የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አለባበስህና አጋጌጥህ በአምላክ ፊት የሚያመጣው ለውጥ ይኖራልን?
“ማውጫው የመጽሐፉን ይዘት እንደሚናገር ሁሉ ... የአንድ ወንድ ወይም የአንዲት ሴት ውጫዊ አቋምና የለበሱት ልብስ ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንዳላቸው ያሳያል።”—እንግሊዛዊው ጸሐፌ ተውኔት ፊሊፕ ማሲንጀር
ሦስተኛው መቶ ዘመን አዘአ የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊ የነበረው ታይተስ ክሌመንስ አለባበስንና አጋጌጥን የሚመለከት ረዥም ዝርዝር ደንብ አዘጋጅቶ ነበር። ጌጣ ጌጦችና የቅንጦት ወይም በቀለማት ያሸበረቁ ልብሶች የተከለከሉ ነበሩ። ሴቶች ፀጉራቸውን ቀለም መቀባትም ሆነ “ሌላውን ሊያጠምዱ የሚችሉ አሳሳች ማባበያዎች ፊታቸውን መቀባባት” ማለትም “መኳኳል” የለባቸውም። ወንዶች በራሳቸው ላይ ያለውን ፀጉር እንዲላጩ ታዘዋል፤ ምክንያቱም “ቀምቀሞ ፀጉር ... ሰውዬው ኮስታራ ገጽታ እንዲኖረው ያደርጋል።” ሆኖም በአገጭ ላይ የሚገኘው ጢም “ለፊት ሞገስንና የአባትነትን ግርማ ስለሚያላብስ” መነካት የለበትም።a
ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ የፕሮቴስታንቱ መሪ ጆን ካልቪን ተከታዮቹ የሚለብሱትን ልብስ ቀለምና ዓይነት የሚወስኑ ሕጎች አውጥቶ ነበር። ጌጣ ጌጥና የዳንቴል ልብሶች የተከለከሉ ነበሩ፤ እንዲሁም አንዲት ሴት ፀጉሯን “ሥነ ምግባር የጎደለው እስከሚባለው ደረጃ ካስረዘመች” ትታሰር ነበር።
ሃይማኖታዊ መሪዎች ከጊዜ በኋላ የፈጠሯቸው እንደነዚህ ያሉ ጽንፈኝነት የሚንጸባረቅባቸው አመለካከቶች ቅን ልቦና ያላቸው ብዙ ሰዎች እንደሚከተለው ብለው እንዲጠይቁ አድርገዋቸዋል:- የምለብሰው ልብስ በአምላክ ፊት የሚያመጣው ለውጥ ይኖራልን? አንዳንድ ዘመን አመጣሽ አለባበሶችን መከተል ወይም ውበት በሚሰጡ ቅባቶች መጠቀም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውምን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?
የግል ጉዳይ
ደስ የሚለው ነገር በዮሐንስ 8:31, 32 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “በቃሌ ብትኖሩ ... እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏቸዋል። አዎን፣ ኢየሱስ ያስተማራቸው እውነቶች ሰዎችን ከአጉል ባህልና የሐሰት ትምህርቶች ካስከተሏቸው ጨቋኝ ሸክሞች ነፃ ለማውጣት የታቀዱ ነበሩ። ‘ደካሞችንና ሸክማቸው የከበዳቸውን’ ለማሳረፍ የታለሙ ነበሩ። (ማቴዎስ 11:28) ኢየሱስም ሆነ አባቱ ይሖዋ አምላክ ግለሰቦች የግል ጉዳዮቻቸውን በራሳቸው ተነሳስተውና የማመዛዘን ችሎታቸውን ተጠቅመው መወሰን እስከማይችሉ ድረስ ሕይወታቸውን የመቆጣጠር ፍላጎት የላቸውም። ይሖዋ ‘መልካሙንና ክፉውን በመለየት ረገድ የሠለጠነ የማስተዋል ችሎታ ያላቸው’ የጎለመሱ ሰዎች እንዲሆኑ ይፈልጋል።—ዕብራውያን 5:14
ይህም በመሆኑ አይሁዳውያን በዙሪያቸው ከነበሩት ብሔራትና ሥነ ምግባር ከጎደለው ተጽእኗቸው የተለዩ እንዲሆኑ ታስቦ ከተሰጧቸው በሙሴ ሕግ ውስጥ ከተካተቱ አለባበስን ከሚመለከቱ አንዳንድ ቀጥተኛ ደንቦች በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስ አለባበስንና አጋጌጥን ወይም መኳኳያ ቅባቶችን አስመልክቶ ዝርዝር ሕጎችን አይሰጥም። (ዘኁልቁ 15:38–41፤ ዘዳግም 22:5) በመሠረቱ በክርስቲያናዊው ዝግጅት ውስጥ አለባበስና አጋጌጥ ለግል ምርጫ የተተወ ጉዳይ ነው።
ይሁን እንጂ የምንለብሰው ልብስ በአምላክ ፊት ለውጥ የለውም ወይም ማንኛውም ዓይነት ልብስ ተቀባይነት አለው ማለት አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ በአለባበስና በአጋጌጥ ረገድ የአምላክን አመለካከት የሚያንጸባርቁ ምክንያታዊ መመሪያዎች ይዟል።
“በልከኝነትና ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ”
ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ሴቶች “በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር [“በልከኝነትና ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣” NW] ሰውነታቸውን ይሸልሙ . . . እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቊ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ” ሲል ጽፏል። በተመሳሳይም ጴጥሮስ ‘ጠጉርን መሸረብንና ወርቅን ማንጠልጠልን’ በመቃወም ጽፏል።—1 ጢሞቴዎስ 2:9፤ 1 ጴጥሮስ 3:3
ጴጥሮስና ጳውሎስ ክርስቲያን ሴቶችና ወንዶች ውጫዊ ገጽታቸውን የሚያስውብ ምንም ነገር ማድረግ የለባቸውም ማለታቸው ነበርን? በጭራሽ! እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ጌጣጌጦችን ወይም የመኳኳያ ቅባቶችንና ሽቶዎችን የተጠቀሙ የታመኑ ወንዶችንና ሴቶችን ይጠቅሳል። አስቴር ንጉሥ አርጤክስስ ፊት ከመቅረቧ በፊት ጥሩ መዓዛ ያላቸውን ቅባቶች በመጠቀምና ሰውነቷን በመታሸት ረዘም ላለ ጊዜ ውበቷን ስትንከባከብ ቆይታለች። እንዲሁም ዮሴፍ ከተልባ እግር የተሠራ የሚያምር ልብስና የወርቅ ሃብል አድርጎ ነበር።—ዘፍጥረት 41:42፤ ዘጸአት 32:2, 3፤ አስቴር 2:7, 12, 15
ጳውሎስ “ጤናማ አስተሳሰብ” የሚለውን ሐረግ የተጠቀመበት መንገድ የሰጠውን ማሳሰቢያ እንድናስተውል ይረዳናል። መሠረታዊው የግሪክኛ ቃል ረጋ ማለትንና ራስን መግዛትን ያመለክታል። ጭምት መሆንን ማለትም የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ አለመሞከርን ያመለክታል። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ቃል “ልባምነት፣” “አስተዋይነት፣” “ጥንቁቅነት” ወይም “ራስን መግዛት” የሚል ፍቺ ይሰጡታል። ይህ ባሕርይ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሊያሟሉት የሚገባ ተፈላጊ ብቃት ነው።—1 ጢሞቴዎስ 3:2
ስለዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች አለባበሳችንና አጋጌጣችን ልከኛና ሥርዓታማ እንዲሆን ሲመክሩን ሌሎችን ቅር ሊያሰኙ የሚችሉ እንዲሁም ራሳችንንም ሆነ ክርስቲያን ጉባኤን የሚያስነቅፉ ቅጥ ያጡ አለባበሶችንና አጋጌጦችን እንድናስወግድ ማበረታታቸው ነው። አምላክን እንፈራለን የሚሉ ሰዎች ሰውነታቸውን በማሳመር ሌሎች በውጫዊ ገጽታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ከማድረግ ይልቅ ጤናማ አስተሳሰብ እንዳላቸው ማሳየትና “የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው” ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል። ጴጥሮስ ሲያጠቃልል ይህ “በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ” ነው ብሏል።—1 ጴጥሮስ 3:4
ክርስቲያኖች ‘ለዓለም በቲያትር መድረክ ላይ እንዳሉ ተዋንያን’ ናቸው። በተለይ ደግሞ የተጣለባቸውን ምሥራቹን የመስበክ አደራ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሌሎች ላይ ስለሚያሳድሩት ተጽእኖ ማሰብ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 4:9፤ ማቴዎስ 24:14) ስለዚህ አለባበሳቸውንና አጋጌጣቸውን ጨምሮ ሰዎች ይህን አስፈላጊ መልእክት እንዳይሰሙ ትኩረታቸውን የሚሰርቅ ምንም ነገር ማድረግ አይፈልጉም።—2 ቆሮንቶስ 4:2
አለባበስም ሆነ አጋጌጥ ከቦታ ወደ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ግለሰቦች ጥበብ ባለበት መንገድ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ግልጽና ምክንያታዊ መመሪያዎች ይሰጣል። ሰዎች እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች አጥብቀው እስከተከተሉ ድረስ አምላክ በነፃነትና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በአለባበስና በአጋጌጥ ረገድ ሁሉም ሰው የግል ምርጫውን እንዲያደርግ ይፈቅዳል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን በማጣመም እነዚህን እገዳዎች የሚደግፉ ሐሳቦች ለማግኘት ተሞክሮ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ነገር ባይናገርም ሰፊ ተደማጭነት የነበረው የሃይማኖት ምሁሩ ተርቱሊያን፣ ሴት ልጅ “ለመጀመሪያው ኃጢአትና ለሰው ልጅ ኩነኔ” መንስዔ በመሆኗ ሴቶች “እንደ ሔዋን በሐዘን እየተደቆሱና እየተጸጸቱ” መኖር አለባቸው ሲል አስተምሯል። እንዲያውም በተፈጥሮ ቆንጆ የሆነች ሴት ውበቷን መደበቅ አለባት እስከ ማለት ደርሶ ነበር።—ከሮሜ 5:12–14፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:13, 14 ጋር አወዳድር።