-
መጻተኞች ወደ አምላክ የጸሎት ቤት ተሰበሰቡየኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2
-
-
ለመጻተኛውና ለጃንደረባው የተሰጠ ማጽናኛ
6. ይሖዋ በመቀጠል ትኩረቱን ያደረገው በየትኞቹ ሰዎች ላይ ነው?
6 ይሖዋ በመቀጠል እሱን ለማገልገል ቢፈልጉም እንኳ በሙሴ ሕግ መሠረት በአይሁድ ጉባኤ የመገኘት መብት የሌላቸውን ሁለት ዓይነት ሰዎች የሚመለከት ቃል ተናገረ። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ወደ እግዚአብሔርም የተጠጋ መጻተኛ:- በእውነት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ይለየኛል አይበል፤ ጃንደረባም:- እነሆ፣ እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ አይበል።” (ኢሳይያስ 56:3) መጻተኛው ከእስራኤል ምድር እወገዳለሁ የሚል ስጋት አለበት። ጃንደረባው ደግሞ ስሙን የሚያቆዩ ልጆች መውለድ አለመቻሉ ያሳስበዋል። ይሁንና ሁለቱም ተስፋ ሊቆርጡ አይገባም። ተስፋ መቁረጥ የማይገባቸው ለምን እንደሆነ ከመመርመራችን በፊት ግን እነዚህ ሰዎች በሙሴ ሕግ መሠረት በእስራኤል ሕዝብ መካከል ምን ቦታ እንዳላቸው እንመልከት።
7. ሕጉ በእስራኤል በሚኖሩ መጻተኞች ላይ ምን ገደቦች አበጅቷል?
7 ያልተገረዙ መጻተኞች ከእስራኤላውያን ጋር በአምልኮ ሥርዓት የመካፈል መብት የላቸውም። ለምሳሌ ያህል በማለፍ በዓል ላይ መካፈል አይችሉም። (ዘጸአት 12:43) መጻተኞች የአገሪቱን ሕግ በግልጽ እስካልተጻረሩ ድረስ ጥሩ መስተንግዶ ያገኙ የነበረ ከመሆኑም በላይ ምንም ዓይነት አድልዎ አይደረግባቸውም ነበር። ይሁን እንጂ ከሕዝቡ ጋር ቋሚ የሆነ ትስስር መፍጠር አይችሉም። እርግጥ አንዳንዶቹ ሕጉን ሙሉ በሙሉ ይቀበሉ የነበረ ሲሆን ይህንንም ለማሳየት ወንዶቹ ይገረዙ ነበር። በዚህ መንገድ ወደ ይሁዲነት ከተለወጡ በኋላ በይሖዋ ቤት አደባባይ የማምለክ መብት ያገኛሉ፤ እንዲሁም የእስራኤል ጉባኤ አባላት ተደርገው ይቆጠራሉ። (ዘሌዋውያን 17:10-14፤ 20:2፤ 24:22) ይሁንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎችም እንኳ ይሖዋ ከእስራኤል ጋር የገባው ቃል ኪዳን ሙሉ ተካፋዮች አይሆኑም። በተስፋይቱ ምድርም የራሳቸው የሆነ ርስት አያገኙም። ሌሎች መጻተኞች ወደ ቤተ መቅደሱ መጥተው መጸለይ ይችሉ የነበረ ሲሆን በካህናቱ አማካኝነት የሕጉን መስፈርት ያሟላ መሥዋዕት ማቅረብ ይችሉ እንደነበረም ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (ዘሌዋውያን 22:25፤ 1 ነገሥት 8:41-43) ያም ሆኖ እስራኤላውያን ከእነዚህ ሰዎች ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት አይችሉም።
ጃንደረቦች የዘላለም ስም ይሰጣቸዋል
8. (ሀ) ጃንደረባ የሆኑ ሰዎችን በተመለከተ ሕጉ ምን ይላል? (ለ) አረማውያን ብሔራት ጃንደረቦችን ለምን ዓላማ ይጠቀሙባቸው ነበር? “ጃንደረባ” የሚለው ቃል አንዳንድ ጊዜ ምን ሊያመለክት ይችላል?
8 ጃንደረቦች ከአይሁዳውያን ወላጆች የተወለዱ ቢሆኑም እንኳ በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሙሉ የአባልነት መብት አያገኙም።a (ዘዳግም 23:1) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንዳንድ አረማውያን ሕዝቦች ጃንደረቦችን ልዩ ቦታ ይሰጧቸው የነበረ ሲሆን በጦርነት ወቅት ከሚማርኳቸው ልጆች መካከል አንዳንዶቹን የመስለብ ልማድ ነበራቸው። ጃንደረቦች በቤተ መንግሥት ውስጥ ባለ ሥልጣናት ሆነው ይሾሙ ነበር። አንድ ጃንደረባ ‘ሴቶችን የሚጠብቅ፣’ ‘ቁባቶችን የሚጠብቅ’ ወይም የንግሥቲቱ አገልጋይ ሊሆን ይችላል። (አስቴር 2:3, 12-15፤ 4:4-6, 9) እስራኤላውያን እንዲህ ዓይነት ልማድ እንደነበራቸው የሚጠቁም ወይም ጃንደረባ የሆኑ ሰዎች እየተመረጡ እስራኤላውያን ነገሥታትን እንዲያገለግሉ ይደረግ እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።b
9. ይሖዋ ቃል በቃል ጃንደረባ ለሆኑ ሰዎች ምን የማጽናኛ ቃል ተናግሯል?
9 በእስራኤል ምድር ቃል በቃል የተሰለቡ ሰዎች የሌላውን ሰው ያህል በእውነተኛው አምልኮ ሙሉ በሙሉ የመካፈል መብት የሌላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ የቤተሰባቸውን ስም ሊያስጠሩ የሚችሉ ልጆች መውለድ የማይችሉ መሆናቸው ትልቅ ኃፍረት ያስከትልባቸዋል። ከዚህ አንጻር ሲታይ በትንቢቱ ላይ ቀጥሎ የሰፈሩት ቃላት ምንኛ የሚያጽናኑ ናቸው! ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና:- በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።”—ኢሳይያስ 56:4, 5
-
-
መጻተኞች ወደ አምላክ የጸሎት ቤት ተሰበሰቡየኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2
-
-
a “ጃንደረባ” የሚለው ቃል ያልተሰለበ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣንን ለማመልከትም ተሠርቶበታል። ፊልጶስ ያጠመቀው ኢትዮጵያዊ ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ሰው የተጠመቀው ምሥራቹ አይሁዳውያን ላልሆኑ ያልተገረዙ ሰዎች መነገር ከመጀመሩ በፊት ስለሆነ ጃንደረባ የተባለው የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን መሆኑን ለማመልከት ነው።—ሥራ 8:27-39
b ኤርምያስን የረዳውና ከንጉሥ ሴዴቅያስ ጋር በቀጥታ የመነጋገር መብት የነበረው አቤሜሌክ ጃንደረባ ተብሏል። ጃንደረባ ተብሎ የተጠራው የተሰለበ ሰው ነው ለማለት ሳይሆን የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን መሆኑን ለማመልከት እንደሆነ መገመት ይቻላል።—ኤርምያስ 38:7-13
-