የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 8/1 ገጽ 15-20
  • ምክንያታዊነትን አዳብር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምክንያታዊነትን አዳብር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን’
  • ሁኔታዎች ሲለወጡ እርምጃንም አብሮ ማስተካከል
  • በሥልጣን አጠቃቀም ረገድ ምክንያታዊነትን ማሳየት
  • ይሖዋን ምሰሉ—ምክንያታዊ ሁኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • ይሖዋ ምክንያታዊ ነው!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ስለ ይሖዋ ልግስና እና ምክንያታዊነት ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • “ጥበበኛ ልብ አለው”—ግን ትሑት ነው
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 8/1 ገጽ 15-20

ምክንያታዊነትን አዳብር

“ምክንያታዊነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። ጌታ ቅርብ ነው።”—ፊልጵስዩስ 4:5 አዓት

1. በዛሬው ዓለም ውስጥ ምክንያታዊ መሆን ለምን ያታግላል?

“ምክንያታዊውን ሰው” እንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ሰር አላን ፓትሪክ ኸርበርት በገሃዱ ዓለም የሌለ ሰው ብለው ጠርተውታል። እውነት ነው፣ አንዳንድ ጊዜ በዚህ በብጥብጥ በተቦጫጨቀ ዓለም ውስጥ ምክንያታዊ ሰዎች ከነአካቴው የጠፉ ሊመስል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ አስጨናቂ በሆነው “በመጨረሻው ቀን” ሰዎች “ጨካኞች፣” “እኔ ያልኩት ይሁን ባዮች [አዓት]” እና “ዕርቅን የማይሰሙ”፤ በሌላ አነጋገር ምክንያታዊነት የሚባል ነገር የማያውቁ እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ያም ሆኖ ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች ምክንያታዊነት የመለኮታዊ ጥበብ አንዱ ምልክት መሆኑን በማወቅ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። (ያዕቆብ 3:17 አዓት) ምክንያታዊ ባልሆነ ዓለም ውስጥ ምክንያታዊ መሆን የማይታሰብ ነገር ነው የሚል ስሜት አያድርብንም። ከዚህ ይልቅ በፊልጵስዩስ 4:5 [አዓት] ላይ የሚገኘውን ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሣሽነት “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይታወቅ” በማለት የሰጠውን ምክር በሥራ ለማዋል የሚገጥመንን ፈታኝ ሁኔታ በጸጋ እንቀበላለን።

2. በፊልጵስዩስ 4:5 ላይ ያሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ምክንያታዊ መሆናችንንና አለመሆናችንን ለይተን ለማወቅ የሚረዱን እንዴት ነው?

2 የጳውሎስ ቃላት ምክንያታዊ መሆናችንንና አለመሆናችንን ለማወቅ እንዴት እንደሚረዱን ልብ በል። ጥያቄው እኛ ራሳችንን እንዴት እንመለከታለን የሚለው አይደለም፤ ጥያቄው ሌሎች እኛን የሚመለከቱን እንዴት ነው? በሌሎች ዘንድ የምንታወቀው በምንድን ነው? የሚል ነው። የእንግሊዝኛው የፊሊፕስ ትርጉም ይህን ጥቅስ “ምክንያታዊ ናቸው የሚል ስም ይኑራችሁ” ሲል ተርጉሞታል። እያንዳንዳችን ‘በሌሎች ዘንድ የምታወቀው በምንድን ነው? ምክንያታዊ ነው፣ እሺ ባይ ነው፣ ገር ነው የምባል ነኝን? ወይስ ሰዎች እርሱ ችክ ያለ፣ አስቸጋሪ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል ሰው ነው ይላሉ?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

3. (ሀ) “ምክንያታዊ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ምን ማለት ነው? ይህ ባሕርይ ማራኪ የሆነውስ ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን ይበልጥ ምክንያታዊ መሆንን መማር የሚችለው እንዴት ነው?

3 በዚህ ረገድ ያተረፍነው ስም በቀላሉ ኢየሱስ ክርስቶስን ምን ያህል እንደመሰልነው ያሳያል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የአባቱን አቻ የማይገኝለት የምክንያታዊነት ምሳሌ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐንስ 14:9) እንዲያውም ጳውሎስ “በክርስቶስ የዋህነትና ደግነት” ብሎ ሲጽፍ ደግነት ለሚለው የተጠቀመው ግሪክኛ ቃል (ኤፒኤኪያስ) “ምክንያታዊነት” ማለትም ነው። ወይም ቃል በቃል ሲተረጎም “እሺ ባይነት” ማለት ነው። (2 ቆሮንቶስ 10:1 አዓት) ዘ ኤክስፖዚተርስ ባይብል ኮመንታሪ “በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካሉት ዋና ዋና የጠባይ መግለጫ ቃላት አንዱ” ሲል ጠርቶታል። በጣም ማራኪ የሆነን ባሕርይ የሚገልጽ በመሆኑ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ቃሉን “ደስ የሚል ምክንያታዊነት” ብለው ተርጉመውታል። እንግዲያው ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ እንደ ይሖዋ ምክንያታዊነትን ያሳየባቸውን ሦስት መንገዶች እንወያይባቸው። በዚህ መንገድ ራሳችን ይበልጥ ምክንያታዊ መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ መማር እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 2:21

‘ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን’

4. ኢየሱስ ራሱ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ በተደጋጋሚ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” በመሆን ምክንያታዊነትን አሳይቷል። (መዝሙር 86:5 አዓት) የቅርብ ጓደኛው ጴጥሮስ ኢየሱስ በተያዘበትና ለፍርድ በቀረበበት ሌሊት ሦስት ጊዜ ኢየሱስን የካደበትን ወቅት ወደ ኋላ መለስ ብለህ ተመልከት። ኢየሱስ ራሱ ከዚያ ቀደም ብሎ “በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ” ሲል ገልጾ ነበር። (ማቴዎስ 10:33) ኢየሱስ በግትርነት ያላንዳች ምሕረት ይህን ደንብ በጴጥሮስ ላይ አዋለውን? በፍጹም፤ ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ጴጥሮስን በግል አነጋግሮታል። ይህን ያደረገው ንስሐ የገባውንና ልቡ በሐዘን ጦር የተወጋውን ሐዋርያ ለማጽናናትና አይዞህ ለማለት እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። (ሉቃስ 24:34፤ 1 ቆሮንቶስ 15:5) ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጴጥሮስ ትልቅ ኃላፊነት ተቀብሎ እንዲሠራ ኢየሱስ ፈቅዶለታል። (ሥራ 2:1–41) በዚህ ወቅት ደስ የሚል ምክንያታዊነት ከሁሉ በላቀ መንገድ በሥራ ላይ ውሎ እንመለከታለን። ይሖዋ በመላው የሰው ዘር ላይ ኢየሱስን ፈራጅ አድርጎ እንደሾመው ማሰቡ የሚያጽናና አይደለምን?—ኢሳይያስ 11:1–4፤ ዮሐንስ 5:22

5. (ሀ) ሽማግሌዎች በበጎቹ ዘንድ ምን ዓይነት ስም ሊኖራቸው ይገባል? (ለ) ሽማግሌዎች የፍርድ ጉዳዮችን ከመመልከታቸው በፊት የትኛውን ትምህርት መከለስ ይችላሉ? ለምንስ?

5 ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ፈራጆች ሆነው ሲሠሩ የኢየሱስን የምክንያታዊነት ምሳሌ ለመከተል ይጥራሉ። በጎቹ እነሱ እኛን ለመቅጣት የቆሙ ናቸው የሚል ስሜት ተሰምቷቸው እንዲፈሯቸው አይፈልጉም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስን ለመምሰል ስለሚጥሩ በጎቹ እነርሱን እንደ አፍቃሪ እረኞች አድርገው በማየት ደህንነት ይሰማቸዋል። የፍርድ ጉዳዮችን በሚመለከቱበት ጊዜ ምክንያታዊና ይቅር ለማለት ዝግጁ ለመሆን የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ከማየታቸው በፊት አንዳንድ ሽማግሌዎች በሐምሌ 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡትን “ይሖዋ፣ የማያዳላው ‘የምድር ሁሉ ፈራጅ’” እና “ሽማግሌዎች፣ በጽድቅ ፍረዱ” የሚሉትን ርዕሶች መከለሱ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። በዚህ መንገድ “አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅ መሆን፤ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ምሕረት ማድረግ” የሚለው ይሖዋ ፍርድ የሚሰጥበትን መንገድ ጠቅለል አድርጎ የሚገልጸው ሐሳብ ትዝ ሊላቸው ይችላል። ምክንያታዊ መሠረት እስካለ ድረስ ፍርድ ሲሰጥ ምሕረት ወደ ማድረግ ማዘንበሉ ስህተት አይደለም። (ማቴዎስ 12:7) ክፉ ወይም ጨካኝ መሆን ከባድ ስህተት ነው። (ሕዝቅኤል 34:4) ስለዚህ ሽማግሌዎች በፍትሕ ድንበር ውስጥ ሆነው ከፍተኛ ፍቅር የሚገለጽበትንና የምሕረትን ጎዳና መከተል የሚቻልበትን መንገድ ተግተው በመሻት ስህተት ከመፈጸም ሊድኑ ይችላሉ።—ከማቴዎስ 23:23ና ከያዕቆብ 2:13 ጋር አወዳድር።

ሁኔታዎች ሲለወጡ እርምጃንም አብሮ ማስተካከል

6. ኢየሱስ ልጅዋን የአጋንንት መንፈስ የተጠናወተባትን ሴት ባነጋገረ ጊዜ ምክንያታዊነትን ያሳየው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ ልክ እንደ ይሖዋ አዳዲስ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ወዲያውኑ ሊወስድ ያሰበውን እርምጃ እንደሚለውጥ ወይም ክስተቶቹን እንደ ሁኔታው እንደሚያስተናግድ አስመስክሯል። በአንድ ወቅት አንዲት ከአሕዛብ ወገን የሆነች ሴት የአጋንንት መንፈስ ክፉኛ የተጠናወታትን ልጅዋን እንዲፈውስላት ተማጸነችው። በመጀመሪያ በሦስት የተለያዩ መንገዶች በመጠቀም ይኸውም አንደኛ ላቀረበችው ጥያቄ መልስ ከመስጠት በመታቀብ፤ ሁለተኛ ወደ ምድር የተላከው ለአሕዛብ ሳይሆን ለአይሁዶች እንደሆነ በቀጥታ በመግለጽና ሦስተኛ ደግሞ ይህንኑ ነጥብ በደግነት የሚያስገነዝብ ምሳሌ በመናገር ሊረዳት እንደማይችል ነገራት። ሴትየዋ ግን ይህን ሁሉ በመቋቋም ከፍተኛ እምነት እንዳላት አሳየች። ኢየሱስ ይህን ያልተለመደ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ወቅት አጠቃላይ የሆነ ደንብ የሚተገበርበት ጊዜ ሳይሆን ታላላቅ ለሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምላሽ በመስጠት እርምጃን ማስተካከል የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን ተረዳ።a ስለዚህ ኢየሱስ ሦስት ጊዜ አላደርገውም ብሎ የጠቆመውን ነገር አደረገ። የሴቲቱን ልጅ ፈወሳት!—ማቴዎስ 15:21–28

7. ወላጆች ምክንያታዊነትን በምን መንገዶች ማሳየት ይችላሉ? ለምንስ?

7 እኛም ልክ እንደዚሁ ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ እርምጃቸውን ለማስተካከል ፈቃደኞች ናቸው የሚባልልን ነንን? ወላጆች ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ምክንያታዊነት ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። እያንዳንዱ ልጅ ከሌላው ፈጽሞ የተለየ በመሆኑ በአንዱ ልጅ ላይ ጥሩ ውጤት ያስገኘው ዘዴ ለሌላው ላይስማማ ይችላል። ከዚህም በላይ ልጆች እያደጉ ሲሄዱ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይለወጣሉ። ወላጆች ከዚህ ሰዓት በፊት እቤት እንድትገቡ ብለው ቀደም ሲል ለልጆቻቸው አውጥተውት የነበረውን ደንብ ከጊዜ በኋላ ማስተካከል ይኖርባቸው ይሆን? የቤተሰቡ ጥናት ሕያው በሆነ መንገድ ቢካሄድ ይሻል ይሆን? አንድ ወላጅ በአንዳንድ አነስተኛ በሆኑ ስህተቶች ከሚገባው በላይ በሚቆጣበት ጊዜ እርሱ ወይም እርሷ ትሑት ለመሆንና የፈጠሩትን ችግር ለማስተካከል ፈቃደኞች ናቸውን? በዚህ መንገድ አቋማቸውን የሚያስተካክሉ ወላጆች ሳያስፈልግ ልጆቻቸውን ከማበሳጨትና ከይሖዋ እንዲለዩ ከማድረግ መዳን ይችላሉ።—ኤፌሶን 6:4

8. የጉባኤ ሽማግሌዎች የአገልግሎት ክልሉ ከሚያስፈልጉት ነገሮች ጋር ራሳቸውን በማስማማት ረገድ ቀዳሚ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

8 ሽማግሌዎችም አዳዲስ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ግልጽ የሆኑ የአምላክ ሕግጋትን ሳይጥሱ የተከሰቱትን ነገሮች እንደሁኔታው ማስተናገድ ያስፈልጋቸዋል። የስብከቱን ሥራ በበላይነት በምትመራበት ጊዜ በክልሉ ውስጥ የሚከሰቱትን ለውጦች በንቃት ትከታተላለህን? በአካባቢው ያሉ ሰዎች የአኗኗር ዘይቤያቸው ሲለወጥ ምናልባት በምሽት የሚደረግ ምሥክርነት፣ ከመንገድ ወደ መንገድ የሚደረግ ምሥክርነት ወይም የስልክ ምሥክርነት በይበልጥ ማጠናከር ያስፈልግ ይሆናል። እነዚህን በመሰሉ መንገዶች አዳዲስ ክስተቶችን እንደሁኔታው ማስተናገድ የስብከት ተልዕኮአችንን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንወጣ ይረዳናል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 9:26) በተጨማሪም ጳውሎስ በአገልግሎቱ ራሱን ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁኔታ ጋር ያስማማ ነበር። እኛስ ለምሳሌ ያህል ሰዎችን ለመርዳት እንድንችል በአካባቢያችን ያሉ ሃይማኖቶችንና ባህሎችን ጠንቅቀን በማወቅ ልክ እንደ ጳውሎስ እናደርጋለንን?—1 ቆሮንቶስ 9:19–23

9. አንድ ሽማግሌ ችግሮቹን ለመፍታት ሲጥር ሁልጊዜ ቀደም ሲል ሲጠቀምበት በነበረው መንገድ ላይ ችክ ማለት የማይኖርበት ለምንድን ነው?

9 እነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ከምን ጊዜውም በበለጠ አስጨናቂ እየሆኑ በሄዱ መጠን እረኞች በአሁኑ ጊዜ መንጋቸው የተጋረጡበትን አንዳንድ መያዣ መጨበጫ የሚያሳጡና አስጨናቂ ችግሮች እንደሁኔታው ማስተናገድ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ሽማግሌዎች ሆይ፣ አሁን ግትር የምትሆኑበት ጊዜ አይደለም! አንድ ሽማግሌ ችግሮችን ለመፍታት የተጠቀመባቸው መንገዶች ሳይሰምሩ ቀርተው ከሆነ ወይም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ችግሮቹን አስመልክቶ አዲስ ትምህርት ማውጣቱን ተገቢ ሆኖ ካገኘው ቀደም ሲል እጠቀምበት የነበረውን ዘዴ መጠቀም አለብኝ ብሎ ችክ ማለት የለበትም። (ማቴዎስ 24:45፤ ከመክብብ 7:10​ና ከ1 ቆሮንቶስ 7:31 ጋር አወዳድር።) አንድ ታማኝ ሽማግሌ አንዲት ችግሯን በጥሞና የሚያዳምጣት ሰው በጣም ትፈልግ የነበረችን የመንፈስ ጭንቀት ያደረባት እህት ከልቡ ለመርዳት ሞከረ። ነገር ግን የመንፈስ ጭንቀቷን አቅሎ ስለተመለከተው አጥጋቢ መፍትሔ ሳይሰጣት ቀረ። ከጊዜ በኋላ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የእሷን ችግር የሚመለከት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት አትሞ አወጣ። ሽማግሌው እንደገና እርሷን ለማነጋገር ወሰነ፤ በዚህ ወቅት አዲሱን ትምህርት በመጠቀምና ጭንቀቷን በእሷ ቦታ ሆኖ በመረዳት አነጋገራት። (ከ1 ተሰሎንቄ 5:14, 15 ጋር አወዳድር።) እንዴት ያለ ግሩም የምክንያታዊነት ምሳሌ ነው!

10. (ሀ) ሽማግሌዎች እርስ በእርሳቸውና ለአጠቃላዩ የሽማግሌዎች አካል እሺ ባይነትን ማሳየት የሚኖርባቸው እንዴት ነው? (ለ) የሽማግሌዎች አካል ምክንያታዊነት የማያሳዩትን እንዴት ሊመለከታቸው ይገባል?

10 በተጨማሪም ሽማግሌዎች አንዳቸው ለሌላው የእሺ ባይነትን ጠባይ ማሳየት አለባቸው። የሽማግሌዎች አካል በሚሰበሰብበት ጊዜ ማንኛውም ሽማግሌ ስብሰባውን እሱ በፈለገው መንገድ ለማስኬድ ጫና አለማድረጉ ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ሉቃስ 9:48) በተለይ ስብሰባውን የሚመራው ሽማግሌ በዚህ ረገድ ራሱን መግታት ያስፈልገዋል። እንዲሁም አንድ ወይም ሁለት ሽማግሌዎች ከመላው የሽማግሌዎች አካል ውሳኔ ጋር ሳይስማሙ ሲቀሩ እኛ ያልነው ካልሆነ ብለው ችክ ማለት የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ አንድም ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ ምክንያታዊነት ከሽማግሌዎች እንደሚፈለግ በማስታወስ እሺ ብለው ይስማማሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3) በሌላ በኩል ደግሞ የሽማግሌዎች አካል ጳውሎስ ራሳቸውን “ልዩ ሐዋርያት” አድርገው ያቀረቡ ‘ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎችን በማስተናገዳቸው’ የቆሮንቶስ ጉባኤ ሰዎችን እንደወቀሳቸው ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:5, 19, 20 አዓት) ስለዚህ አንድን ግትር የሆነና ምክንያታዊ ያልሆነ ጠባይ የሚያሳይን ሽማግሌ ለመምከር ፈቃደኛ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህን ሲያደርጉ ግን ራሳቸውም ገርና ደግ መሆን ይኖርባቸዋል።—ገላትያ 6:1

በሥልጣን አጠቃቀም ረገድ ምክንያታዊነትን ማሳየት

11. በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ሥልጣናቸውን ይጠቀሙበት የነበረው መንገድና ኢየሱስ ሥልጣኑን ይጠቀምበት የነበረው መንገድ ምን ልዩነት አላቸው?

11 ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አባቱ የሰጠውን ሥልጣን የተጠቀመበት መንገድ ምክንያታዊ ሰው መሆኑን በደንብ አንጸባርቋል። በጊዜው ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ምንኛ የተለየ ነበር! አንድ ምሳሌ ተመልከት። የአምላክ ሕግ በሰንበት አንዳችም ዓይነት ሥራ መሥራትን ሌላው ቀርቶ እንጨት መሰብሰብን እንኳ አይፈቅድም ነበር። (ዘጸአት 20:10፤ ዘኁልቁ 15:32–36) ሃይማኖታዊ መሪዎቹ ሰዎች ሕጉን እንዴት በሥራ እንደሚያውሉት መቆጣጠር ፈለጉ። ስለዚህ በሰንበት አንድ ሰው ምን ያህል ክብደት ያለው ነገር ማንሣት እንደሚችል የመወሰኑን ሥልጣን ራሳቸው ወሰዱ። ከሁለት ደረቅ በለሶች የከበደን ነገር ማንሣት አይቻልም የሚል ደንብ አወጡ። አልፎ ተርፎም በምስማር ተመተው የተሠሩ ጫማዎች በሰንበት መደረግ የለባቸውም በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ይሟገቱ ነበር! ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት ምስማሮቹ የሚያስከትሉትን ተጨማሪ ክብደት ማንሣት ሥራን የሚጠይቅ ነገር ነው የሚል ነበር። በጠቅላላ ረቢዎቹ አምላክ ስለ ሰንበት ባወጣው ሕግ ላይ 39 ደንቦችን እንደጨመሩና በእነዚህም ላይ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሌሎች ደንቦችን እንዳከሉ ይነገራል። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ጥብቅ ደንቦችን በመጫን ወይም ውልፍት የማያደርጉ የአቋም ደረጃዎችን በማውጣት ሰዎች እየተሸማቀቁ እንዲገዙለት ለማድረግ አልጣረም።—ማቴዎስ 23:2–4፤ ዮሐንስ 7:47–49

12. ኢየሱስ የይሖዋን የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች በተመለከተ የሚወላውል አቋም አልነበረውም ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

12 ታዲያ ኢየሱስ የአምላክን የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ጠበቅ አድርጎ አልያዘም ብለን ማሰብ አለብንን? የአቋም ደረጃዎቹን በሚገባ ጠብቋል! ሕጎች ይበልጥ ውጤታማ የሚሆኑት ሰዎች ከሕጎቹ በስተጀርባ ያሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች ወደ ልባቸው ጠልቀው ሲገቡ እንደሆነ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ፈሪሳውያን ለቁጥር የሚታክቱ ደንቦችን በማውጣት ሰዎችን ለመቆጣጠር በመጣር ደፋ ቀና ሲሉ ኢየሱስ ግን ልባቸውን ለመንካት ይጥር ነበር። ለምሳሌ ያህል “ከዝሙት ሽሹ” የሚለውን የመሰሉ መለኮታዊ ሕጎችን በተመለከተ ልል መሆን እንደማይገባ አሳምሮ ያውቅ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ስለዚህ ኢየሱስ ሰዎች ወደ ጾታ ብልግና ሊመሩ ከሚችሉ ሐሳቦች እንዲጠበቁ አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴዎስ 5:28) እንዲህ ዓይነት ትምህርቶች የማያወላዱና በዚህ ግባ በዚህ ውጣ የሚሉ ሕጎችን ከመጫን የበለጠ ጥበብና ማስተዋል የሚጠይቁ ነበሩ።

13. (ሀ) ሽማግሌዎች የማይታጠፉ ሕጎችንና ደንቦችን ከማውጣት መቆጠብ ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) የአንድን ግለሰብ ሕሊና ማክበር አስፈላጊ የሚሆንባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

13 በዛሬው ጊዜም ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ልክ እንደዚሁ የሰዎችን ልብ ለመንካት ይፈልጋሉ። ስለሆነም የራሳቸውን ጥብቅ ደንብ ከመጫን ወይም የራሳቸውን አመለካከትና አስተሳሰብ ወደ ሕግ ከመለወጥ ሊጠበቁ ይችላሉ። (ከዳንኤል 6:7–16 ጋር አወዳድር።) አንዳንድ ጊዜ አለባበስንና የጸጉር አያያዝን አስመልክቶ ደግነት የተሞላበት ማሳሰቢያ መስጠቱ ተገቢና ወቅታዊ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ሽማግሌ እነዚህን የመሰሉ ጉዳዮችን ሁልጊዜ እያነሣ የሚወተውት ከሆነ ወይም እርሱን በግል ደስ የሚያሰኙትን አለባበሶች እንዲከተሉ ለመጫን የሚሞክር ከሆነ ምክንያታዊ ሰው መባሉ ሊቀርና ስሙ ሊጠፋ ይችላል። በእርግጥም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ ሌሎችን ለመቆጣጠር ከመጣር መቆጠብ አለባቸው።—ከ2 ቆሮንቶስ 1:24​ና ከፊልጵስዩስ 2:12 ጋር አወዳድር።

14. ኢየሱስ ከሌሎች የሚጠብቀው ነገር ምክንያታዊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነበር?

14 ሽማግሌዎች ‘ከሌሎች የምጠብቀው ነገር ምክንያታዊ ነውን?’ በማለት በሌላ ጉዳይም ራሳቸውን መመርመር ይፈልጉ ይሆናል። ኢየሱስ በዚህ ረገድ ምክንያታዊ ነበር። ተከታዮቹን በሙሉ ነፍስ ከሚያደርጓቸው ጥረቶች የበለጠ ነገር እንደማይጠብቅባቸውና ይህንንም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ዘወትር ይገልጽላቸው ነበር። ድሀዋ መበለት አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን ሳንቲሞቿን በመለገሷ አወድሷታል። (ማርቆስ 12:42, 43) ደቀ መዛሙርቱ ማርያም ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ነገር በማበርከቷ በነቀፏት ጊዜ “ተዉአት . . . የተቻላትን አደረገች” በማለት በኃይለ ቃል ተናግሯቸዋል። (ማርቆስ 14:6, 8) ሌላው ቀርቶ ተከታዮቹ እንደተፈለገው ሆነው ባልተገኙበት ወቅትም እንኳ ምክንያታዊ ነበር። ለምሳሌ ያህል በተያዘበት ሌሊት ሦስት የቅርብ ሐዋርያቱን ከእርሱ ጋር ነቅተው እንዲጠብቁ ቢያሳስባቸውም በተደጋጋሚ በማንቀላፋት እንደጠበቀው ሆነው አልተገኙም ነበር። ሆኖም ችግራቸውን ተረድቶ በአዘኔታ “መንፈስስ ተዘጋጅታለች፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥቷል።—ማርቆስ 14:34–38

15, 16. (ሀ) ሽማግሌዎች መንጋውን መጫን ወይም መነዝነዝ የሌለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) አንዲት ታማኝ እህት ከሌሎች የምትጠብቀውን ነገር በተመለከተ የነበራትን አመለካከት ያስተካከለችው እንዴት ነው?

15 እውነት ነው፣ ኢየሱስ ተከታዮቹን “ተጋደሉ” ሲል አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 13:24) ነገር ግን እንደዚያ እንዲያደርጉ በፍጹም ተጭኗቸው አያውቅም! መንፈሳቸውን ያነሳሳ ነበር፤ ምሳሌ ትቶላቸዋል፤ ፊት ለፊት እየሄደ ይመራቸው ነበር፤ እንዲሁም ልባቸውን ለመንካት ጥረት አድርጓል። የተቀረውን የይሖዋ መንፈስ እንዲሠራው በእምነት ተወው። ዛሬም ልክ እንደዚሁ ሽማግሌዎች መንጋው ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገል እንዲችል ማበረታታት ይኖርባቸዋል፤ ሆኖም በወቅቱ ለይሖዋ እየሰጡ ያሉት አገልግሎት በሆነ መንገድ የተጓደለ ወይም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመጠቆም በጥፋተኝነት ስሜት ማሠቃየት ወይም በኃፍረት ማሸማቀቅ አይገባቸውም። “አሁንም ብዙ ይቀራችኋል፤ አሁንም ብዙ ይቀራችኋል፤ አሁንም ብዙ ይቀራችኋል!” በማለት ችክ ያለ ግፊት ማሳደር አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ያህል እየሠሩ ያሉትን ወንድሞች ቅስም ሊሰብር ይችላል። አንድ ሽማግሌ እርሱን “ማስደሰት አስቸጋሪ” ነው የሚል ስም ካለው ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል! እንዲህ ዓይነት ባሕርይና ምክንያታዊነት አራምባና ቆቦ ናቸው!—1 ጴጥሮስ 2:18 አዓት

16 ሁላችንም ከሌሎች የምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ መሆን ይኖርበታል! አንዲት እህት እርሷና ባሏ በጠና የታመሙ እናቷን ለማስታመም የሚስዮናዊነት ሥራቸውን ካቋረጡ በኋላ እንዲህ ስትል ጻፈች፦ “በጉባኤዎች ውስጥ አስፋፊዎች ሆነን የምናገለግልባቸው እነዚህ ጊዜያት በእርግጥም ለእኛ በጣም አስቸጋሪ ጊዜያት ናቸው። በክልልና በወረዳ ሥራዎች ተጠምደን ስለነበር ይህን ከመሰሉ ብዙ ተጽዕኖዎች መጠለል ችለን ነበር። ይህንን መገንዘብ የቻልነው በድንገትና በሥቃይ ነው። ለምሳሌ ያህል ‘ያቺ እህት ለምን በዚህ ወር መበርከት ያለበትን ትክክለኛ ጽሑፍ አታበረክትም? የመንግሥት አገልግሎታችንን አላነበበችም እንዴ?’ እያልኩ አስብ ነበር። አሁን ግን ለምን እንደሆነ አውቄያለሁ። አንዳንዶች [በአገልግሎት] ማከናወን የሚችሉትና አቅማቸው የሚፈቅድላቸው ይኸው ነው።” ለምን እንዲህ አላደረጉም እያልን በወንድሞቻችን ላይ ከመፍረድ ይልቅ ላደረጉት ነገር ማመስገን ምንኛ የተሻለ ነው!

17. ምክንያታዊነትን በተመለከተ ኢየሱስ ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ ሥልጣኑን እንዴት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እንደተጠቀመበት የሚያሳይ አንድ ግሩም ምሳሌ ተመልከት። ልክ እንደ አባቱ ኢየሱስም ለሥልጣኑ አልተንገበገበም። እሱም ቢሆን ሥልጣን በውክልና የሚሰጥ ጌታ ነው። በዚህ ምድር ላይ ‘ያለውን ንብረት ሁሉ’ እንዲንከባከብ ታማኝና ልባም ባሪያውን ሾሞታል። (ማቴዎስ 24:45–47) የሌሎችን ሐሳብ ማዳመጥ አያስፈራውም ነበር። ብዙውን ጊዜ አድማጮቹን “ምን ይመስላችኋል?” እያለ ይጠይቃቸው ነበር። (ማቴዎስ 17:25፤ 18:12፤ 21:28፤ 22:42) ስለዚህ ይህ ነገር በዛሬው ጊዜ በክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ላይ መታየት ይኖርበታል። የትኛውም ዓይነት የሥልጣን ደረጃ ለማዳመጥ ፈቃደኛ እንዳይሆኑ ሊያደርጋቸው አይገባም። ወላጆች አድምጡ! ባሎች አድምጡ! ሽማግሌዎች አድምጡ!

18. (ሀ) ምክንያታዊ ናቸው የሚል ስም ያለን መሆናችንንና አለመሆናችንን እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) ሁላችንም ምን ቁርጥ ውሳኔ ብናደርግ ጥሩ ነው?

18 እያንዳንዳችን “ምክንያታዊ ናቸው” መባል እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:5 ፊሊፕስ) ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ስም እንዳለንና እንደሌለን በምን ማወቅ እንችላለን? ኢየሱስ ሰዎች ስለ እርሱ ምን እንደሚሉ ለማወቅ ጉጉት ሲያድርበት የሚያምናቸውን ወዳጆቹን ጠይቋቸው ነበር። (ማቴዎስ 16:13) ለምን ምሳሌውን አንከተልም? እርሱ ምክንያታዊ ነው፤ ግትር አይደለም ይባልልህ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ እውነቱን እንደሚነግርህ የምትተማመንበትን ሰው ልትጠይቀው ትችላለህ። በእርግጥም የኢየሱስን ፍጹም የሆነ የምክንያታዊነት ምሳሌ ለመኮረጅ ማድረግ የምትችለው ብዙ ነገር አለ! በተለይም በሌሎች ላይ የተወሰነ ሥልጣን ካለን ሥልጣናችንን ሁልጊዜ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በመጠቀምና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ከምን ጊዜውም በበለጠ ይቅር ለማለት፣ እንደ ሁኔታው ለመስተካከል ወይም አሺ ባይ ለመሆን ዝግጁ በመሆን ሁልጊዜ የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ እንከተል። እያንዳንዳችን “ምክንያታዊ” ለመሆን እንጣር!—ቲቶ 3:2

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ቴስታመንት ወርድስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥቷል፦ “ኤፒኤኪስ [ምክንያታዊ] የሆነ ሰው አንድ ነገር በሕግ ደረጃ ፍጹም ተቀባይነት ያገኘ በሥነ ምግባር ደረጃ ግን ፍጹም ስህተት የሚሆንባቸው ጊዜያት እንዳሉ ያውቃል። ኤፒኤኪስ የሆነ ሰው ከሕግ የበለጠና የላቀ አስገዳጅ ኃይል በሚኖርበት ጊዜ ሕጉን መቼ ማላላት እንደሚገባው ያውቃል።”

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ክርስቲያኖች ምክንያታዊ ለመሆን መፈለግ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

◻ ሽማግሌዎች ይቅር ለማለት ዝግጁ በመሆን ኢየሱስን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?

◻ ልክ እንደ ኢየሱስ አዲስ ሁኔታዎች ሲከሰቱ እንደ አስፈላጊነቱ እርምጃችንን ለማስተካከል መጣር የሚኖርብን ለምንድን ነው?

◻ በሥልጣን አጠቃቀም ረገድ ምክንያታዊነትን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

◻ ምክንያታዊ መሆናችንንና አለመሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ንስሐ የገባውን ጴጥሮስን ሳያቅማማ ይቅር ብሎታል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዲት ሴት ከፍተኛ እምነት ባሳየች ጊዜ ኢየሱስ አጠቃላይ የሆነ ደንብ የሚከተልበት ወቅት እንዳልሆነ ተረድቶ ነበር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች አድምጡ!

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባሎች አድምጡ!

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች አድምጡ!

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ