የአንባቢያን ጥያቄዎች
የምሳሌ 30:19 ጸሐፊ አንድ ወንድ አንዲትን ቆንጆ በተንኮል ማሳሳቱ “በጣም ድንቅ” እንደሆነ በእርግጥ ተሰምቶት ነበርን?
የምሳሌ 30:19 አንዱ ትርጉም ይህ ሊሆን ይችላል። የጥቅሱ ትርጉሙ በቀላሉ ሊገባን እንደማይችል የማይካድ ነው።
የዚህን ጥቅስ ትክክለኛ ስሜት ለማወቅ በምንፈልግበት ጊዜ በዙሪያው ያሉትን ሐሳቦች መመልከት ይኖርብናል። በመንፈስ ተመርቶ የጻፈው ጸሐፊ ከዚህ ሐረግ በፊት በቃኝ የማይሉ አራት ነገሮችን ጠቅሷል። (ምሳሌ 30:15, 16) ከዚያም በመቀጠል የሚከተሉትን ዘርዝሯል፦ “ሦስት ነገር ይገርመኛል [በጣም ድንቅ የሆኑብኝ ሦስት ነገሮች አሉ አዓት] አራተኛውንም ከቶ አላስተውለውም፤ እነርሱም የንስር መንገድ በሰማይ፣ የእባብ መንገድ በድንጋይ ላይ፣ የመርከብም መንገድ በባሕር ልብ ላይ፣ የሰውም መንገድ ከቆንጆ ጋር ናቸው።”—ምሳሌ 30:18, 19
በእነዚህ አራት ነገሮች ውስጥ ‘ድንቅ’ የሆነው ነገር ምን ሊሆን ይችላል?
ምናልባት ‘ድንቅ’ የሚለው ቃል መልካም ወይም ጥሩ የሆነን ነገር ስለሚያመለክት አንዳንድ ምሁራን በምሳሌ ላይ የተጠቀሱት አራቱም ነገሮች የአምላክን የፍጥረት ጥበብ ያሳያሉ ይላሉ። ይኸውም አንድ ትልቅ ወፍ በሰማይ ለመብረር መቻሉ፣ እግር የሌለው እባብ ከዐለት ወደ ዐለት ለመሄድ መቻሉ፣ ከባድ የሆነው መርከብ በሚናወጠው ባሕር ላይ ለመንሳፈፍ መቻሉና ጠንካራው ወጣት በቀላሉ በአንዲት ቆንጆ ፍቅር መውደቁ፣ እሷንም ማግባቱና ከዚያም ድንቅ ልጅ መውለዳቸው ያስገርማል። አንድ ፕሮፌሰር በአራቱ ነገሮች ተመሳሳይነት ያለው ሌላ ነገር አግኝተዋል። ይኸውም እያንዳንዳቸው የሚጓዙት ሁልጊዜ አዲስ በሆነ መሥመር ነው። ንስር፣ እባብና መርከብ ሁልጊዜ በአዲስ መንገድ ይጓዛሉ። ሁለት ፍቅረኛሞች የሚጀምሩትም ፍቅር አዲስ ነው።
ይሁን እንጂ አራቱም ነገሮች በጋራ መልካም ነገር ያላቸው እንደሆነ ተደርጎ የግድ ለጥሩ ነገር ብቻ ‘አስደናቂ’ መባል አያስፈልጋቸውም። ምሳሌ 6:16-19 “ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች” ይዘረዝራል። እዚህም ላይ ልብ ለማለት እንደሚቻለው በጥያቄው ላይ ያለውን ጥቅስ ከመግለጹ በፊት ምሳሌ 30:15, 16 በፍጹም ‘በቃን የማይሉትን’ (ሲኦልን፣ የማትወልድ ማህፀንን፣ ውኃ የማትጠግብ ምድርንና በቃኝ የማትል እሳትን) ይዘረዝራል። እነዚህ ነገሮች በጥሩነታቸው ‘ድንቅ’ የሆኑ ነገሮች እንዳልሆኑ የተረጋገጠ ነው።
በምሳሌ 30:18 ላይ ‘ድንቅ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል “መለየት፣ ለይቶ ማወቅ፣ ልዩ ማድረግ፣ ዕፁብ ድንቅ፣ አስገራሚ” ተብሎ ይተረጎማል። ጥሩ ያልሆነ ነገርም ቢሆን ዕፁብ ድንቅ፣ ወይም አስገራሚ ሊሆን ይችላል። ዳንኤል 8:23, 24 አንድ ጨካኝ ንጉሥ እንደሚነሳና ‘በድንቅም እንደሚያጠፋ’ እንዲሁም “ኃያላንንና” ቅዱሳንንም ጭምር እንደሚያጠፋ አስቀድሞ ተናግሯል።—ከዘዳግም 17:8፤ 28:59፤ ዘካርያስ 8:6 ጋር አወዳድር።
ከምሳሌ 30:18, 19 ቀጥሎ ያለው ጥቅስ ጸሐፊው ለመረዳት ያስቸገረው ነገር ምን እንደሆነ ፍንጭ ይሰጠናል። ቁጥር 20 ላይ ስለ አንዲት “በልታ አፍዋን የምታብስ፦ አንዳች ክፉ ነገር አላደረግሁም” ስለምትል አንዲት አመንዝራ ሴት ይገልጻል። በምስጢርና በዘዴ ኃጢአት ትሠራለች ሆኖም ጥፋቷን የሚያሳይ ምልክት ስለሌለ ንጹህ ነኝ ትላለች።
ይህ አነጋገር ቀደም ብለው ከተዘረዘሩት ሐሳቦች ጋር ተመሳሳይነት አለው። ንስር በሰማይ ይበራል፣ እባብም በዐለት ላይ ይሄዳል፣ መርከብም ሞገድ ያቋርጣል ነገር ግን አንዳቸውም ቢሆኑ ትተውት የሚያልፉት ምልክት ስለሌለ ሦስቱም ያለፉበትን መንገድ ለማመልከት አስቸጋሪ ይሆናል። ሦስቱ በጋራ የሚመሳሰሉበት መንገድ ይህ ከሆነ “የሰውም መንገድ ከቆንጆ ጋር” ስለሚለው አራተኛ ሐሳብስ ምን ሊባል ይቻላል?
ይህም እንደ ሌሎቹ ከበስተኋላው ትቶት የሚያልፈው ምልክት የለም። አንድ ወጣት አንዲትን ልጃገረድ እንድታፈቅረው ለማድረግ በብልሃት፣ በመቅለስለስና በብልጠት ዘዴዎች ሊጠቀም ይችላል። ልጃገረዷ ለእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ተሞክሮው ስለማይኖራት ተንኮሉን አስቀድማ ላትነቃበት ትችላለች። አባብሎ ካሳሳታት በኋላ እንኳን እንዴት እንዳሸነፋት ማስረዳት ሊያቅታት ይችላል። ሁኔታውን የተመለከቱ ሰዎችም ቢሆኑ ነገሩን መግለጽ ሊያስቸግራቸው ይችላል። ያም ሆኖ ግን ብዙ ወጣት ሴቶች አታላይ በሆኑ ወንዶች ሥነ ምግባራዊ ንጽህናቸውን እያጡ ነው። እንደዚህ ያሉትን አታላይ ወንዶች መንገድ ማወቅ ከባድ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ በሰማይ እንደሚበረው ንስርም ሆነ በዐለት ላይ እንደሚሹለከለከው እባብ ወይም በባሕር ላይ እንደሚሄደው መርከብ ግብ አላቸው። እነዚህ አሳሳቾች ዋና ዓላማቸው የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ነው።
በዚህ ማብራሪያ መሠረት የምሳሌ 30:18, 19 ዐላማ በፍጥረት ውስጥ ስላሉ ሳይንሳዊ ወይም ውስብስብ ስለሆኑ ነገሮች መግለጽ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምሳሌ 7:1-27 አታላይ ከሆነች አንዲት አመንዝራ ወጥመድ መራቅ እንዳለብን እንደሚያስጠነቅቀን ሁሉ ይህም ሐረግ ሥነ ምግባራዊ ንጽህናችንን እንድንጠብቅ ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል። ክርስቲያን እህቶች የምሳሌ 30:18, 19ን ማስጠንቀቂያ ልብ ሊሉት የሚገባቸው አንዱ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንፈልጋለን የሚሉ ወንዶችን በተመለከተ ነው። አንዲት እህት አንድ የምታውቀው ወንድ ወይም የሥራ ባልደረባዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፍላጎት እንዳለው በሚያሳይበት ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ካለ ወንድም ጋር ማገናኘት ይኖርባታል። ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እውነተኛ ፍላጎት ካለው ይህ ወንድም ‘የሰው መንገድ ከቆንጆ ጋር በመሆኑ’ የሚደርስበት ምንም አደጋ ሳይኖር ሊረዳው ይችላል።