‘ከክፉ ትውልድ’ መዳን
“እናንተ የማታምን ጠማማ ትውልድ፣ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ?”—ሉቃስ 9:41
1. (ሀ) መከራ የተሞላበት የዘመናችን ሁኔታ ወደፊት ምን እንደሚመጣ ይጠቁማል? (ለ) ቅዱሳን ጽሑፎች በሕይወት ስለሚተርፉ ሰዎች ምን ይላሉ?
የምንኖረው ሥቃይና መከራ በሞላበት ዘመን ውስጥ ነው። አሁን ባለንበት በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የመሬት መንቀጥቀጦች፣ የውኃ መጥለቅለቆች፣ ረሃብ፣ ዓመፅ፣ የቦምብ ድብደባ፣ አስፈሪ ጦርነቶችና ሌሎች መከራዎች የሰውን ልጅ ሕይወት በእጅጉ ነክተውታል። ሆኖም በቅርቡ የሰው ልጅ እስከ ዛሬ ድረስ ከደረሱበት መከራዎች ሁሉ እጅግ የከፋ መከራ ይገጥመዋል። ይህ መከራ ምንድን ነው? ይህ መከራ “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል” የተባለው ነው። (ማቴዎስ 24:21) ሆኖም ብዙዎቻችን ወደፊት አስደሳች ጊዜ እንደሚመጣ ልንጠባበቅ እንችላለን! እንደዚህ የምንለው ለምንድን ነው? የአምላክ ቃል ራሱ እንዲህ በማለት ስለሚገልጽ ነው፦ “አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ . . . እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ . . . ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፣ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፣ . . . እግዚአብሔርም እንባዎቸን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።”—ራእይ 7:1, 9, 14–17
2. የማቴዎስ 24፣ የማርቆስ 13 እና የሉቃስ 21 የመክፈቻ ጥቅሶች ምን የመጀመሪያ ትንቢታዊ ፍጻሜ ነበራቸው?
2 በማቴዎስ 24:3–22፣ በማርቆስ 13:3–20 እና በሉቃስ 21:7–24 ላይ በመንፈስ አነሣሽነት የሰፈረው ታሪክ ኢየሱስ ስለ ‘ሥርዓቱ መደምደሚያ’ የተናገረውን ትንቢት ይገልጻል።a ይህ ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በተደመደመው የአይሁድ ብልሹ የነገሮች ሥርዓት ላይ የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቷል። ይህም በአይሁዳውያን ላይ ታይቶ የማይታወቅ “ታላቅ መከራ” አስከትሏል። በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ላይ ያተኮረው ጠቅላላው የአይሁድ ሥርዓት ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መዋቅር እንደገና መጠገን በማይችልበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ጠፋ።
3. በዛሬው ጊዜ የኢየሱስን ትንቢት መታዘዝ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
3 አሁን ከኢየሱስ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜ ጋር በቅርበት የሚያያዙትን ሁኔታዎች እስቲ እንመልከት። ይህም በዘመናችን የሚፈጸመውን ተመሳሳይ ነገር በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያስችለናል። በመላው የሰው ልጆች ላይ ከሚደርሰው ታላቅ መከራ ለመዳን አሁኑኑ አዎንታዊ እርምጃ መውሰዳችን ምን ያህል አጣዳፊ መሆኑን ይጠቁመናል።—ሮሜ 10:9–13፤ 15:4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:11፤ 15:18
“መጨረሻው” የሚመጣው መቼ ነው?
4, 5. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው አይሁዳውያን በዳንኤል 9:24–27 [አዓት] ላይ ትኩረት ያደረጉት ለምን ነበር? (ለ) ይህ ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነው?
4 በ539 ከዘአበ ገደማ የአምላክ ነቢይ የነበረው ዳንኤል ‘በሰባ [የዓመታት] ሳምንታት’ የመጨረሻ “ሳምንት” ውስጥ የሚፈጸሙ ሁኔታዎቸን የሚገልጽ አንድ ራእይ ተመለከተ። (ዳንኤል 9:24–27 አዓት) እነዚህ “ሳምንታት” የጀመሩት የፋርሱ ንጉሥ አርጤክስስ የኢየሩሳሌም ከተማ እንደገና እንድትሠራ ባዘዘበት በ455 ከዘአበ ነው። የመጨረሻው “ሳምንት” የጀመረው መሲሕ ሲመጣ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በ29 እዘአ ሲጠመቅና ሲቀባ ነው።b በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የነበሩ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው አይሁዳውያን ይህ ጊዜ የዳንኤል ትንቢት የሚፈጸምበት ጊዜ እንደሆነ አሳምረው ያውቁ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በ29 እዘአ አጥማቂው ዮሐንስን ለመስማት የመጡ አይሁዳውያንን በተመለከተ ሉቃስ 3:15 “ሕዝቡም ሲጠብቁ ሳሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ፦ ይህ ክርስቶስ ይሆንን? ብለው ሲያስቡ ነበር” ይላል።
5 ሰባኛው “ሳምንት” ለአይሁዳውያን ልዩ ሞገስ የተደረጉባቸው ሰባት ዓመታት ነበሩ። ይህ “ሳምንት” ከ29 እዘአ ይጀምርና ኢየሱስ የተጠመቀበትንና ያገለገለበትን ወቅት፣ በ33 እዘአ “በሳምንቱ አጋማሽ” የተፈጸመውን መሥዋዕታዊ ሞቱን እንዲሁም እስከ 36 እዘአ ያለውን ሌላ “የሳምንት አጋማሽ” ይጨምራል። በዚህ “ሳምንት” የኢየሱስ ቅቡዓን ደቀ መዛሙርት የመሆን አጋጣሚ የተከፈተላቸው ፈሪሃ አምላክ ላላቸው አይሁዳውያንና ወደ አይሁድ እምነት ለተለወጡ ሰዎች ብቻ ነበር። ከዚያም በ70 እዘአ በቲቶ የሚመራው የሮም ሠራዊት ከሃዲውን የአይሁድ ሥርዓት አጠፋ። ይህ ጊዜ በቅድሚያ አልታወቀም ነበር።—ዳንኤል 9:26, 27 አዓት
6. (ሀ) በ66 እዘአ የጀመረው “መከራ” ምን ያህል ጥፋት አስከትሎ ነበር? (ለ) ከጥፋቱ የተረፉት እነማን ናቸው? ከጥፋቱ ሊተርፉ የቻሉትስ ምን አጣዳፊ እርምጃ ስለወሰዱ ነው?
6 በዚህ መንገድ የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ያረከሰውና የራሱን የአምላክ ልጅን ሳይቀር ለመግደል ያሤረው የአይሁድ ክህነታዊ ሥርዓት ጠፋ። በተጨማሪም የብሔሩን ታሪክና የነገዶችን ስም ዝርዝር የያዙ መዛግብት ከቤተ መቅደሱ ጋር ጠፉ። ከዚያ በኋላ አንድም አይሁዳዊ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የክህነትም ሆነ የንግሥና መብት ይገባኛል ሊል አልቻለም። ሆኖም የተቀቡ መንፈሳዊ አይሁዳውያን የይሖዋ አምላክን ‘በጎነት ለመናገር’ ንጉሣዊ ካህናት ለመሆን ከሕዝቡ መካከል መለየታቸው ያስደስታል። (1 ጴጥሮስ 2:9) በ66 እዘአ የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ለመጀመሪያ ጊዜ ከበበ። እንዲያውም በቤተ መቅደሱ አካባቢ የሚገኘውን ግንብ ሰረሰረ። ክርስቲያኖች ይህ ወታደራዊ ኃይል ‘ነቢዩ ዳንኤል በተቀደሰችው ስፍራ እንደሚቆም’ የተናገረለት ‘የጥፋት ርኩሰት’ እንደሆነ ተገነዘቡ። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የነበሩ ክርስቲያኖች ለኢየሱስ ትንቢታዊ ትእዛዝ በመታዘዝ ጥበቃ ለማግኘት ወደ ተራራማ ቦታዎች ሸሹ።—ማቴዎስ 24:15, 16፤ ሉቃስ 21:20, 21
7, 8. ክርስቲያኖች የትኛውን “ምልክት” ተመልክተዋል? ይሁን እንጂ ያላወቁት ነገር ምን ነበር?
7 እነዚህ ታማኝ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የዳንኤልን ትንቢት ፍጻሜ ተመልክተዋል። በተጨማሪም ኢየሱስ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት” እንደሚሆኑ አስቀድሞ የተናገራቸው አሠቃቂ ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረቶች፣ ቸነፈሮች፣ የመሬት መንቀጥቀጦችና ዓመፅ ሲከሰቱ በዓይናቸው ተመልክተዋል። (ማቴዎስ 24:3 አዓት) ይሁን እንጂ ይሖዋ በዚያ ብልሹ ሥርዓት ላይ መቼ እንደሚፈርድ አስቀድሞ ነግሯቸው ነበርን? አልነገራቸውም። ኢየሱስ በንጉሣዊ መገኘቱ መደምደሚያ ላይ ምን እንደሚሆን ሲገልጽ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” በማለት የተናገረው ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተከስቶ ለነበረው “ታላቅ መከራ” ጭምር እንደሠራ ምንም አያጠራጥርም።—ማቴዎስ 24:36
8 አይሁዳውያን በዳንኤል ትንቢት መሠረት መሲሕ የሚመጣበትን ጊዜ ማስላት ይችሉ ነበር። (ዳንኤል 9:25) ሆኖም ከሃዲው የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት የሚጠፋበት “ታላቅ መከራ” መቼ እንደሚሆን አልተነገራቸውም። ይህ ጊዜ 70 እዘአ መሆኑን ያወቁት ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ ከጠፉ በኋላ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” በማለት የተናገረውን ትንቢት ያውቁ ነበር። (ማቴዎስ 24:34) እዚህ ላይ “ትውልድ” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል ትውልዶች በተከታታይ ስለ መፈራረቃቸው ከሚናገረው በመክብብ 1:4 ላይ ከተሠራበት ሐሳብ የተለየ ትርጉም ያለው ይመስላል።
“ይህ ትውልድ” የተባለው የትኛው ነው?
9. የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች ጄኒያ ለተባለው የግሪክኛ ቃል የሚሰጡት ፍቺ ምንድን ነው?
9 አራት ሐዋርያት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ከኢየሱስ ጋር ተቀምጠው በነበረበት ወቅት ስለ ‘ሥርዓቱ መደምደሚያ’ የሚገልጸውን የእሱን ትንቢት ሲሰሙ “ይህ ትውልድ” የሚለውን ቃል የተረዱት እንዴት ነበር? በወንጌሎች ውስጥ “ትውልድ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ጄኒያ ከተባለው ግሪክኛ ቃል የተወሰደ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ያሉ የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች ይህን ቃል እንዲህ በማለት ይፈቱታል፦ “ቃል በቃል ሲተረጎም ከአንድ ቅድመ አያት የመጡ ሰዎችን ያመለክታል።” (ዋልተር ባርስ ግሪክ ኢንግሊሽ ሌክስከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት) “ከአንድ ቤተሰብ የተገኙ ሰዎች ናቸው፤ . . . የአንድ የዘር ግንድ ተከታታይ አባላት . . . ወይም ከአንድ ዘር የተገኙ ሰዎች . . . ወይም በማቴ. 24:34፤ በማር. 13:30፤ በሉቃ. 1:48፤ 21:32፤ በፊልጵ. 2:15 ላይ እንደተገለጸው በአንድ ወቅት የሚኖሩ ሰዎችን በጠቅላላ በተለይም በአንድ ወቅት የሚኖሩ የአይሁድ ዘሮችን ያመለክታል።” (ደብልዩ ኢ ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ) “ከአንድ ቤተሰብ ወይም ከአንድ የዘር ግንድ የተገኙ ሰዎች፤ . . . በማቴ. 24:34፤ በማር. 13:30 እና በሉቃ. 1:48 ላይ እንደተገለጸው በአንድ ወቅት የሚኖሩ ሰዎችን በጠቅላላ . . . በተለይም ደግሞ በአንድ ወቅት የሚኖሩ የአይሁድ ዘሮችን ለመግለጽ ተሠርቶበታል።”—ጄ ኤች ታየርስ ግሪክ—ኢንግሊሽ ሌክስከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት
10. (ሀ) ሁለት ምሁራን ማቴዎስ 24:34ን ጠቅሰው የሰጡት ተመሳሳይ ፍቺ ምንድን ነው? (ለ) አንድ ሃይማኖታዊ መዝገበ ቃላትና አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ፍቺ የሚደግፉት እንዴት ነው?
10 ስለዚህ ቫይንም ሆኑ ታየር “ይህ ትውልድ” (ሂ ጄኒያ ሃውቴ) “በአንድ ወቅት የሚኖሩ ሰዎችን በጠቅላላ” እንደሚያመለክት ሲያብራሩ ማቴዎስ 24:34ን ጠቅሰዋል። ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት (1964) እንዲህ በማለት ለዚህ ማብራሪያ ድጋፍ ይሰጣል፦ “ኢየሱስ ‘ትውልድ’ በማለት የተጠቀመበት ቃል አጠቃላይ ዓላማውን ይገልጻል። ሁሉም ሰዎች ኃጢአት ለመሥራት አንድ ላይ ማበራቸውን ለመግለጽ አስቦ ነበር።” በእርግጥም በአሁኑ ጊዜ ያለው የዓለም ሥርዓት በሰፊው እንደሚያደርገው ሁሉ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የአይሁድ ሕዝብ ‘ኃጢአት ለመሥራት አንድ ላይ አብረው’ ነበር።c
11. (ሀ) በመሠረቱ ሂ ጄኒያ ሃውቴ የተባለው ቃል አጠቃቀም ምን እንደሆነ ለማወቅ የምንመራው በየትኛው ባለ ሥልጣን ነው? (ለ) ይህ ባለ ሥልጣን ይህን ቃል የተጠቀመበት እንዴት ነው?
11 በመሠረቱ ይህን ጉዳይ የሚመረምሩ ክርስቲያኖች አስተሳሰባቸውን የሚመሩት በመንፈስ አነሣሽነት የጻፉት የወንጌል ጸሐፊዎች የኢየሱስን ቃላት ለመዘገብ ሂ ጄኒያ ሃውቴ ወይም “ይህ ትውልድ” የሚሉትን የግሪክኛ ቃላት እንዴት እንደተጠቀመባቸው በማጤን ነው። ቃሉ በተደጋጋሚ ጊዜያት አሉታዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። ይህም በመሆኑ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችን “እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች” ካላቸው በኋላ “በዚህ ትውልድ” ላይ የገሃነም ፍርድ እንደሚበየን ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:33, 36) ይሁን እንጂ ይህ ፍርድ የሚበየነው በግብዞቹ ቀሳውስት ላይ ብቻ ነበርን? ፈጽሞ አልነበረም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በተደጋጋሚ ጊዜያት “ይህ ትውልድ” የሚሉትን ቃላት ሰፋ ባለ መንገድ በአንድ ዓይነት ሁኔታ ሲጠቀምባቸው ሰምተዋል። ይህ ሁኔታ ምን ነበር?
‘ይህ ክፉ ትውልድ’
12. ኢየሱስ ሐዋርያት በተገኙበት “ሕዝቡ”ን “ይህ ትውልድ” ብሎ ከጠራው ጋር ያያያዘው እንዴት ነው?
12 በ31 እዘአ የማለፍ በዓል ከተከበረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባደረገው ከፍተኛ አገልግሎት ወቅት “ለሕዝቡ” እንዲህ በማለት ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ ሰምተዋል፦ “ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፣ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ፦ እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል። ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፣ እነርሱም፦ ጋኔን አለበት አሉት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፣ እነርሱም፦ እነሆ፣ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጪ፣ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል።” ያንን ሥነ ምግባር የጎደለው “ሕዝብ” ምንም የሚያስደስተው ነገር አልነበረም!—ማቴዎስ 11:7, 16–19
13. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በተገኙበት ‘ይህ ክፉ ትውልድ’ በማለት የጠራቸውና ያወገዛቸው እነማንን ነው?
13 በ31 እዘአ መገባደጃ ላይ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ የሚያደርጉትን ሁለተኛ የስብከት ዘመቻቸውን ሲጀምሩ “ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ” ኢየሱስን ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። ኢየሱስ ለእነሱና በዚያ ለነበሩት ‘ሕዝብ’ እንዲህ አላቸው፦ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፣ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።. . . ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።” (ማቴዎስ 12:38–46) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው “ይህ ክፉ ትውልድ” የሃይማኖት መሪዎችን እና በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አማካኝነት የተፈጸመውን ምልክት በፍጹም ያላስተዋለውን ‘ሕዝብ’ ያቀፈ ነው።d
14. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ሰዱቃውያንንና ፈሪሳውያንን ምን ብሎ ሲያወግዛቸው ሰምተዋል?
14 በ32 እዘአ የማለፍ በዓልን ካከበሩ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ አውራጃ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ መጌዶል ሲመጡ ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን ኢየሱስ ምልክት እንዲያሳያቸው በድጋሜ ጠየቁት። እሱም እንደገና “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፣ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም” አላቸውና “ትቷቸው ሄደ።” (ማቴዎስ 16:1–4) እነዚህ ግብዝ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ ‘ይህ ክፉ ትውልድ’ በማለት ካወገዛቸው ‘ከሃዲ ሰዎች’ መካከል ይበልጥ ተነቃፊዎች ነበሩ።
15. ኢየሱስ በተአምር ከመለወጡ ጥቂት ቀደም ብሎና ከተለወጠ በኋላ እሱና ደቀ መዛሙርቱ ‘ከዚህ ትውልድ’ ምን ሁኔታዎች አጋጠማቸው?
15 ኢየሱስ በገሊላ ባደረገው አገልግሎት መጨረሻ ገደማ ሕዝቡንና ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ “በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅ ደግሞ . . . በእርሱ ያፍርበታል” አላቸው። (ማርቆስ 8:34, 38) ስለዚህ በዚያን ጊዜ የነበሩት ንስሐ ያልገቡ አይሁዳውያን በሙሉ ‘ይህ ዘማዊና ኃጢአተኛ ትውልድ’ የተባለውን እንደሚያካትቱ ግልጽ ነው። ኢየሱስ በተአምር ከተለወጠ ከጥቂት ቀናት በኋላ እሱና ደቀ መዛሙርቱ “ወደ ሕዝቡ ሲደርሱ” አንድ ሰው ልጁን እንዲፈውስለት ጠየቀው። ኢየሱስ “የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፣ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ?” አላቸው።—ማቴዎስ 17:14–17፤ ሉቃስ 9:37–41
16. (ሀ) ኢየሱስ በይሁዳ ውስጥ “ሕዝቡ”ን በድጋሜ ያወገዛቸው ምን ብሎ ነው? (ለ) “ይህ ትውልድ” ሰዎች ከፈጸሙት ወንጀል ሁሉ የከፋ ወንጀል የፈጸመው እንዴት ነው?
16 በ32 እዘአ የዳስ በዓል ከተደረገ በኋላ “ብዙ ሕዝብ” ወደ ኢየሱስ “በተሰበሰቡ ጊዜ” እንደገና “ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ምልክት ይፈልጋል፣ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም” በማለት ያወገዛቸው በይሁዳ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። (ሉቃስ 11:29) በመጨረሻም የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስን ለፍርድ ሲያቀርቡት ጲላጦስ ሊለቀው እንደፈለገ ገለጸ። የታሪክ መዝገቡ እንዲህ ይላል፦ “የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች . . . በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ። . . . ጲላጦስ፦ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው ሁሉም፦ ይሰቀል አሉ። ገዢውም ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን፦ ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ።” ያ “ክፉ ትውልድ” ኢየሱስ እንዲገደል ጠየቀ።—ማቴዎስ 27:20–25
17. “ከዚህ ጠማማ ትውልድ” መካከል አንዳንዶቹ ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት ለሰበከላቸው መልእክት አዎንታዊ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነበር?
17 በመሆኑም በሃይማኖታዊ መሪዎቹ የተገፋፋው “የማያምን ጠማማ ትውልድ” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመግደል ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ኢየሱስ ከተገደለ ከአምሳ ቀናት በኋላ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉና በልዩ ልዩ ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ። ይህን ድምፅ የሰሙ ብዙ ‘ሰዎች’ ወደ እነሱ ሲመጡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሕዝቡን “አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሆይ” ብሎ በመጥራት ንግግሩን ከፈተና “እርሱንም [ኢየሱስን] በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት” አላቸው። ከእነዚህ አድማጮች ውስጥ አንዳንዶቹ ምን ምላሽ ሰጡ? “ልባቸው ተነካ።” ከዚያም ጴጥሮስ ንስሐ እንዲገቡ ጠየቃቸው። “በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና፦ ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው።” ለዚህ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ‘ቃሉን ተቀበሉና ተጠመቁ።’—ሥራ 2:6, 14, 23, 37, 40, 41
“ይህ ትውልድ” ተለይቶ ታወቀ
18. ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ጊዜያት ይጠቀምበት የነበረው የትኛውን ነገር ለማመልከት ነበር?
18 ታዲያ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ባሉበት በተደጋጋሚ ጊዜያት ይጠቅሰው የነበረው “ትውልድ” የትኛው ነው? “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ብሎ ሲናገር የተረዱት ነገር ምን ነበር? ኢየሱስ ከዚህ በፊት “ይህ ትውልድ” በሚሉት ቃላት ሲጠቀም ከነበረው ሐሳብ የተለየ ሐሳብ እንዳልገለጸ የተረጋገጠ ነው። እነዚህን ቃላት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ጊዜያት የተጠቀመባቸው የአይሁድ ብሔር አባላት የነበሩትን የዘመኑን ሰዎችና ‘ዕውር መሪዎቻቸውን’ ለማመልከት ነበር። (ማቴዎስ 15:14) “ይህ ትውልድ” ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረው መከራ ሁሉ ከደረሰበት በኋላ በኢየሩሳሌም ላይ በተከሰተው ታይቶ የማይታወቅ “ታላቅ መከራ” አለፈ።—ማቴዎስ 24:21, 34
19. ‘በሰማይና ምድር’ የተመሰለው የአይሁድ ሥርዓት ያለፈው መቼና እንዴት ባለ ሁኔታ ነው?
19 ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአይሁድ ሕዝቦች ላይ እየፈረደ ነበር። ይሖዋ በክርስቶስ በኩል ባዘጋጀው የምሕረት ዝግጅት ያመኑና ንስሐ የገቡ ሰዎች ከዚያ “ታላቅ መከራ” ድነዋል። ኢየሱስ የተናገራቸው ትንቢቶች በሙሉ በትክክል ተፈጽመዋል። በዚያን ጊዜ የአይሁድ ሥርዓት “ሰማይና ምድር” የሆነው ጠቅላላው ብሔር ከሃይማኖታዊ መሪዎቹና ከክፉ ኅብረተሰቡ ጋር አለፈ። ይሖዋ ፍርዱን አስፈጸመ!—ማቴዎስ 24:35፤ ከ2 ጴጥሮስ 3:7 ጋር አወዳድር።
20. ሁሉም ክርስቲያኖች የተሰጣቸው ወቅታዊ የሆነ አጣዳፊ የማስጠንቀቂያ ምክር የትኛው ነው?
20 በኢየሱስ ትንቢታዊ ቃላት ላይ ትኩረት ያደረጉ አይሁዳውያን ደኅንነታቸው የተመካው የአንድ “ትውልድ” ርዝመትን ወይም አንዳንድ “ወራትንና ዘመናትን” ለማስላት በመሞከራቸው ሳይሆን በጊዜያቸው ከነበረው ክፉ ትውልድ በመለየታቸው እና የአምላክን ፈቃድ በቅንዓት በማድረጋቸው ላይ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። የኢየሱስ ትንቢት የመጨረሻ ቃላት በከፍተኛ ደረጃ የሚፈጸሙት በዘመናችን ቢሆንም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ” የሚለውን ምክር መቀበል ነበረባቸው።—ሉቃስ 21:32–36፤ ሥራ 1:6–8
21. በቅርቡ በድንገት ምን ሁኔታ እንደሚፈጸም ልንጠብቅ እንችላለን?
21 በአሁኑ ጊዜ “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ . . . እጅግም ፈጥኗል።” (ሶፎንያስ 1:14–18፤ ኢሳይያስ 13:9, 13) በድንገት፣ ይሖዋ ራሱ አስቀድሞ በወሰነው ‘ቀንና ሰዓት’ በዓለም ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና የንግድ ተቋማትም ሆነ የዘመናችን “ክፉና ዘማዊ ትውልድ” በሆኑት በሥነ ሥርዓት በማይመላለሱ ሰዎች ላይ ቁጣው ይፈሳል። (ማቴዎስ 12:39፤ 24:36፤ ራእይ 7:1–3, 9, 14) ከ“ታላቁ መከራ” መዳን የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕሳችን ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ ወደፊት ስለሚኖረን ታላቅ ተስፋ ይነግረናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ይህን ትንቢት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት እባክህ በየካቲት 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 14, 15 ላይ የሚገኘውን ሠንጠረዥ ተመልከት።
b ‘የሳምንታት’ ዓመታትን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 130–2 ተመ ልከት።
c አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች በማቴዎስ 24:34 ላይ የሚገኙትን ሂ ጄኒያ ሃውቴ የተባሉትን ቃላት እንደሚከተለው ተርጉመዋቸዋል፦ “እነዚህ ሰዎች” (ዘ ሆሊ ባይብል ኢን ዘ ላንግዊጅ ኦቭ ቱዴይ [1976]፣ በደብልዩ ኤፍ ቤክ)፤ “ይህ ብሔር” (ዘ ኒው ቴስታመንት—አን ኤክስፓንድድ ትራንስሌሽን [1961]፣ በኬ ኤስ ውስት)፤ “ይህ ሕዝብ” (ጁዊሽ ኒው ቴስታመንት [1979] በዲ ኤች ስተርን)
d ይህ ከሃዲ “ሕዝብ” ኩራተኞቹ የሃይማኖት መሪዎች ከማይተባበሯቸው ኢየሱስ ግን ‘ካዘነላቸው’ በተለምዶ አምሃሬትስ ወይም “የምድር ሰዎች” ይባሉ ከነበሩት ሰዎች መካከል አይደለም።—ማቴዎስ 9:36፤ ዮሐንስ 7:49
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ከዳንኤል 9:24–27 ፍጻሜ ምን ልንማር እንችላለን?
◻ በአሁኑ ጊዜ ያሉ የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች “ይህ ትውልድ” የሚሉትን ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ በተጠቀመበት መንገድ የፈቱት እንዴት ነው?
◻ ኢየሱስ “ትውልድ” በሚለው ቃል በተደጋጋሚ ጊዜያት የተጠቀመው በምን መንገድ ነው?
◻ ማቴዎስ 24:34, 35 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸመው እንዴት ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ “ይህን ትውልድ” ከማይታዘዙ ልጆች ቡድን ጋር አወዳድሮታል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በክፉው የአይሁድ ሥርዓት ላይ ፍርድ የሚሰጥበትን ሰዓት በቅድሚያ ያወቀው ይሖዋ ብቻ ነበር