የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 3/8 ገጽ 22-23
  • ድህነት ለስርቆት ማሳበቢያ ሊሆን ይችላልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ድህነት ለስርቆት ማሳበቢያ ሊሆን ይችላልን?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አምላክ ምን ይላል?
  • ድሆች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
  • ስርቆት ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—1996
  • ስርቆት እየጨመረ ያለው ለምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ሌባ እንዳትሆን ተጠንቀቅ!
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • ሁልጊዜ ሐቀኛ መሆን ይኖርብሃል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 3/8 ገጽ 22-23

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ድህነት ለስርቆት ማሳበቢያ ሊሆን ይችላልን?

“የሰው ልጅ ደስታ እንዳያገኝ ቀንደኛ ጠላት የሆነው ነገር ድህነት ነው። ድህነት ነፃነት ያሳጣል፣ በጎ ባሕርያት እንዳይኖሩ ያደርጋል እንዲሁም ለሌሎች በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች መፈጠር ምክንያት ነው።”—ሳሙኤል ጆንሰን፣ የ18ኛው መቶ ዘመን ደራሲ

የሮማ መንግሥታዊ ባለ ሥልጣን የነበሩት ማግነስ ኦሪሊየስ ካሲዮዶረስ “ድህነት የወንጀል ምንጭ ነው” ብለው ነበር። እነዚህ አመለካከቶች በድህነት ሳቢያ አንዳንድ ወንጀሎች መፈጸማቸው የማይቀር ነው የሚል ሐሳብ የሚያስተላልፉ ይመስላል። በዛሬው ጊዜ በተለይ የስርቆት ወንጀል ሲፈጸም ብዙዎች በዚህ ሐሳብ ሳይስማሙ አይቀርም።

አንድ ሰው ጭቆና ከደረሰበትና ድሃ ከሆነ መስረቁ አግባብነት አለው የሚለው እምነት በሰፊው ተቀባይነት አግኝቷል። ከሀብታሞች እየሰረቀ ለድሆች ያከፋፍል ስለ ነበረው ስለ ታዋቂው ሽፍታ ስለ ሮቢን ሁድ የሚተርከውን ዝነኛውን የ14ኛው መቶ ዘመን የእንግሊዝ የውዳሴ ግጥም እንውሰድ። ሮቢን ሁድ ለብዙ ምዕተ ዓመታት እንደ ጀግና ይታይ ነበር።

በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች ከባድ የኢኮኖሚ ችግሮች እንዳሉባቸው አይካድም። በቅርቡ የዓለም ባንክ እንደዘገበው 1.3 ቢልዮን ሰዎች በቀን ከአንድ ዶላር በሚያንስ ገቢ ይተዳደራሉ። ከፊልፒንስ ዜጎች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ራሳቸውን ድሃ አድርገው እንደሚቆጥሩ ከአንድ ጥናት የተገኘው ውጤት ያሳያል። በብራዚል 20 በመቶ የሚሆኑት በጣም ሀብታም ሰዎች፣ 20 በመቶ ከሚሆኑት በጣም ድሃ ሰዎች 32 እጅ የሚበልጥ ገቢ አላቸው። እንደዚህ ያሉት ሁኔታዎች አንዳንድ ሰዎችን በጣም ስለሚያበሳጯቸው የትኛውንም ዘዴ፣ ስርቆትንም ቢሆን ተጠቅመው በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማግኘት እንዲጥሩ ያደርጋቸው ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስርቆትን በግልጽ ያወግዛል። ከአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ ስምንተኛው “አትስረቅ” የሚል ነው። (ዘጸአት 20:15) ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አስከፊ በሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ሌባ የሚፈጽመው ስርቆት ስህተት የለውም ብለው ያምናሉ።

ይህም የሚከተሉትን አሳሳቢ ጥያቄዎች ያስነሣል:- ድህነት በእርግጥ ለስርቆት ማሳበቢያ ሊሆን ይችላልን? አንድ ሰው አስከፊ የሆነ የኢኮኖሚ ችግር ካለበት ምን ማድረግ ይኖርበታል? የታመሙ ወይም የተራቡ ልጆች ቢኖሩትስ? በተለይ የተሰረቁት ነገሮች ባለ ንብረቱን ምንም የማይጎዱ ቢሆኑ ይሖዋ አምላክ በእነዚህ ሁኔታዎች ረገድ ስርቆትን ይፈቅዳልን?

አምላክ ምን ይላል?

ኢየሱስ የአባቱን ስብዕና ያንጸባረቀ እንደ መሆኑ መጠን እሱ የተወልን ምሳሌ የአምላክን አመለካከት እንድናስተውል ይረዳናል። (ዮሐንስ 12:49) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከችግረኞች ጋር ባለው ግንኙነት በጣም አዛኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ . . . አዘነላቸው” ይላል። (ማቴዎስ 9:36) ሆኖም በማንኛውም ሁኔታ ሥር ስርቆትን አልፈቀደም። በተመሳሳይም አምላክ ለድሆች ቢያስብም ድህነትን ለስርቆት ማሳበቢያ አድርጎ አይመለከተውም። መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳይያስ 61:8 ላይ አምላክ ‘ስርቆትንና በደልን እንደሚጠላ’ ይነግረናል። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ሌቦች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ በግልጽ ተናግሯል። ስለዚህ የአምላክ አመለካከት ምን እንደሆነ ጥርጣሬ እንዲገባን አልተተውንም።—1 ቆሮንቶስ 6:10

ይሁን እንጂ ምሳሌ 6:30 “ሌባ በተራበ ጊዜ ነፍሱን ሊያጠግብ ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም” ይላል። ይህ ዐረፍተ ነገር ለስርቆት ተገቢ ምክንያት እንዳለ ይገልጻልን? በፍጹም አይገልጽም። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ አምላክ የተሳሳተውን ግለሰብ እንደሚቀጣው ያሳያል። ቀጥሎ ያለው ጥቅስ “ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፣ በቤቱም ያለውን ሁሉ ይሰጣል” ይላል።—ምሳሌ 6:31

በረሃብ ምክንያት የሰረቀ ሌባ በስግብግብነት ወይም ባለ ንብረቱን ለመጉዳት ሲል ከሰረቀ ሰው ጋር እኩል ሊታይ ባይችልም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ በማንኛውም ዓይነት የስርቆት ተግባር መካፈል አይገባቸውም። በአስከፊ ድህነት ውስጥ የተዘፈቀ ግለሰብም እንኳ ቢሰርቅ የአምላክን ስም ያሰድባል። ምሳሌ 30:8, 9 (የ1980 ትርጉም) ነገሩን እንዲህ ሲል አስቀምጦታል:- “የሚያስፈልገኝን ያህል ምግብ ስጠኝ። . . . ድኻ ብሆን ደግሞ እሰርቅ ይሆናል፤ በዚህም ሁኔታ የአንተን የአምላኬን ስም አሰድባለሁ።” አዎን፣ ሌባ አምላክን ያሰድባል። ስርቆት ፍቅር የጎደለው አድራጎት በመሆኑ በድሃም ይሁን በሀብታም ላይ ቢፈጸም ኃጢአት ነው። አምላክንና ሌሎች ሰዎችን የሚወዱ ሁሉ ለመስረቅ ሰበብ አይፈጥሩም።—ማቴዎስ 22:39፤ ሮሜ 13:9, 10

ጎስቋላ ኑሮ ያለው ሰው የመስረቅ መብት አለው የሚለው ሐሳብ ምክንያታዊ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ አባባል ዝቅተኛ የአካል ብቃት ያለው አትሌት የተከለከሉ መድኃኒቶችን ወስዶ ለማሸነፍ ቢጥር መብቱ ነው ከማለት እምብዛም አይለይም። አትሌቱ ቢያሸንፍም እንኳ የማጭበርበር ድርጊት ፈጽሟል። ሌሎች አትሌቶች ሕገ ወጥ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ድላችንን ነጥቆብናል የሚል ስሜት ቢያድርባቸው ትክክል ናቸው። በሌባውም ረገድ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሐቀኝነት በጎደለው መንገድ የሌሎችን ንብረት ወስዷል። ጎስቋላ ኑሮ መግፋቱ ብቻ የተጠቀመበት ዘዴ ትክክል እንዲሆን አያደርግም።

ማንኛውም ሌባ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከፈለገ ከአካሄዱ ንስሐ መግባት ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፣ . . . በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም” ሲል አጥብቆ ይመክራል። (ኤፌሶን 4:28) ቀደም ሲል ሌቦች የነበሩ ሰዎች ከልባቸው ንስሐ ከገቡ ይሖዋ ይቅር እንደሚላቸው እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።—ሕዝቅኤል 33:14-16

ድሆች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር የጻድቁን ነፍስ አያስርብም፤ የኃጢአንን ምኞት ግን ይገለብጣል” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (ምሳሌ 10:3) አምላክ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ሆን ብለው ሕጉን የሚተላለፉ ሰዎችን አይረዳም። ይሁን እንጂ እርሱን ለመታዘዝ ከልባቸው ለሚጥሩ ሰዎች የሚራራ ከመሆኑም በላይ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማግኘት የሚያደርጉትን ልፋት ይባርካል።—መዝሙር 37:25

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተላቸው ኑሯቸውን እንዳሻሻለላቸው ተገንዝበዋል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ጠንክረው እንዲሠሩ እንዲሁም እንደ ቁማር፣ ስካር፣ ማጨስና አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ ከመሳሰሉት አልባሌ ተግባራት እንዲርቁ የሚሰጣቸውን ምክር በሥራ ላይ ማዋላቸው ከሚያስፈልጋቸው በላይ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። (ገላትያ 5:19-21) ይህ እምነት ማሳየት የሚጠይቅ ሲሆን እንዲህ ያደረጉ ሁሉ “እግዚአብሔር ቸር” እንደሆነና በእሱ የሚተማመኑትን እንደሚረዳ ተገንዝበዋል።—መዝሙር 34:8

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮቢን ሁድ:- General Research Division/The New York Public Library/Astor, Lenox and Tilden Foundations

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ