በ“ብርሃን አብሪዎች” የወረዳ ስብሰባ ላይ የተገኙ ብዙ በረከቶች
ነቢዩ ኢሳይያስ 2,700 ከሚያህሉ ዓመታት በፊት “እነሆ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል” ሲል ጽፎ ነበር። (አሳ 60:2) እነዚህ ቃላት እውነት መሆናቸው በአስደናቂ ሁኔታ ተረጋግጦአል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ብርሃን እንዲወጣ ስላደረገ ተስፋ ቢስ ሆነን አልቀረንም። የአምላክን ብርሃን የሚወዱ ሰዎች ሁሉ ባለፈው ዓመት በ“ብርሃን አብሪዎች” የወረዳ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ሞቅ ያለ ግብዣ ቀርቦላቸው ነበር።
የስብሰባው ፕሮግራም ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው በሰሜን አሜሪካ በሰኔ ወር ላይ ነበር። ከዚያ በኋላ ባሉት ወራት በምስራቅና በምዕራብ አውሮፓ፣ በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ፣ በአፍሪቃ፣ በእስያና በተለያዩ ደሴቶች ቀርቦአል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በስብሰባው ተገኝተዋል። ሁሉም በቀረበላቸው ግሩም መንፈሳዊ ድግስ ተደስተዋል።
“ብርሃን አብሪዎች በሙሉ እንኳን ደህና መጣችሁ!”
በአብዛኞቹ ቦታዎች ስብሰባው ዓርብ ቀን ተጀምሮ ዕሁድ ቀን ከሰዓት በኋላ አልቆአል። ዓርብ ዕለት ጠዋት ተሰብሳቢዎቹ በየቦታቸው እንደተቀመጡ የይሖዋ ብርሃን በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት እንዴት እንደበራ የሚገልጽ አጭር ማብራሪያ አዳመጡ። ከዚህ በኋላ የስብሰባው ሊቀመንበር መድረኩን ያዘ። እርሱም እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ ብርሃን አብሪዎች መሆን እንደሚኖርባቸው ከተናገረ በኋላ ሞቅ ባለ መንፈስ “ብርሃን አብሪዎች በሙሉ እንኳን ደህና መጣችሁ!” አለ። የስብሰባው ፕሮግራም በስብሰባው ላይ የተገኙት በሙሉ የይሖዋን ብርሃን በማንጸባረቅ እንዲቀጥሉ የሚረዳቸው ነበር።
የስብሰባውን አጠቃላይ ዓላማ የሚገልጸው ንግግር መላው ስብሰባ የሚኖረውን መንፈስ አስተዋወቀ። ተናጋሪው የሰው ልጆች ብርሃን የጨለመው ጥንት በኤደን ገነት ውስጥ እንደሆነ ተናገረ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰይጣን የሰው ልጆች የእውነትን ብርሃን እንዳይመለከቱ ሲያሳውራቸው ቆይቶአል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ቢሆንም ኢየሱስ “የዓለም ብርሃን” ሆኖ መጣ። (ኢሳይያስ 42:1–6) እርሱም ሃይማኖታዊ ውሸቶችን አጋለጠ፣ የጨለማ ሥራዎችን ለይቶ አሳወቀ፣ የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፎ ቆመ፣ የመንግሥቱን ምሥራች ሰበከ። የኢየሱስ ተከታዮችም ይህንን አድርገዋል፣ አሁንም በማድረግ ላይ ይገኛሉ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ተናጋሪው ቀስቃሽ በሆነ አነጋገር “እኛም እንደ ኢየሱስ ብርሃን አብሪዎች ልንሆን እንችላለን። በዘመናችን ከዚህ የበለጠ አስፈላጊነት ያለው ሌላ ሥራ የለም። ከዚህም የበለጠ መብት ሊኖር አይችልም” አለ።
የመጀመሪያው የስብሰባ ክፍል ሊያልቅ እንደተቃረበ አንድ ያልተጠበቀ አስደሳች ነገር ሆነ። የስብሰባው ሊቀመንበር ወደ መድረኩ ተመለሰና አራት ተከታታይ ትራክቶች መውጣታቸውን አስታወቀ። በዚህ ጊዜ የደስታ ጭብጨባ አስተጋብቶአል። በስብሰባው ላይ ለተገኘ ለእያንዳንዱ ሰው የትራክቶቹ አንዳንድ ቅጂዎች ታድለዋል።
ዓርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ የስብሰባው ፕሮግራም የጀመረው ብርሃን አብሪዎች ለሆኑ ክርስቲያኖች በቀረቡ መሠረታዊ ምክሮች ነበር። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ንግግሮች በዚህ ዓለም ጨለማ ከመበከል እንዴት ራስን መጠበቅ እንደሚቻል የሚገልጽ ምክር አቀረቡ። ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ሊቀርብ ስለሚችልና የዚህ ዓለም ርኩስ ነገሮች ሊያታልሉን ስለሚችሉ ዘወትር መንፈሳዊ አመለካከት ይዞ መገኘት አስፈላጊ ነው። (2 ቆሮንቶስ 11:14) ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” ሲል መክሮአል። (ሮሜ 12:2) አንድ ክርስቲያን የሚያደርገው የባሕርይ መለወጥ የማያቋርጥ ሂደት እንደሆነ ተሰብሳቢዎቹ ተነገራቸው። የአምላክን ቃል በማጥናትና ያጠናነውን ሥራ ላይ በማዋል አእምሮአችን ይጠራል፣ ይስተካከላል። በዚህም መንገድ “እውነትንና ጸጋን ተሞልቶ” የነበረውን ኢየሱስን በይበልጥ እየመሰልነው እንሄዳለን። — ዮሐንስ 1:14
ወጣት ብርሃን አብሪዎች
የዓርብ ከሰዓት በኋላው ስብሰባ የመጨረሻ ክፍል ያተኮረው በወጣቶች ላይ ነበር። (“ወጣቶች፣ የምትከታተሉት ምንን ነው?”) የሚለው ንግግር ለታማኝነት በጣም ጥሩ ምሳሌ የሆኑትን ወጣቶች በሙሉ አሞገሰ። ይሁን እንጂ ልዩ የሰይጣን ዒላማ መሆናቸውን ንግግሩ አሳሰባቸው። በጣም ጥሩ ሥልጠና የተሰጠው ስፖርተኛ እንኳን የቅርብ አማካሪ ያስፈልገዋል። ወጣቶችም በተመሳሳይ በብርሃን መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ የወላጆቻቸውና የጉባዔው እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
ይህ ቁምነገር ለዓርብ ዕለቱ ስብሰባ መደምደሚያ በሆነው በይሖዋ ዓይን ቅን የሆነውን ማድረግ በተባለው አስደናቂ ድራማ ጎላ ብሎ ተገልጾአል። በዚህ ድራማ የቀረበው የንጉሥ ኢዮስያስ ጥሩ ምሳሌነት ነበር። ኢዮስያስ ገና ልጅ በነበረበት ጊዜ እንኳን ይሖዋን ለማገልገል ቆርጦ ነበር። በአካባቢው ወደ መጥፎ ሊመሩት የሚችሉ ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ኢዮስያስ ከሊቀካህኑ ከኬልቅያስ ባገኘው ሥልጠናና ለአምላክ ሕግ በነበረው ፍቅር ምክንያት በይሖዋ ፊት ቅን የሆነውን ለማድረግ ችሎአል። ዛሬም ወጣት ክርስቲያኖች እንዲሁ እንዲያደርጉ እንመኛለን።
ብርሃን ይብራ
ተሰብሳቢዎቹ ከአንድ ሌሊት ዕረፍት በኋላ ቅዳሜ ጠዋት ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመቀበል ዝግጁ ሆነው መጡ። የጠበቁትንም አላጡም። የዕለቱ ፕሮግራም በዕለቱ ጥቅስ ላይ በተደረገ ውይይት ተከፍቶ አንድ ክርስቲያን ብርሃኑ እንዲበራ ሊያደርግ ስለሚችልባቸው የተለያዩ መንገዶች በሚገልጹ ተከታታይ ንግግሮች ቀጠለ። (ማቴዎስ 5:14–16) አንደኛው ትልቅ መንገድ ስብከት ሲሆን መልካም ጠባይ ማሳየትም ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል። ተናጋሪው እንዳለው “ስብከት ሰዎች ምን እንደምናምን እንዲያውቁ ያስችላቸዋል፤ ፍቅር ማሳየት ግን የምናምነውን በተግባር ያሳያል።”
ከዚህ በኋላ ተሰብሳቢዎቹ አስፈላጊ በሆነ የመስበኪያ መሣሪያ ላይ እንዲያተኩሩ ተደረገ። ባለፈው ቀን የቀረበው ማስታወቂያ ገና ከተሰብሳቢዎቹ አእምሮ ሳይወጣ እነዚህ ትናንሽ መሣሪያዎች ምን ያህል ከፍተኛ ኃይል እንዳላቸው የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን ሰሙ። ተሰብሳቢዎች በማንኛውም አጋጣሚ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ትራክቶች በበቂ መጠን ሁልጊዜ እንዲይዙ ማበረታቻ ተሰጣቸው።
ከዚህ በኋላ ትኩረት የተደረገው ብርሃን እንዲበራ በማድረግ ረገድ ተግተው በሚሠሩት የሙሉ ጊዜ የመንግሥት ሰባኪዎች ወይም አቅኚዎች ላይ ነበር። በትጋት የሚሠሩትን አቅኚዎች እናደንቃቸዋለን። ቁጥራቸውም እየጨመረ መጥቶአል። የአምልኮ ነፃነት በቅርብ ዓመታት በተሰጣቸው አገሮች እንኳን የአቅኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮአል። አቅኚዎች መብታቸውን እንደውድ ሀብት እንዲጠብቁት ማበረታቻ ተሰጥቶአቸዋል። እስከአሁን አቅኚ ያልሆኑም ሁኔታቸውን እንዲመረምሩ ተመክረዋል። ምናልባት እነርሱም ጉዳዮቻቸውን አስተካክለው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል ብርሃናቸው በይበልጥ እንዲበራ ለማድረግ ይችሉ ይሆናል።
ብርሃን አብሪ መሆን ብዙውን ጊዜ መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ ነው። ይህም “ራስን መሥዋዕት በማድረግ መንፈስ ይሖዋን ማገልገል” በሚለው ቀጣይ ንግግር ጎላ ብሎ ተገልጾአል። ጳውሎስ “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ” አቅርቡ ሲል አሳስቦአል። (ሮሜ 12:1) በስደት የጸኑ ሁሉ ራሳቸውን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ያሳያሉ። አቅኚዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቆየት ሲሉ በየቀኑ መሥዋዕትነት ይከፍላሉ። እንዲያውም እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ የዚህን ዓለም የራስ ወዳድነትና ቁሳዊ ሀብት የማግበስበስ መንገድ ከመከተል ይልቅ ራሳቸውን በይሖዋ አገልግሎት በማስጠመድ መሥዋዕት ይከፍላሉ። ይህ ዓይነቱ አኗኗር ከይሖዋ ብዙ በረከት ያስገኛል።
ይህ ንግግር ቀጥሎ ለተደረገው የጥምቀት ንግግር ጥሩ መግቢያ ሆኖ ነበር። በ“ብርሃን አብሪዎች” ስብሰባ ላይ የተጠመቁ ሁሉ ይህንን ንግግር እንደማይረሱት የታወቀ ነው። ጥምቀታቸው በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፍተኛውን ቦታ ይዞ ይኖራል። በ30 ዓመት ዕድሜው የተጠመቀውን የኢየሱስን ምሳሌ መከተላቸው እንደሆነ እንዲያስታውሱ ተደርገዋል። ከዚህም በላይ ዕጩ ተጠማቂዎቹ ‘የጨለማ ሥራዎችን አስወግደው’ የይሖዋ ባሮች ለመሆን መወሰናቸውን ሲያስታውሱ ደስ ይላቸዋል። (ሮሜ 12:11፤ 13:12) ወደሚጠመቁበት ሥፍራ ከመሄዳቸው በፊት በጣም ብዙ በሆኑት ተሰብሳቢዎች ፊት ቆመው ጮክ ያለ ድምፅ በማሰማት በሕዝብ ፊት አቋማቸውን አሳውቀዋል። (ሮሜ 10:10) በ“ብርሃን አብሪዎች” ስብሰባ ላይ በውኃ በመጠመቅ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ያሳዩትን ሁሉ ይሖዋ አብዝቶ እንዲባርክ እንጸልያለን።
የቅዳሜ ከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ግልጽ ማስጠንቀቂያዎች የተሰጡበት ጊዜ ነበር። “ከስግብግብነት መንፈስ ተጠበቁ”፣ “ጠቃሚ ልማዳችሁን የሚያበላሽባችሁ ሰው አለን?”፣ “ከማንኛውም ዓይነት ጣዖት አምልኮ ራሳችሁን ጠብቁ” በሚሉ ንግግሮች አማካኝነት ይህ ማስጠንቀቂያ ቀርቦ ነበር። እነዚህ ሦስት ንግግሮች ሰይጣን አንድን ክርስቲያን ለማዳከም ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች አንዳንዶቹን ገልጸዋል። የአስቆሮቱ ይሁዳ ሐዋርያ ነበር፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስን በገንዘብ አሳልፎ ሰጥቷል። ወጣቱ ሳሙኤል ያደገው የይሖዋ አምልኮ በሚፈጸምበት ብሔራዊ ማዕከል ነበር። ቢሆንም መጥፎ ባልንጀሮች አጋጥመውት ነበር። (1 ሳሙኤል 2:12, 18–20) የጣዖት አምልኮ እንደ ጾታ ርኩሰትና እንደ መጎምጀት የመሰሉትን ድርጊቶች ሊጨምር ይችላል። (ኤፌሶን 5:5፤ ቆላስይስ 3:5) አዎ ስግብግብነት፣ መጥፎ ባልንጀርነትና የጣዖት አምልኮ በጣም መጥፎ ነገሮች ናቸው። መወገድም ይኖርባቸዋል።
ከዚህ በኋላ የስብሰባው ፕሮግራም አቀራረብ ተለወጠ። ቀጣዩ ፕሮግራም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ በርካታ ጥያቄዎችን ካነሳ በኋላ መልሶቻቸውን ሰጠ። ለምሳሌ ያህል ከታላቁ መከራ በፊት እውነትን ሳይቀበሉ የሞቱ ሰዎች ትንሣዔ ያገኙ ወይም አያገኙ እንደሆነ ልታስረዳ ትችላለህን? አንድ ክርስቲያን ወይም አንዲት ክርስቲያን ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ማግኘት ባይችል ወይም ባትችል ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ በተለይም “የአንባብያን ጥያቄዎች” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን በመመርመር የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ ማበረታቻ ተሰጥቶአቸዋል።
የክርስቶስ መገኘትና መገለጥ
የቅዳሜው ፕሮግራም የመደምደሚያ ክፍል ያተኮረው በትንቢት ላይ ሲሆን “በክርስቶስ መገኘትና መገለጥ ላይ ብርሃን ማብራት” በሚል ርዕስ ተከታታይ ንግግር ቀርቦአል። (ማቴዎስ 24:3) በሁለተኛው ንግግር ላይ ታማኝና ልባም ባሪያ በዘመናችን የሚያንቀሳቅሳቸው ሥራዎች ተብራርተዋል። (ማቴዎስ 24:45–47) የባሪያው ክፍል ከ1919 ጀምሮ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ሥራ በግንባር ቀደምትነት በመምራት ላይ እንደሚገኝ ተጠቀሰ። በኋላም እጅግ ብዙ ሕዝብ ከብሔራት ሁሉ ተሰብስቦ የይሖዋን ብርሃን በማንጸባረቅ ሥራ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር መካፈል ጀምሮአል። ተናጋሪው በመደምደሚያው ላይ እንዲህ አለ፣ “ሁላችሁም ታማኝና ልባም ባሪያን በቅንዓት መደገፋችሁን ቀጥሉ። በግ መሰል ሰዎች ሁሉ በቅርቡ በሚመጣ አንድ ቀን ‘እናንተ የአባቴ ብሩካን ኑ፣ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን የአባቴን መንግሥት ውረሱ’ የሚለውን አስደሳች ቃል ሊሰሙ የሚችሉት ይህን ካደረጉ ብቻ ነው።” — ማቴዎስ 25:34
የመጨረሻው ተናጋሪ ያብራራው የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ የሚኖረውን ትርጉምና ውጤት ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:7) ይህ መገለጥ እንዴት ያለ የሚያስደንቅ ተሞክሮ ይሆናል! ታላቂቱ ባቢሎን ፈጽማ ትጠፋለች። ኢየሱስ ከመላእክቱ ጋር ሆኖ ከሰይጣን ዓለም ጋር በሚያደርገው ታላቅ ጦርነት ይህ ሥርዓት ይጠፋል። በመጨረሻም ሰይጣን ራሱ በጥልቁ ውስጥ ይጣልና ተሽመድምዶ እንዲቆይ ይደረጋል። የአምላክ ሕዝቦች ግን የበጉ ሠርግ በሰማይ ስለሚፈጸምና አዲሱ ምድር ስለሚጀምር እፎይታ ያገኛሉ። በመጨረሻም ተናጋሪው አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የሚል አዲስ ብሮሹር መውጣቱን በማስታወቅ አድማጮቹን አስደስቶአል። ይህ ጽሑፍ አሳቢ ስለሆነው ፈጣሪያችንና እርሱ ለእኛ ስላለው ዓላማው ማወቅ የሚያስፈልጋቸውን ትሁት ሰዎች በእጅጉ የሚረዳ እንደሚሆን የታወቀ ነው።
ክርስቲያን ቤተሰቦች
አሁን የስብሰባው የመጨረሻ ቀን የሆነው እሁድ ቀን ደረሰ። ይሁን እንጂ አሁንም መቅረብ ያለበት ገና ብዙ ትምህርት አለ። የዕለቱ ጥቅስ ከተብራራ በኋላ ትኩረት የተደረገው በክርስቲያን ቤተሰብ ላይ ነበር። “በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ እርስበርስ መተሳሰብ” በሚል ርዕስ ተከታታይ ንግግሮች ቀረቡ። በመጀመሪያው ንግግር ተሰብሳቢዎች የተሳካለት የቤተሰብ ሕይወት የሚገኝበትን ቁልፍ ለማወቅ ችለዋል። እርሱም መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም ነው። ሁለተኛው ንግግር ቤተሰቦች ማንኛውንም ነገር አብረው እንዲሠሩ የሚያበረታታ ነበር። አብረው በስብሰባዎች እንዲካፈሉ፣ አብረው በመስክ እንዲያገለግሉ፣ አብረው የቤተሰብ ጥናት እንዲያደርጉና አብረው እንዲዝናኑ መክሮአል። ሦስተኛው ንግግር ደግሞ ተሰብሳቢዎች ለአረጋውያን እንክብካቤ የማድረግ መብትና ኃላፊነት እንዳላቸው አስገንዝቦአል። ተናጋሪው “አረጋውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለጉባዔው ትልቅ ንብረት ናቸው። የሕይወት ተሞክሮአቸውን እንደውድ ሀብት እንመልከት፤ ፍጹም አቋም ጠባቂነታቸውን ለመከተል እንጣር” ብሎአል።
ቀጥሎ “በአስተሳሰብ ጤናማ መሆን” የሚለው አነጋገር ትርጉሙ ምን እንደሆነ ተመርምሯል። (1 ጴጥሮስ 4:7) በአስተሳሰቡ ጤናማ የሆነ ሰው ሚዛናዊ፣ አስተዋይ፤ ምክንያታዊ፣ ትሁትና በትክክል የሚያስብ ነው። ትክክለኛውን ከስህተት፣ እውነቱን ከውሸት መለየት ይችላል። ከዚህም በላይ ጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት ይዞ ለመኖር ይጣጣራል።
እሁድ ጠዋት የቀረበው የመጨረሻ ንግግር ለአምላክና ለክርስቶስ የመገዛታችንን ጉዳይ የሚያብራራ ነበር። ተናጋሪው “ለይሖዋ አምላክና ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ በታማኝነት የመገዛት አስፈላጊነት ተደጋግሞ ምክር ቢሰጥበት ከመጠን በላይ ተጋንኖአል ሊባል አይችልም” አለ። ንግግሩን በመቀጠል ይህ ጉዳይ እያንዳንዱን የኑሮአቸን ክፍል እንዴት እንደሚነካ አብራርቶአል። ዘወትር እንድንገዛ የሚረዳን ምንድን ነው? አራት ባሕርያት ናቸው። ፍቅር፣ አምላካዊ ፍርሐት፣ እምነትና ትህትና።
እሁድ ከሰዓት በኋላ
ጊዜው ሳይታወቅ በድንገት የስብሰባው የመጨረሻ ክፍል የሆነው እሁድ ከሰዓት በኋላ ደረሰ። ብዙዎች ስብሰባው ገና መጀመሩ መስሎ የታያቸው ቢሆንም ወደ መደምደሚያው ተቃርቦ ነበር።
የሕዝብ ንግግሩ ርዕስ “የዓለምን ብርሃን ተከተሉ” የሚል ነበር። በንግግሩ ላይ የተገኙ ሁሉ በተፈጥሮ የምናገኘው ብርሃን ሕይወት እንዲኖር በማስቻል ረገድ እንዴት ያለ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ሲብራራላቸው አዳምጠዋል። ተናጋሪው በመቀጠል መንፈሳዊ ብርሃን ከዚህ የበለጠ አስፈላጊነት እንዳለው አብራራ። በተፈጥሮ የምናገኘው ብርሃን በሕይወት የሚያቆየን ለጥቂት አሥርተ ዓመታት ብቻ ነው። መንፈሳዊ ብርሃን ግን ለዘላለም ሊያኖረን ይችላል። ንግግሩ በዮሐንስ 1:1–16 የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ቁጥር በቁጥር የሚያብራራ ነበር። በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ የዓለም ብርሃን እንደሆነ ተገልጾአል። ይህ ክፉ ሥርዓት ሊጠፋ በተቃረበበት በዚህ የመጨረሻ ጊዜ ኢየሱስን በዚህ ረገድ መከተል በጣም አጣዳፊ ሆኖአል።
በሳምንቱ መጠናት የነበረበት የመጠበቂያ ግንብ ርዕሰ ትምህርት አጠር ብሎ ከቀረበ በኋላ የመደምደሚያው ንግግር ቀረበ። ተናጋሪው ከፊታችን ባሉት ቀናት የምንጠብቃቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ገለጸ። ለምሳሌ ያህል የአምላክን ፈቃድ በቅንዓት ማድረግ የሚል ድራማ በካሴት መዘጋጀቱን አስታውቆአል። በዚህ ብቻ አላበቃም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሐቀኛ ታሪኮችና የትንቢት መጽሐፍ በሚል ርዕስ ተከታታይ የቪዲዮ ካሴቶች እንደሚወጡና የመጀመሪያው ካሴት ርዕስ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ትክክለኛ ታሪክና አስተማማኝ ትንቢት እንደሚሆን ተናጋሪው አስታውቋል።
በመጨረሻም ተናጋሪው በ1993 ለአራት ቀናት የሚቆዩ የወረዳ ስብሰባዎችና በአንዳንድ የአፍሪቃ፣ የእስያ፣ የአውሮፓና የደቡብ አሜሪካ አገሮች ልዩ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች እንደሚደረጉ አስታውቆአል። የ“ብርሃን አብሪዎች” ስብሰባ ቢያልቅም ተሰብሳቢዎቹ ለሚቀጥለው ዓመት እቅድ ማውጣት ሊጀምሩ ይችላሉ።
ከዚህ በኋላ ተሰብሳቢዎች ወደየቤቶቻቸው የሚሄዱበት ጊዜ ደረሰ። በዚህ በጨለማ ዓለም ውስጥ ብርሃናቸው በይበልጥ እንዲታይ ለማድረግ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ቁርጥ ሐሳብ ይዘዋል። ብዙ መንፈሳዊ ነገሮች የሞሉባቸው ሦስት ቀናት ካለቁ በኋላ በመጨረሻው ንግግር ላይ የተጠቀሰው የመጨረሻ ጥቅስ ልዩ የሆነ ትርጉም አግኝቶአል። “ይሖዋ መለኮት ነው፤ ብርሃንም ይሰጣል። . . . ይሖዋ ጥሩ ነውና አመስግኑት ፍቅራዊ ደግነቱ ላልተወሰነ ጊዜ ይቀጥላልና።” — መዝሙር 118:27, 29 አዓት
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የስብሰባው ፕሮግራም በሩስያ ቋንቋ
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በብዙ ስብሰባዎች ላይ የአስተዳደር አካል አባሎች ንግግር አድርገው ነበር
በሩስያ በሴንት ፒተርስበርግ ከተሰበሰቡት መካከል ከጃፓን የመጡ ተወካዮችም ነበሩ
በይሖዋ ዓይን ቅን የሆነውን ማድረግን የሚያጎላው ስሜት ቀስቃሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ
አዲስ ብርሃን አብሪዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት ሲያሳዩ
በሴንት ፒተርስበርግ በተደረገው ስብሰባ ላይ ተሰብሳቢዎቹ በተመስጦ ሲያዳምጡ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተወካዮቹ “አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?” የሚለውን አዲስ ብሮሹር በማግኘታቸው በጣም ተደስተው ነበር