መልአክ
መልአኽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃልም ሆነ አጌሎስ የሚለው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎሙ “መልእክተኛ” የሚል ፍቺ አላቸው። ከመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ እነዚህ ቃላት 400 ያህል ጊዜ ተጠቅሰው ይገኛሉ። እነዚህ ቃላት መንፈሳዊ አካል ያላቸውን መልእክተኞች ለማመልከት ሲሠራባቸው “መላእክት” ተብለው ተተርጉመዋል፤ ሰብዓዊ ፍጥረታትን ለማመልከት በተሠራባቸው ቦታዎች ላይ ግን “መልእክተኞች” ተብለው ተተርጉመዋል። (ዘፍ 16:7፤ 32:3፤ ያዕ 2:25፤ ራእይ 22:8፤ “MESSENGER” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) ይሁን እንጂ በምሳሌያዊ መግለጫዎች በተሞላው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ‘መላእክት’ የሚለው ቃል ሰብዓዊ ፍጥረታትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።—ራእይ 2:1, 8, 12, 18፤ 3:1, 7, 14
መላእክት፣ መናፍስት ተብለው የተጠሩባቸው ጊዜያት አሉ፤ መንፈስ በዓይን የማይታይ ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ኃይል አለው። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘አንድ መንፈስ ወደ ፊት ወጥቶ ይሖዋ ፊት ቆመ’ እንዲሁም ‘ሁሉም ቅዱስ አገልግሎት የሚያከናውኑ መናፍስት አይደሉም?’ የሚሉ አገላለጾች ይገኛሉ። (1ነገ 22:21፤ ዕብ 1:14) መላእክት በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ አካል የለበሱ በመሆናቸው የሚኖሩት “በሰማያት” ነው። (ማር 12:25፤ 1ቆሮ 15:44, 50) በተጨማሪም “የእውነተኛው አምላክ ልጆች፣” “አጥቢያ ከዋክብት” እና “አእላፋት ቅዱሳን” ተብለው ተጠርተዋል።—ኢዮብ 1:6፤ 2:1፤ 38:7፤ ዘዳ 33:2
መላእክት እንዲያገቡና እንዲዋለዱ ተደርገው አልተፈጠሩም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ “ከአምላክ ፍጥረት የመጀመሪያ” በሆነው በበኩር ልጁ አማካኝነት አንድ በአንድ የፈጠራቸው ፍጥረታት ናቸው። (ማቴ 22:30፤ ራእይ 3:14) “[የማይታዩት ነገሮችን ጨምሮ] በሰማያት . . . ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ፣ . . . የተፈጠሩት በእሱ [ቃል ተብሎ በሚጠራው በበኩር ልጁ] አማካኝነት ነው። በተጨማሪም እሱ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በፊት ነው፤ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ወደ ሕልውና የመጡትም በእሱ አማካኝነት ነው።” (ቆላ 1:15-17፤ ዮሐ 1:1-3) መላእክት የተፈጠሩት የሰው ልጅ ከመፈጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው፤ ምክንያቱም ‘ምድር በተመሠረተች ጊዜ አጥቢያ ከዋክብት በአንድነት እልል ብለዋል፣ የአምላክም ልጆች ሁሉ በደስታ ጮኸዋል።’—ኢዮብ 38:4-7
በሰማይ ያለውን የመላእክት ሠራዊት ብዛት በተመለከተ ደግሞ ዳንኤል በራእይ ያየውን ሲገልጽ “ሺህ ጊዜ ሺዎች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍም በፊቱ ቆመው ነበር” ብሏል።—ዳን 7:10፤ ዕብ 12:22፤ ይሁዳ 14
አደረጃጀት እና ማዕረግ። በዓይን የሚታዩት ፍጥረታት የተደራጁና ማዕረግ ያላቸው እንደሆኑ ሁሉ በማይታየው ዓለም ያሉት መላእክትም የራሳቸው የሆነ አደረጃጀትና ማዕረግ አላቸው። በኃይልም ሆነ በሥልጣን ከሁሉም የሚበልጠው መልአክ የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል ነው። (ዳን 10:13, 21፤ 12:1፤ ይሁዳ 9፤ ራእይ 12:7፤ “ARCHANGEL” እና “MICHAEL No. 1” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።) ከሁሉ የላቀ ቦታ ያለው ስለሆነና ‘ለአምላክ ሕዝብ የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል’ ተብሎ ስለተጠራ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ የመራቸው መልአክ እሱ እንደሆነ ይታመናል። (ዘፀ 23:20-23) የላቀ መብትና ክብር ካላቸው መላእክት መካከል ሱራፌል ይገኙበታል። (ኢሳ 6:2, 6፤ “ሱራፌል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ (90 ጊዜ ገደማ) የተጠቀሱት ኪሩቦች ሲሆኑ ኃላፊነታቸውንና ሥራቸውን በተመለከተ ከተሰጠው መግለጫ አንጻር እነሱም በመላእክት መካከል ለየት ያለ ቦታ እንዳላቸው መረዳት ይቻላል። (ዘፍ 3:24፤ ሕዝ 10:1-22፤ “ኪሩብ ቁ. 1” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) በተጨማሪም በአምላክና በሰዎች መካከል መልእክተኞች ሆነው ያገለገሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መላእክት አሉ። ሆኖም ሥራቸው መልእክት በማስተላለፍ ብቻ የተወሰነ አይደለም። የልዑሉ አምላክ ወኪሎች እንደመሆናቸው መጠን የአምላክን ሕዝቦች በመጠበቅና በማዳን እንዲሁም ክፉዎችን በማጥፋት የአምላክን ዓላማ የማስፈጸም ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።—ዘፍ 19:1-26
ማንነት። አንዳንድ ሰዎች፣ መላእክት የአምላክን ፈቃድ እንዲፈጽሙ የሚላኩ ኃይሎች ብቻ እንደሆኑ እንጂ የራሳቸው የሆነ ማንነት እንደሌላቸው ያስባሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ብሎ አያስተምርም። እያንዳንዳቸው ስም ያላቸው መሆኑ የየራሳቸው ማንነት እንዳላቸው ያሳያል። የሁለቱ ስም ይኸውም የሚካኤልና የገብርኤል ስም መጠቀሱ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው። (ዳን 12:1፤ ሉቃስ 1:26) የሌሎቹ ስም አለመጠቀሱ ሰዎች፣ ለእነዚህ ፍጥረታት ተገቢ ያልሆነ ክብር ለመስጠትና አምልኮ ለማቅረብ እንዳይፈተኑ ጥበቃ ይሆናል። መላእክት የአምላክ ወኪሎች ሆነው ሲላኩ ተልእኳቸውን የሚፈጽሙት በራሳቸው ስም ሳይሆን በአምላክ ስም ነው። ለምሳሌ ያህል ያዕቆብ አንድን መልአክ ስሙን እንዲነግረው ቢጠይቀው መልአኩ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። (ዘፍ 32:29) ኢያሱ ጋ መጥቶ የነበረው መልአክ ማንነቱን እንዲናገር ሲጠየቅ የተናገረው “የይሖዋ ሠራዊት አለቃ” እንደሆነ ብቻ ነው። (ኢያሱ 5:14) የሳምሶን ወላጆች ወደ እነሱ የመጣውን መልአክ ስሙን በጠየቁት ጊዜ “ስሜ የሚያስደንቅ ሆኖ ሳለ ለምን ስሜን ትጠይቀኛለህ?” የሚል መልስ ለአባትየው በመስጠት ስሙን ከመናገር ተቆጥቧል። (መሳ 13:17, 18) ሐዋርያው ዮሐንስ ለመላእክት አምልኮ ለማቅረብ ሞክሮ ነበር፤ ይሁንና ከአንዴም ሁለቴ “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ እንዳታደርገው! . . . ለአምላክ ስገድ” የሚል ተግሣጽ ተሰጥቶታል።—ራእይ 19:10፤ 22:8, 9
መላእክት የራሳቸው ማንነት ያላቸው ፍጥረታት እንደመሆናቸው መጠን እርስ በርስ የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ አላቸው (1ቆሮ 13:1)፣ ሰዎች የሚናገሯቸውን የተለያዩ ቋንቋዎች መናገር ይችላሉ (ዘኁ 22:32-35፤ ዳን 4:23፤ ሥራ 10:3-7) እንዲሁም የማሰብ ችሎታቸውን ተጠቅመው ይሖዋን ማክበርና ማወደስ ይችላሉ (መዝ 148:2፤ ሉቃስ 2:13)። እርግጥ ነው፣ መላእክት ፆታ የላቸውም፤ ይህ የሆነው ግን እያንዳንዱ መልአክ የራሱ ማንነት የሌለው ኃይል ስለሆነ ሳይሆን ይሖዋ በዚህ መንገድ ስለፈጠራቸው ነው። ይሁንና መላእክት የሚገለጹት በወንድ ፆታ ነው፤ አምላክም ሆነ ልጁ ወንድ እንደሆኑ ተደርገው ስለሚገለጹ መላእክትም ሥጋ ለብሰው የሚገለጡት ምንጊዜም በወንድ ፆታ ነው። ይሁን እንጂ በኖኅ ዘመን አንዳንድ መላእክት ሥጋ ለብሰው ከሰዎች ጋር የፆታ ግንኙነት በመፈጸማቸው በሰማይ ካለው የይሖዋ መኖሪያ ተባረዋል። ይህም መላእክት እንደ ሰው ልጆች ሁሉ ትክክልና ስህተት የሆነውን የመምረጥ ነፃነትና የራሳቸው ማንነት ያላቸው ፍጥረታት እንደሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ዘፍ 6:2, 4፤ 2ጴጥ 2:4) ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መላእክት በራሳቸው ምርጫ ተነሳስተው ሰይጣን ያስነሳው ዓመጽ ተባባሪ ሆነዋል።—ራእይ 12:7-9፤ ማቴ 25:41
ኃይል እና መብት። አምላክ ሰውን የፈጠረው ‘ከመላእክት ጥቂት አሳንሶ’ (ዕብ 2:7) እንደሆነ መገለጹ መላእክት ከሰው የበለጠ የማሰብ ችሎታ እንዳላቸው ያሳያል። በኃይልም ቢሆን ከሰዎች እጅግ ይበልጣሉ። “ቃሉን የምትፈጽሙ፣ እናንተ ብርቱዎችና ኃያላን መላእክቱ ሁሉ፣ ይሖዋን አወድሱ።” ሁለት መላእክት ሰዶምና ገሞራን በእሳት ባጠፉ ጊዜ መላእክት ምን ያህል እውቀትና ኃይል እንዳላቸው ታይቷል። አንድ መልአክ ብቻ 185,000 አሦራውያን ወታደሮችን ገድሏል።—መዝ 103:20፤ ዘፍ 19:13, 24፤ 2ነገ 19:35
ከዚህ በተጨማሪ መላእክት በከፍተኛ ፍጥነት መጓዝ ይችላሉ፤ እኛ በግዑዙ ዓለም ከምናውቀው እጅግ የላቀ ፍጥነት አላቸው። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ዳንኤል እየጸለየ ሳለ ለጸሎቱ ምላሽ እንዲሰጠው አምላክ የላከው መልአክ ዳንኤል ጸሎቱን ሳይጨርስ በቅጽበት መድረስ ችሏል።—ዳን 9:20-23
መላእክት ከፍተኛ የሆነ የማሰብ ችሎታና ኃይል ያላቸው መንፈሳዊ አካላት ቢሆኑም እንኳ አንዳንድ ገደቦች አሉባቸው። ኢየሱስ እንደተናገረው ይህ ሥርዓት የሚጠፋበትን “ቀንና ሰዓት” አያውቁም። (ማቴ 24:36) የይሖዋ ዓላማዎች የሚፈጸሙበትን መንገድ በከፍተኛ ጉጉት የሚከታተሉ ቢሆንም የማያውቋቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። (1ጴጥ 1:12) አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ ሲገባ የሚደሰቱ ከመሆኑም ሌላ ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም መድረክ ላይ ሥራቸውን በይፋ ሲያከናውኑ እንደ “ትርዒት” በትኩረት ይከታተሏቸዋል። በተጨማሪም ሥልጣን ላላቸው አክብሮት ለማሳየት ሲሉ ራሳቸው ላይ ምልክት የሚያደርጉ ክርስቲያን ሴቶች፣ የሚተዉትን ግሩም ምሳሌ ይመለከታሉ።—ሉቃስ 15:10፤ 1ቆሮ 4:9፤ 11:10፤ “የማይሞት ሕይወት (የመንግሥቱ ወራሾች የማይሞት ሕይወት ያገኛሉ)” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
መላእክት የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናቸው መጠን ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት ብዙ መብቶች አግኝተዋል። መላእክት ብዙ ሰዎችን ያገለገሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አብርሃም፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ፣ ኢያሱ፣ ኢሳይያስ፣ ዳንኤል፣ ዘካርያስ፣ ጴጥሮስ፣ ጳውሎስና ዮሐንስ ይገኙበታል። (ዘፍ 22:11፤ 31:11፤ ኢያሱ 5:14, 15፤ ኢሳ 6:6, 7፤ ዳን 6:22፤ ዘካ 1:9፤ ሥራ 5:19, 20፤ 7:35፤ 12:7, 8፤ 27:23, 24፤ ራእይ 1:1) መላእክት ለሰዎች ያደረሱት መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። ከየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ይበልጥ መላእክት ብዙ ጊዜ የተጠቀሱት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ነው። በይሖዋ ታላቅ ዙፋን ዙሪያ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መላእክት ታይተዋል፤ ሰባት መላእክት ሰባቱን መለከት የነፉ ሲሆን ሌሎች ሰባት መላእክት ደግሞ የአምላክን ቁጣ የያዙትን ሰባት ሳህኖች አፍስሰዋል፤ “የዘላለም ምሥራች” የያዘ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር ነበር፤ ሌላ መልአክ ደግሞ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች” እያለ ያውጅ ነበር።—ራእይ 5:11፤ 7:11፤ 8:6፤ 14:6, 8፤ 16:1
ለክርስቶስ እና ለተከታዮቹ የሚሰጡት ድጋፍ። የአምላክ ቅዱሳን መላእክት ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈውን ሕይወት ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ በከፍተኛ ትኩረት ተከታትለዋል። የኢየሱስን መፀነስም ሆነ መወለድ ያሳወቁ ከመሆኑም ሌላ ለ40 ቀናት ከጾመ በኋላ አገልግለውታል። ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት በጌቴሴማኒ ሲጸልይ አንድ መልአክ መጥቶ አበረታቶታል። ሰዎች ሊይዙት በመጡ ጊዜ ቢፈልግ ኖሮ ከ12 ሌጌዎን የሚበልጡ መላእክትን መጥራት ይችል ነበር። በተጨማሪም መላእክት ከሞት መነሳቱን ያሳወቁ ከመሆኑም ሌላ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ በቦታው ተገኝተው ነበር።—ማቴ 4:11፤ 26:53፤ 28:5-7፤ ሉቃስ 1:30, 31፤ 2:10, 11፤ 22:43፤ ሥራ 1:10, 11
ከዚያም በኋላ ቢሆን መናፍስት የሆኑት የአምላክ መልእክተኞች በምድር ላይ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮችን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል፤ ይህም “በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው በሰማይ ባለው አባቴ ፊት ዘወትር ስለሚቀርቡ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ” በማለት ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ማቴ 18:10) “ሁሉም መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ ቅዱስ አገልግሎት የሚያከናውኑ መናፍስት አይደሉም?” (ዕብ 1:14) እነዚህ ኃያላን መላእክት ሐዋርያትን ከእስር ቤት ባስወጡበት ጊዜ እንዳደረጉት፣ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችን ለመርዳት በሚታይ ሁኔታ አይገለጡም፤ ይሁንና የአምላክ አገልጋዮች፣ በነቢዩ ኤልሳዕና በአገልጋዩ ዙሪያ እንደነበሩት መላእክት ሁሉ በዓይን የማይታየው የመላእክት ሠራዊት ጥበቃ ለማድረግ ምንጊዜም በዙሪያቸው እንደሚገኝ እርግጠኞች ናቸው። “በመንገድህ ሁሉ እንዲጠብቁህ መላእክቱን ስለ አንተ ያዛል።” በእርግጥም፣ “የይሖዋ መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል፤ ደግሞም ይታደጋቸዋል።”—መዝ 91:11፤ 34:7፤ ሥራ 5:19፤ 2ነገ 6:15-17
በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ “ስንዴውን ከእንክርዳዱ” እንዲሁም “በጎቹን ከፍየሎቹ” ለይቶ ፍርድ ለመስጠት በሚመጣበት ጊዜ መላእክት አጅበውት እንደሚመጡ ተገልጿል። የአምላክ መንግሥት በሰማይ በተወለደበት ጊዜ ሚካኤል ከዘንዶውና ከአጋንንቱ ጋር ሲዋጋ መላእክት ከጎኑ ተሰልፈው ነበር። ከዚህም ሌላ የነገሥታት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ፣ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን በሚያደርገው ውጊያ መላእክት ድጋፍ ይሰጡታል።—ማቴ 13:41፤ 25:31-33፤ ራእይ 12:7-10፤ 19:14-16