የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ከፍተኛ ወሮታ ያስገኘ ጉብኝት
ንግሥቲቱ ከሳባ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገችው ጉዞ አድካሚ ሳይሆንባት አልቀረም። በተንደላቀቀ ሁኔታ መኖር የለመደች ናት። አሁን ግን በአብዛኛው እንደ እሳት በሚያቃጥለው በረሃ በግመል ፍጥነት የ2,400 ኪሎ ሜትር ጉዞ እያደረገች ነው። በአንድ ግምት መሠረት ያደረገችውን ጉዞ ለማጠናቀቅ ወደ 75 ቀናት ገደማ ሊፈጅባት ይችላል፤ ይህ ደግሞ ለመሄድ ወይም ለመመለስ ብቻ የሚፈጅባት ጊዜ ነው!a
ይህች ባለጸጋ ንግሥት በሳባ የሚገኘውን ምቹ መኖሪያዋን ትታ እንዲህ ዓይነት አድካሚ ጉዞ ያደረገችው ለምን ነበር?
ጉጉት የሚቀሰቅስ ወሬ
የሳባ ንግሥት ወደ ኢየሩሳሌም የመጣችው ‘እግዚአብሔር ለሰሎሞን ስለሰጠው አስደናቂ ጥበብ የሚነገረውን ሁሉ ከሰማች’ በኋላ ነበር። (1 ነገሥት 10:1 የ1980 ትርጉም) በትክክል ንግሥቲቱ የሰማችው ነገር ምን እንደሆነ አልተጻፈም። ሆኖም ይሖዋ ሰሎሞንን ወደር የሌለው ጥበብ፣ ሀብትና ክብር በመስጠት ባርኮት እንደነበር እናውቃለን። (2 ዜና መዋዕል 1:11, 12) ንግሥቲቱ ስለዚህ ነገር እንዴት ልታውቅ ቻለች? ሳባ የንግድ ማዕከል ስለነበረች ንግሥቲቱ ወደ አገሯ በሚመጡ ነጋዴዎች አማካኝነት ስለ ሰሎሞን ዝና ሰምታ ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ አንዳንዶቹ ሰሎሞን ከፍተኛ የንግድ ግንኙነት ያደርግባት ወደነበረው ወደ ኦፊር ምድር የሚጓዙ ሊሆኑ ይችላሉ።—1 ነገሥት 9:26-28
ያም ሆነ ይህ ንግሥቲቱ “በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቁ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር” ኢየሩሳሌም ደረሰች። (1 ነገሥት 10:2) አንዳንዶች “ታላቅ ጓዝ” የተባለው ነገር መሣሪያ የታጠቁ አጃቢዎችን እንደሚጨምር ይናገራሉ። ንግሥቲቱ ከፍተኛ ሥልጣን ያላት መሆኗንና በአሥር ሚልዮኖች ዶላር የሚገመቱ ውድ ዕቃዎች መያዝዋን ስናስብ አጃቢ ያስፈለገበት ምክንያት ሊገባን ይችላል።b
ሆኖም ንግሥቲቱ ‘ከይሖዋ ስም ጋር በተያያዘ’ የሚነገረውን የሰሎሞን ዝና እንደሰማች ልብ በል። በመሆኑም ይህ ለንግድ ብቻ ተብሎ የተደረገ ጉዞ አልነበረም። ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ንግሥቲቱ በአንደኛ ደረጃ የመጣችበት ዓላማ የሰሎሞንን ጥበብ፣ አልፎ ተርፎም ስለ አምላኩ ስለ ይሖዋ የሆነ ነገር ለማወቅ ፈልጋ ሳይሆን አይቀርም። የይሖዋ አምላኪዎች የሆኑት የሴም ወይም የካም ዝርያ ልትሆን ስለምትችል ቅድመ አያቶቿ ይከተሉት ስለነበረው ሃይማኖት የማወቅ ጉጉት አድሮባት ሊሆን ይችላል።
አመራማሪ ጥያቄዎች፣ አርኪ መልሶች
ንግሥቲቱ ከሰሎሞን ጋር በተገናኘች ጊዜ “አመራማሪ በሆኑ ጥያቄዎች” ትፈትነው ጀመር። (1 ነገሥት 10:1 NW) እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “እንቆቅልሽ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ሆኖም እንዲህ ሲባል ንግሥቲቱ ሰሎሞንን በአልባሌ ቀልዶች አጥምዳዋለች ማለት አይደለም። በመዝሙር 49:4 NW ላይ ኃጢአትን፣ ሞትንና ቤዛን የሚመለከቱ አሳሳቢ ጥያቄዎችን ለመግለጽ ይኸው የዕብራይስጥ ቃል የተሠራበት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ስለዚህ የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን የማስተዋል ጥልቀት የሚፈትኑ ከበድ ያሉ ጉዳዮችን ሳታወያየው አትቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ “በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው” ሲል ይገልጻል። በአጸፋው ደግሞ ሰሎሞን “የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም።”—1 ነገሥት 10:2, 3
የሳባ ንግሥት በሰሎሞን ጥበብና በመንግሥቱ ብልጽግና ከመደነቋ የተነሳ “ነፍስ አልቀረላትም” ነበር። (1 ነገሥት 10:4, 5) አንዳንዶች ይህን ሐረግ ንግሥቲቱ “እስትንፋሷ ቀጥ አለ” ማለት እንደሆነ አድርገው ይረዱታል። እንዲያውም አንድ ሃይማኖታዊ ምሁር ሕሊናዋን እንደሳተች ተናግረዋል! ያም ሆነ ይህ ንግሥቲቱ ባየችውና በሰማችው ነገር ተደንቃ ነበር። የሰሎሞን አገልጋዮች የዚህን ንጉሥ ጥበብ መስማት በመቻላቸው ደስተኞች መሆናቸውን ከመግለጿም በላይ ሰሎሞንን በማንገሡ ይሖዋን ባርካለች። ከዚያም ለንጉሡ በጣም ውድ ስጦታዎች የሰጠችው ሲሆን ወርቁ ብቻ እንኳ አሁን ባለው የዋጋ ተመን 40,000,000 የአሜሪካ ዶላር ያወጣል። ሰሎሞንም ስጦታዎች በማምጣት “የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ” ለንግሥቲቱ ሰጣት።c—1 ነገሥት 10:6-13
ከዚህ የምናገኘው ትምህርት
ኢየሱስ ጻፎችና ፈሪሳውያንን ለማስተማር የሳባን ንግሥት ተግባራዊ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞባታል። “ንግሥተ ዓዜብ [“የደቡብ ንግሥት፣” የ1980 ትርጉም] በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፣ እነሆም፣ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ” በማለት ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 12:42) አዎን፣ የሳባ ንግሥት ከአምላክ ለተገኘ ጥበብ ከፍተኛ አድናቆት አሳይታለች። እርሷ ሰሎሞን የሚናገረውን ለመስማት 2,400 ኪሎ ሜትር ተጉዛ ከመጣች በእርግጥም ጻፎችና ፈሪሳውያን እዚያው አጠገባቸው የነበረውን ኢየሱስን በጥሞና ሊያዳምጡት ይገባ ነበር።
ዛሬ እኛ ለታላቁ ሰሎሞን ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥልቅ አድናቆት ማሳየት እንችላለን። እንዴት? አንደኛው መንገድ ‘አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ በማለት የሰጠንን መመሪያ በመታዘዝ ነው። (ማቴዎስ 28:19) ሌላው ደግሞ የኢየሱስን ምሳሌና አስተሳሰብ በቅርብ ተመልክተን እርሱን ለመምሰል በመጣር ነው።—ፊልጵስዩስ 2:5፤ ዕብራውያን 12:1-3
እውነት ነው፣ የታላቁን ሰሎሞን ምሳሌ ለመከተል በእኛ በኩል ጥረት ይጠይቅብናል። ሆኖም እንዲህ በማድረጋችን ከፍተኛ ወሮታ እናገኛለን። በእርግጥም የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ካሳዩ ይሖዋ ‘የሰማይን መስኮት እንደሚከፍትላቸውና በረከትንም አትረፍርፎ እንደሚያፈስላቸው’ ለሕዝቦቹ ቃል ገብቷል።—ሚልክያስ 3:10
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ብዙ ሃይማኖታዊ ምሁራን ሳባ በዛሬው ጊዜ የየመን ሪፑብሊክ ተብላ በምትታወቀው በደቡብ ምዕራብ አረቢያ ትገኝ እንደነበር ይገምታሉ።
b በድሮ ዘመን የኖሩት ግሪካዊ የጂኦግራፊ ባለሙያ ስትራቦ እንዳሉት ከሆነ የሳባ ነዋሪዎች እጅግ ባለጸጋ ነበሩ። በቤት ውስጥ ዕቃዎቻቸው፣ ለምግብ ማብሰያ በሚገለገሉባቸው ዕቃዎች አልፎ ተርፎም በቤታቸው ግድግዳ፣ በርና ሰገነት ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ይጠቀሙ እንደነበር ተናግረዋል።
c አንዳንዶች ይህ አባባል ንግሥቲቱ ከሰሎሞን ጋር የጾታ ግንኙነት ፈጽማለች ማለት እንደሆነ ያስባሉ። አልፎ ተርፎም ወንድ ልጅ እንደወለዱ በአፈ ታሪክ ይነገራል። ይሁን እንጂ እነዚህን ሐሳቦች የሚደግፍ ምንም ማስረጃ የለም።