በይሖዋ ደስ ይበላችሁ!
“ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:4
1. ጳውሎስ ክርስቲያኖች ዘወትር መደሰት አለባቸው ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ሊያስገርመን የሚችለው ለምንድን ነው?
በአሁኑ ጊዜ ለመደሰት የሚያበቁ ነገሮች በጣም ጥቂትና አልፎ አልፎ ብቻ ብቅ የሚሉ መስሎ ይታያል። ከአፈር የተሠሩ ሰዎች ሁሉ ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳን ሳይቀሩ እንደ ሥራ አጥነት፣ የጤና መታወክ፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት፣ መጥፎ ባሕርይ የሚያስከትላቸው ችግሮች ወይም ከማያምኑ የቤተሰብ አባሎች ወይም ከቀድሞ ጓደኞች የሚመጡ ተቃውሞዎችና የመሳሰሉ ሐዘን የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ታዲያ “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር የምንረዳው እንዴት ነው? ሁላችንም ትግል የሚጠይቁና የሚያስከፉና ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ታዲያ ነገሩ ከዚህ አንፃር ሲታይ ይህ የሚቻል ነውን? በእነዚህ ቃላት ዙሪያ ባሉት ሐሳቦች ላይ ብንወያይ ነገሩ ግልጽ ይሆናል።
ደስ ይበላችሁ—ለምን እና እንዴት?
2, 3. በኢየሱስና በጥንት እስራኤላውያን እንደታየው ደስታ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ።” ይህ አነጋገር ከ2,400 ዓመታት በፊት ለእስራኤላውያን የተነገሩትን “የይሖዋ ደስታ አምባችሁ ነው [አዓት]” ወይም በሞፋት ትርጉም መሠረት ደግሞ “ዘላለማዊ በሆነው አምላክ መደሰት ኃይላችሁ ነው” የሚሉትን ቃላት ሊያስታውሰን ይችላል። (ነህምያ 8:10) ደስታ ኃይል ይሰጣል፤ እንዲሁም አንድ ሰው መጽናኛ ሊያገኝበትና ሊከለልበት እንደሚችል አንድ ምሽግ ነው። ደስታ ፍጹም ሰው የነበረውን ኢየሱስን እንኳ እንዲጸና ረድቶታል። “እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” (ዕብራውያን 12:2) ችግሮች እያሉ ለመደሰት መቻል ለመዳን በጣም አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ ነው።
3 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው ቀደም ብሎ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር፦ “አንተም በመካከልህም ያለ ሌዋዊና መጻተኛ አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለቤትህ በሰጠው ቸርነት ሁሉ ደስ ይበላችሁ።” ይሖዋን በደስታ ለማገልገል አለመቻል የሚያስከትለው ውጤት በጣም ከባድ ነበር። “እስክትጠፋ ድረስ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይወርዱብሃል፣ ያሳድዱህማል፣ ያገኙህማል። . . . ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሥሐና በሐሤት አላመለክህምና።”—ዘዳግም 26:11፤ 28:45–47
4. ምን ነገሮች ደስታ ሊያሳጡን ይችላሉ?
4 እንግዲያው ዛሬ ያሉት ቅቡአን ቀሪዎችና ጓደኞቻቸው የሆኑት “ሌሎች በጎች” መደሰታቸው የግድ አስፈላጊ ነው! (ዮሐንስ 10:16) ጳውሎስ “ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ” ብሎ ምክሩን በመድገም ይሖዋ ባደረገልን መልካም ነገሮች ሁሉ መደሰት አስፈላጊ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። ታዲያ እየተደሰትን ነውን? ወይስ በዕለታዊ የሕይወት ሩጫ ተጠምደን እንድንደሰት የሚያደርጉንን ብዙ ምክንያቶች አንዳንድ ጊዜ እንረሳለን? መንግሥቲቱና የምታመጣቸው በረከቶች እንዳይታዩን እስከሚጋርዱብን ድረስ ችግሮች ይከመሩብናልን? የአምላክን ሕጎች አለመታዘዝ፣ መለኮታዊ የሆኑትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ቸል ማለት ወይም ክርስቲያናዊ ግዴታዎችን ገሸሽ ማድረግ እና የመሳሰሉት ሌሎች ነገሮች ደስታችንን እንዲሰርቁብን እንፈቅድላቸዋለንን?
5. ምክንያታዊ ያልሆነ ሰው ለመደሰት አስቸጋሪ የሚሆንበት ለምንድን ነው?
5 “ምክንያታዊነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። ጌታ ቅርብ ነው።” (ፊልጵስዩስ 4:5 አዓት) ምክንያታዊ ያልሆነ ሰው ሚዛኑን አይጠብቅም። ሳያስፈልግ በራሱ ላይ ጭንቀትና ውጥረት በመፍጠር ጤንነቱን ሊጎዳ ይችላል። ምናልባት አቅሙን አውቆ በዚያ መሠረት መኖርን ገና አልተማረ ይሆናል። ከአቅሙ በላይ የሆኑ ግቦችን በማውጣት የፈለገው ዓይነት ጉዳት ቢደርስበትም እነዚያ ግቦች ላይ ለመድረስ እየተፍጨረጨረ ይሆናል። ወይም ደግሞ ሥራ ለማጓተት ወይም በትጋት ላለመሥራት በአቅሙ አነስተኛነት ላይ ሊያሳብብ ይችላል። ሚዛኑን ስለማይጠብቅና ምክንያታዊ ስላልሆነ መደሰት አስቸጋሪ ይሆንበታል።
6. (ሀ) ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ከእኛ ምን ማየት ይኖርባቸዋል? ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ምን ከሆነ ብቻ ነው? (ለ) በ2 ቆሮንቶስ 1:24 እና በሮሜ 14:4 ላይ ያሉት ቃላት ምክንያታዊ ለመሆን የሚረዱን እንዴት ነው?
6 ምንም እንኳ ተቃዋሚዎች ጭፍን አቋም እንዳለን አድርገው ቢመለከቱንም ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ግን ምክንያታዊነታችንን ለመመልከት መቻል አለባቸው። ሚዛናዊ ከሆንና ከራሳችንም ሆነ ከሌሎች ፍጽምናን የማንጠብቅ ከሆነ ምክንያታውያን እንደሆንን አድርገው ይመለከቱናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአምላክ ቃል ከሚጠይቀው በላይ በሌሎች ላይ ከባድ ሸክም ከመጫን መቆጠብ አለብን። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፣ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 1:24) ጳውሎስ ቀደም ሲል ፈሪሳዊ የነበረ ሰው እንደመሆኑ መጠን በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች በሌሎች ላይ የሚጭኗቸው ድርቅ ያሉ ሕጎች መፈናፈኛ በማሳጣት ደስታ እንደሚነፍጉና አብረዋቸው የሚሠሩ ሰዎች የሚሰጧቸው ጠቃሚ የመፍትሔ ሐሳቦች ደግሞ ደስታ እንደሚጨምሩ በሚገባ ያውቅ ነበር። “የጌታ ቅርብ መሆን” አንድን ምክንያታዊ ሰው እኛ ‘በሌላው ሎሌ ላይ መፍረድ እንደማይገባንና እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው መሆኑን’ እንዲገነዘብ ሊረዳው ይገባል።—ሮሜ 14:4
7, 8. ክርስቲያኖች ችግሮች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ መጠበቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ መደሰታቸውን ሊቀጥሉ የሚችሉት እንዴት ነው?
7 “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።” (ፊልጵስዩስ 4:6) የምንኖረው ጳውሎስ “የሚያስጨንቅ ዘመን” በማለት በጻፈለት ጊዜ ላይ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ስለዚህ ክርስቲያኖች ችግሮች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ መጠበቅ አለባቸው። “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ” የሚለው የጳውሎስ አነጋገር አንድ ታማኝ ክርስቲያን አልፎ አልፎ የሚያሳዝንና የሚያስተክዝ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ አያጋጥመውም ማለት አይደለም። ጳውሎስ የራሱን ሁኔታ በተመለከተ “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም” በማለት እውነታውን ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። (2 ቆሮንቶስ 4:8, 9) ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ያለው ደስታ ጊዜያዊ ጭንቀቱንና ሐዘኑን ሊቀንስለት ውሎ አድሮ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ሊያስወግድለት ይችላል። ይህ ክርስቲያናዊ ደስታ ወደፊት ለመግፋት የሚያስፈልገውን ኃይል ይሰጠናል፤ ለመደሰት የሚያበቁንን ነገሮች ፈጽሞ እንዳንረሳ ይረዳናል።
8 ደስተኛ የሆነ ክርስቲያን ችግሮች ሲያጋጥሙት ችግሮቹ ምንም ዓይነት ይሁኑ በጸሎት አማካኝነት በትሕትና የይሖዋን እርዳታ ይጠይቃል። ከመጠን በላይ አይጨነቅም። ችግሩን ለመፍታት አቅሙ የሚፈቅድለትን ያህል ካደረገ በኋላ “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል” በሚለው ግብዣ መሠረት ይሖዋ የሚያደርገውን ይጠብቃል። እስከዚያው ግን ክርስቲያኑ ይሖዋ ላሳየው ጥሩነት ሁሉ ማመስገኑን ይቀጥላል።—መዝሙር 55:22፤ በተጨማሪም ማቴዎስ 6:25–34ን ተመልከት።
9. የእውነት እውቀት የአእምሮ ሰላም የሚሰጠን እንዴት ነው? ይህስ በአንድ ክርስቲያን ላይ ምን ጥሩ ውጤት ይኖረዋል?
9 “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:7) አንድ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቁ አእምሮውን ከውሸት ነፃ ስለሚያደርግለት ጤናማ አስተሳሰቦችን ያዳብራል። (2 ጢሞቴዎስ 1:13) በዚህ መንገድ ከሌሎች ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት አደጋ ላይ ሊጥል ከሚችል ከተሳሳተ ወይም ጥበብ ከጎደለው ጠባይ ለመራቅ ይችላል። በፍትሕ መጓደልና በክፋት ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ለሰው ዘር ችግሮች መፍትሔ እንደሚያመጣ በመተማመን በእርሱ ላይ ትምክህቱን ይጥላል። እንዲህ ዓይነቱ የአእምሮ ሰላም ልቡን ይጠብቅለታል፣ ውስጣዊ የልቡ ዓላማ ዘወትር ንጹሕ እንዲሆን ያደርጋል፤ እንዲሁም አስተሳሰቡን በጽድቅ መንገድ ይመራለታል። ምንም እንኳን ይህ ምስቅልቅሉ የወጣ ዓለም የሚያመጣቸው ችግሮችና ተጽዕኖዎች ቢኖሩም ንጹሕ የሆነ ውስጣዊ የልብ ዓላማና ትክክለኛ አስተሳሰብ መያዙ በአጸፋው ለደስታ ምክንያት የሚሆኑትን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ነገሮች ያስገኝለታል።
10. እውነተኛ ደስታ ሊገኝ የሚችለው ስለምን በመናገር ወይም በማሰብ ነው?
10 “በቀረውስ፣ ወንድሞች ሆይ፣ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ።” (ፊልጵስዩስ 4:8) አንድ ክርስቲያን መጥፎ ስለሆኑ ነገሮች በመናገርም ሆነ በማሰብ ምንም ደስታ አያገኝም። ዓለም የሚያቀርባቸው አብዛኛዎቹ መዝናኛዎች ደግሞ በመጥፎ ነገሮች የተሞሉ ናቸው። ማንም ሰው ቢሆን ልቡንና አእምሮውን በውሸት፣ በአጉል ቀልድ፣ ርኩስ በሆኑ፣ ብልግና ባለባቸው፣ አስነዋሪ በሆኑ፣ ጥላቻ ባለባቸውና አጸያፊ በሆኑ ነገሮች የሚሞላ ከሆነ ክርስቲያናዊ ደስታ ሊያገኝ አይችልም። በቀላል አነጋገር አእምሮውንና ልቡን በቆሻሻ ነገር በመሙላት ማንም እውነተኛ ደስታ ሊያገኝ አይችልም። በዚህ በተበላሸ የሰይጣን ዓለም ውስጥ ክርስቲያኖች የሚያሰላስሉባቸውና የሚወያዩባቸው ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች እንዳሏቸው ማወቅ ምንኛ የሚያንጽ ነው!
እንድንደሰት የሚያደርጉን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ነገሮች
11. (ሀ) በፍጹም እንደ ቀላል ነገር መታየት የሌለበት ምንድን ነው? ለምንስ? (ለ) በአንድ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ መገኘቱ ከሌላ አገር በመጣ በአንድ እንግዳና በሚስቱ ላይ ምን ስሜት አሳደረ?
11 ለደስታ ምክንያት ስለሚሆኑት ነገሮች በምንናገርበት ጊዜ ዓለም አቀፍ የሆነውን ወንድማማችነታችንን ሳንጠቅስ ማለፍ አንችልም። (1 ጴጥሮስ 2:17) የዓለም ብሔረሰቦችና ጎሣዎች በጣም እየተጠላሉ ሲሆን የአምላክ ሕዝቦች ግን እርስ በርሳቸው በፍቅር በጣም ይቀራረባሉ። በተለይ በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ይህ አንድነታቸው በግልጽ ይታያል። የዩክሬይን ዋና ከተማ በሆነችው በኪየቭ በ1993 በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከዩናይትድ ስቴትስ የሄደ አንድ እንግዳ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የደስታ እምባ፣ ብሩህ ፊት፣ እንደ ቤተሰብ ያለማቋረጥ እየተቃቀፉ መሳሳም እንዲሁም በኳስ ሜዳው ውስጥ ማዶ ለማዶ እየተያዩ በቀለማት ያሸበረቁ ጥላዎቻቸውንና መሐረባቸውን ከሚያውለበልቡት የተለያዩ ቡድኖች የሚተላለፉት ሰላምታዎች የቲኦክራሲያዊ አንድነት ጉልህ ማስረጃዎች ናቸው። ይሖዋ ዓለም አቀፍ በሆነው ወንድማማችነታችን ላይ ተአምራታዊ በሆነ መንገድ ባከናወነው ነገር ልባችን በኩራት ተሞላ። ይህም ባለቤቴንና እኔን በጥልቅ ነክቶናል። ለእምነታችንም የበለጠ ትርጉም ጨምሮለታል።”
12. ኢሳይያስ 60:22 ዓይናችን እያየ በመፈጸም ላይ ያለው እንዴት ነው?
12 ዛሬ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በፊታቸው ሲፈጸሙ ማየታቸው እንዴት እምነታቸውን የሚያጠነክርላቸው ነው! ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን የኢሳይያስ 60:22 ቃላት ተመልከት፦ “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ።” በ1914 መንግሥቲቱ በተወለደችበት ጊዜ ሲሰብክ የነበረው ታናሽ ሕዝብ ቁጥሩ 5,100 ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ባለፉት አምስት ዓመታት በእያንዳንዱ ሳምንት በአማካይ 5,628 አዲስ የተጠመቁ ምሥክሮችን በመጨመር የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ቁጥር በጣም ከፍ ብሏል። በ1993 የአገልጋዮች አዲስ ከፍተኛ ቁጥር 4,709,889 ደርሶ ነበር። እስቲ አስበው! ይህም ማለት በ1914 “ታናሽ” የነበረው ቃል በቃል “ለሺህ” ለመሆን ተጠግቷል።
13. (ሀ) ከ1914 ጀምሮ ምን ነገር እየተፈጸመ ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች በ2 ቆሮንቶስ 9:7 ላይ ያሉትን የጳውሎስ ቃላት መሠረታዊ ሥርዓት የሚጠብቁት እንዴት ነው?
13 ከ1914 ጀምሮ መሲሐዊው ንጉሥ በጠላቶቹ መካከል መግዛት ጀምሯል። ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራና የግንባታ ዘመቻ ለማካሄድ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን አስተዋጽዖ በሚያደርጉ ፈቃደኛ በሆኑ ሰብአዊ ተከታዮች አማካኝነት መሲሐዊው አገዛዙ ድጋፍ አግኝቷል። (መዝሙር 110:2, 3) የይሖዋ ምሥክሮች የሚደረገው የገንዘብ መዋጮ እነዚህን ሥራዎች ለማካሄድ ሲውል በማየታቸው በጣም ይደሰታሉ። ሆኖም በስብሰባዎቻቸው ላይ ስለ ገንዘብ ጉዳይ እምብዛም አይጠቀስም።a (ከ1 ዜና መዋዕል 29:9 ጋር አወዳድር) እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲሰጡ ጉትጎታ አያስፈልጋቸውም። እውነተኛ ክርስቲያኖች አቅማቸው በሚፈቅድላቸው መጠን ለንጉሣቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደ መብት ይቆጥሩታል። ‘እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይሰጣል፤ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።’— 2 ቆሮንቶስ 9:7
14. ከ1919 ጀምሮ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ምን ነገር ግልጽ እየሆነ መጥቷል? ይህስ ምን ለደስታ ምክንያት የሚሆን ነገር አስገኝቶላቸዋል?
14 በአምላክ ሕዝቦች መካከል ንጹሕ አምልኮ ተመልሶ እንደሚቋቋም የተነገረው ትንቢት መፈጸም መንፈሳዊ ገነት እንዲመሠረት አድርጓል። ይህ መንፈሳዊ ገነት ከ1919 ጀምሮ ደረጃ በደረጃ ወሰኑ እየሰፋ መጥቷል። (መዝሙር 14:10፤ ኢሳይያስ 52:9, 10) ውጤቱ ምን ሆነ? እውነተኛ ክርስቲያኖች “ደስታንና ተድላን” እያገኙ ነው። (ኢሳይያስ 51:11) የተገኘው ጥሩ ፍሬ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍጽምና በሌላቸው ሰዎች አማካኝነት ምን ማከናወን እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ለዚህ ሁሉ የሚመሰገነውም ሆነ የሚከበረው ይሖዋ ነው። ይሁን እንጂ የአምላክ የሥራ ባልደረቦች ከመሆን የበለጠ ምን መብት ሊኖር ይችላል? (1 ቆሮንቶስ 3:9) ቢያስፍልግ ኖሮ ይሖዋ ድንጋዮች እንኳን የእውነትን መልእክት ጮክ ብለው እንዲናገሩ ማድረግ ይችል ነበር። ሆኖም በዚህ መንገድ ለመጠቀም አልመረጠም። ከዚህ ይልቅ ከአፈር የተሠሩ ፈቃደኛ ፍጥረታት ፈቃዱን እንዲፈጽሙ ለማነሳሳት መረጠ።—ሉቃስ 19:40
15. (ሀ) በትኩረት የምንከታተለው በዘመናችን የሚፈጸሙ ምን ሁኔታዎችን ነው? (ለ) የትኛውንስ ሁኔታ በደስታ እንጠባበቃለን?
15 በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች ጎላ ካሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጋር የተያያዙትን የዓለም ሁኔታዎች በከፍተኛ ስሜት ይከታተላሉ። መንግሥታት አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት እየተፍጨረጨሩ ነው። ይሁን እንጂ ጥረታቸው ሁሉ ከንቱ ነው። እየተከሰቱ ያሉት ሁኔታዎች በተለያዩ የዓለም ችግሮች ላይ እርምጃ እንዲወስድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን እንዲጠሩ እያስገደዷቸው ነው። (ራእይ 13:15–17) ይህ በእንዲህ እንዳለ የአምላክ ሕዝቦች ከምን ጊዜውም የበለጠ አስደሳች የሆነውን ሁኔታ በጉጉት እየተጠባበቁ ናቸው። ይህ ሁኔታ የሚፈጸምበት ጊዜ በጣም እየቀረበ ነው። “የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ።”—ራእይ 19:7
መስበክ—የሚያስደስት ነው ወይስ ሸክም
16. አንድ ክርስቲያን የተማረውን በሥራ ላይ አለማዋሉ እንዴት ደስታውን ሊያሳጣው እንደሚችል በምሳሌ አስረዳ።
16 “ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። (ፊልጵስዩስ 4:9) ክርስቲያኖች የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ ካዋሉ የአምላክን በረከቶች እንደሚያገኙ ሊጠባበቁ ይችላሉ። ከተማሯቸው በጣም አስፈላጊ ነገሮች አንዱ ምሥራቹን ለሌሎች መስበክ ነው። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሕይወታቸው የተመካው ይህን መልእክት በመስማታቸው ላይ ሆኖ ሳለ ምንም ሳይነግራቸው ዝም ካለ የአእምሮ ሰላም ሊያገኝ ወይም ደስተኛ ሊሆን የሚችለው ማን ነው?—ሕዝቅኤል 3:17–21፤ 1 ቆሮንቶስ 9:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16
17. የስብከት ሥራችን ሁልጊዜ የደስታ ምንጭ ሊሆንልን የሚገባው ለምንድን ነው?
17 ስለ ይሖዋ ለመማር የሚፈልጉ በግ መሰል ሰዎችን ማግኘቱ እንዴት ያስደስታል! በትክክለኛ የልብ ዓላማ ተነሳስተው ለሚያገለግሉ ሁሉ የመንግሥቱ አገልግሎት ሁልጊዜ የደስታ ምንጭ ይሆንላቸዋል። ምክንያቱም የይሖዋ ምሥክር መሆን ማለት ዋና ዓላማው ስሙን መቀደስና ሉዓላዊ ገዢ በመሆን ያለውን ሥልጣን ከፍ ከፍ ማድረግ ስለሆነ ነው። (1 ዜና መዋዕል 16:31) ይህን ሐቅ የተገነዘበ ሰው ሰዎች ጥበብ ጎድሏቸው የሚነግራቸውን ምሥራች አንቀበልም ቢሉት እንኳን ይደሰታል። ለማያምኑ ሰዎች የሚደረገው ስብከት አንድ ቀን እንደሚያቆም ያውቃል፤ የይሖዋን ስም መቀደስ ግን ለዘላለም ይቀጥላል።
18. ክርስቲያኖች የይሖዋን ፈቃድ እንዲያደርጉ የሚገፋፋቸው ምንድን ነው?
18 እውነተኛ ሃይማኖት የተማሩትን ተግባራዊ የሚያደርጉትን ሰዎች ግዴታ ስለሆነባቸው ሳይሆን ፈልገው ይሖዋ የሚጠይቃቸውን ነገሮች ሁሉ እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል። (መዝሙር 40:8፤ ዮሐንስ 4:34) ብዙ ሰዎች ይህን መረዳት አዳጋች ሆኖባቸዋል። አንዲት ሴት ልታነጋግራት ለመጣች አንዲት የይሖዋ ምሥክር “ታውቂያለሽ፣ አንቺ ልትደነቂ ይገባሻል። እኔ አንቺ እንደምታደርጊው ስለ ሃይማኖቴ ለመስበክ ከቤት ወደ ቤት በፍጹም አልሄድም።” የይሖዋ ምሥክሯም ፈገግ በማለት “እንዴት እንደሚሰማሽ ይገባኛል። እኔ የይሖዋ ምሥክር ከመሆኔ በፊት ማንም ሰው ሄጄ ለሌሎች ሰዎች ስለ ሃይማኖት እንድናገር ሊያደርገኝ አይችልም ነበር። አሁን ግን ሄጄ መናገር እፈልጋለሁ” ስትል መለሰችላት። ሴትየዋም ትንሽ አሰበችና “የእኔ ሃይማኖት የማይሰጠው የአንቺ ሃይማኖት ግን የሚሰጠው አንድ ነገር እንዳለ ግልጽ ነው። ምናልባት ይህን ነገር መመርመር ይኖርብኛል” ስትል አስተያየቷን ደመደመች።
19. ከመቼውም ይልቅ ለመደሰት ጊዜው አሁን የሆነው ለምንድን ነው?
19 በመንግሥት አዳራሾቻችን ውስጥ ፊት ለፊት ተሰቅሎ የሚታየው የ1994 የዓመት ጥቅስ “በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን” በማለት ዘወትር ያሳስበናል። (ምሳሌ 3:5 አዓት) መሸሸጊያችን በሆነው በይሖዋ ላይ ትምክህታችንን ለመጣል ከመቻል የበለጠ እንድንደሰት ሊያደርገን የሚችል ነገር ይኖራልን? መዝሙር 64:10 “ጻድቅ በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ደስ ይለዋል፣ በእርሱም ይታመናል” በማለት ይገልጻል። ይህ የምንገዳገድበት ወይም ተስፋ የምንቆርጥበት ጊዜ አይደለም። እያንዳንዱ ወር ባለፈ ቁጥር ከአቤል ዘመን ጀምረው የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮች ሊያዩት ይጓጉለት ወደነበረው እውነታ ይበልጥ እንድንቀርብ ያደርገናል። እንድንደሰት የሚያደርጉን ከምን ጊዜውም የበለጡ ብዙ ምክንያቶች እንዳሉን በማወቅ በሙሉ ልባችን በይሖዋ ላይ የምንታመንበት ጊዜ አሁን ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ፣ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በወር አንድ ጊዜ በፈቃደኝነት ከሚደረገው መዋጮ የተገኘውን ገንዘብና የወጣውን ወጪ የሚገልጽ አጭር የሒሳብ ሪፖርት ይቀርባል። ይህ መዋጮ እንዴት ጥቅም ላይ እየዋለ እንዳለ የሚያስታውቁ ደብዳቤዎች አልፎ አልፎ ይላካሉ። በዚህ መንገድ ዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ስላለው የገንዘብ አቅም ሁሉም እንዲያውቅ ይደረጋል።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በነህምያ 8:10 መሠረት መደሰት ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ዘዳግም 26:11 እና 28:45–47 የመደሰትን አስፈላጊነት የሚያሳዩት እንዴት ነው?
◻ ፊልጵስዩስ 4:4–9 ሁልጊዜ እንድንደሰት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ የ1994 የዓመት ጥቅስ እንድንደሰት የሚያደርግ ምን ምክንያት ይሰጠናል?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩሲያውያንና ጀርመናውያን ምሥክሮች የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ክፍል በመሆናቸው ደስተኞች ናቸው
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነትን ለሌሎች ማካፈል አንዱ ለደስታ ምክንያት የሚሆን ነገር ነው