የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 1/15 ገጽ 8-13
  • ብርሃን አብሪዎች የሆንነው ለምን ዓላማ ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ብርሃን አብሪዎች የሆንነው ለምን ዓላማ ነው?
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሰው ልጆች ‘መብራት ሲጠፋ’
  • “ለአሕዛብ ብርሃን” እንዲሆን የተሰጠ
  • “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ”
  • እኛን ለመምራት ከአምላክ የመጣ ብርሃንና እውነት
  • የይሖዋ ክብር አብርቷል
  • የዓለምን ብርሃን ተከተሉ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • “ብርሃንም ወደ ዓለም መጣ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • መለኮታዊ ብርሃን ጨለማን ገፍፎ ይጥላል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • የዓለምን ብርሃን እየተከተሉ ያሉት እነማን ናቸው?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 1/15 ገጽ 8-13

ብርሃን አብሪዎች የሆንነው ለምን ዓላማ ነው?

“ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ።” — ሥራ 13:​47

1. ሐዋርያው ጳውሎስ በሥራ 13:⁠47 ላይ በተጠቀሰው ትዕዛዝ ስሜቱ የተነካው እንዴት ነበር?

“ጌታ [ይሖዋ አዓት] እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና” ሲል ሐዋርያው ጳውሎስ ተናገረ። (ሥራ 13:⁠47) ጳውሎስ ይህንን መናገር ብቻ ሳይሆን የነገሩንም ክብደት ተገንዝቦታል። ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ሕይወቱን ይህንን ትእዛዝ ለመፈጸም ተጠቅሞበታል። (ሥራ 26:​14–20) እኛስ ይህንን ትእዛዝ እንድንፈጽም ኃላፊነት ተጥሎብናልን? የተጣለብን ከሆነስ በዘመናችን ይህ ትእዛዝ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው?

የሰው ልጆች ‘መብራት ሲጠፋ’

2. (ሀ) ዓለም ወደ ፍጻሜው ዘመን ሲገባ መንፈሳዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ሁኔታውን በጥልቅ የሚነካ ምን ነገር ተከሰተ? (ለ) አንድ የብሪታንያ የፖለቲካ ሰው በነሐሴ 1914 ላይ ሲፈጸም ስለተመለከቱት ነገር ምን አሉ?

2 ዛሬ በሕይወት ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች ከመወለዳቸው በፊት ይህ ዓለም ወደ ፍጻሜው ዘመን ገባ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ብዙ ታላላቅ ክንውኖች በተፋጠነ ሁኔታ ተፈራርቀዋል። የመንፈሳዊና የሥነ ምግባር ጨለማ ዋነኛ አስፋፊ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ከሰማይ ወደ ምድር ተጣለ። (ኤፌሶን 6:⁠12፤ ራእይ 12:​7–12) የሰው ዘር በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ውስጥ ተዘፈቀ። ጦርነቱ የማይቀር በመሰለበት በነሐሴ ወር 1914 መጀመሪያ ላይ የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሰር ኤድዋርድ ግሬይ በለንደን ቢሮአቸው መስኮት ብቅ ብለው እየተመለከቱ “መላው አውሮፓ መብራቱ እየጠፋበት ነው። ዳግመኛ ይህን መብራት በኛ የሕይወት ዘመን ለማየት አንችልም” አሉ።

3. የዓለም መሪዎች በሰው ልጆች የወደፊት ሁኔታ ላይ ብርሃን ለማብራት ያደረጉት ሙከራ ምን ያህል ተሳክቶላቸዋል?

3 ይህ መብራት ዳግመኛ እንዲበራ ለማድረግ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ድርጅት በ1920 ተቋቋመ። ይሁን እንጂ ብርሃኑ ብልጭ እንኳን አላለም። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ የዓለም መሪዎች ድጋሚ ሙከራ በማድረግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን አቋቋሙ። በዚህም ጊዜ ቢሆን ብርሃኑ ቦግ ብሎ ሊበራ አልቻለም። ይሁን እንጂ በቅርቡ በተከናወኑት ሁኔታዎች ምክንያት የዓለም መሪዎች “አዲስ የዓለም ሥርዓት” ስለመምጣቱ መናገር ጀምረዋል። ነገር ግን ይህ የእነርሱ “አዲስ ዓለም” እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት አስገኝቷል ለማለት የሚቻል አይደለም። በተቃራኒው ግን ጦርነት፣ የጎሣ አምባጓሮ፣ ወንጀል፣ ሥራ አጥነት፣ ድህነት፣ የአካባቢ መበከልና በሽታዎች ሰዎች በሕይወታቸው እንዳይደሰቱ እንቅፋቶች ሆነው ቀጥ ለዋል።

4, 5. (ሀ) ሰብዓዊውን ቤተሰብ ጨለማ የሸፈነው መቼና እንዴት ነበር? (ለ) እፎይታ ለማስገኘት የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው?

4 እንደ እውነቱ ከሆነ የሰው ልጅ መብራት የጠፋው የ1914 ዓመት ከመድረሱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነበር። መብራቱ የጠፋው ከ6,000 ዓመታት በፊት በኤደን ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ወላጆቻችን በግልጽ ከተነገራቸው የአምላክ ፈቃድ በመውጣት የራሳቸውን ውሳኔ ለማድረግ በመረጡ ጊዜ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሰው ዘር ላይ የደረሱት አሳዛኝ ሁኔታዎች መጽሐፍ ቅዱስ ‘የጨለማው ሥልጣን’ ብሎ በሚጠራው ባለ ሥልጣን ግዛት ሥር የሰው ልጅ የሚኖረው ኑሮ ገጽታዎች ናቸው። (ቆላስይስ 1:⁠13) የመጀመሪያው ሰው አዳም ዓለምን በሙሉ ወደ ኃጢአት አዘቅት የጣለው እንዲሁም በአዳም ምክንያት ኃጢአትና ሞት ለሰው ልጆች ሁሉ ሊሰራጭ የቻለው በሰይጣን ዲያብሎስ ግፊት ነበር። (ዘፍጥረት 3:​1–6፤ ሮሜ 5:⁠12) በዚህ መንገድ የሰው ልጅ የብርሃንና የሕይወት ምንጭ የሆነውን የይሖዋን ሞገስ አጣ። — መዝሙር 36:⁠9

5 ብርሃኑ ለሰው ልጆች እንደገና ሊበራላቸው የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ሰዎች የሰው ዘሮች ፈጣሪ የሆነውን የይሖዋ አምላክን ሞገስ ካገኙ ነው። ይህ ከሆነ “በአሕዛብ ሁሉ ላይ የተዘረጋው መሸፈኛ” ማለትም በኃጢአት ምክንያት የመጣው ኩነኔ ሊነሳ ይችላል። ታዲያ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? — ኢሳይያስ 25:7

“ለአሕዛብ ብርሃን” እንዲሆን የተሰጠ

6. ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንድናገኘው ያስቻለን ምን አስደናቂ ተስፋ ነው?

6 ገና አዳምና ሔዋን ከገነት ከመባረራቸው በፊት ይሖዋ ጽድቅ ወዳዶችን ነጻ የሚያወጣ “ዘር” እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናገረ። (ዘፍጥረት 3:⁠15) ይህ ተስፋ የተደረገው ዘር ሰው ሆኖ እንደ ተወለደ ይሖዋ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረው ስምዖን የተባለ አረጋዊ ሕፃኑ “ለአሕዛብ ሁሉ [መሸፈኛውን አዓት] የሚገልጥ ብርሃን” ይሆናል ብሎ በመናገር ማንቱን እንዲያሳውቅ አድርጓል። (ሉቃስ 2:​29–32) የሰው ልጆች ፍጹሙ የኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወት መሥዋዕት መሆኑን በማመን በወረሱት ኃጢአት ምክንያት ከመጣባቸው ኩነኔ ነፃ ሊወጡ ይችላሉ። (ዮሐንስ 3:⁠36) ከዚህ በኋላ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ የሰማያዊ መንግሥት ክፍል ሆነው ወይም በገነቲቱ ምድር የሚኖሩ የመንግሥቲቱ ተገዢዎች በመሆን ፍጹም የሆነ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ። ምንኛ አስደናቂ ዝግጅት ነው!

7. በኢሳይያስ 42:​1–4 ላይ ያለው ተስፋም ሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ትንቢቱ ያገኘው ፍጻሜ በተስፋ እንድንሞላ የሚያደርገን ለምንድን ነው?

7 እነዚህ አስደናቂ ተስፋዎች የሚፈጸሙ ለመሆናቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ዋስትና ሆኗል። ሐዋርያው ማቴዎስ ኢየሱስ በሥቃይ ላይ የነበሩትን ሰዎች ከመፈወሱ ጋር በማያያዝ በኢሳይያስ 42:​1–4 ላይ የተጻፈው ትንቢት በእርሱ ላይ እንደሚሠራ ገልጿል። ጥቅሱ በከፊል እንዲህ ይላል:- “እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፣ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል።” ታዲያ ለምድር ወገኖች የሚያስፈልገው ነገር ይህ አይደለምን? ትንቢቱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፣ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። የተቀጠቀጠን ሸንበቆ አይሰብርም፣ የሚጤስንም ክር አያጠፋም።” ኢየሱስ ከዚህ ትንቢት ጋር የሚስማማ ነገር አድርጓል፤ በሥቃይ የሚገኙትን ሰዎች አላስጨነቀም። አዘነላቸው፣ ስለ ይሖዋ ዓላማዎች አስተማራቸው፣ ከሕመማቸውም ፈወሳቸው። — ማቴዎስ 12:​15–21

8. ይሖዋ ኢየሱስን “ለሕዝብ ቃል ኪዳን” እንዲሁም “ለአሕዛብ ብርሃን” አድርጎ የሰጠው በምን መንገድ ነው?

8 የዚህ ትንቢት ሰጭ ለአገልጋዩ ለኢየሱስ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፣ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅህማለሁ፣ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ።” (ኢሳይያስ 42:​6, 7) አዎን፣ ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን “ቃል ኪዳን” ወይም የተስፋ ዋስትና አድርጎ ሰጥቷል። ይህ እንዴት የሚያበረታታ ነው! ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የሰው ልጆች ሁኔታ ከልብ እንደሚያሳስበው አሳይቷል። እንዲያውም ሕይወቱን ለሰው ልጆች ሲል አሳልፎ ሰጥቷል። ይሖዋ አሕዛብን በሙሉ የመግዛት ሥልጣን የሰጠው ለእርሱ ነው። ይሖዋ እርሱን “የአሕዛብ ብርሃን” ብሎ መጥራቱ አያስደንቅም። ኢየሱስ ራሱም በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሏል። — ዮሐንስ 8:12

9. ኢየሱስ በዚያን ጊዜ የነበረውን የነገሮች ሥርዓት ለማሻሻል በመድከም ጊዜውን ያላጠፋው ለምን ነበር?

9 ኢየሱስ “የዓለም ብርሃን” ሆኖ ያገለገለው ለምን ዓላማ ነበር? ሥጋዊ ወይም ቁሳዊ የሆነ ዓላማ ለማሳካት እንዳልነበረ የተረጋገጠ ነው። የዚህ ዓለም ገዢ ከሆነው ከሰይጣንም ሆነ ከሕዝቦቹ የቀረበለትን የንግሥና ሥልጣንም ሆነ በጊዜው የነበረውን የፖለቲካ ሥርዓት ለማቃናት የቀረበለትን ግብዣ አልተቀበለም። (ሉቃስ 4:​5–8፤ ዮሐንስ 6:⁠15፤ 14:⁠30) ኢየሱስ በሥቃይና በመከራ ላይ ለነበሩ ሰዎች ታላቅ ርኅራኄ አሳይቷል። እንዲሁም ሌሎች ሊያደርጉት ባልቻሉት መንገድ ከሥቃይ እንዲገላገሉ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ በውርሻ በመጣ ኃጢአት ምክንያት በመለኮታዊ ኩነኔ ውስጥ በሚገኝና በማይታዩት የክፋት መናፍስታዊ ኃይላት ቁጥጥር ሥር በሚገኝ ማኅበረሰብ ውስጥ ዘላቂ የሆነ እፎይታና ፈውስ ሊገኝ እንደማይችል ያውቅ ነበር። አምላካዊ ማስተዋል ስለነበረው መላ ሕይወቱን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ተጠቅሞበታል። — ዕብራውያን 10:7

10. ኢየሱስ የዓለም ብርሃን ሆኖ ያገለገለው በምን መንገዶችና ለምን ዓላማ ነበር?

10 ታዲያ ኢየሱስ “የዓለም ብርሃን” ሆኖ ያገለገለው በምን መንገዶችና ለምን ዓላማ ነበር? ጊዜውን የአምላክን መንግሥት የምሥራች በመስበኩ ሥራ ላይ አውሏል። (ሉቃስ 4:⁠43፤ ዮሐንስ 18:⁠37) በተጨማሪም ኢየሱስ የይሖዋን ዓላማ በተመለከተ ስለ እውነት በመመስከሩ የሰማዩ አባቱን ስም ክብር አጎናጽፎታል። (ዮሐንስ 17:​4, 6) ከዚህ በተጨማሪም የዓለም ብርሃን እንደመሆኑ መጠን ሃይማኖታዊ ውሸቶችን አጋልጧል። ይህንን በማድረጉም በሃይማኖታዊ እስራት ውስጥ ለነበሩት ሰዎች መንፈሳዊ ነፃነት አስገኝቶላቸዋል። ሰይጣን እርሱ እንዲጠቀምባቸው ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች በማይታይ ሁኔታ እየተቆጣጠረ እንዳለ ኢየሱስ አጋልጧል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ የጨለማ ሥራዎችን በግልጽ ለይቶ አመልክቷል። (ማቴዎስ 15:​3–9፤ ዮሐንስ 3:​19–21፤ 8:⁠44) ከሁሉ በላይ ደግሞ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት የዓለም ብርሃን ሆኖ ተገኝቷል። ይህን በማድረጉም በዚህ ዝግጅት ለሚያምኑ ሰዎች ሁሉ የኃጢአት ሥርየት የማግኘት፣ ከአምላክ ጋር ተቀባይነት ያለው ዝምድና የመመሥረትና የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ክፍል ሆኖ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (ማቴዎስ 20:⁠28፤ ዮሐንስ 3:⁠16) በመጨረሻም ኢየሱስ በሕይወቱ በሙሉ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ለአምላክ በማደሩ ለይሖዋ ሉዓላዊነት ደጋፊ ሆኖ ቆሟል፤ ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑንም አረጋግጧል። ይህም ጽድቅ ወዳድ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ የዘላለም ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። ይሁን እንጂ ብርሃን አብሪ የሆነው ኢየሱስ ብቻ ነበርን?

“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ”

11. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ብርሃን አብሪዎች ለመሆን ይችሉ ዘንድ ምን ማድረግ አስፈልጓቸዋል?

11 ኢየሱስ በማቴዎስ 5:⁠14 ላይ ለደቀ መዛሙርቱ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ሲል ነግሯቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ የእርሱን ፈለግ መከተል ነበረባቸው። በአኗኗራቸውና በስብከታቸው ሌሎች ሰዎችን የእውነተኛ ብርሃን ምንጭ ወደሆነው ወደ ይሖዋ እየመሩ ማምጣት ነበረባቸው። የኢየሱስን አርዓያ በመከተል የይሖዋን ስም ማሳወቅና ሉዓላዊነቱን መደገፍ ነበረባቸው። ልክ ኢየሱስ እንዳደረገው የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን ማወጅ ይኖርባቸው ነበር። እንዲሁም ሃይማኖታዊ ውሸቶችን፣ የጨለማ ሥራዎችንና ከነዚህ ነገሮች በስተኋላ ያለውን ክፉውን ማጋለጥ ነበረባቸው። የክርስቶስ ተከታዮች በየትም ቦታ ላሉ ሰዎች ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ስላዘጋጀው ፍቅራዊ የመዳን ዝግጅት መንገር ነበረባቸው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን አካባቢ የነበሩት ክርስቲያኖች ልክ ኢየሱስ እንዳዘዛቸው ከኢየሩሳሌም ጀምረው በይሁዳና በሰማርያ ይህንን ሥራ እንዴት ባለ ቅንዓት ፈጽመዋል! — ሥራ 1:⁠8

12. (ሀ) መንፈሳዊው ብርሃን እስከ ምን ድረስ መብራት ይኖርበታል? (ለ) የይሖዋ መንፈስ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢሳይያስ 42:⁠6 ምን እንዲገነዘብ አስቻለው? ይህ ትንቢት የእኛንስ ሕይወት እንዴት ሊነካው ይገባል?

12 ይሁን እንጂ የምሥራቹ ስብከት በዚህ የምድር ክፍል ብቻ ተወስኖ የሚቀር አልነበረም። ኢየሱስ ተከታዮቹን “አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል አዟል። (ማቴዎስ 28:⁠19) የጠርሴሱ ሳውል (በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለው) ወደ ክርስትና በተለወጠበት ጊዜ ጌታ ለአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ለአሕዛብም እንደሚሰብክ በግልጽ ነግሮታል። (ሥራ 9:⁠15) ጳውሎስም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ይህ ትዕዛዝ ምን ማድረግን እንደሚጠይቅ ተገንዝቧል። በዚህም ምክንያት በኢየሱስ ላይ በቀጥታ የተፈጸመው የኢሳይያስ 42:⁠6 ትንቢት በክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ በተዘዋዋሪ የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን ተገንዝቧል። ስለዚህ በሥራ 13:⁠47 ላይ ከኢሳይያስ ትንቢት ጠቅሶ “ጌታ [ይሖዋ አዓት] እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና” ብሏል። አንተስ? ይህንን ብርሃን አብሪ የመሆን ግዴታ በቁም ነገር አስበህበታልን? እንደ ኢየሱስና እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወትህ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ እንዲያተኩር አድርገሃልን?

እኛን ለመምራት ከአምላክ የመጣ ብርሃንና እውነት

13. ከመዝሙር 43:⁠3 ጋር በሚስማማ ሁኔታ ምን በማለት አጥብቀን እንጸልያለን? ይህስ ከምን ይጠብቀናል?

13 በራሳችን ዕቅድና ዘዴ የሰው ልጅ የተስፋ መብራት ተመልሶ እንዲበራ ለማድረግ ብንሞክር በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክን ቃል ዓላማ በከፍተኛ ሁኔታ እንስታለን። ጠቅላላው ዓለም የፈለገውን ቢያደርግም እውነተኛ ክርስቲያኖች የእውነተኛ ብርሃን ምንጭ አድርገው የሚመለከቱት ይሖዋን ነው። ጸሎታቸው በመዝሙር 43:⁠3 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው “ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፣ ወደ ቅድስና ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ” እንደሚለው ዓይነት ነው።

14, 15. (ሀ) ይሖዋ ብርሃኑንና እውነቱን አሁንም እየላከ ያለው በምን በምን መንገዶች ነው? (ለ) የአምላክ ብርሃንና እውነት በእርግጥ እንደሚመሩን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

14 ይሖዋ ታማኝ ሆነው ከጎኑ የሚቆሙለት አገልጋዮቹ ለሚያቀርቡለት ለዚህ ጸሎት መልስ መስጠቱን ቀጥሏል። ዓላማውን በማሳወቅ፣ አገልጋዮቹ ዓላማውን እንዲረዱ በማድረግና በግልጽ ያሳወቀውንም ዓላማ በመፈጸም ብርሃን እየላከ ነው። ወደ አምላክ የምንጸልየው እንዲሁ ደንቡን ለማድረስ ወይም ቅዱሳን መስለን ለመታየት አይደለም። አጥብቀን የምንፈልገው መዝሙሩ እንደሚለው ከይሖዋ የሚመጣው ብርሃን እንዲመራን ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ አምላክ የሚሰጠውን ብርሃን መቀበል የሚያስከትለውን ኃላፊነት እንቀበላለን። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እኛም የይሖዋን ቃል መፈጸም ቃሉን በሚያምኑ ሁሉ ላይ በተዘዋዋሪ የሚያስከትለው ትዕዛዝ እንደሚኖር እናስተውላለን። አምላክ በአደራ የሰጠንን የምሥራች እስክናካፍላቸው ድረስ ለሰዎች ዕዳ እንዳለብን ሆኖ ይሰማናል። — ሮሜ 1:​14, 15

15 ይሖዋ በዘመናችን የላካቸው ብርሃንና እውነት ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊ ዙፋኑ ላይ ሆኖ በመግዛት ላይ እንዳለ ግልጽ ያደርጉልናል። (መዝሙር 2:​6–8፤ ራእይ 11:⁠15) ኢየሱስ በንጉሣዊ ክብሩ በሚገኝበት ጊዜ ይህ የመንግሥት ምሥራች ምስክር እንዲሆን ሰው በሚኖርባቸው የምድር ክፍሎች በሙሉ እንደሚሰበክ ተንብዮአል። (ማቴዎስ 24:​3, 14) ይህ ሥራ በአሁኑ ጊዜ በመላው ምድር ላይ በተፋፋመ ሁኔታ እየተካሄደ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሰጠነው ለዚህ ሥራ ከሆነ መዝሙራዊው እንደተናገረው የአምላክ ብርሃንና እውነት እየመሩን ነው ማለት ነው።

የይሖዋ ክብር አብርቷል

16, 17. ይሖዋ ሴት መሰል በሆነችው ድርጅቱ ላይ በ1914 ክብሩ እንዲበራ ያደረገው እንዴት ነበር? ምን ትዕዛዝስ ሰጣት?

16 ቅዱሳን ጽሑፎች መለኮታዊው ብርሃን በምድር በሙሉ የሚፈነጥቅበትን ሁኔታ ልብ ቀስቃሽ በሆነ አነጋገር ይገልጻሉ። ኢሳይያስ 60:​1–3 ለይሖዋ “ሴት” ወይም ለታማኝ አገልጋዮቹ ሰማያዊት ድርጅት የተነገረ ነው። እንዲህ ይላል:- “ብርሃንሽ መጥቶአልና፣ የእግዚአብሔርም [የይሖዋም አዓት] ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፣ አብሪ። እነሆ፣ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ይወጣል፤ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።”

17 ሰማያዊቷ ሴት መሰል ድርጅት ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኋላ በ1914 ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ የሆነለትን መሲሐዊ መንግሥት በወለደች ጊዜ የይሖዋ ክብር በላይዋ ላይ አበራ። (ራእይ 12:​1–5) ይህ መንግሥት ለምድር ትክክለኛው መስተዳድር በመሆኑ የይሖዋ ክብራማ ብርሃን በመለኮታዊ ሞገስ ያበራበታል።

18. (ሀ) በኢሳይያስ 60:⁠2 ላይ በቅድሚያ በተነገረው መሠረት ጨለማ ምድርን የሸፈነው ለምንድን ነው? (ለ) ግለሰቦች ከምድር ጨለማ ሊወጡ የሚችሉት እንዴት ነው?

18 በተቃራኒው ግን ምድር በጨለማ አሕዛብም በድቅድቅ ጨለማ ተሸፍነዋል። ለምን? ብሔራት ሰብዓዊ አገዛዝ ይሻለናል ብለው የአምላክን ውድ ልጅ መንግሥት አንቀበልም በማለታቸው ነው። አንድን ዓይነት መስተዳድር አስወግደው በሌላ ዓይነት መስተዳድር በመተካት ችግሮቻቸውን የሚፈቱ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ይህን ማድረጋቸው የሚጓጉለትን እፎይታ አላመጣላቸውም። በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ሆኖ ብሔራትን የሚቆጣጠረው ማን እንደሆነ መገንዘብ ተስኗቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:⁠4) የእውነተኛ ብርሃን ምንጭ የሆነውን አምላክ ባለመቀበላቸው በጨለማ ውስጥ ናቸው። (ኤፌሶን 6:⁠12) ይሁን እንጂ ብሔራት በምንም ዓይነት መንገድ ይመላለሱ፣ ግለሰቦች ከዚህ ጨለማ ወጥተው ሊድኑ ይችላሉ። በምን መንገድ? አምላክ ባቋቋመው መንግሥት ላይ ሙሉ እምነት በመጣልና ለዚህም መንግሥት በመገዛት ነው።

19, 20. (ሀ) የይሖዋ ክብር በኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ላይ የበራው ለምንና እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ቅቡዓኑን ብርሃን አብሪዎች ያደረጋቸው ለምን ዓላማ ነው? (ሐ) አስቀድሞ እንደተነገረው “ነገሥታትና” “አሕዛብ” አምላክ በሰጠን ብርሃን ተስበው የመጡት እንዴት ነው?

19 ሕዝበ ክርስትና በአምላክ መንግሥት ላይ እምነት የላትም፤ ራስዋንም ለመንግሥቱ ፈቃድ አላስገዛችም። በመንፈስ የተቀቡት የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ግን ይህንን አድርገዋል። በዚህም ምክንያት የይሖዋ መለኮታዊ ሞገስ ብርሃን በእነዚህ በሰማያዊቷ ሴት የሚታዩ ወኪሎች ላይ አብርቷል። ክብሩም በእነሱ ላይ በግልጽ ታይቷል። (ኢሳይያስ 60:​19–21) በፖለቲካው ዓለም ወይም በኢኮኖሚው መድረክ የሚደርስ ማንኛውም ዓይነት ለውጥ ሊወስድባቸው የማይችል መንፈሳዊ ብርሃን በማግኘት ተደስተው ይኖራሉ። ይሖዋ ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ አውጥቷቸዋል። (ራእይ 18:⁠4) የይሖዋን ተግሣጽና እርማት ስለ ተቀበሉ እንዲሁም የእርሱን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት በመደገፍ በታማኝነት ከጎኑ ስለቆሙ ይሖዋ በሞገሱ ይመለከታቸዋል። ከፊታቸው ብሩህ ጊዜ ይጠብቃቸዋል፤ እርሱ ባስቀመጠላቸውም ተስፋ ይደሰታሉ።

20 ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህን ሁሉ ያደረገላቸው ለምን ዓላማ ነው? በኢሳይያስ 60:⁠21 ላይ እርሱ ራሱ እንደተናገረው ይሖዋ ‘ይከብር ዘንድ’ ማለትም ስሙ እንዲከበር ሌሎች ሰዎችም እውነተኛ አምላክ እሱ ብቻ መሆኑን አውቀው ወደ እርሱ እንዲመጡና ለራሳቸው ዘላለማዊ ጥቅም እንዲያገኙ አስቦ ነው። በዚህ መሠረት በ1931 እነዚህ የእውነተኛው አምላክ አምላኪዎች የይሖዋ ምስክሮች የሚለውን ስም ተቀበሉ። ይህን በማድረጋቸውስ ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናረው “ነገሥታት” እነርሱ ወዳንጸባረቁት ብርሃን ተስበው መጥተዋልን? አዎን! እነዚህ ነገሥታት ግን የምድር ፖለቲካዊ ገዢዎች ሳይሆኑ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥት ነገሥታት ሆነው የመግዛት ተስፋ ያላቸው ቀሪዎች ናቸው። (ራእይ 1:​5, 6፤ 21:⁠24) “አሕዛብስ” በብርሃኑ ተስበዋልን? በእርግጥ ተስበዋል! በዚህ ብርሃን በጅምላ የተሳበ የፖለቲካ ብሔር የለም። ሆኖም ከእነዚህ የፖለቲካ ብሔራት የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ከአምላክ መንግሥት ጎን ተሰልፈዋል። ከዚህ ዓለም ለመገላገልና ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ለመግባትም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ይህም ዓለም ጽድቅ የሚሰፍንበት እውነተኛ አዲስ ዓለም ይሆናል። — 2 ጴጥሮስ 3:⁠13፤ ራእይ 7:​9, 10

21. ይሖዋ ፈቃዱን እንድንረዳ በማድረግ በኩል ያሳየንን ይገባናል የማንለውን ደግነት ዓላማ እንዳልሳትን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

21 አንተስ የዚህ በቁጥር እየጨመረ የሚሄደው የብርሃን አብሪዎች ሠራዊት ክፍል ነህን? እኛም እንደ ኢየሱስ ብርሃን አብሪዎች እንድንሆን ይሖዋ ፈቃዱን እንድናስተውል አድርጓል። ሁላችንም ይሖዋ በዚህ በዘመናችን ለአገልጋዮቹ በሰጠው ሥራ በቅንዓት በመካፈል ይገባናል የማንለውን ይህን ደግነት ለኛ የዘረጋበትን ዓላማ አለመሳታችንን እናሳይ። (2 ቆሮንቶስ 6:​1, 2) በዘመናችን ከዚህ የሚበልጥ ሌላ ሥራ የለም። ከአምላክ የሚመጣውን ክብራማ ብርሃን ለሌሎች በማብራት ይሖዋን ከማክበር የሚበልጥ መብትም አናገኝም።

እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

◻ በሰው ልጆች ላይ ለመጡት አሳዛኝ ችግሮች ሥረ መሠረት የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?

◻ ኢየሱስና ተከታዮቹ “የዓለም ብርሃን” የሆኑት በምን መንገዶች ነው?

◻ የይሖዋ ብርሃንና እውነት እየመሩን ያሉት እንዴት ነው?

◻ ይሖዋ ክብሩ በድርጅቱ ላይ እንዲበራ ያደረገው እንዴት ነው?

◻ ይሖዋ ሕዝቦቹን ብርሃን አብሪዎች ያደረጋቸው ለምን ዓላማ ነው?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኤደን ውስጥ የተፈጸመ አንድ ሁኔታ በዛሬው ጊዜ ያሉትን የሰዎችን አሳዛኝ ችግሮች መንስዔ ለመረዳት ያስችለናል

[ምንጭ]

Tom Haley/Sipa

Paringaux/Sipa

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ