የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 11/1 ገጽ 19-21
  • በጃፓን የሃይማኖት ነፃነት ተከበረ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በጃፓን የሃይማኖት ነፃነት ተከበረ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • አከራካሪው ጉዳይ ምን ነበር?
  • የአውራጃው ፍርድ ቤት ውሳኔ ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ ሰዎችን አስቆጣ
  • የከሳሾቹ ራስ ወዳድነት የሌለበት ዝንባሌ
  • ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት
  • ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 11/1 ገጽ 19-21

በጃፓን የሃይማኖት ነፃነት ተከበረ

በጃፓን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ወጣት ተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን የመከተል አሊያም ሕሊናቸውን የሚያስጥሳቸውን ሥርዓተ ትምህርት የመቀበል አስቸጋሪ ምርጫ ለበርካታ ዓመታት ከፊታቸው ተደቅኖ ነበር። የዚህ አስቸጋሪ ምርጫ መንስኤ ምን ነበር? ራስን የመከላከያ ዘዴዎች መለማመድ በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የአካል ማጎልመሻ ትምህርት አንዱ ክፍል ስለ ነበር ነው። ወጣት የይሖዋ ምሥክሮቹ እነዚህ ልምምዶች እንደ ኢሳይያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 4 ካሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እንደማይጣጣሙ ተሰማቸው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፣ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።”

ወጣት ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮቹ ሌላን ሰው መጉዳትን የሚጨምሩትን ከጦርነት ጋር የሚዛመዱ ስልቶች ለመማር ሕሊናቸው ስላልፈቀደላቸው በዚህ ሥልጠና እንደማይሳተፉ ለአስተማሪዎቻቸው ገለጹ። ብዙ አስተዋይ አስተማሪዎች እነዚህ ተማሪዎች የትምህርት ቤቱን ሥርዓተ ትምህርት እንዲቀበሉ ለማሳመን ከሞከሩ በኋላ የተማሪዎቹን ሕሊና ለማክበርና ሌሎች አማራጭ እንቅስቃሴዎችን ለማዘጋጀት ተስማምተው ነበር።

ሆኖም አንዳንድ መምህራን በዚህ በጣም ከመቆጣታቸውም በላይ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች እነዚህ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በአካል ማጎልመሻ ትምህርት ምክንያት ለውጤት እንዳይበቁ አድርገዋቸዋል። ራስን የመከላከያ ዘዴዎች አንማርም በማለታቸው የተነሣ በ1993 ቢያንስ ዘጠኝ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሁለተኛ ዓመት እንዳይዛወሩና በግድ ትምህርት እንዲያቋርጡ ወይም ከትምህርት ቤት እንዲባረሩ ተደርገዋል።

ወጣት ክርስቲያኖቹ ሕሊናቸውን ሳይጥሱ አንድን ትምህርት መከታተል እንዲችሉ መብታቸውን ማስከበር የሚያስፈልግበት ጊዜ እንደ ነበር ግልጽ ነው። የኮቤ ከተማ የኢንዱስትሪ ቴክኒካል ኮሌጅ (በአጭሩ የኮቤ ቴክ) ወደ ሁለተኛ ዓመት እንዳይዛወሩ ያደረጋቸው አምስት ተማሪዎች ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ወሰኑ።

አከራካሪው ጉዳይ ምን ነበር?

በ1990 የጸደይ ወራት አምስት ተማሪዎች ወደ ኮቤ ቴክ ኮሌጅ ሲገቡ በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናቸው ምክንያት በኪንዶ (በጃፓናውያን የሻሞላ ጨዋታ) ልምምዶች እንደማይካፈሉ ለአስተማሪዎቻቸው ገልጸው ነበር። ይህን ጉዳይ የአካል ማጎልመሻ ትምህርት ፋኩልቲ አጥብቆ የተቃወመ ከመሆኑም በላይ በአካል ማጎልመሻ ትምህርት ውጤት ማግኘት የሚያስችሏቸውን ማናቸውንም አማራጭ መንገዶች ነፈጋቸው። ከዚህ በኋላ ተማሪዎቹ በአካል ማጎልመሻ ትምህርት በመውደቃቸው ምክንያት የመጀመሪያውን ክፍል (የመጀመሪያውን ዓመት የኮሌጅ ኮርስ) ለመድገም ተገደዱ። ትምህርት ቤቱ የወሰደው እርምጃ ሕገ መንግሥቱ ካረጋገጠው የሃይማኖት ነፃነት ጋር የሚጻረር ነው በማለት ተማሪዎቹ በኮቤ የአውራጃ ፍርድ ቤት ሚያዝያ 1991 የክስ ፋይል ከፈቱ።a

ትምህርት ቤቱ አማራጭ እንቅስቃሴዎችን ማዘጋጀት ለአንድ ሃይማኖት ማዳላት ይሆናል፤ ይህ ደግሞ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ያላቸውን የገለልተኛነት አቋም ያስጥሳል ሲል ተናገረ። ከዚህም በላይ አማራጭ የአካል ማጎልመሻ ትምህርት ለማዘጋጀት የሚረዱ መሣሪያዎችም ሆኑ የሰው ኃይል የለንም አለ።

የአውራጃው ፍርድ ቤት ውሳኔ ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ ሰዎችን አስቆጣ

ክሱ እየተደመጠ ባለበት ወቅት ከአምስቱ ተማሪዎች መካከል ሁለቱ አሁንም በአካል ማጎልመሻ ትምህርት የተነሣ ሲወድቁ ሦስቱ ለጥቂት አልፈው ወደ ሁለተኛ ዓመት ገቡ። የትምህርት ቤቱ ደንብ የትምህርት ችሎታቸው ደካማ የሆነና በተከታታይ ለሁለት ዓመት የሚደግሙ ተማሪዎች እንደሚባረሩ ይገልጻል። በዚህ ምክንያት ከሁለቱ ተማሪዎች አንዱ ከመባረሩ በፊት ትምህርት ለማቋረጥ የወሰነ ሲሆን ኩኒሂቶ ኮባያሺ የተባለው ሌላው ተማሪ ግን ትምህርቱን ለመቀጠል ፈለገ። በዚህም ምክንያት ከትምህርት ቤቱ ተባረረ። ኩኒሂቶ 48 ነጥብ በማግኘት የወደቀበትን የአካል ማጎልመሻ ትምህርት ጨምሮ በሁሉም ትምህርቶች ያመጣው አማካይ ውጤት 90.2 ከመቶ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። በክፍሉ ውስጥ ከነበሩት 42 ተማሪዎች መካከል አንደኛ ወጥቶ ነበር።

የካቲት 22, 1993 የዋለው የኮቤ አውራጃ ፍርድ ቤት ችሎት እንዲህ በማለት ለኮቤ ቴክኒካል ኮሌጅ ፈረደ፦ ምንም እንኳ “በኪንዶ ልምምዶች መሳተፍን የሚጠይቀው የትምህርት ቤቱ መመሪያ የከሳሾቹን የአምልኮ ነፃነት በመጠኑ እንደገደበ ባይካድም ትምህርት ቤቱ የወሰደው እርምጃ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር አይደለም።”

ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ከሳሾቹ ለከፍተኛ የሕግ ባለ ሥልጣናት ይግባኝ አሉ። (ሥራ 25:11, 12) ክሱ ወደ ኦሳካው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተዛወረ።

የከሳሾቹ ራስ ወዳድነት የሌለበት ዝንባሌ

ፕሮፌሰር ቴትሶ ሺሞሙራ የተባሉ አንድ የትሱኩባ ዩኒቨርሲቲ ታዋቂ ምሁር በሙያቸው የዓይን ምሥክር በመሆን በኦሳካው ፍርድ ቤት ውስጥ የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ተስማሙ። የትምህርትና የሕግ ባለሙያ እንደ መሆናቸው መጠን ትምህርት ቤቱ በተማሪዎቹ ላይ እርምጃ ሲወስድ ምን ያህል መብታቸውን እንደተጋፋ ጠበቅ አድርገው ገለጹ። ኩኒሂቶ ኮባያሺ አስተያየቱን ለፍርድ ቤቱ የገለጸ ሲሆን ቀና አመለካከቱ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ልብ ነክቷል። ከዚህም በላይ በየካቲት 22, 1994 የኮቤ ጠበቆች ማኅበር ትምህርት ቤቱ የወሰዳቸው እርምጃዎች የኩኒሂቶን የአምልኮ ነፃነትና የመማር መብት የሚጋፋ እንደሆነ በመግለጽ ትምህርት ቤቱ እንደገና እንዲያስገባው ጠይቋል።

የኦሳካው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚደመጥበት ጊዜ ሲቃረብ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወጣት ክርስቲያኖች በሙሉ በሙግቱ እስከ መጨረሻው ለመግፋት ጓጉተው ነበር። በጃፓን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ የሆነ አከራካሪ ጉዳይ ላጋጠማቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ትግል በማድረግ ላይ እንዳሉ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ስላልተባረሩ ፍርድ ቤቱ ክሳቸውን ሊሰርዘው ይችል ነበር። በተጨማሪም ጥያቄያቸውን ቢተዉት ትምህርት ቤቱ ኩኒሂቶን አለአግባብ ማባረሩ በግልጽ እንደሚታወቅ ለመረዳት ችለው ነበር። ስለዚህ ከኩኒሂቶ በስተቀር ሁሉም ተማሪዎች ክሱን ለመተው ወሰኑ።

ታኅሣሥ 22, 1994 የኦሳካው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ የሆኑት ራሱኪ ሺማዳ የኮቤ የአውራጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ብያኔ የሚሽር ውሳኔ አስተላለፉ። ፍርድ ቤቱ ኩኒሂቶ የኪንዶ ልምምዶችን ያልተቀበለው በቅንነት እንደሆነና በእምነቱ ምክንያት በወሰደው እርምጃ ሳቢያ የደረሰበት ጉዳት በጣም ከፍተኛ መሆኑን ለመረዳት ቻለ። ዋና ዳኛ የነበሩት ሺማዳ ትምህርት ቤቱ አማራጭ እንቅስቃሴዎችን ማዘጋጀት ነበረበት ብለዋል። ፍርድ ቤቱ የሰጠው ጥሩ ውሳኔ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል። ሆኖም ትምህርት ቤቱ ጉዳዩን ለጃፓን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት ኩኒሂቶ ለሌላ ከአንድ ዓመት በላይ የሆነ ጊዜ የመማር ዕድል እንዲያጣ አድርጓል።

ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ቆየት ብሎ ኮቤ ሺምቡን የተባለ አንድ ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ላይ እንዲህ በማለት ገልጾ ነበር፦ “የኮቤ ከተማ ትምህርት ቤቶች ቦርድም ሆነ ትምህርት ቤቱ በዚያን ጊዜ [የኦሳካው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሰጠው ውሳኔ በኋላ] አቶ ኮባያሺ ወደ ትምህርት ቤቱ ተመልሶ እንዲገባ መፍቀድ ነበረባቸው። . . . ተገቢ ባልሆነ የአመለካከት ግጭት ሳቢያ ተማሪው በወጣትነቱ እውቀት ሊቀስምበት የሚገባውን በጣም አስፈላጊ የሆነ ጊዜ በከንቱ እንዲያልፍ አድርገዋል።” ያም ሆኖ ግን የኮቤ ቴክኒካል ኮሌጅ በዚህ ረገድ ጥብቅ አቋም ወስዷል። በዚህም ምክንያት ጉዳዩ አገር አቀፍ መወያያ ርዕስ ሆኖ ነበር። በመላው አገሪቱ የሚገኙ አስተማሪዎችና የትምህርት ቤት ባለ ሥልጣናት ስለ ጉዳዩ ያወቁ ሲሆን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ብያኔ ወደፊት ተመሳሳይ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ጠንካራ ሕጋዊ መሠረት የሚሆን ነበር።

ትምህርት ቤቱ ጉዳዩን ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ካለ ከአንድ ሳምንት በኋላ ጥር 17, 1995 በኮቤ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ኩኒሂቶና ቤተሰቡ የሚኖሩባትን የአሺያ ከተማ አናወጠ። የመሬት መንቀጥቀጡ አካባቢውን ከመምታቱ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሰዓት ተኩል ሊሆን ሲል ኩኒሂቶ የትርፍ ጊዜ ሥራውን ለማከናወን ከቤቱ ወጥቶ ነበር። ከሃንሺን ኤክስፕረስ ጎዳና በታች በብስክሌት በሚጓዝበት ወቅት የመሬት መናወጡ ተከሰቶ ድምጥማጡ ወደ ጠፋበት አካባቢ ተቃርቦ ነበር። ወዲያውኑ ወደ ቤቱ ሲመለስ ምድር ቤቱን ፈጽሞ ፈራርሶ አገኘው። ኩኒሂቶ በመሬት መንቀጥቀጡ ሕይወቱን በቀላሉ ሊያጣ ይችል እንደ ነበር ተገነዘበ፤ በሕይወት እንዲተርፍ በመፍቀዱም ይሖዋን አመሰገነ። ቢሞት ኖሮ የኪንዶ ልምምድን አስመልክቶ የተነሣው ክስ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሳይሰጥበት ሊቀር ይችል ነበር።

ብዙውን ጊዜ በጃፓን የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኞችን በጽሑፍ ከመረመረ በኋላ ሌሎች የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጧቸው ብያኔዎች ትክክል መሆናቸውን ወይም አለመሆናችውን ይፈርዳል። የበታች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብያኔ ለመሻር የሚያስችል ከባድ ምክንያት ካልኖረ በስተቀር ክርክሮች አይደመጡም። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚያሳልፍበት ቀን መቼ እንደሆነ ለከሳሹም ሆነ ለተከሳሹ አያሳውቅም። ስለዚህ መጋቢት 8, 1996 ጠዋት ብያኔው እንደሚሰጥ ሲነገረው ኩኒሂቶ ፈጽሞ ያላሰበው ነገር ነበር። ኩኒሂቶ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የኦሳካው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ እንደደገፈ ሲሰማ በደስታ ፈነደቀ።

ዳኛው ሺኒቺ ካዊ የመሩት የአራት ዳኞች ቡድን “ትምህርት ቤቱ የወሰደው እርምጃ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ካገኙ ልማዶች አንፃር ሲታይ እጅግ ተገቢ ያልሆነና ሕጉ የሚሰጣቸውን መብቶች ካለማጤን የተፈጸመ ስለሆነ ፈጽሞ ሕገ ወጥ እንደሆነ ተደርጎ መታየት ይኖርበታል” በማለት በሙሉ ድምፅ ወስኗል። ኩኒሂቶ በኪንዶ ልምምዶች ለመሳተፍ ያልፈለገው በቅን ልቦና መሆኑን ፍርድ ቤቱ ሲያረጋግጥ “በይግባኝ የተከሰሰው ግለሰብ በኪንዶ ልምምዶች ለመሳተፍ ያልፈለገው በቅን ልቦና ሲሆን ይህም ከመሠረታዊ እምነቱ ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው” ብሏል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትምህርት ቤቱ በይግባኝ የተከሰሰውን ግለሰብ እምነት በማክበር አማራጭ መንገዶችን ሊያዘጋጅ ይችል እንደ ነበርና ማዘጋጀትም እንዳለበት ፈርዷል።

ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል

ይህ ውሳኔ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የአምልኮ ነፃነት እንዲከበር ጥሩ ሕጋዊ መሠረት እንደሚሆን አያጠራጥርም። ዘ ጃፓን ታይምስ “በትምህርትና በሃይማኖት ነፃነት ረገድ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው ነው” ብሏል። ሆኖም ውሳኔው የእምነት ፈተናዎች ሲያጋጥሙት እያንዳንዱ ወጣት ተማሪ የራሱን የሕሊና አቋም እንዲወስድ ካለበት ኃላፊነት ነፃ እንዲሆን አያደርግም።

የቱሱኩባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማሳዩኪ ዩኪኖ እንዳሉት ዳኞቹ ለኩኒሂቶ እንዲፈርዱለት ከገፋፋቸው ምክንያቶች አንዱ “የላቀ ውጤት ያስመዘገበ ጎበዝ ተማሪ” መሆኑ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የእምነት ፈተናዎች ለሚያጋጥሟቸው ክርስቲያኖች የሚከተለውን ምክር ይሰጣል፦ “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 2:12) ታማኝ የሆኑ ወጣት ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው በመኖር ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋማቸው በሰዎቸ ዘንድ አክብሮት እንዲያስገኝላቸው ሊያደርጉ ይችላሉ።

ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ኩኒሂቶ ኮባያሺ እንደገና ወደ ኮቤ ቴክኒካል ኮሌጅ እንዲገባ ተፈቅዶለታል። ከኩኒሂቶ ጋር ወደ ትምህርት ቤቱ ገብተው የነበሩ አብዛኞቹ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ተመርቀዋል። ኩኒሂቶ በአሁኑ ጊዜ በዕድሜ ከእሱ በአምስት ዓመት ከሚያንሱ ተማሪዎች ጋር በመማር ላይ ነው። በአብዛኞቹ ዓለማውያን አመለካከት አምስት ዓመት ሙሉ በጣም አስፈላጊ የሆኑ የመማር አጋጣሚዎችን አጥቷል። ሆኖም ኩኒሂቶ ያሳየው ፍጹም አቋም በይሖዋ አምላክ ፊት ትልቅ ግምት የሚሰጠው ከመሆኑም በተጨማሪ እሱ የከፈላቸው መሥዋዕቶች ከንቱ ሆነው እንዳልቀሩ ግልጽ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት እባክህ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የጥቅምት 8, 1995 የእንግሊዝኛ ንቁ! ከገጽ 10 እስከ 14 ተመልከት።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በስተግራ፦ የኩኒሂቶ ቤት ከመሬት መንቀጥቀጡ በኋላ

ከታች፦ ኩኒሂቶ በዛሬው ጊዜ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ