የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 5/1 ገጽ 8-13
  • “ይህ ሊሆን ግድ ነውና”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ይህ ሊሆን ግድ ነውና”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በደጅ የቀረበ አሳዛኝ ፍጻሜ
  • በዘመኑ የሚኖሩት ሰዎች መከራውን ያያሉ
  • ሌላ ፍጻሜ ይመጣል
  • ወደፊት የሚሆን ፍርድ!
  • አምላክ እርምጃ በሚወስድበት ወቅት ከጥፋት ትድን ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • የመገኘትህ ምልክት ምን ይሆናል?’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ‘ከክፉ ትውልድ’ መዳን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • “ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው?”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 5/1 ገጽ 8-13

“ይህ ሊሆን ግድ ነውና”

“ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው:-. . . ይህ ሊሆን ግድ ነውና . . . ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።”—⁠ማቴዎስ 24:​4-6

1. ትኩረታችንን ሊስብ የሚገባው ጉዳይ የትኛው ነው?

መቼም ስለ ሕይወትህና ወደፊት ስለሚገጥምህ ነገር እንደምታስብ ምንም አያጠራጥርም። እንግዲያው በ1877 የሲ ቲ ራስልን ትኩረት ስቦ የነበረው ጉዳይ የአንተንም ትኩረት ሊስብ ይገባል። ከጊዜ በኋላ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን የመሠረተው ራስል ዚ ኦብጀክት ኤንድ ማነር ኦቭ አወር ሎርድስ ሪተርን (እንግሊዝኛ) የተባለ ቡክሌት አሳትሞ ነበር። ይህ ባለ 64 ገጽ ቡክሌት ስለ ኢየሱስ መመለስ ወይም ወደፊት መምጣት የሚያወሳ ነበር። (ዮሐንስ 14:​3) በአንድ ወቅት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሳሉ ሐዋርያቱ የእሱን መመለስ በተመለከተ ጥያቄ አቅርበው ነበር:- “ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና [“የመገኘትህና፣” NW] የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?”​—⁠ማቴዎስ 24:​3

2. ኢየሱስ ስለተነበየው ነገር እርስ በርስ የሚጋጩ ብዙ አመለካከቶች የኖሩት ለምንድን ነው?

2 ኢየሱስ የሰጠው መልስ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ትርጉሙንስ አስተውለኸዋል? መልሱ በሦስቱ የወንጌል መጽሐፎች ውስጥ ይገኛል። ፕሮፌሰር ዲ ኤ ካርሰን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “የማቴዎስ 24ን እንዲሁም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን የማርቆስ 13 እና የሉቃስ 21ን ያክል በአተረጓጎም ረገድ ውዝግብ የሚያስነሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች የሉም ለማለት ይቻላል።” ከዚያም እርስ በርስ ከሚጋጩት ሰብዓዊ አመለካከቶች ጎን የሚፈረጀውን የራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። ላለፉት መቶ ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት እነዚህን የመሳሰሉ አመለካከቶች ሰዎች እምነት የጎደላቸው መሆኑን አንጸባርቀዋል። እነዚህን አስተያየቶች የሚሰነዝሩ ሰዎች በወንጌሎች ውስጥ ተመዝግቦ የምናገኘው ሐሳብ ኢየሱስ የተናገረው አይደለም፣ እሱ የተናገራቸው ነገሮች ከጊዜ በኋላ ተበርዘዋል ወይም የተነበየው ነገር ሳይፈጸም ቀርቷል የሚሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት ውጤት የሆኑ አመለካከቶች አሏቸው። እንዲያውም አንድ ተንታኝ የማርቆስን ወንጌል ‘ከማሃያና-ቡዲስት ፍልስፍና አንጻር’ ለመመልከት ሞክሮ ነበር!

3. የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ትንቢት እንዴት ይመለከቱታል?

3 ከዚህ በተቃራኒ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ከመሞቱ ከሦስት ቀናት በፊት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሳለ ለአራት ሐዋርያቱ የነገራቸውን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛና ተዓማኒ መሆኑን ያምናሉ። የአምላክ ሕዝቦች ኢየሱስ በዚያ ቦታ ላይ ስለ ሰጠው ትንቢት ያላቸው ማስተዋል ከሲ ቲ ራስል ዘመን አንስቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄዷል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እንኳ መጠበቂያ ግንብ ስለዚህ ትንቢት ያላቸውን አመለካከት ይበልጥ ግልጽ አድርጎላቸዋል። ይህን እውቀት ቀስመሃል? በሕይወትህስ ላይ ምን ተጽእኖ አሳድሯል?a እስቲ እንደገና እንመርምረው።

በደጅ የቀረበ አሳዛኝ ፍጻሜ

4. ሐዋርያቱ ኢየሱስን ስለ ወደፊቱ ጊዜ የጠየቁት ለምን ሊሆን ይችላል?

4 ሐዋርያቱ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ያውቁ ነበር። ስለዚህ ስለ ሞቱ፣ ስለ ትንሣኤውና ስለ መመለሱ ሲናገር ሲሰሙት ‘ኢየሱስ የሚሞትና የሚሄድ ከሆነ መሲሑ ያከናውናቸዋል ተብለው የሚጠበቁትን አስደናቂ ነገሮች እንዴት ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል?’ ብለው ሳያስቡ አይቀርም። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ቤተ መቅደሷ መጥፋት ተናግሯል። ሐዋርያቱ ‘ይህ የሚሆነው መቼና እንዴት ነው?’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። እነዚህን ነገሮች ማስተዋል ስለፈለጉ ሐዋርያቱ እንዲህ ሲሉ ጠየቁ:- “ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው?”​—⁠ማርቆስ 13:​4፤ ማቴዎስ 16:​21, 27, 28፤ 23:​37–24:​2

5. ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?

5 ኢየሱስ ጦርነት፣ ረሃብ፣ ቸነፈርና የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሚኖር፣ ክርስቲያኖች እንደሚጠሉና እንደሚሰደዱ፣ ሐሰተኛ መሲሖች እንደሚነሱ እንዲሁም የአምላክ መንግሥት ምሥራች በስፋት እንደሚሰበክ ተንብዮአል። መጨረሻው የሚመጣው ከዚህ በኋላ ነበር። (ማቴዎስ 24:​4-14፤ ማርቆስ 13:​5-13፤ ሉቃስ 21:​8-19) ኢየሱስ ይህን የተናገረው በ33 እዘአ መጀመሪያ ላይ ነበር። ንቁ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ አስቀድመው የተተነበዩት ነገሮች በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት ተጨባጭ በሆነ መንገድ እየተፈጸሙ መሆናቸውን ተገንዝበው ነበር። አዎን፣ ምልክቱ ከ66-70 እዘአ ባለው ጊዜ ውስጥ የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት በሮማውያን እጅ መደምደሙን አስከትሎ በዚያን ጊዜ ፍጻሜውን ማግኘቱን ታሪክ ያረጋግጣል። ይህ የሆነው እንዴት ነበር?

6. በ66 እዘአ በሮማውያንና በአይሁዶች መካከል ምን ተከስቶ ነበር?

6 በ66 እዘአ በሞቃታማው የአይሁዳውያን የበጋ ወቅት ላይ ዜለትስ በመባል የሚታወቁት ቀናኢ አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ አቅራቢያ መሽገው በሮማውያን ጠባቂዎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው በሌሎች አካባቢዎችም ዓመፅ እንዲቀሰቀስ አድርጓል። ፕሮፌሰር ሃይንሪሽ ግሬትስ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ጁውስ በተባለው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “የሮማውያንን ሠራዊት ክብር የማስጠበቅ ኃላፊነት የነበረው . . . የሶርያው ገዥ ሴስቲየስ ጋለስ በዙሪያው በመስፋፋት ላይ የነበረውን ዓመፅ በቸልታ ሊያልፈው አልፈለገም። ሠራዊቱን ሰበሰበ፤ በአጎራባች አገሮች የሚገኙ ገዥዎችም በፈቃደኝነት ወታደሮቻቸውን ላኩ።” ይህ 30,000 ሰዎችን ያቀፈ ጦር ኢየሩሳሌምን ከበበ። አይሁዳውያኑ ጥቂት ከተዋጉ በኋላ አፈግፍገው በቤተ መቅደሱ አቅራቢያ በሚገኙ ቅጥሮች ጀርባ መሸጉ። “ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሮማውያኑ ግንቦቹን ለማፍረስ ቢጥሩም ከአይሁዳውያኑ የሚወረወሩት ፍላጻዎች በተደጋጋሚ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ያስገድዷቸው ነበር። በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት በሰሜን በኩል የሚገኘውን ቅጥር በከፊል መሰርሰር የቻሉት በስድስተኛው ቀን ነበር።”

7. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለነገሮች የነበራቸው አመለካከት ከአብዛኞቹ አይሁዶች የተለየ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?

7 አምላክ እነሱንም ሆነ ቅድስት ከተማቸውን ይጠብቃል ብለው ያስቡ የነበሩት አይሁዳውያን ምን ያህል ግራ እንደሚጋቡ አስቡት! የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሩሳሌም ጥፋት እንደሚጠብቃት ቀደም ሲል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተንብዮ ነበር:- “ወራት ይመጣብሻልና፣ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፣ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፣ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።” (ሉቃስ 19:​43, 44) ታዲያ በ66 እዘአ በኢየሩሳሌም ውስጥ ይገኙ የነበሩት ክርስቲያኖች እጣ ፈንታ ሞት ይሆናል ማለት ነው?

8. ኢየሱስ ምን አሳዛኝ መከራ እንደሚመጣ ተንብዮ ነበር? ወራቱ ያጥሩላቸዋል የተባሉት ‘ምርጦችስ’ እነማን ነበሩ?

8 ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ለሐዋርያቱ መልስ በሰጠበት ጊዜ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፣ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።” (ማርቆስ 13:​19, 20፤ ማቴዎስ 24:​21, 22) ስለዚህ ቀናቱ እንዲያ​ጥሩ ይደረጋሉ፤ ‘የተመረጡትም’ ይድናሉ። እነዚህ እነማን ናቸው? ይሖዋን እናመልካለን ቢሉም ልጁን ግን ያልተቀበሉትን ዓመፀኛ አይሁዳውያን እንደማያመለክት የተረጋገጠ ነው። (ዮሐንስ 19:​1-7፤ ሥራ 2:​22, 23, 36) በዚያን ወቅት እውነተኞቹ ምርጦች ኢየሱስ መሲሕና አዳኝ መሆኑን ያመኑ አይሁዶችና አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ነበሩ። አምላክ የመረጠው እንዲህ ያሉትን ሲሆን በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት እነሱን አዲስ መንፈሳዊ ብሔር ማለትም ‘የአምላክ እስራኤል’ አድርጎ አደራጃቸው።​—⁠ገላትያ 6:​16፤ ሉቃስ 18:​7፤ ሥራ 10:​34-45፤ 1 ጴጥሮስ 2:​9

9, 10. ሮማውያን ጥቃት የሰነዘሩባቸው ወራት ‘ያጠሩት’ እንዴት ነበር? ከምንስ ውጤት ጋር?

9 ታዲያ ወራቱ ‘እንዲያጥሩ’ ተደርጎ በኢየሩሳሌም የሚገኙ የተመረጡ ቅቡዓን ድነዋልን? ፕሮፌሰር ግሬትስ እንዲህ ይላሉ:- “[ሴስቲየስ ጋለስ] ከጀብደኛ አቀንቃኞች ጋር ውጊያ መቀጠሉ እንዲሁም ለሠራዊቱ ስንቅና ትጥቅ እንዳይደርስ እንቅፋት ሊሆን የሚችለው የበልግ ዝናብ ሊጀምር በተቃረበበት ወቅት ረዥም ጊዜ የሚወስድ ዘመቻ ማካሄዱ ጥሩ እንደማይሆን አሰበ። ስለሆነም ወደ ኋላ ማፈግፈጉ ብልህነት እንደሆነ ሳያስብ አልቀረም።” ሴስቲየስ ጋለስ ያሰበው ነገር ምንም ይሁን ምን የሮማ ሠራዊት ከተማዋን ጥሎ ወደ ኋላ ያፈገፈገ ሲሆን ያሳድዱት የነበሩት አይሁዳውያንም ከፍተኛ ጉዳት አድርሰውበታል።

10 ይህ ያልተጠበቀ የሮማውያኑ ማፈግፈግ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ የነበረው በኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኙ ‘ሥጋ የለበሱ’ ማለትም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲድኑ አስችሏል። ታሪካዊ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ክርስቲያኖች ይህችን አጋጣሚ ሲያገኙ አገሩን ጥለው ሸሹ። አምላክ ወደፊት የሚሆነውን የማወቅም ሆነ አምላኪዎቹን በሕይወት የማትረፍ ችሎታ እንዳለው የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው! ይሁንና በኢየሩሳሌምና በይሁዳ መኖራቸውን የቀጠሉት እነዚያ የማያምኑ አይሁዳውያን ምን ደረሰባቸው?

በዘመኑ የሚኖሩት ሰዎች መከራውን ያያሉ

11. ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ብሎ ስለጠቀሰው የሰዎች ቡድን ምን ተናግሯል?

11 ብዙ አይሁዶች ቤተ መቅደሱን ማዕከል ያደረገው የአምልኮ ሥርዓታቸው ላልተወሰነ ጊዜ ይቀጥላል ብለው ያስቡ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቊጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም።”​—⁠ማቴዎስ 24:​32-35 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

12, 13. ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ብሎ ሲጠቅስ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት ተረድተውት ሊሆን ይችላል?

12 ከ66 እዘአ ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ክርስቲያኖች ድርብ ተፈጻሚነት ያለውን የዚህን ምልክት የመጀመሪያ ፍጻሜ ማለትም ጦርነት፣ ረሃብና የመንግሥቱ ምሥራች በስፋት መሰበኩን ሳይቀር ተመልክተው ነበር። (ሥራ 11:​28፤ ቆላስይስ 1:​23) ይሁንና መጨረሻው የሚመጣው መቼ ነው? ኢየሱስ “ይህ ትውልድ [በግሪክኛ ዬኔአ] አያልፍም” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ሃይማኖታዊ መሪዎችን ጨምሮ በዚያን ዘመን ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ተቃዋሚ ወገኖችን “ክፉና አመንዝራ ትውልድ” ብሎ ይጠራቸው ነበር። (ማቴዎስ 11:​16፤ 12:​39, 45፤ 16:​4፤ 17:​17፤ 23:​36) ስለዚህ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በድጋሚ “ይህ ትውልድ” ሲል በታሪክ ዘመናት በሙሉ የነበረውን ጠቅላላውን የአይሁድ ብሔር ወይም “የተመረጠ ትውልድ” ተብለው የተጠሩትን ተከታዮቹን ማመልከቱ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:​9) ወይም ደግሞ ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” የተወሰነ የጊዜ ርዝማኔን ያመለክታል ማለቱ አልነበረም።

13 ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ በአእምሮው ይዞ የነበረው የሰጠው ምልክት ሲፈጸም የሚመለከቱትን ተቃዋሚ አይሁዶች ነበር። በሉቃስ 21:​32 ላይ “ይህ ትውልድ” ተብሎ የተጠቀሰውን ሐሳብ በሚመለከት ፕሮፌሰር ጆኤል ቢ ግሪን እንዲህ ብለዋል:- “በሦስተኛው ወንጌል ላይ የሚገኘው ‘ይህ ትውልድ’ የሚለው ሐረግ (እና ሌሎች ተመሳሳይ መግለጫዎች) አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው የአምላክን ዓላማ የሚቃወመውን የሰዎች ክፍል ነው። . . . አውቀውና ሆነ ብለው ለመለኮታዊው ዓላማ ጀርባቸውን የሚሰጡ ሰዎችን [ያመለክታል።]”b

14. በዚያን ጊዜ የነበረው “ትውልድ” ምን ደረሰበት? ሆኖም ክርስቲያኖች ያጋጠማቸው ነገር የተለየ የሆነው እንዴት ነበር?

14 የምልክቱን መፈጸም ለማስተዋል የሚችልበት አጋጣሚ የነበረው የተቃዋሚ አይሁዶች ክፉ ትውልድ መጨረሻውን ማየት ነበረበት። (ማቴዎስ 24:​6, 13, 14) ደግሞም አይቷል! በ70 እዘአ በንጉሠ ነገሥት ቬስፓሲያን ልጅ በቲቶ የሚመራው የሮማ ሠራዊት ተመልሶ መጣ። አሁንም እዚያው ከተማዋ ውስጥ እንዳሉ የታገቱት አይሁዶች የደረሰባቸው መከራ ለማመን የሚያዳግት ነበር።c የዓይን ምሥክር የነበረው ፍላቪየስ ጆሴፈስ ሪፖርት እንዳደረገው ሮማውያን ከተማዋን በደመሰሱ ጊዜ ወደ 1,100,000 አይሁዶች የሞቱ ሲሆን ወደ 100,000 የሚጠጉ ደግሞ በምርኮ ተወስደዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ብዙም ሳይቆዩ በረሃብ ወይም በሮማውያን ቲያትር ቤቶች ውስጥ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ አልቀዋል። በእርግጥም ከ66-70 እዘአ የነበረው መከራ ኢየሩሳሌምና የአይሁድ ሥርዓት እስከዚያን ጊዜ ድረስ ካጋጠማቸውም ሆነ ወደፊት ሊያጋጥማቸው ከሚችለው መከራ እጅግ የከፋ ነበር። የኢየሱስን ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ሰምተው በ66 እዘአ የሮማ ሠራዊት ከሄደ በኋላ ኢየሩሳሌምን ትተው ለወጡት ክርስቲያኖች ግን ሁኔታው ምንኛ የተለየ ነበር! ‘የተመረጡት’ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ70 እዘአ ከደረሰው ጥፋት ‘ድነዋል’ ወይም ደኅንነታቸው ተጠብቋል።​—⁠ማቴዎስ 24:​16, 22

ሌላ ፍጻሜ ይመጣል

15. የኢየሱስ ትንቢት በ70 እዘአ ከሆነው የበለጠ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?

15 ይሁን እንጂ ሁኔታው በዚህ አያበቃም። ቀደም ሲል ኢየሱስ ከተማዋ ከወደመች በኋላ በይሖዋ ስም እንደሚመጣ አመልክቶ ነበር። (ማቴዎስ 23:​38, 39፤ 24:​2) ከዚያም ይህን ሐሳብ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በተናገረው ትንቢት ይበልጥ ግልጽ አድርጎታል። መጪውን “ታላቅ መከራ” ጠቅሶ ከጊዜ በኋላ ሐሰተኛ ክርስቶሶች እንደሚነሱና ኢየሩሳሌም ለረዥም ዘመን በአሕዛብ የተረገጠች እንደምትሆን ገልጿል። (ማቴዎስ 24:​21, 23-28፤ ሉቃስ 21:​24) ታዲያ ሌላ የሚበልጥ ፍጻሜ ይመጣ ይሆን? እውነታዎቹ አዎን፣ የሚል መልስ ይሰጣሉ። ራእይ 6:​2-8ን (በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው መከራ በኋላ የተጻፈ) ከማቴዎስ 24:​6-8​ና ከሉቃስ 21:​10, 11 ጋር ስናወዳድር መጠነ ሰፊ የሆነ ጦርነት፣ የምግብ እጥረትና መቅሰፍት እንደሚከሰት እንገነዘባለን። እነዚህ የኢየሱስ ቃላት አንደኛው የዓለም ጦርነት በ1914 ከፈነዳ ጀምሮ ከፍተኛ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ቆይተዋል።

16-18. ወደፊት ምን ነገር ይሆናል ብለን እንጠብቃለን?

16 የይሖዋ ምሥክሮች ላለፉት አሥርተ ዓመታት ምልክቱ በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜ ማግኘቱ ወደፊት “ታላቅ መከራ” እንደሚኖር የሚያረጋግጥ መሆኑን ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በአሁኑ ጊዜ ያለው ክፉ “ትውልድ” ይህን መከራ ያያል። በ66 እዘአ ጋለስ የሰነዘረው ጥቃት በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰውን መከራ እንዳስጀመረ ሁሉ አሁንም እንደገና መክፈቻ የሚሆን ነገር (በሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት) የሚኖር ይመስላል።d ከዚያም በውል የማይታወቅ የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ በ70 እዘአ ከሆነው ጋር የሚመጣጠን ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ጥፋትን አስከትሎ መጨረሻው ይመጣል።

17 ከፊታችን ያለውን መከራ አስመልክቶ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ [ከሐሰት ሃይማኖት ጥፋት] ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፣ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።”​—⁠ማቴዎስ 24:​29, 30

18 በመሆኑም ኢየሱስ ራሱ “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ” በሰማይ ላይ የሚታዩ አንዳንድ ክስተቶች እንደሚኖሩ ተናግሯል። (ከኢዩኤል 2:​28-32፤ 3:​15 ጋር አወዳድር።) ይህም ዓመፀኛ የሆኑ የሰው ልጆችን በጣም ስለሚያስደነግጥና ስለሚያሸብር “ዋይ ዋይ ይላሉ።” ብዙዎች “ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ።” ይሁን እንጂ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ሁኔታ ከዚህ የተለየ ነው! ‘መዳናቸው ስለቀረበ ራሳቸውን ያነሳሉ።’​—⁠ሉቃስ 21:​25, 26, 28

ወደፊት የሚሆን ፍርድ!

19. የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ የሚፈጸምበትን ጊዜ ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው?

19 ማቴዎስ 24:​29-31 (1) የሰው ልጅ እንደሚመጣ፣ (2) የሚመጣውም በታላቅ ክብር እንደሚሆን፣ (3) መላእክት ከእሱ ጋር እንደሚሆኑና (4) የምድር አሕዛብ ሁሉ እንደሚያዩት እንደሚተነብይ ልብ በል። ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች በተናገረው ምሳሌ ላይ እነዚህን ገጽታዎች በድጋሚ ገልጿቸዋል። (ማቴዎስ 25:​31-46) በመሆኑም ይህ ምሳሌ መከራው መጀመሩን የሚያሳዩ ነገሮች ከታዩ በኋላ ኢየሱስ ከመላእክቱ ጋር ስለሚመጣበትና በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ስለሚፈርድበት ጊዜ የሚያወሳ ነው ብለን ልንደመድም እንችላለን። (ዮሐንስ 5:​22፤ ሥራ 17:​31፤ ከ1 ነገሥት 7:​7፤ ዳንኤል 7:​10, 13, 14, 22, 26፤ ማቴዎስ 19:​28 ጋር አወዳድር።) ፍርድ የሚሰጠው ለእነማን ነው? ከምንስ ውጤት ጋር? ኢየሱስ በሰማያዊው ዙፋኑ ፊት የተሰበሰቡ ያህል በሁሉም አሕዛብ ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ ምሳሌው ያሳያል።

20, 21. (ሀ) በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት በጎች ምን ይጠብቃቸዋል? (ለ) የፍየሎቹ የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

20 በግ መሰል ወንዶችና ሴቶች የኢየሱስን ሞገስ በማግኘት ተለይተው በቀኙ ይቆማሉ። ለምን? ምክንያቱም በክርስቶስ ሰማያዊ መንግሥት ተካፋዮች ለሚሆኑት የተቀቡ ክርስቲያን ወንድሞቹ መልካም ለማድረግ የነበራቸውን አጋጣሚ በሚገባ ስለ ተጠቀሙበት ነው። (ዳንኤል 7:​27፤ ዕብራውያን 2:​9–3:​1) በሚልዮን የሚቆጠሩ በግ መሰል ክርስቲያኖች ከምሳሌው ጋር በመስማማት ለኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞች እውቅና በመስጠት እነሱን ሲደግፉ ቆይተዋል። በዚህ ምክንያት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት የማለፍና ከዚያም በአምላክ መንግሥት ምድራዊ ግዛት ላይ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋ አላቸው።​—⁠ራእይ 7:​9, 14፤ 21:​3, 4፤ ዮሐንስ 10:​16

21 ፍየሎቹ የሚጠብቃቸው ነገር ከዚህ ምንኛ የተለየ ነው! በማቴዎስ 24:​30 ላይ ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ “ዋይ ዋይ” ይላሉ ተብሏል። የመንግሥቱን ምሥራች ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆን፣ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት በመቃወምና የሚያልፈውን ዓለም የሙጥኝ በማለት ባስመዘገቡት ታሪክ ምክንያት ዋይ ዋይ ሊሉ ይገባቸዋል። (ማቴዎስ 10:​16-18፤ 1 ዮሐንስ 2:​15-17) ፍየሎቹ እነማን መሆናቸውን የሚወስነው ኢየሱስ እንጂ በምድር ላይ የሚገኙት ደቀ መዛሙርቱ አይደሉም። ስለ እነሱ ሲናገር “እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት . . . ይሄዳሉ” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 25:​46

22. ይበልጥ ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባው የትኛው የኢየሱስ ትንቢት ክፍል ነው?

22 በማቴዎስ ምዕራፍ 24ና 25 ላይ ስላለው ትንቢት ያገኘነው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ማስተዋል በጣም የሚያስደስት ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ‘በተቀደሰው ስፍራ ስለ ቆመው የጥፋት ርኲሰት’ የሚናገረው የኢየሱስ ትንቢት ክፍል ትኩረታችንን የሚሻ ነው። ኢየሱስ ይህን ጉዳይ እንዲያስተውሉና እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁዎች እንዲሆኑ ተከታዮቹን አሳስቧል። (ማቴዎስ 24:​15, 16) ይህ “ርኩሰት” ምንድን ነው? በተቀደሰው ስፍራ የሚቆመው መቼ ነው? የአሁኑና የወደፊቱ ሕይወታችን በዚህ ጉዳይ የሚነካው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ማብራሪያ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የየካቲት 15, 1994፤ የጥቅምት 15 እና የኅዳር 1, 1995፤ እንዲሁም የነሐሴ 15, 1996ን መጠበቂያ ግንብ ቅጂዎች የጥናት ርዕሶችን ተመልከት።

b ብሪታኒያዊው ምሁር ጂ አር ቢዝሊ-መርኢ እንዲህ ብለዋል:- “‘ይህ ትውልድ’ የሚለው ሐረግ በትርጉም ረገድ ምንም ዓይነት ችግር ሊፈጥር አይገባም። በጥንቱ ግሪክ ዬኔአ ማለት ልደት፣ ተወላጆች ብሎም ዘር የሚል ትርጉም ስላለው [በግሪክኛው ሴፕቱጀንት] ላይ አብዛኛውን ጊዜ . . . እድሜ፣ የሰው ልጅ እድሜ ወይም በአንድ ወቅት የሚኖሩ ሰዎችን ትውልድ የሚያመለክተውን ዶር የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል ለመተርጎም አገልግሏል። . . . ኢየሱስ ተናግሯቸዋል በሚባሉ ሐሳቦች ላይ ቃሉ ድርብ ትርጉም የሚያስተላልፍ ሲሆን በአንድ በኩል በዘመኑ የነበሩ ሰዎችን ለማመልከት ብቻ የተሠራበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ነቀፋ አዘል መሆኑን የሚያሳይ ነበር።”

c ፕሮፌሰር ግሬትስ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ጁውስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አንዳንድ ጊዜ ሮማውያን በቀን 500 እስረኞችን ይሰቅሉ ነበር ብለዋል። ሌሎች ምርኮኛ አይሁዶች ደግሞ እጃቸውን ከተቆረጡ በኋላ ወደ ከተማዋ ይላኩ ነበር። እዚያስ ምን ዓይነት ሁኔታ ሰፍኖ ነበር? “ገንዘብ ዋጋውን በማጣቱ ዳቦ መግዛት አይችልም ነበር። ሰዎች እጅግ አስጸያፊ ለሆነ ምግብ፣ እፍኝ ለማይሞላ የሣር ድርቆሽ፣ ለቁራጭ ቆዳ ወይም ለውሾች የሚጣል ትርፍራፊ ለማግኘት በየመንገዱ ይሻሙ ነበር። . . . በየሜዳው የሚረፈረፈው አስከሬን ሞቃታማውን የበጋ አየር በተላላፊ በሽታዎች በክሎት የነበረ ሲሆን ሕዝቡም በበሽታ፣ በረሃብና በሰይፍ አለቀ።”

d የሚቀጥለው ርዕስ ይህን የወደፊቱን መከራ ገጽታ ያብራራል።

ታስታውሳለህ?

◻ ማቴዎስ 24:​4-14 በመጀመሪያ መቶ ዘመን ምን ተፈጻሚነት ነበረው?

◻ በማቴዎስ 24:​21, 22 ላይ በተተነበየው መሠረት በሐዋርያት ዘመን ወራቱ ያጠሩትና ሥጋ የለበሱ የዳኑት እንዴት ነበር?

◻ በማቴዎስ 24:​34 ላይ የተጠቀሰውን “ትውልድ” ለይቶ የሚያሳውቀው ምንድን ነው?

◻ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ የተነገረው ትንቢት ሌላ ከፍተኛ ፍጻሜ እንደሚኖረው እንዴት እናውቃለን?

◻ የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ ተፈጻሚነቱን የሚያገኘው መቼና እንዴት ይሆናል?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሩሳሌም ጥፋት ወቅት የተጋዘውን ምርኮ የሚያሳይ በሮም ከሚገኘው የቲቶ ቅስት የተወሰደ ምስል

[ምንጭ]

Soprintendenza Archeologica di Roma

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ