የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 11/1 ገጽ 12-18
  • ይሖዋ የሚሰጠውን ማጽናኛ ማካፈል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ የሚሰጠውን ማጽናኛ ማካፈል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ”
  • አጽናኞች ለመሆን መሠልጠን
  • ጳውሎስ በእስያ የደረሰበት መከራ
  • ዘመናዊ ምሳሌዎች
  • በሩዋንዳ ውስጥ ለደረሰው ሰቆቃ ተጠያቂው ማን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ‘የመጽናናት ሁሉ አምላክ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ‘ያዘኑትን አጽናኑ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ‘ከመጽናናት ሁሉ አምላክ’ የሚገኝ መጽናኛ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 11/1 ገጽ 12-18

ይሖዋ የሚሰጠውን ማጽናኛ ማካፈል

“ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና።” —2 ቆሮንቶስ 1:7

1, 2. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የሆኑ ብዙ ሰዎች ምን ተሞክሮ አላቸው?

ብዙዎቹ የመጠበቂያ ግንብ አንባብያን ቀደም ሲል የአምላክ እውነት እውቀት አልነበራቸውም። የአንተም ሁኔታ ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። እንደዚያ ከነበረ የማስተዋል ዓይኖችህ ሲከፈቱ ተሰምቶህ የነበረውን ስሜት እስቲ ለአንድ አፍታ አስብ። ለምሳሌ ያህል ሙታን እየተሠቃዩ ሳይሆን ምንም የማያውቁ በድኖች መሆናቸውን ስታውቅ እፎይታ አልተሰማህምን? በቢልዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ እንዳላቸው ስታውቅ አልተጽናናህምን?—መክብብ 9:5, 10፤ ዮሐንስ 5:28, 29

2 አምላክ ክፋትን አስወግዶ ይህችን ምድር ወደ ገነትነት እንደሚለውጥ የሰጠው ተስፋስ? ይህን ተስፋ ማወቅህ እንድትጽናናና የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እንድትጠባበቅ አላደረገህምን? ሞትን ሳይቀምሱ ከጥፋት ተርፎ በመጪው ምድራዊ ገነት ውስጥ መኖር የሚቻልበት መንገድ እንዳለ መጀመሪያ ስትሰማ ምን ተሰምቶህ ነበር? እጅግ እንደተደሰትክ ጥርጥር የለውም። አዎን፣ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በይሖዋ ምሥክሮች በመሰበክ ላይ ያለውን የአምላክ አጽናኝ መልእክት ተቀብለሃል።—መዝሙር 37:9-11, 29፤ ዮሐንስ 11:26፤ ራእይ 21:3-5

3. የአምላክን አጽናኝ መልእክት ለሌሎች የሚያካፍሉ ሰዎችም መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

3 ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች ለማካፈል በሞከርክበት ጊዜ ‘እምነት ለሁሉ እንዳይደለ’ ሳትገነዘብ አልቀረህም። (2 ተሰሎንቄ 3:2) ምናልባትም ከቀድሞ ጓደኞችህ መካከል አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ላይ ያለህን እምነት በመግለጽህ ሊያሾፉብህ ይችላሉ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት በመቀጠልህ ስደት ደርሶብህ ሊሆን ይችላል። ሕይወትህን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ለማጣጣም አንዳንድ ለውጦች ማድረግ ስትጀምር ተቃውሞው ይበልጥ ተጠናክሮ ይሆናል። ሰይጣንና የእሱ ዓለም የአምላክን ማጽናኛ በሚቀበሉ ሰዎች ላይ የሚያመጡት መከራና ችግር እየደረሰብህ ነው።

4. ለእውነት ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች ለሚደርስባቸው መከራ ምላሽ የሚሰጡት በምን የተለያዩ መንገዶች ሊሆን ይችላል?

4 የሚያሳዝነው ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው አንዳንዶች ችግርና መከራው እንዲደናቀፉና ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ያደርጋቸዋል። (ማቴዎስ 13:5, 6, 20, 21) ሌሎች ደግሞ እየተማሯቸው ባሉት አጽናኝ ተስፋዎች ላይ አእምሮአቸው እንዲያተኩር በማድረግ መከራውን ተቋቁመውታል። ከጊዜ በኋላም ሕይወታቸውን ለይሖዋ በመወሰን የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ተጠምቀዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ማርቆስ 8:34) እርግጥ አንድ ክርስቲያን ሲጠመቅ በእሱ ላይ የሚደርሰው መከራ ያቆማል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል ብልሹ ሥነ ምግባር የነበረው ሰው ንጹሕ ሆኖ መኖር ከባድ ትግል ሊጠይቅበት ይችላል። ሌሎች ደግሞ ከማያምኑ የቤተሰብ አባላት የሚደርስባቸውን የማያቋርጥ ተቃውሞ መቋቋም አለባቸው። ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው በታማኝነት የሚኖሩ ሁሉ የሚደርስባቸው መከራ ምንም ይሁን ምን ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። በግለሰብ ደረጃ የአምላክን ማጽናኛና እርዳታ ያገኛሉ።

“የመጽናናትም ሁሉ አምላክ”

5. ጳውሎስ ከደረሱበት ብዙ ፈተናዎች ጎን ለጎን ምን አስደሳች ተሞክሮ አጋጥሞታል?

5 አምላክ የሚሰጠውን ማጽናኛ እጅግ ካደነቁት ሰዎች አንዱ ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። በእስያና በመቄዶንያ ለየት ያለ ፈታኝ ሁኔታ ካጋጠመው በኋላ የቆሮንቶስ ጉባኤ ክርስቲያኖች ጽፎላቸው ለነበረው ወቀሳ አዘል ደብዳቤ ጥሩ ምላሽ እንደሰጡ በመስማቱ ትልቅ እፎይታ አግኝቷል። ይህም የሚከተለውን ምስጋና ያዘለ ሁለተኛ ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ገፋፍቶታል፦ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።”—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

6. በ2 ቆሮንቶስ 1:3, 4 ላይ ከሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ምን እንማራለን?

6 እነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ ቃላት ብዙ ትርጉም ያዘሉ ናቸው። እስቲ እንመርምራቸው። ጳውሎስ በደብዳቤዎቹ ላይ አምላክን ሲያወድስ ወይም ሲያመሰግን ወይም ደግሞ አምላክን ሲለምን ብዙውን ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ለሆነው ለኢየሱስ ያለውን የጠለቀ አድናቆት ይገልጻል። (ሮሜ 1:8፤ 7:25፤ ኤፌሶን 1:3፤ ዕብራውያን 13:20, 21) በመሆኑም ጳውሎስ ይህን የውዳሴ ቃል ያሰማው ‘ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት’ ነው። ከዚያም ጳውሎስ እሱ በጻፋቸው ጽሑፎች ውስጥ “ርኅራኄ” ተብሎ የተተረጎመውን የግሪክኛ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሟል። ይህ ስም የመጣው በሌላ ሰው ላይ በደረሰ መከራ ሳቢያ ማዘንን ከሚገልጽ ቃል ነው። ስለዚህ ጳውሎስ የገለጸው መከራ ለሚደርስባቸው ታማኝ አገልጋዮቹ ሁሉ አምላክ የሚሰማውን የርኅራኄ ስሜት ነው። በምሕረት መንፈስ እነርሱን ለመርዳት እርምጃ እንዲወስድ የሚገፋፋውን የርኅራኄ ስሜት ገልጿል። በመጨረሻም፣ ጳውሎስ “የርኅራኄ አባት” ብሎ በመጥራት ይሖዋን የዚህ ጥሩ ባሕርይ ምንጭ አድርጎ ተመልክቶታል።

7. ይሖዋ “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

7 የአምላክ “ርኅራኄ” መከራ የሚደርስበትን ሰው እፎይታ ያስገኝለታል። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ በመቀጠል ይሖዋን “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ብሎ ገልጾታል። ስለዚህ ከመሰል አማኞች ደግነት ምንም ዓይነት ማጽናኛ ብናገኝ የማጽናኛው ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ አድርገን ልንመለከት እንችላለን። ምንጩ አምላክ ያልሆነ ማጽናኛ እውነተኛና ዘላቂ ሊሆን አይችልም። በተጨማሪም ሰውን በራሱ መልክ የፈጠረው እሱ ስለሆነ አጽናኞች እንድንሆን የሚያስችለን እሱ ነው። አገልጋዮቹ ማጽናኛ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ርኅራኄ እንዲያሳዩ የሚያነሳሳቸውም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነው።

አጽናኞች ለመሆን መሠልጠን

8. የፈተናዎቻችን ምንጭ አምላክ ባይሆንም እንኳ በመከራ መጽናታችን ምን ጠቃሚ ውጤት ሊያስገኝልን ይችላል?

8 ምንም እንኳ ይሖዋ አምላክ በታማኝ አገልጋዮቹ ላይ የተለያዩ ፈተናዎች እንዲደርሱ ቢፈቅድም የእነዚህ ፈተናዎች ምንጭ ግን እሱ አይደለም። (ያዕቆብ 1:13) ይሁን እንጂ መከራ ሲደርስብን የሚሰጠን ማጽናኛ የሌሎች ሰዎች ችግር ቶሎ የሚሰማን እንድንሆን ሊያሠለጥነን ይችላል። ይህ ምን ውጤት አለው? “እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን።” (2 ቆሮንቶስ 1:4) በመሆኑም የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ‘የሚያለቅሱትን ሰዎች ሁሉ ስናጽናና’ ማጽናኛውን ለመሰል አማኞችና በመስክ ለምናገኛቸው ሰዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድናካፍል ይሖዋ ያሠለጥነናል።—ኢሳይያስ 61:2፤ ማቴዎስ 5:4

9. (ሀ) መከራን ለመቋቋም ምን ይረዳናል? (ለ) መከራን በታማኝነት ስንቋቋም ሌሎች የሚጽናኑት እንዴት ነው?

9 ጳውሎስ በክርስቶስ በኩል ከአምላክ ባገኘው ብዙ ማጽናኛ አማካኝነት የተለያዩ መከራዎችን ተቋቁሟል። (2 ቆሮንቶስ 1:5) እኛም በአምላክ ውድ ተስፋዎች ላይ በማሰላሰል፣ የቅዱስ መንፈሱን እርዳታ በጸሎት በመጠየቅና አምላክ ለጸሎታችን በሚሰጠው ምላሽ አማካኝነት ብዙ ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን። በዚህ መንገድ የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፋችንንና ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑን ማስመስከራችንን ለመቀጠል ብርታት እናገኛለን። (ኢዮብ 2:4፤ ምሳሌ 27:11) ማንኛውንም ዓይነት መከራ በታማኝነት ስንቋቋም ክብሩን ልክ ጳውሎስ እንዳደረገው ክርስቲያኖች በፈተና ሥር ታማኝ ሆነው እንዲቆሙ የሚያስችል ማጽናኛ ለሚሰጠው ለይሖዋ መስጠት አለብን። የታማኝ ክርስቲያኖች ጽናት ሌሎችም ‘በዚያ ሥቃይ ለመጽናት’ ቁርጥ ውሳኔ እንዲወስዱ በማድረግ በወንድማማቹ ማኅበር ላይ የሚያጽናና ውጤት ያስገኛል።—2 ቆሮንቶስ 1:6

10, 11. (ሀ) በጥንቱ የቆሮንቶስ ጉባኤ ላይ መከራ አምጥተው የነበሩት አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ጳውሎስ የቆሮንቶስን ጉባኤ ያጽናናው እንዴት ነው? ምን ተስፋስ ገልጿል?

10 የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው መከራ ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም ዝሙት ሠርቶ ንስሐ ያልገባን አንድ ሰው እንዲያስወግዱ መመከር አስፈልጓቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 5:1, 2, 11, 13) ይህን እርምጃ አለመውሰዳቸውና በመካከላቸው ተነስቶ የነበረውን ጠብና ክፍፍል አለማስወገዳቸው በጉባኤው ላይ ነቀፋ አስከትሎ ነበር። ሆኖም በመጨረሻ የጳውሎስን ምክር በተግባር በማዋል እውነተኛ ንስሐ አሳይተዋል። በመሆኑም የጋለ ምስጋና አቅርቦላቸዋል፤ በተጨማሪም ለጻፈው ደብዳቤ ጥሩ ምላሽ በማሳየታቸው እንደተጽናና ገልጾላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:8, 10, 11, 13) ተወግዶ የነበረውም ሰው ንስሐ የገባ ይመስላል። ስለዚህ ጳውሎስ ‘እንደዚህ ያለው ሰው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ ይቅር እንዲሉትና እንዲያጽናኑት’ መክሯቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 2:7

11 ሁለተኛው የጳውሎስ ደብዳቤ የቆሮንቶስን ጉባኤ አጽናንቶ መሆን አለበት። ከጳውሎስ ዓላማዎችም አንዱ ይህ ነበር። “ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና” ሲል ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 1:7) ጳውሎስ በደብዳቤው መደምደሚያ ላይ “መጽናናታችሁን . . . ቀጥሉ፤ . . . የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል” ሲል አሳስቧል።—2 ቆሮንቶስ 13:11 አዓት

12. ሁሉም ክርስቲያኖች ምን ያስፈልጋቸዋል?

12 ከዚህ እንዴት ያለ ጠቃሚ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን! እያንዳንዱ የክርስቲያን ጉባኤ አባል አምላክ በቃሉ፣ በቅዱስ መንፈሱና በምድራዊ ድርጅቱ አማካኝነት ከሚሰጠው ‘ማጽናኛ መካፈል’ ይኖርበታል። ሌላው ቀርቶ የተወገዱ ሰዎች እንኳ ንስሐ ከገቡና ከተሳሳተ አካሄዳቸው ከተመለሱ ማጽናኛ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በመሆኑም “ታማኝና ልባም ባሪያ” እነሱን ለመርዳት የምሕረት ዝግጅት አድርጓል። በዓመት አንዴ ሁለት ሽማግሌዎች አንዳንድ የተወገዱ ሰዎችን ሄደው ማነጋገር ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች የዓመፀኝነት መንፈስ ማሳየት ያቆሙ ወይም ደግሞ ከባድ ኃጢአት መሥራት ያቆሙና እንደገና ለመመለስ የሚያስችሏቸውን እርምጃዎች እንዲወስዱ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሊሆኑ ይችላሉ።—ማቴዎስ 24:45፤ ሕዝቅኤል 34:16

ጳውሎስ በእስያ የደረሰበት መከራ

13, 14. (ሀ) ጳውሎስ በእስያ ውስጥ ያጋጠመውን ከባድ የመከራ ጊዜ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ የትኛውን ድርጊት በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል?

13 የቆሮንቶስ ጉባኤ እስከዚህ ደረጃ ድረስ የደረሰበት መከራ ጳውሎስ ከደረሰበት ብዙ መከራ ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም። በመሆኑም እንዲህ ሲል ሊያሳስባቸው ችሏል፦ “በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፣ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፣ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፣ ያድነንማል፤ . . . ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል።”—2 ቆሮንቶስ 1:8-11

14 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ጳውሎስ የእሱንም ሆነ ከእሱ ጋር አብረው ተጉዘው የነበሩትን የመቄዶንያ ተወላጆች የጋይዮስንና የአርስጥሮኮስን ሕይወት ሊያሳጣ ይችል የነበረውን የኤፌሶን ከተማ ረብሻ መጥቀሱ ነበር ብለው ያምናሉ። እነዚህ ሁለት ክርስቲያኖች “የኤፌሶን [የሴት አምላክ] አርጤምስ ታላቅ ናት” እያሉ ለሁለት ሰዓት ይጮኹ በነበሩ ሰዎች ወደተሞላ ቲያትር ቤት በኃይል ተወሰዱ። በመጨረሻ የከተማው ባለ ሥልጣን ሕዝቡን ዝም ማሰኘት ቻለ። በጋይዮስና በአርስጥሮኮስ ሕይወት ላይ አንዣብቦ የነበረው ይህ አደጋ ጳውሎስን እጅግ ሳያስጨንቀው አልቀረም። እንዲያውም ወደ ውስጥ ገብቶ እነዚያን አክራሪ ረብሸኞች ለማሳመን ፈልጎ ነበር፤ ሆኖም ይህን በማድረግ ሕይወቱን አደጋ ላይ እንዳይጥል ከለከሉት።—ሥራ 19:26-41

15. በ1 ቆሮንቶስ 15:32 ላይ የተገለጸው ምን የከፋ ሁኔታ ሊሆን ይችላል?

15 ይሁን እንጂ ጳውሎስ ከላይ ከተገለጸው ድርጊት እጅግ የከፋ ሁኔታን መግለጹ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤው “እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ . . . ምን ይጠቅመኛል?” ሲል ጠይቋል። (1 ቆሮንቶስ 15:32) ይህ ማለት ምናልባት የጳውሎስ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ የነበረው የአውሬነት ጠባይ ባላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ቃል በቃል በኤፌሶን ስታድየም ከእንስሳት ጋር በሚደረገው ትግል ጭምር ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ወንጀለኞች ደም የተጠሙ ሰዎች ቁጭ ብለው እየተመለከቱ ከአውሬዎች ጋር እንዲታገሉ በማድረግ ይቀጡ ነበር። ጳውሎስ ቃል በቃል ከአውሬዎች ጋር እንዲታገል ተደርጎ እንደነበረ መጥቀሱ ከሆነ ልክ ዳንኤል ከአንበሶች አፍ እንደዳነ ሁሉ እሱም መጨረሻ ላይ ከአሠቃቂ ሞት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ተርፏል ማለት ነው።—ዳንኤል 6:22

ዘመናዊ ምሳሌዎች

16. (ሀ) ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በጳውሎስ ላይ የደረሱትን መከራዎች በሚገባ ሊያውቋቸው የሚችሉት ለምንድን ነው? (ለ) በእምነታቸው ምክንያት የሞቱትን በተመለከተ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? (ሐ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ከሞት የተረፉባቸው በጣም አስገራሚ ሁኔታዎች ምን ጥሩ ውጤት አስገኝተዋል?

16 በዘመናችን ያሉ ብዙ ክርስቲያኖች በጳውሎስ ላይ የደረሱትን ዓይነት መከራዎች እንደተቀበሉ መናገር ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 11:23-27) በዛሬው ጊዜም ክርስቲያኖች ‘ከዓቅማቸው በላይ የሆኑ ከባድ መከራዎች’ አሳልፈዋል፤ ብዙዎቹም ‘ስለ ሕይወታቸው እንኳ ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጉ’ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:8) አንዳንዶች የጅምላ ጭፍጨፋ ባካሄዱ ሰዎችና ጨካኝ በሆኑ አሳዳጆች እጅ ሕይወታቸው ጠፍቷል። የአምላክ አጽናኝ ኃይል መጽናት እንዲችሉ እንደረዳቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ተስፋቸው ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ ልባቸውና አእምሮአቸው በተስፋቸው ፍጻሜ ላይ እንዳተኮረ ሞተዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:13፤ ፊልጵስዩስ 4:13፤ ራእይ 2:10) በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ ይሖዋ አንዳንድ ጉዳዮች አቅጣጫቸውን እንዲለውጡ በማድረግ ወንድሞቻችን ከሞት እንዲተርፉ አድርጓል። በዚህ መንገድ የተረፉ ወንድሞች ‘ሙታንን በሚያስነሳው አምላክ’ ላይ ያላቸው ትምክህት ይበልጥ እንደጨመረ ጥርጥር የለውም። (2 ቆሮንቶስ 1:9) ከዚህ በኋላ የአምላክን አጽናኝ መልእክት ለሌሎች ሲያካፍሉ ከበፊቱ የበለጠ ሙሉ እምነት አድሮባቸው መናገር ይችላሉ።—ማቴዎስ 24:14

17-19. በሩዋንዳ የሚገኙ ወንድሞቻችን የአምላክን ማጽናኛ እንዳገኙ የትኞቹ ተሞክሮዎች ያሳያሉ?

17 በቅርቡ በሩዋንዳ የሚኖሩ ውድ ወንድሞቻችን በጳውሎስና በጓደኞቹ ላይ የደረሰባቸው ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። ብዙ ወንድሞች ሕይወታቸውን ቢያጡም ሰይጣን እምነታቸውን ለማጥፋት ያደረገው ጥረት አልሰመረም። ከዚህ ይልቅ በዚህች አገር የሚኖሩ ወንድሞቻችን የአምላክን ማጽናኛ በግለሰብ ደረጃ በብዙ መንገዶች አግኝተዋል። በሩዋንዳ በሚኖሩ ቱትሲና ሁቱዎች መካከል በተካሄደው ዘር የማጥፋት ዘመቻ ሁቱዎች ቱትሲዎችን ለማዳን፣ ቱትሲዎች ደግሞ ሁቱዎችን ለማዳን ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነበር። አንዳንዶቹ መሰል አማኞችን በመደበቃቸው ምክንያት በአክራሪዎች ተገድለዋል። ለምሳሌ ያህል ጋሂዚ የተባለ አንድ ሁቱ ምሥክር ቻንታል የተባለች ቱትሲ እህት በመደበቁ ምክንያት ተገድሏል። ቱትሲ የሆነው የቻንታል ባል ዣን ደግሞ በሌላ አካባቢ ሻርሎት የምትባል ሁቱ እህት ጋር ተደብቆ ነበር። ዣንና ሌላ ቱትሲ ወንድም ሌሊት ሌሊት ብቻ ለአጭር ጊዜ እየወጡ ለ40 ቀናት በአንድ ትልቅ ጭስ ማውጫ ውስጥ ተደብቀው ቆይተዋል። ሻርሎት ምንም እንኳ የምትኖረው በአንድ የሁቱ የጦር ሠፈር አቅራቢያ የነበረ ቢሆንም በዚህ ጊዜ ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ትሰጣቸው ነበር፤ እንዲሁም ጥበቃ ታደርግላቸው ነበር። እንደገና የተገናኙትን የዣንንና የቻንታል ፎቶ በዚህ ገጽ ላይ መመልከት ትችላላችሁ፤ ልክ ጵርስቅላና አቂላ ለሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረጉት የሁቱ ተወላጆች የሆኑ መሰል አምላኪዎችም ለእነሱ ሲሉ ‘ነፍሳቸውን ለሞት በማቅረባቸው’ አመስጋኝ ናቸው።—ሮሜ 16:3, 4

18 ሩዋካቡቡ የተባለ አንድ ሌላ ሁቱ ምሥክር ቱትሲ የሆኑ መሰል አማኞችን በመደበቁ ኢንታረሜራ የተባለ ጋዜጣ አወድሶታል።a ጋዜጣው እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ሩዋካቡቡ የተባለውም የይሖዋ ምሥክር ወንድሞቹን (አማኞች እርስ በርሳቸው የሚጠራሩት በዚህ መንገድ ነው) በተለያየ ቦታ ደብቆ ነበር። ምንም እንኳ የአስም በሽታ ያለበት ቢሆንም ቀኑን ሙሉ ምግብና የሚጠጣ ውኃ ሲያመላልስ ይውል ነበር። ሆኖም አምላክ ልዩ የሆነ ብርታት ሰጥቶታል።”

19 በተጨማሪም ኒኮዴም እና አታናዚ የተባሉትን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፍላጎት ያሳዩ ሁቱ ባልና ሚስት ታሪክ ተመልከት። የዘር ማጥፋት ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት እነዚህ ባልና ሚስት አልፎንስ ከሚባል አንድ ቱትሲ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ያጠኑ ነበር። ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው አልፎንስን ቤታቸው ውስጥ ደበቁት። ከጊዜ በኋላ ግን ቤቱ አስተማማኝ ቦታ እንዳልሆነ ተገነዘቡ፤ ምክንያቱም የሁቱ ተወላጆች የሆኑት ጎረቤቶቻቸው ስለዚህ ቱትሲ ጓደኛቸው ያውቁ ነበር። ስለዚህ ኒኮዴም እና አታናዚ አልፎንስን ግቢያቸው ውስጥ በሚገኝ አንድ ጉድጓድ ውስጥ ደበቁት። ይህ ጥሩ እርምጃ ነበር፤ ምክንያቱም ጎረቤቶቻቸው በየቀኑ ማለት ይቻላል፣ አልፎንስን ለመፈለግ ይመጡ ነበር። አልፎንስ በዚህ ጉድጓድ ውስጥ ለ28 ቀናት ተደብቆ በነበረበት ወቅት ሁለቱን እስራኤላውያን ኢያሪኮ በሚገኘው ቤቷ ጣሪያ ውስጥ ደብቃ ስለነበረችው ረዓብ የሚናገረውን የመሳሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ያሰላስል ነበር። (ኢያሱ 6:17) በአሁኑ ጊዜ አልፎንስ በሩዋንዳ ውስጥ የምሥራቹ ሰባኪ ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል፤ የሁቱ ተወላጆች የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቹ እሱን ለማዳን ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣላቸው አመስጋኝ ነው። ኒኮዴምና አታናዚስ? በአሁኑ ጊዜ የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ከመሆናቸውም በላይ ፍላጎት ያሳዩ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ላይ ናቸው።

20. በሩዋንዳ የሚገኙ ወንድሞቻችንን ይሖዋ ያጽናናቸው በምን መንገድ ነው? ሆኖም ብዙዎቹ አሁንም ምን ያስፈልጋቸዋል?

20 በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ዘመቻው ሲጀምር በአገሪቱ ውስጥ 2,500 የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች ይገኙ ነበር። ምንም እንኳ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸውን ቢያጡም ወይም አገሪቱን ለቀው ለመሰደድ ቢገደዱም የምሥክሮቹ ቁጥር ከ3,000 በላይ ሆኗል። ይህ ሁኔታ አምላክ ወንድሞቻችንን በእርግጥም እንዳጽናናቸው የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙት ብዛት ያላቸው ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶችና ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆችስ? እነዚህ ሰዎች አሁንም ቢሆን መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ ግልጽ ነው፤ የማያቋርጥ ማጽናኛ ሊሰጣቸው ይገባል። (ያዕቆብ 1:27) እንባቸው ሙሉ በሙሉ የሚደርቀው በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ ትንሣኤ ሲከናወን ነው። ሆኖም ወንድሞቻቸው በሚሰጧቸው አገልግሎት አማካኝነትና “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” አምላኪዎች በመሆናቸው ኑሮውን መቋቋም ይችላሉ።

21. (ሀ) የአምላክ ማጽናኛ እጅግ የሚያስፈልጋቸው በየት የሚገኙ ወንድሞቻችንም ናቸው? ሁላችንም እርዳታ ልናደርግ የምንችልበት አንዱ መንገድስ ምንድን ነው? (“በአራት የጦርነት ዓመታት የተገኘ ማጽናኛ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) ማጽናኛ የማግኘት ፍላጎታችን ፍጹም በሆነ መንገድ የሚሟላው መቼ ነው?

21 እንደ ኤርትራ፣ ሲንጋፖርና የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በመሳሰሉ ሌሎች ብዙ ቦታዎች ወንድሞቻችን መከራ እየደረሰባቸው ቢሆንም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ማጽናኛ ማግኘት እንዲችሉ ዘወትር በመጸለይ እነዚህን ወንድሞች እንርዳቸው። (2 ቆሮንቶስ 1:11) በተጨማሪም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሙሉ በሙሉ ‘እንባዎቻችን ከዓይኖቻችን የሚያብስበት’ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በታማኝነት ጸንተን እንኑር። ከዚያ በኋላ ይሖዋ ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚሰጠንን ማጽናኛ ፍጹም በሆነ ሁኔታ እናገኛለን።—ራእይ 7:17፤ 21:4፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የጥር 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26 ላይ የሁቱ ወታደሮችን ልብ የነካና ቤተሰቡን ከሞት ያተረፈ ጸሎት የጸለየችውን የሩዋካቡቡን ሴት ልጅ የዲቦራን ተሞክሮ ይዞ ወጥቷል።

መልሱ ምንድን ነው?

◻ ይሖዋ “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” የተባለው ለምንድን ነው?

◻ መከራን ማየት ያለብን እንዴት ነው?

◻ ማጽናኛን ለእነማን ማካፈል እንችላለን?

◻ ማጽናኛ የማግኘት ፍላጎታችን ፍጹም በሆነ መንገድ የሚሟላው እንዴት ነው?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዣንና ቻንታል ምንም እንኳ ቱትሲ ምሥክሮች ቢሆኑም በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ይካሄድ በነበረበት ወቅት በሁቱ ምሥክሮች አማካኝነት በተለያዩ ቦታዎች ተደብቀው ነበር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሩዋንዳ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን አጽናኝ መልእክት ለሰዎች ማካፈላቸውን ቀጥለዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ