የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ጭንቀትን ለመቋቋም ምን ሊረዳህ ይችላል?
ጭንቀት ያጠቃሃልን? እንዲህ ከሆነ ችግሩ በአንተ ላይ ብቻ የደረሰ አይደለም። ያለንበት ጊዜ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ነው፤ በማናቸውም ዕድሜና የኑሮ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጭንቀት ያጋጥማቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ለሕክምና ወደ ዶክተሮች ከሚሄዱት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ያሉባቸው ችግሮች ከጭንቀት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ አንዳንድ ኤክስፐርቶች ይናገራሉ።
ሆኖም ጭንቀት በራሱ መጥፎ ነው ማለት አይደለም። ጭንቀት ያጋጠማቸው ሰዎችን የሚያክም የአንድ ክሊኒክ ዲሬክተር እንዲህ ብለዋል:- “እንዲያውም ጭንቀት እርካታ፣ የመኖር ፍላጎትና ብዙ ነገሮችን ለመሥራት የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። ልንቆጣጠረው ከቻልን ደስታ እናገኝበታለን።”
በሌላ በኩል ደግሞ ጭንቀት ጎጂ ሊሆን ይችላል። ጭንቀት የሚያስቸግርህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላ ለህ? ከዚህ በታች ጭንቀት የሚያስከትልብህን መጥፎ ውጤቶች ለመ ቀነስ ሊረዱህ የሚችሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው ጥበብ ላይ የተመሠረቱ ጥቂት ሐሳቦች ቀርበዋል።
ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮችን ከመጠበቅ ተቆጠብ
መጽሐፍ ቅዱስ “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 13:12) በተስፋ ስንጠባበቃቸው የነበሩ ነገሮች ሳይፈጸሙ ሲቀሩ ጭንቀት በጣም ሊያይልብን ይችላል። ይህ ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው ፈጽሞ ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮችን ተስፋ ስናደርግ ነው።
ለምሳሌ ያህል፣ በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡት ማስታወቂያዎች ብዙዎች ደስታ ማግኘታቸው የተመካው ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት ላይ እንደሆነ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። አንድ ሰው ከአቅሙ በላይ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት የሚመኝ ከሆነ ጭንቀትና ብስጭት ሊያጋጥመው ይችላል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” የሚል ምክር ይሰጣል። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) አዎን፣ ምንም እንኳ ለማግኘት የምትፈልገው መኪና፣ ቤት ወይም የቤት ቁሳቁሶች ባይኖርህም ያለህን አድንቅ። ለቁሳዊ ነገሮች ያለህ አመለካከት ልከኛ ይሁን።
ከሰዎች ከሚገባው በላይ መጠበቅም ጭንቀት ያስከትላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አሠሪ ወይም ተቆጣጣሪ ከሚያሠራቸው ሰዎች ምክንያታዊ የሆነ ነገር እንዲሠሩ ሊጠብቅባቸው ቢችልም ከእነሱ ፍጽምናን መጠበቅ ሞኝነት ይሆናል። በብራዚል የሚኖሩ ካርሎስ የተባሉ የአንድ ፋብሪካ ተቆጣጣሪ እንዲህ አሉ:- “የሰዎችን አቅም ማወቅ አለብህ። ሊያደርጉት ከሚችሉት ነገር በላይ የምትጠብቅባቸው ከሆነ የጭንቀቱ መጠን ይጨምራል። ሁሉንም ደስታ ያሳጣል።”— ከኤርምያስ 17:5–8 ጋር አወዳድር።
ለከፍተኛ የሥራ ክንውን መጣጣር የሚፈጥረውን ጭንቀት ተቆጣጠረው
ላቲን አሜሪካ ዴይሊ ፖስት የተባለው ጋዜጣ ‘አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ የሚደረገው ከፍተኛ ትግልና ፉክክር የልብ በሽታ ዋነኛ መንስኤ ነው’ ሲል በመግለጽ ሌላውን የጭንቀት መንስኤ ጠቁሟል። አንድ ወጣት የሒሳብ ሠራተኛ “በቢሮ ውስጥ ስሠራ በጣም እጨነቃለሁ፤ ምንም ዓይነት ድክመት እንዳይገኝብኝ እጠነቀቃለሁ። ሥራዬን የምሠራው ውጥረት በተሞላበት ሁኔታ ነው፤ ከሌሎች ምስጋና አለማግኘቴ ደግሞ ያበሳጨኛል” ብሏል።
ሰሎሞን እውቅናና ከፍተኛ የሥራ ውጤት ለማግኘት የሚደረጉትን እንደነዚህ የመሳሰሉ ጥረቶች በተመለከተ “የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፣ በባልንጀራውም ዘንድ ቅንዓት እንዲያስነሣ አየሁ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው” ብሏል።— መክብብ 4:4
“ፈጣን ርዋጮች ዘወትር በአሸናፊነት አይወጡም” የሚለው እውነታ በሥራ እድገት ወይም እውቅና በማግኘት ረገድም ይሠራል። (መክብብ 9:11 የ1980 ትርጉም ) ማሪያ የተባለች አንዲት ብራዚላዊ የቢሮ ሠራተኛ ሁኔታውን በሚከተለው መንገድ አስቀምጣዋለች:- “አንድ ግለሰብ ችሎታ ሊኖረው ይችላል፤ ይሁን እንጂ አንዳንድ ሁኔታዎች ምናልባትም አድልዎ የሥራ እድገት እንዳያገኝ ሊያደርገው ይችላል።”— ከመክብብ 2:21 እና ከ10:6 ጋር አወ ዳድር።
በተስፋ የምትጠባበቃቸው ነገሮች ከልክ ያለፉ መሆን የለባቸውም፤ አቅምህን እወቅ። ሥራ መሥራት ያለብህ እድገት ለማግኘት ብለህ ሳይሆን ሥራው የሚሰጠውን ደስታ ለማግኘት መሆን ይኖርበታል። (መክብብ 2:24) በእርግጥም ከፍተኛ የሥራ ውጤት ለማግኘት ብቻ የሚያስብ ሰው በሕይወት ውስጥ የሚገኘውን ብዙውን ደስታ ያጣል፤ በውስጡ ያለው ውጥረትም ጥረቱ ስኬታማ እንዳይሆን ያደርግበታል። ስለዚህ ዶክተር አርኖልድ ፎክስ የሚከተለውን ምክር ሰጥተዋል:- “ባለህ የሥራ መስክ የተሻልክ ሰው ለመሆን መጣርህ የሚደነቅ ግብ ቢሆንም ይህ አሳብ ሕይወትህን እንዲገዛው አትፍቀድለት። ፍቅርን፣ ሳቅንና ከሕይወት የሚገኘውን ደስታ ችላ ካልክ ወይም አንድ ነገር ላይ ከመጠን በላይ ከማተኮርህ የተነሳ ሕይወት የምትሰጠውን ደስታ ማጣጣም ከተውክ ራስህን እያስጨነቅህ ነው።”
ልታደርጋቸው የምትችላቸው ነገሮች
በየቀኑ የሚያጋጥሙ ውጥረቶች የሚፈጥሩትን ጭንቀት ለመዋጋት የሚቻልበት ሌላው መንገድ ተጫዋች መሆን ነው። (መክብብ 3:4) የደስተኛነት መንፈስ ለማሳየት የግድ ቀልደኛ መሆን አያስፈልግህም። “ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፣ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች።”— ምሳሌ 17:22
ሥራዎችን ለነገ የማቆየት ዝንባሌ አለህን? ሥራን ዛሬ ነገ እያሉ ማቆየት የኋላ ኋላ ጭንቀትን ይጨምራል እንጂ አይቀንስም። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ” ሲል ይመክራል። (ሮሜ 12:11) መሥራት የሚያስፈልጉህን ነገሮች አንድ በአንድ በጽሑፍ ወይም በአእምሮህ ያዝ። (ምሳሌ 21:5) ከዚያም በቅድሚያ ሊሠሩ የሚገባቸውን ነገሮች ወስንና እነሱን መሥራት ጀምር።
ሆኖም የምትችለውን ያህል እየጣርክም ጭንቀት የሚሰማህ ከሆነ ምን ማድረግ አለብህ? አስተሳሰብህን ለመለወጥ የታሰበበት ጥረት ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። ከዚህ በፊት የሠራሃቸውን ስሕተቶች አታብሰልስል። ይህ አሁን ያለብህን ጭንቀት ሊያባብሰው ይችላል። አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋ የሚከተለውን ጽፈዋል:- “ትምህርት ማግኘት የሚቻለው ካሳለፍነው የሕይወት ተሞክሮ ነው፤ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው ግን ከፊታችን ባለው ጊዜ ነው።” ከሠራነው ስሕተት መማር የምንችል ብንሆንም እንኳ አሁን የምናደርጋቸው ነገሮች የወደፊቱን ሕይወታችንን ይቀርጹታል።
ንጉሥ ዳዊት “የልቤ ችግር ብዙ ነው፤ ከጭንቀቴ አውጣኝ” ብሎ ወደ ይሖዋ በጸለየበት ወቅት ከሁሉ የተሻለውን የጭንቀት መፍትሔ ጠቁሟል። (መዝሙር 25:17) አዎን፣ ዳዊት ከጭንቀቶቹ እንደሚያላቅቀው የተማመነው በአምላክ ነበር። ጊዜ ወስደህ የአምላክን ቃል ካነበብክና ካሰላሰልክ አንተም እንደዚሁ ወደ አምላክ ይበልጥ እንደቀረብክ ይሰማሃል። የአምላክን ዓላማዎች ይበልጥ እየተረዳህ በሄድክ መጠን በሕይወትህ ውስጥ ለእሱ ፍላጎቶች ቅድሚያ መስጠትን ትማራለህ፤ ይህም አላስፈላጊ ከሆኑ ከብዙ ጭንቀቶች ይገላግልሃል። (ማቴዎስ 6:31, 33) ስለ ዛሬ ብቻ ማሰብን ተማር። የነገውን ጭንቀቶች በዛሬዎቹ ጭንቀቶች ላይ ለምን ትጨምራለህ? ኢየሱስ ሁኔታውን በዚህ መንገድ አስቀምጦታል:- “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።”— ማቴዎስ 6:34
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“አንድ ግለሰብ ችሎታ ሊኖረው ይችላል፤ ይሁን እንጂ አንዳንድ ሁኔታዎች ምናልባትም አድልዎ የሥራ እድገት እንዳያገኝ ሊያደርገው ይችላል”
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
The Metropolitan Museum of Art, Funds given by the Josephine Bay Paul and C. Michael Paul Foundation, Inc, and the Charles Ulrik and Josephine Bay Foundation, Inc, and the Fletcher Fund, 1967.