የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 8/1 ገጽ 7-12
  • ይሖዋ—የእውነተኛ ፍትሕና ጽድቅ ምንጭ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ—የእውነተኛ ፍትሕና ጽድቅ ምንጭ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የይሖዋ ፍትሕ እጅግ የሚያስደስት ነው
  • ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ማድረግ
  • መለኮታዊ ፍትሕና የተዛባ ፍትሕ
  • ጽድቅ ለሁሉም ነው
  • ፍትሕንና ጽድቅን በማሳየት ይሖዋን ምሰሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ይሖዋ ጽድቅንና ፍትሕን ይወድዳል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸው”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • ኢየሱስ ‘ፍትሕን በምድር ላይ ያሰፍናል’
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 8/1 ገጽ 7-12

ይሖዋ​—⁠የእውነተኛ ፍትሕና ጽድቅ ምንጭ

“እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራው ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና [“ፍትሐዊ፣” NW] ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት [“ፍትሕ የማያጓድል፣” NW] . . . ነው።”​—⁠ዘዳግም 32:​4

1. ለፍትሕ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ያለን ለምንድን ነው?

ማንኛውም ሰው ተፈጥሯዊ የሆነ የመወደድ ፍላጎት እንዳለው ሁሉ ሁላችንም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንድንያዝ እንፈልጋለን። አሜሪካዊው የመንግሥት ባለ ሥልጣን ቶማስ ጄፈርሰን “[ፍትሕ] የተፈጥሯችን ክፍል እንደሆኑት እንደ መዳሰስ፣ ማየት ወይም መስማት . . . ተፈጥሯዊና አብሮን የሚወለድ ነገር ነው” በማለት ጽፈዋል። ይሖዋ በአምሳሉ ስለ ፈጠረን ይህ የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። (ዘፍጥረት 1:​26) የራሱን ማንነት የሚያንጸባርቁ ባሕርያቱን አላብሶናል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ፍትሕ ነው። ለፍትሕ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ሊኖረን የቻለውና እውነተኛ ፍትሕና ጽድቅ በሰፈነበት ዓለም ውስጥ ለመኖር የምንናፍቀው ለዚህ ነው።

2. ይሖዋ ፍትሕን ምን ያህል ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል? የመለኮታዊውን ፍትሕ ትርጉም ማወቅ ያለብንስ ለምንድን ነው?

2 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን በተመለከተ “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሐዊ ናቸው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ዘዳግም 32:​4 NW) ይሁን እንጂ በፍትሕ መጓደል በተበከለ ዓለም ውስጥ የመለኮታዊ ፍትሕን ትርጉም ማወቅ ቀላል አይደለም። ሆኖም በአምላክ ቃል አማካኝነት አምላክ ፍትሕን የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ ልናስተውልና አስደናቂ መንገዶቹን ይበልጥ ልናደንቅ እንችላለን። (ሮሜ 11:​33) ሰብዓዊ አስተሳሰቦች ስለ ፍትሕ ያለንን አመለካከት ሊያዛቡት ስለሚችሉ ቅዱስ ጽሑፋዊውን የፍትሕ ትርጉም መገንዘባችን አስፈላጊ ነው። ከሰብዓዊ አመለካከት አንፃር ሲታይ ፍትሕ የሕግን ደንብ በተገቢው መንገድ ከማስፈጸም ውጪ ሌላ ትርጉም አይሰጠውም። ወይም ደግሞ ፈላስፋው ፍራንሲስ ቤከን እንደጻፉት “ፍትሕ ለእያንዳንዱ ሰው የሚገባውን መስጠት ማለት ነው።” የይሖዋ ፍትሕ ግን ከዚህ የበለጠ ነገርን ይጨምራል።

የይሖዋ ፍትሕ እጅግ የሚያስደስት ነው

3. መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ፍትሕንና ጽድቅን ለማመልከት የተሠራባቸውን ቃላት በመመርመር ምን መገንዘብ እንችላለን?

3 መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ የተጠቀሱት ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት እንደተሠራባቸው መመልከታችን የአምላክ ፍትሕ ያለውን ስፋት በተሻለ መንገድ ለመረዳት ያስችለናል።a በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በፍትሕና በጽድቅ መካከል ይህ ነው የሚባል የጎላ ልዩነት አለመኖሩ ትኩረት የሚስብ ነው። እንዲያውም በአሞጽ 5:​24 ላይ ይሖዋ ለሕዝቡ የሰጠው የሚከተለው ማሳሰቢያ እንደሚያሳየው አንዳንድ ጊዜ የዕብራይስጡ ቃላት ጎን ለጎን ይሠራባቸዋል:- “ነገር ግን ፍርድ [“ፍትሕ፣” NW] እንደ ውኃ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍሰስ።” ከዚህም በላይ ለማጉላት ሲባል “ፍትሕና ጽድቅ [NW]” የሚሉት ቃላት በበርካታ ቦታዎች አንድ ላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ።​—⁠መዝሙር 33:​5፤ ኢሳይያስ 33:​5፤ ኤርምያስ 33:​15፤ ሕዝቅኤል 18:​21፤ 45:​9

4. ፍትሕ ማሳየት ማለት ምን ማለት ነው? ከፍተኛው የፍትሕ መስፈርትስ ምንድን ነው?

4 በእነዚህ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት የተላለፈው ሐሳብ ምንድን ነው? በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ፍትሕ ማሳየት ማለት ትክክልና አድሎ የሌለበት ነገር ማድረግ ማለት ነው። የሥነ ምግባር ሕጎችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያወጣው ወይም ትክክልና ከአድሎ የጠራ ነው የሚያሰኘውን ደንብ የሚደነግገው ይሖዋ በመሆኑ ከፍተኛው የፍትሕ መስፈርት እሱ ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ ነው። ቲኦሎጂካል ወርድቡክ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት ጽድቅ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል (ጼዴቅ) “የግብረ ገብና የሥነ ምግባር መስፈርትን ያመለክታል፤ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ደግሞ ይህ መስፈርት የአምላክ ባሕርይና ፈቃድ ነው” ሲል ይገልጻል። ስለዚህ አምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ተግባራዊ የሚያደርግበት መንገድና በተለይ ደግሞ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ግንኙነት የሚያደርግበት መንገድ የእውነተኛ ፍትሕንና ጽድቅን ገጽታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

5. ከአምላክ ፍትሕ ጋር ጠንካራ ትስስር ያላቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

5 ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ እንደሚያሳዩት አምላካዊ ፍትሕ ደስ የሚያሰኝ እንጂ ጨቋኝና የማያፈናፍን አይደለም። ዳዊት “እግዚአብሔር ፍርድን [“ፍትሕን፣” NW] ይወድዳልና፣ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 37:​28) የአምላክ ፍትሕ ለአገልጋዮቹ ታማኝነትና ርኅራኄ እንዲያሳያቸው ይገፋፋዋል። መለኮታዊ ፍትሕ ለሚያስፈልጉን ነገሮች ንቁ ነው፤ እንዲሁም አለፍጽምናችንን ግምት ውስጥ ያስገባል። (መዝሙር 103:​14) ይህ ማለት ግን አምላክ ክፋትን ችላ ብሎ ያልፋል ማለት አይደለም፤ እንዲህ ማድረግ የፍትሕ መጓደል እንዲስፋፋ በር ይከፍታል። (1 ሳሙኤል 3:​12, 13፤ መክብብ 8:​11) ይሖዋ ለሙሴ “መሐሪ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” መሆኑን ነግሮታል። አምላክ ስህተት በሚሠራበትና ሕግ በሚጣስበት ጊዜ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ቢሆንም ቅጣት የሚገባቸውን ግን ዝም ብሎ አያልፍም።​—⁠ዘጸአት 34:​6, 7

6. ይሖዋ ምድራዊ ልጆቹን የሚይዛቸው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ ፍትሑን ስለሚጠቀምበት መንገድ ስናሰላስል በጥፋተኞች ላይ ፍርድ ከማስተላለፍ ውጪ ምንም ነገር የማያሳስበው ጨካኝ ዳኛ አድርገን ልንመለከተው አይገባም። ከዚህ ይልቅ ልጆቹን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንደሚይዝ አፍቃሪ ነገር ግን ጥብቅ የሆነ አባት አድርገን ልንመለከተው ይገባል። ነቢዩ ኢሳይያስ “አቤቱ [“ይሖዋ፣” NW]፣ አንተ አባታችን ነህ” ብሏል። (ኢሳይያስ 64:​8) ይሖዋ ፍትሐዊና ጻድቅ አባት እንደመሆኑ መጠን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ወይም በሥጋዊ ድካም ምክንያት እርዳታ ወይም ይቅርታ ለሚፈልጉ ምድራዊ ልጆቹ ሲል ትክክል ለሆነ ነገር ያለውን ጥብቅ አቋም ከርህራሄው ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል።​—⁠መዝሙር 103:​6, 10, 13

ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ማድረግ

7. (ሀ) መለኮታዊውን ፍትሕ በተመለከተ ከኢሳይያስ ትንቢት ምን እንማራለን? (ለ) ኢየሱስ አሕዛብን ስለ ፍትሕ በማስተማር ረገድ ምን ሚና ነበረው?

7 የመሲሑ መምጣት የይሖዋ ፍትሕ ርኅራኄ የተላበሰ መሆኑን ጎላ አድርጎ ያሳያል። አስቀድሞ በነቢዩ ኢሳይያስ በተነገረው መሠረት ኢየሱስ ስለ መለኮታዊ ፍትሕ ከማስተማሩም በላይ አኗኗሩ ከዚህ ፍትሕ ጋር የሚስማማ ነበር። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የአምላክ ፍትሕ በግፍ የተደቆሱ ሰዎችን በርህራሄ መያዝን ያካትታል። ስለዚህ ሊያገግሙ እንደማይችሉ ሆነው አይጎዱም። የይሖዋ ‘አገልጋይ’ የሆነው ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ይህን የአምላክ ፍትሕ ዘርፍ ‘ለአሕዛብ ለማውራት’ ነበር። በተለይ ደግሞ ይህን ያደረገው መለኮታዊ ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ የሚያሳይ ሕያው ምሳሌ በመተው ነበር። ኢየሱስ የንጉሥ ዳዊት ‘የጽድቅ ቁጥቋጥ’ እንደመሆኑ መጠን ‘ፍትሕን የመሻትና ጽድቅን የማፍጠን’ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው።​—⁠ኢሳይያስ 16:​5፤ 42:​1-4፤ ማቴዎስ 12:​18-21፤ ኤርምያስ 33:​14, 15

8. በመጀመሪያው መቶ ዘመን እውነተኛ ፍትሕና ጽድቅ ግልጽ ያልነበሩት ለምንድን ነበር?

8 ይሖዋ ስላለው የፍትሕ ባሕርይ የተሰጠው ይህን መሳዩ ማብራሪያ በተለይ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ አስፈላጊ ነበር። አይሁዳውያን ሽማግሌዎችና ሃይማኖታዊ መሪዎች የሆኑት ጻፎች፣ ፈሪሳውያንና ሌሎችም የሚናገሩትና የሚያደርጉት ነገር ፍትሕንና ጽድቅን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት እንደነበራቸው የሚያሳይ ነው። በዚህ ምክንያት ጻፎችና ፈሪሳውያን ያወጡትን የአቋም መስፈርት ማሟላት ያቃተው ተራው ሕዝብ የአምላክ ጽድቅ ሊደረስበት የማይቻል ነገር እንደሆነ አድርጎ ሳይመለከተው አልቀረም። (ማቴዎስ 23:​4፤ ሉቃስ 11:​46) ኢየሱስ ሁኔታው እንዲህ እንዳልሆነ አሳይቷል። ደቀ መዛሙርቱን የመረጠው ከእነዚህ ተራ ሰዎች መካከል ሲሆን የአምላክን የጽድቅ አቋም ደረጃዎች አስተምሯቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 9:​36፤ 11:​28-30

9, 10. (ሀ) ጻፎችና ፈሪሳውያን ጻድቅነታቸውን ለማሳየት ሲሉ ምን ያደርጉ ነበር? (ለ) ኢየሱስ የጻፎችና የፈሪሳውያን ተግባር ከንቱ መሆኑን ያሳየው እንዴትና ለምን ነበር?

9 በሌላ በኩል ግን ፈሪሳውያን በአደባባይ በመጸለይና መዋጮ በማድረግ ‘ጻድቅ’ መሆናቸውን ለማሳየት አጋጣሚዎችን ይፈልጉ ነበር። (ማቴዎስ 6:​1-6) በተጨማሪም በአብዛኛው ራሳቸው ያወጧቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕጎችና መመሪያዎች አጥብቀው በመከተል ጻድቅነታቸውን ለማሳየት ይሞክሩ ነበር። ይህን የመሰለው ጥረት ‘ፍርድንና [“ፍትሕንና፣” NW] እግዚአብሔርን መውደድ ወደ መተላለፍ’ መርቷቸዋል። (ሉቃስ 11:​42) ከውጪ ሲታዩ ጻድቅ ቢመስሉም ውስጣቸው ግን ‘በዓመፅ’ ወይም በኃጢአት የተሞላ ነበር። (ማቴዎስ 23:​28) ስለ አምላክ ጽድቅ የሚያውቁት ነገር አልነበረም ቢባል ይቀላል።

10 በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ተከታዮቹን “ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፣ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም” ሲል አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴዎስ 5:​20) በኢየሱስ ሕይወት በተግባር በታየው መለኮታዊ ፍትሕና ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው በሚቆጥሩት ጠባብ አስተሳሰብ ባላቸው ጻፎችና ፈሪሳውያን መካከል ከፍተኛ ልዩነት የነበረ በመሆኑ በየጊዜው በመካከላቸው ግጭት ይፈጠር ነበር።

መለኮታዊ ፍትሕና የተዛባ ፍትሕ

11. (ሀ) ፈሪሳውያን ኢየሱስን በሰንበት ቀን ስለ መፈወስ የጠየቁት ለምን ነበር? (ለ) የኢየሱስ መልስ ምን የሚያሳይ ነበር?

11 ኢየሱስ በ31 እዘአ የፀደይ ወራት በገሊላ በማገልገል ላይ እንዳለ በአንድ ምኩራብ ውስጥ እጁ የሰለለች ሰው ይመለከታል። ቀኑ ሰንበት ስለነበረ ፈሪሳውያን ኢየሱስን “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት። ለዚህ ምስኪን ሰው ስቃይ እውነተኛ አሳቢነት ከማሳየት ይልቅ ኢየሱስን የሚወነጅሉበት ነገር ለማግኘት ይፈልጉ እንደነበር ከጥያቄያቸው መገንዘብ ይቻላል። ኢየሱስ ጨካኝ በሆነው ልባቸው ማዘኑ ምንም አያስገርምም! ከዚያም ኢየሱስ “በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን?” በማለት ጥያቄያቸውን በጥያቄ መለሰላቸው። ዝም ባሉት ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ ጉድጓድ የገባን በግ ያወጡ ወይም አያወጡ እንደሆነ በመጠየቅ የራሱን ጥያቄ መለሰ።b ኢየሱስ “እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም!” በማለት ማንም ሊክደው የማይችል ሐቅ ተናገረ። “ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል [ወይም፣ ትክክል ነው]” በማለት ደመደመ። የአምላክ ፍትሕ በሰብዓዊ ወጎች ማነቆ ውስጥ መግባት የለበትም። ኢየሱስ ይህን ነጥብ ግልጽ ካደረገ በኋላ የሰውየውን እጅ ፈወሰለት።​—⁠ማቴዎስ 12:​9-13፤ ማርቆስ 3:​1-5

12, 13. (ሀ) ከጻፎችና ከፈሪሳውያን በተቃራኒ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለመርዳት ፍላጎት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነበር? (ለ) በመለኮታዊ ፍትሕና ራስን በማመጻደቅ ባሕርይ መካከል ምን ልዩነት አለ?

12 ፈሪሳውያን አካላዊ እክል ላለባቸው ሰዎች እምብዛም የማያስቡ ከሆነ በመንፈሳዊ ድሆች ለሆኑትማ ምንም አያስቡላቸውም ለማለት ይቻላል። ስለ ጽድቅ ያላቸው የተዛባ አመለካከት ቀረጥ ሰብሳቢዎችንና ኃጢአተኞችን እንዲያገሏቸውና እንዲንቋቸው አድርጓቸዋል። (ዮሐንስ 7:​49) ሆኖም እንዲህ ያሉ ብዙ ሰዎች ለኢየሱስ ትምህርት ምላሽ የሰጡ ሲሆን ይህ ደግሞ ሊፈርድባቸው ሳይሆን ሊረዳቸው እንደሚፈልግ መገንዘባቸውን ያሳያል። (ማቴዎስ 21:​31፤ ሉቃስ 15:​1) ይሁን እንጂ ፈሪሳውያን ኢየሱስ በመንፈሳዊ የታመሙትን ለመፈወስ የሚያደርገውን ጥረት አንቋሸዋል። “ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል” የሚል ወቀሳ ሰነዘሩ። (ሉቃስ 15:​2) ኢየሱስ ለክሳቸው ምላሽ ለመስጠት ከእረኝነት ሕይወት ጋር የተያያዘ አንድ ሌላ ምሳሌ ተጠቀመ። አንድ እረኛ የጠፋበትን በግ በማግኘቱ እንደሚደሰት ሁሉ በሰማይ የሚገኙት መላእክትም አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ ሲገባ ይደሰታሉ። (ሉቃስ 15:​3-7) ኢየሱስ ራሱ ዘኬዎስ ቀደም ሲል ከነበረበት የኃጢአት መንገድ ንስሐ እንዲገባ ሊረዳው በመቻሉ ተደስቶ ነበር። “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና” ብሏል።​—⁠ሉቃስ 19:​8-10

13 እነዚህ እሰጥ አገባዎች ሰዎችን ለመፈወስና ለማዳን በቆመው መለኮታዊ ፍትሕና ጥቂቶችን ከፍ ከፍ አድርጎ ብዙዎችን በሚኮንነው ራስን የማመጻደቅ ባሕርይ መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ያሳያሉ። ትርጉም የለሽ የሆኑ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችና ሰው ሠራሽ ወጎች ጻፎችንና ፈሪሳውያንን እብሪተኞች ያደረጓቸው ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ አድርገዋቸዋል። ኢየሱስ ግን ‘በሕግ ያለውን ዋና ነገር ማለትም ፍርድን [“ፍትሕን፣” NW]፣ ምሕረትንና ታማኝነትን መተዋቸውን’ አመልክቷል። (ማቴዎስ 23:​23) እኛም በሥራችን ሁሉ ትክክለኛ ፍትሕን በማሳየትና ራስን በማመጻደቅ ወጥመድ እንዳንያዝ በመጠንቀቅ ኢየሱስን እንምሰለው።

14. ኢየሱስ የፈጸመው አንድ ተአምር መለኮታዊ ፍትሕ የሰዎችን ሁኔታ ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ የሚያሳየው እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ ፈሪሳውያን በአምባገነናዊነት ያወጧቸውን ወጎች ወደ ጎን ገሸሽ ቢያደርግም የሙሴን ሕግ ጠብቋል። (ማቴዎስ 5:​17, 18) ይህን በሚያደርግበት ጊዜ ግን የዚያ ጻድቅ ሕግ ፊደላት ከሕጉ በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት እንዲሸፍኑበት አልፈቀደም። ለአሥራ ሁለት ዓመታት ደም ይፈሳት የነበረች አንዲት ሴት መጎናጸፊያውን በመንካት በተፈወሰች ጊዜ ኢየሱስ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” ብሏታል። (ሉቃስ 8:​43-48) በአዘኔታ የተሞሉት እነዚህ የኢየሱስ ቃላት እንደሚያረጋግጡት የአምላክ ፍትሕ ያለችበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ነበር። ተገቢውን የመንጻት ሥርዓት ሳታከናውን ከሕዝብ ጋር በመቀላቀሏ የሙሴን ሕግ ብትጥስም ያሳየችው እምነት ግን ሊካስ የሚገባው ነበር።​—⁠ዘሌዋውያን 15:​25-27፤ ከሮሜ 9:​30-33 ጋር አወዳድር።

ጽድቅ ለሁሉም ነው

15, 16. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረው ምሳሌ ስለ ፍትሕ ምን ያስተምረናል? (ለ) “እጅግ ጻድቅ” እንዳንሆን መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?

15 ኢየሱስ መለኮታዊ ፍትሕ ያለውን የርህራሄ ባሕርይ ከማጉላቱም በላይ ሰዎችን ሁሉ ማቀፍ እንዳለበት ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል። የይሖዋ ፈቃድ ‘ለሕዝቦች ሁሉ ፍትሕን እንዲያስገኝ’ ነው። (ኢሳይያስ 42:​1 የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ታዋቂ ምሳሌው ላይ የጎላው ነጥብ ይህ ነበር። ምሳሌው ‘ጻድቅ መሆኑን ለማሳየት’ የፈለገ አንድ ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ላነሳው ጥያቄ የተሰጠ መልስ ነበር። ሰውየው “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። ሰውየው የባልንጀርነት ኃላፊነቱ በአይሁድ ሕዝብ ላይ ብቻ የተወሰነ እንዲሆን ፈልጎ እንደነበረ አያጠራጥርም። በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ሳምራዊ የሌላ ብሔር አባል የሆነን እንግዳ ሰው ለመርዳት ጊዜውንና ገንዘቡን ለመሠዋት ፈቃደኛ ስለነበር አምላካዊውን ጽድቅ አሳይቷል። ኢየሱስ ጠያቂውን “አንተም እንዲሁ አድርግ” ብሎ በመምከር ምሳሌውን አጠቃሏል። (ሉቃስ 10:​25-37) በተመሳሳይ እኛም ሰዎችን በዘራቸው ወይም በጎሣቸው ሳንለይ ለሁሉም ጥሩ የምናደርግ ከሆነ የአምላክን ፍትሕ እየኮረጅን ነው ማለት ነው።​—⁠ሥራ 10:​34, 35

16 በሌላ በኩል ግን መለኮታዊውን ፍትሕ የምናሳየው “እጅግ ጻድቅ” በመሆን እንዳልሆነ የጻፎችና የፈሪሳውያን ምሳሌ ያሳስበናል። (መክብብ 7:​16) ለታይታ የሚደረጉ የጽድቅ ሥራዎችን በመሥራት የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ መሞከር ወይም ለሰው ሠራሽ ደንቦች ከሚገባው በላይ ከፍ ያለ ግምት መስጠት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አያስገኝልንም።​—⁠ማቴዎስ 6:​1

17. አምላካዊ ፍትሕ ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

17 ኢየሱስ ለአሕዛብ የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ ግልጽ ያደረገበት አንዱ ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ ይህን ባሕርይ ማሳየትን እንዲማሩ ሲል ነው። ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ቅዱሳን ጽሑፎች ‘አምላክን እንድንመስል’ ያሳስቡናል። ሁሉም የአምላክ መንገዶች ደግሞ ፍትሕ ናቸው። (ኤፌሶን 5:​1) በመሆኑም ይሖዋ ከእሱ ጋር በምንመላለስበት ጊዜ ‘ፍትሕን እንድናሳይ’ የሚፈልግብን መሆኑን ሚክያስ 6:​8 (NW) ይገልጻል። ከዚህም በላይ በይሖዋ የቁጣ ቀን ለመሰወር የምንፈልግ ከሆነ ቀኑ ከመድረሱ በፊት ‘ጽድቅን መፈለግ’ እንዳለብን ሶፎንያስ 2:​2, 3 ያሳስበናል።

18. በሚቀጥለው ርዕስ የትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ያገኛሉ?

18 ስለዚህ እነዚህ የመጨረሻ ቀናት ፍትሕን ለማሳየት ‘ይበልጥ ተስማሚ የሆኑ ጊዜያት’ ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 6:​2) እንደ ኢዮብ ‘ጽድቅን ልብሳችን’ እንዲሁም ‘ፍትሕን መጎናጸፊያችን’ ካደረግን ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (ኢዮብ 29:​14) በይሖዋ ፍትሕ ላይ እምነት ማሳደራችን የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድንጠባበቅ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? ከዚህም በላይ ጽድቅ የሚሰፍንባትን “አዲስ ምድር” ስንጠባበቅ አምላካዊ ፍትሕ በመንፈሳዊ ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው? (2 ጴጥሮስ 3:​13) የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ቃላት ተሠርቶባቸዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ (ሚሽፓት) አብዛኛውን ጊዜ “ፍትሕ” ተብሎ ተተርጉሟል። የቀሩት ሁለቱ ቃላት (ጼዴቅ እና ተዛማጅ ቃል የሆነው ጼዳቃህ) በብዙ ቦታዎች ላይ “ጽድቅ” ተብለው ተተርጉመዋል። “ጽድቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛው ቃል (ዲካይኦሲን) “ትክክል ወይም ፍትሐዊ የመሆን ባሕርይ” የሚል ትርጉም አለው።

b የኢየሱስ ምሳሌ በጣም ተስማሚ ነበር፤ ምክንያቱም የአይሁዳውያኑ የቃል ሕግ በሰንበት ቀን ችግር ለገጠመው እንስሳ እርዳታ ማድረግን ይፈቅድ ነበር። በሌሎች ጊዜያትም በዚሁ ጉዳይ ላይ ማለትም በሰንበት ቀን መፈወስ ሕጋዊ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ጉዳይ ላይ አለመግባባቶች ተከስተው ነበር።​—⁠ሉቃስ 13:​10-17፤ 14:​1-6፤ ዮሐንስ 9:​13-16

[ልታብራራ ትችላለህ?]

◻ የመለኮታዊ ፍትሕ ትርጉም ምንድን ነው?

◻ ኢየሱስ ለአሕዛብ ፍትሕን ያስተማረው እንዴት ነበር?

◻ የፈሪሳውያን ጽድቅ የተዛባ የነበረው ለምንድን ነው?

◻ ፍትሕ ማሳየት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ መለኮታዊው ፍትሕ ምን ያህል ስፋት እንዳለው ገልጿል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ