የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መከታተልን ጨርሶ አያበረታታምን?
“ትምህርት የሚንቅ አላዋቂ ብቻ ነው።”—ፑብሊልዩስ ሱሩስ፣ ሞራል ሴይንግስ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከዘአበ
መጽሐፍ ቅዱስ “ተግባራዊ ጥበብንና የማሰብ ችሎታን ጠብቅ” በማለት አጥብቆ ይመክረናል። (ምሳሌ 3:21 NW) የእውቀት አምላክ የሆነው ይሖዋ አገልጋዮቹ የተማሩ እንዲሆኑ ይፈልጋል። (1 ሳሙኤል 2:3፤ ምሳሌ 1:5, 22) ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አነጋገሮች ጥያቄ ያስነሱ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ የቀሰመውን ከፍተኛ ትምህርት ጨምሮ ቀደም ሲል የተከታተለውን ነገር በማስመልከት ሲናገር “ሁሉን ነገር እንደ ቤት ጥራጊ እቆጥራለሁ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 3:3-8 የ1980 ትርጉም) በመንፈስ ተነሳስቶ በጻፈው በሌላ ደብዳቤው ላይ “የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞኝነት ነው” ብሎ ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 3:19
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መከታተልን ጨርሶ አያበረታታም ማለት ነውን? አንድ ክርስቲያን ዓለማዊ ትምህርትን መከታተል የሚኖርበት እስከ ምን ደረጃ ድረስ ነው? ሕግ የሚጠይቅበትን መለስተኛ የትምህርት ደረጃ ማጠናቀቁ ብቻ በቂ ነው? ወይስ ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ያስፈልገዋል?
ትምህርት በመጀመሪያው መቶ ዘመን
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የተለያየ የትምህርት ደረጃ ነበራቸው። የተወሰኑ እውቅ ሰዎች የገሊላ ተወላጅ የነበሩትን ሐዋርያው ጴጥሮስንና ሐዋርያው ዮሐንስን ‘መጽሐፍን እንደማያውቁና እንዳልተማሩ’ አድርገው ቆጥረዋቸው ነበር። (ሥራ 4:5, 6, 13) ይህ ማለት እነዚህ ሁለት ሰዎች ፊደል ያልቆጠሩ መሐይማን ነበሩ ማለት ነውን? በጭራሽ። ከዚህ ይልቅ ኢየሩሳሌም ውስጥ በነበሩት ከፍተኛ ትምህርት በሚሰጥባቸው የዕብራውያን ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው አለመማራቸውን የሚያመለክት ነው። እነዚህ ሁለት ደፋር የክርስትና ጠበቆች ከጊዜ በኋላ የጻፏቸው ጽሑፎች የተማሩ፣ አዋቂዎችና ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠንቅቀው የተረዱ እንደነበሩ መስክረዋል። የቀሰሙት ትምህርት ቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች በማሟላት ረገድ ተግባራዊ መመሪያዎች ያቀፈ ነበር። አትራፊ በነበረው የዓሣ ንግድ በሽርክና ይሠሩ ነበር።—ማርቆስ 1:16-21፤ ሉቃስ 5:7, 10
በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ወንጌልና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የጻፈው ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ ከፍተኛ ትምህርት ቀስሞ ነበር። ሐኪም ነበር። (ቆላስይስ 4:14) የነበረው የሕክምና ሙያ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፋቸው ጽሑፎች ውስጥ ግልጽ በሆነ መንገድ ተንጸባርቋል።—ሉቃስ 4:38ን፤ 5:12ን፤ ሥራ 28:8ን ተመልከት።
ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ ቀደም ብሎ በጊዜው ታዋቂ ምሁር በነበረው በገማልያል እግር አጠገብ የአይሁድን ሕግ ተምሮ ነበር። (ሥራ 22:3) ጳውሎስ የተከታተለው ትምህርት በዛሬው ጊዜ በዩኒቨርሲቲ ከሚሰጠው ትምህርት ጋር ሊወዳደር የሚችል ነው። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ልጅ ከጊዜ በኋላ ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተል የሚደረግ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ በልጅነቱ የእጅ ሙያ መማሩ በአይሁድ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። ጳውሎስ ድንኳን የመስፋት ሙያውን የተማረው ገና ልጅ በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ይህን ሙያ መቅሰሙ በሙሉ ጊዜ አገልግሎቱ ወቅት ራሱን እንዲደግፍ አስችሎታል።
የሆነ ሆኖ ዓለማዊ ትምህርት የሚሰጠው ጥቅም ቢኖርም እንኳ የአምላክ እውቀት ከሚሰጠው የላቀ ጥቅም ጋር ሲነጻጸር የሚያስገኘው ጥቅም በጣም ውስን መሆኑን ጳውሎስ ተገንዝቧል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ እውቀት መቅሰም የላቀ ግምት የሚሰጠው ነገር መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ዓለማዊ ትምህርትን በተመለከተ እንዲህ ያለውን ምክንያታዊ አመለካከት መያዛቸው ተገቢ ነው።—ምሳሌ 2:1-5፤ ዮሐንስ 17:3፤ ቆላስይስ 2:3
ጉዳዩን በጥንቃቄ መመዘን
አንዳንድ ክርስቲያኖች ተጨማሪ የቀለም ወይም የሞያ ትምህርት መከታተላቸው ቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያስችላቸው ሆኖ አግኝተውታል። አንድ ሰው ‘ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ የማቅረብ’ ቅዱስ ግዳጅ ያለበት በመሆኑ ቤተሰቡን መንከባከቡ ተገቢ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ይህን ለማድረግ የሚያስችለውን ሞያ መቅሰሙ ተግባራዊ ጥበብ ነው።
ይሁን እንጂ ይህን ዓላማ ለማሳካት መሠረታዊ ከሆነው ትምህርት አልፈው ከፍተኛ ትምህርት መከታተል እንዳለባቸው ሆኖ የተሰማቸው ሁሉ ጥቅሙንና ጉዳቱን ከወዲሁ ማመዛዘን ይኖርባቸዋል። ከሚገኙት ጥቅሞች አንዱ ግለሰቡ ክርስቲያናዊ አገልግሎቱን በቅንዓት እያከናወነ ራሱንና ቤተሰቡን በበቂ ሁኔታ ለመደገፍ የሚያስችል ሥራ እንዲይዝ የሚረዳው መሆኑ ነው። በተጨማሪም ‘ለጎደለው የሚያካፍለው ነገር ሊኖረውና’ በቁሳዊ መንገድ ሌሎችን ሊረዳ ይችላል።—ኤፌሶን 4:28
ሊያጋጥሙ የሚችሉ አንዳንድ ጉዳቶችስ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ከእነዚህ መካከል አንዱ በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ለሚሸረሽሩ ትምህርቶች መጋለጥ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ‘ከውሸት እውቀት’ እና ‘እንደ ሰው ወግ ባለ በፍልስፍና በከንቱ ከመታለል’ እንዲጠበቁ ክርስቲያኖችን አሳስቧል። (1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21፤ ቆላስይስ 2:8) አንድ ክርስቲያን ለአንዳንድ የትምህርት ዓይነቶች መጋለጡ እምነቱን እንዲያጣ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ተጨማሪ ትምህርት ወይም ሥልጠና ለመውሰድ የሚያስቡ ሁሉ ለእነዚህ ጎጂ ተጽዕኖዎች የመጋለጥ አደጋ እንዳለ ማወቅ ይኖርባቸዋል።
‘የግብፃውያንን ጥበብ ሁሉ የተማረው’ ሙሴ በብዙ አማልክት አምልኮ ማመንን ጨምሮ አምላክን ዝቅ የሚያደርጉ ትምህርቶች የተማረ ቢሆንም የነበረውን ጠንካራ እምነት አላላላም። (ሥራ 7:22) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በማንኛውም ሁኔታ ሥር በሚመጡ ጤናማ ባልሆኑ ትምህርቶች እንዳይበረዙ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።
ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ሊያስከትል የሚችለው ሌላው አደጋ ደግሞ እውቀት ሊያስታብይ ወይም የኩራት ስሜት ሊፈጥር የሚችል መሆኑ ነው። (1 ቆሮንቶስ 8:1) ብዙዎች ትምህርት በመከታተል እውቀት ለመሰብሰብ የሚጥሩት በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስተው ነው። ሌላው ቀርቶ በጥሩ የውስጥ ግፊት ተነሳስቶ ትምህርት መከታተል እንኳ ከሁሉ እበልጣለሁ የሚል አስተሳሰብ ሊፈጥር ወይም ራስን ከፍ ከፍ ወደማድረግ ሊያደርስ ይችላል። እነዚህ ባሕርያት ደግሞ አምላክን አያስደስቱም።—ምሳሌ 8:13
የፈሪሳውያንን ምሳሌ እንመልከት። የዚህ ታዋቂ ሃይማኖታዊ ክፍል አባላት ባካበቱት እውቀትና የይስሙላ ጽድቅ ይታበዩ ነበር። ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን አካትቶ የያዘውን የረቢዎች ወጎች ጠንቅቀው የሚያውቁ ሲሆን የእነሱን ያህል ከፍተኛ ትምህርት ያልተማረውን ተራውን ሕዝብ እንደ ደንቆሮ፣ የተናቀና ሌላው ቀርቶ የተረገመ እንደሆነ አድርገው በመቁጠር ዝቅ አድርገው ይመለከቱት ነበር። (ዮሐንስ 7:49) ከዚህም ሌላ ገንዘብ የሚወዱ ነበሩ። (ሉቃስ 16:14) የእነርሱ ምሳሌ እንደሚያሳየው አንድ ሰው ትምህርት የሚከታተለው በተሳሳተ የውስጥ ዝንባሌ ተነሳስቶ በሚሆንበት ጊዜ ኩራተኛ ሊሆን ወይም የገንዘብ ፍቅር ሊጠናወተው ይችላል። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን የሚመርጠውን የትምህርት ዓይነትና መጠን በተመለከተ ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ ‘ውስጣዊ ዝንባሌዬ ምንድን ነው?’ ብሎ ራሱን መጠየቁ የተገባ ነው።
የግል ምርጫ
ልክ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በዛሬውም ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች የተለያየ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ናቸው። ሕግ የሚጠይቅባቸውን መለስተኛ የትምህርት ደረጃ ያጠናቀቁ ወጣቶች ወላጆቻቸው በሚሰጧቸው አመራር ተጨማሪ ሰብዓዊ ትምህርት ለመከታተል ይመርጡ ይሆናል። በተመሳሳይም የቤተሰባቸውን ገቢ ከፍ ለማድረግ የሚፈልጉ አዋቂ ሰዎችም ይህን ዓላማቸውን ማሳካት ይችሉ ዘንድ ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ይፈልጉ ይሆናል።a አንዳንድ የተለመዱ የቀለም ትምህርቶች አጠቃላይ የሆነ የአእምሮ እውቀት የሚሰጡ እንጂ አንድ ዓይነት ሙያ የሚያስተምሩ አይደሉም። በመሆኑም አንድ ሰው እንዲህ ያለውን ትምህርት ለረዥም ጊዜ ከተከታተለ በኋላም እንኳ በሥራ ዓለም ተፈላጊ የሆኑ ሙያዎችን ሳያዳብር ይቀራል። በዚህ የተነሳ አንዳንዶች የሥራው ዓለም የሚጠይቅባቸውን ሙያ ለመማር ሲሉ የሙያ ወይም የቴክኒክ ሥልጠናዎችን ለመከታተል መርጠዋል።
ያም ሆነ ይህ እንዲህ ያለው ውሳኔ ለእያንዳንዱ ግለሰብ የተተወ ነው። በዚህ ረገድ ክርስቲያኖች አንዳቸው ሌላውን መንቀፍ ወይም በሌላው ላይ መፍረድ አይኖርባቸውም። ያዕቆብ “በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 4:12) አንድ ክርስቲያን ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ሲነሳሳ እንዲህ እንዲያደርግ የገፋፋው ኃይል የራስ ወዳድነት ስሜት ወይም የቁሳዊ ሀብት ጥማት አለመሆኑን ለማረጋገጥ የራሱን ውስጣዊ ዝንባሌ መመርመር ይኖርበታል።
መጽሐፍ ቅዱስ ለትምህርት ሚዛኑን የጠበቀ አመለካከት መያዝን እንደሚያበረታታ ግልጽ ነው። ክርስቲያን ወላጆች በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃል ውስጥ የሚገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ከሁሉ የላቀ ዋጋ እንዳለው ስለሚያውቁ ተጨማሪ ትምህርት መከታተልን በሚመለከት ለልጆቻቸው ሚዛኑን የጠበቀ ምክር ይሰጧቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) የሕይወትን እውነታ ስለሚገነዘቡ ሰብዓዊ ትምህርት ትልልቅ ልጆቻቸው ለራሳቸውም ሆነ ወደፊት ለሚመሠርቱት ቤተሰብ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት የሚያስችላቸውን አስፈላጊ ሙያ እንዲያገኙ በመርዳት ረገድ የሚያበረክተውን ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አይዘነጉም። ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን “የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፣ ለነገር ሁሉ” የሚጠቅመውን ለይሖዋ አምላክ የማደር መንፈስ በመያዝ ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ያስፈልገው እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲሁም እንዲህ ዓይነቱን ትምህርት እስከ ምን ደረጃ መከታተል እንዳለበት የራሱን ምክንያታዊ የሆነ የግል ውሳኔ ሊያደርግ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቀት ያለው መረጃ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተሙትን የኅዳር 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 10-21ንና የይሖዋ ምሥክሮችና ትምህርት (እንግሊዝኛ) የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ተግባራዊ ጥበብንና የማሰብ ችሎታን ጠብቅ።”—ምሳሌ 3:21 NW
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንድ ክርስቲያን ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል በሚያስብበት ጊዜ ‘ውስጣዊ ዝንባሌዬ ምንድን ነው?’ ብሎ ራሱን መጠየቁ ተገቢ ይሆናል