሰጠው ጠይቋል። ጸሎቶቹ ከልብ የመነጩና በጋለ ስሜት የሚቀርቡ ነበሩ። ዛሬም በተመሳሳይ ወደ ክፉ ድርጊት የሚገፋፋ ፈተና ሲያጋጥመን ለሥጋ ፍላጎት እንድንሸነፍና የጋብቻ መሐላችንን እንድናፈርስ የመጣብንን ግፊት ለመቋቋም እንዲረዳን ይሖዋን ብንለምነው ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚያስችል ጥንካሬ ልናገኝ እንችላለን። — መዝሙር 119:101, 102
ጉልህ ልዩነት ያላቸው የጠባይ ምሳሌዎች
14, 15. (ሀ) ዮሴፍ ወደ መጥፎ ድርጊት የሚገፋፋ ፈተና ሲያጋጥመው ምን አደረገ? (ለ) ዮሴፍ ወደ መጥፎ ድርጊት የሚገፋፋውን ፈተና ለመቋቋም እንዲችል የረዳው ምንድን ነው?
14 ወደ ክፉ ድርጊት የሚገፋፋ ፈተናን እንዴት ልንቋቋም እንችላለን? በዚህ ረገድ ዮሴፍና ዳዊት በተከተሏቸው አቅጣጫዎች ላይ ግልጽ ልዩነት እናያለን። የጶጢፋር ሚስት መልከ መልካምና በዚያ ወቅት ነጠላ የነበረውን ዮሴፍን ነጋ ጠባ እየወተወተች ልታሳስተው በሞከረች ጊዜ በመጨረሻው እንዲህ ብሎ መለሰላት:- “ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለ ሆንሽ [ባልሽ] ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” — ዘፍጥረት 39:6–9
15 በፈተናው መሸነፍ ቀላል ሆኖ ሳለ ዮሴፍ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲከተል የረዳው ምንድን ነው? አእምሮውን የሚያንቀሳቅስ ብርቱ ኃይል ነበረው። ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለመጠበቅ በጣም ንቁ ነበር። እንዲሁም ከዚያች የወረት ፍቅር ከያዛት ሴት ጋር ዝሙት ቢፈጽም በባልዋ ላይ ብቻ ሳይሆን ከሁሉ ይበልጥ ደግሞ በአምላክ ላይም ኃጢአት መሥራቱ እንደሆነ ያውቅ ነበር። — ዘፍጥረት 39:12
16. ዳዊት ወደ መጥፎ ድርጊት የሚገፋፋ ፈተና ሲያጋጥመው ምን አደረገ?
16 በተቃራኒው ዳዊት ምን አደረገ? እሱ በሕጉ በተፈቀደው መሠረት ብዙ ሚስቶች የነበሩት ባለ ትዳር ነበር። አንድ ምሽት በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ ሲመለከት ገላዋን የምትታጠብ አንዲት ሴት አየ። እሷም የኦርዮ ሚስት የነበረችው መልከ መልካሟ ቤርሳቤህ ነበረች። ዳዊት ለሚያደርገው ነገር ምርጫ እንደነበረው ግልጽ ነው። ይኸውም የጾታ ፍላጎት በልቡ ውስጥ እያደገ ቢሄድም እሷን መመልከቱን መቀጠል ወይም ከቦታው ዘወር በማለት ወደ ክፉ ድርጊት ከሚገፋፋው ፈተና መራቅ ናቸው። ታዲያ ምን ለማድረግ መረጠ? ወደ ቤተ መንግሥቱ አስመጣትና ከእርሷ ጋር ምንዝር ፈጸመ። ባልዋ እንዲሞት በማድረጉም ከዚህ የከፋ ነገር ፈጽሟል። — 2 ሳሙኤል 11:2–4, 12–27
17. በጊዜው ስለነበረው የዳዊት መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ልንረዳ እንችላለን?
17 የዳዊት ችግር ምን ነበር? በኋላ በመዝሙር 51 ላይ ጸጸት በሞላበት ሁኔታ ከተናዘዘው ውስጥ አንዳንድ እውነታዎችን ልንረዳ እንችላለን። እንዲህ አለ:- “አቤቱ፣ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።” ወደ ክፉ ድርጊት የሚገፋፋ ፈተና ባጋጠመው ወቅት ንጹሕና ጽኑ መንፈስ እንዳልነበረው ግልጽ ነው። ምናልባት የይሖዋን ሕግ ማንበብን ችላ በማለቱ መንፈሳዊነቱ ተዳክሞ ሊሆን ይችላል። ወይም የንግሥና ሥልጣኑና ኃይሉ አስተሳሰቡን እንዲያበላሽበት በመፍቀዱ ለጾታዊ ፍላጎት ሊሸነፍ ችሎ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የነበረው አእምሮውን የሚያንቀሳቅስ ኃይል በእርግጥ ራስ ወዳድና ኃጢአተኛ ነበር። በዚህም ምክንያት ‘አዲስና ጽኑ መንፈስ’ እንደሚያስፈልገው ተገነዘበ። — መዝሙር 51:10፤ ዘዳግም 17:18–20
18. ኢየሱስ ምንዝርን በተመለከተ ምን ምክር ሰጠ?
18 አንዳንድ ክርስቲያኖች ከሁለት አንዳቸው ወይም ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ከዳዊት ጋር የሚመሳሰል መንፈሳዊ ድካም ውስጥ እንዲገቡ በመፍቀዳቸው ትዳራቸው ፈርሷል። የዳዊት ምሳሌ ሌላን ሴት ወይም ወንድ በፍትወታዊ ስሜት በመመልከት እንዳንቀጥል ሊያስጠነቅቀን ይገባል። ምክንያቱም በመጨረሻው ምንዝር ሊያስከትል ይችላል። ኢየሱስ ሰው በዚህ ረገድ ያለውን ስሜት በመረዳት እንዲህ ብሏል:- “አታመንዝር እንደተባለ ሰምታችኋል እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል።” እንዲህ ባለው ሁኔታ አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል መንፈሳዊ ሳይሆን ራስ ወዳድና ሥጋዊ ነው። ታዲያ ክርስቲያኖች ከምንዝር ለመራቅና ትዳራቸውን ደስተኛና የሚያረካ አድርገው ለማቆየት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? — ማቴዎስ 5:27, 28
የጋብቻን ማሰሪያ አጥብቁ
19. ጋብቻ ሊጠናከር የሚችለው እንዴት ነው?
19 ንጉሥ ሰሎሞን “አንዱም አንዱን ቢያሸንፍ ሁለቱ በፊቱ ይቆማሉ፤ በሦስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም” ብሎ ጽፏል። እርግጥ ነው፤ በችግር ጊዜ አንድ ከመሆን ስምምነት ባለበት ትዳር ውስጥ ሁለት መሆን ይሻላል። ነገር ግን አምላክን በማሰሪያቸው ውስጥ በመጨመር ማሰሪያውን በሦስት የተገመደ ቢያደርጉት ጋብቻቸው ጠንካራ ይሆናል። ታዲያ አምላክ በትዳር ውስጥ ሊኖር የሚችለው እንዴት ነው? ባልና ሚስት አምላክ ስለ ጋብቻ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምክሮች በሥራ ላይ በማዋል ነው። — መክብብ 4:12
20. አንድን ባል የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ሊረዱት ይችላሉ?
20 አንድ ባል ቀጥሎ ያሉትን ጥቅሶች ምክር በሥራ ላይ ካዋለ ትዳሩን የተሳካ ለማድረግ የተሻለ መሠረት ይኖረዋል:-
“እንዲሁም፣ እናንተ ባሎች ሆይ፣ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ [እንደ ደካማ ዕቃ አድርጋችሁ በማየት አዓት ] ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል፣ አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።” — 1 ጴጥሮስ 3:7
“ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል።” — ኤፌሶን 5:25, 28
“ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል:- መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፣ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ።” — ምሳሌ 31:28, 29
“በፍም ላይ የሚሄድ፣ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም። የሚያመነዝር . . . ነፍሱን ያጠፋል።” — ምሳሌ 6:28, 29, 32
21. አንዲትን ሚስት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ሊረዷት ይችላሉ?
21 አንዲት ሚስትም ቀጥሎ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቋሚ ሕግጋት ተግታ በሥራ ላይ ብታውል ለትዳሯ ዘላቂነት አስተዋፅኦ ታበረክታለች:-
“እንዲሁም፣ እናንተ ሚስቶች ሆይ፣ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን [እንዲሁም ] የዋህና ዝግተኛ [መንፈሳችሁን ] እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው።” — 1 ጴጥሮስ 3:1–4
“ባል ለሚስቱ [በጾታ ፍላጎቷ ረገድ ] የሚገባትን ያድርግላት፣ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ። . . . ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፣ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ።” — 1 ቆሮንቶስ 7:3–5
22. (ሀ) ጋብቻን በጥሩ ሁኔታ ሊነኩት የሚችሉት ምን ሌሎች ነገሮች ናቸው? (ለ) ይሖዋ መፋታትን እንዴት ይመለከተዋል?
22 በተጨማሪም ዕንቁን የሚያስውቡ የተለያዩ መልኮች እንዳሉት ሁሉ ፍቅር፣ ደግነት፣ ርኅራኄ፣ ትዕግሥት፣ የሰውን ችግር መረዳት፣ ማበረታቻ መስጠትና ምስጋና የጋብቻ ሌሎች አንጸባራቂ ገጽታዎች እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። እነዚህ ነገሮች የሌሉት ጋብቻ ልክ የፀሐይ ብርሃንና ውኃ እንደማያገኝና እንደማያብብ አትክልት ይሆናል። እንግዲያው አእምሮአችንን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል በትዳራችን ውስጥ እርስ በርስ ለመበረታታትና መንፈሱን የምናድስ ለመሆን እንዲገፋፋን እናድርግ። ይሖዋ ‘መፋታትን እንደሚጠላ’ አስታውሱ። ክርስቲያናዊ ፍቅርን የምትሠሩበት ከሆነ ምንዝርና የጋብቻ መፍረስ ምንም ቦታ ሊኖራቸው አይገባም። ለምን? ምክንያቱም “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።” — ሚልክያስ 2:16፤ 1 ቆሮንቶስ 13:4–8፤ ኤፌሶን 5:3–5
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ትዳር ደስታ ያለበት ይሆን ዘንድ ምን መሠረታዊ ነገር ያስፈልጋል?
◻ አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል ትዳርን ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
◻ አእምሮአችንን የሚያንቀሳቅሰውን ኃይል ለማጠናከር ምን ልናደርግ እንችላለን?
◻ ዮሴፍና ዳዊት ወደ ክፉ ድርጊት የሚገፋፋ ፈተና ባጋጠማቸው ወቅት በወሰዱት እርምጃ የተለያዩት እንዴት ነው?
◻ ባሎችና ሚስቶች የጋብቻቸውን ማሠሪያ ለማጠንከር የሚረዷቸው ምን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮች አሉ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጉባኤ ውስጥ ደግ እቤት ደግሞ ክፉ በመሆን ሁለት ዓይነት የአኗኗር ደረጃ አለንን?