የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አድርጉ
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
    • ምዕራፍ አሥራ አንድ

      በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አድርጉ

      1. ቤተሰብን ሊከፋፍሉ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

      ፍቅር፣ ስምምነትና ሰላም በሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ደስተኞች ናቸው። የእናንተም ቤተሰብ እንዲህ እንደሆነ እናምናለን። የሚያሳዝነው ግን ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ቤተሰቦች እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የማይታይባቸውና በተለያየ ምክንያት የተከፋፈሉ ናቸው። ቤተሰቦችን የሚከፋፍሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ቤተሰብን የሚከፋፍሉ ሦስት ነገሮችን እንመለከታለን። በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ የቤተሰቡ አባላት የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ይሆናሉ። በሌሎቹ ቤተሰቦች ውስጥ የሚገኙት ልጆች ከተለያዩ ወላጆች የተወለዱ ሊሆኑ ይችላሉ። በአንዳንዶቹ ቤተሰቦች ውስጥ ደግሞ መተዳደሪያ ለማግኘት የሚደረገው ትግል ወይም ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት የቤተሰቡን አባላት ሊከፋፍላቸው ይችላል። ሆኖም አንዱን ቤተሰብ የሚከፋፍሉት ሁኔታዎች በሌላው ቤተሰብ ላይ ምንም ተጽዕኖ ላያሳድሩ ይችላሉ። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው?

      2. አንዳንዶች ስለ ቤተሰብ ሕይወት መመሪያ ለማግኘት የሚጥሩት ከማን ነው? ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ከሁሉ የተሻለ መመሪያ የሚገኘው ከየት ነው?

      2 በዚህ ረገድ አንዱ ትልቅ ሚና የሚጫወተው ነገር አመለካከት ነው። የሌላውን ሰው አመለካከት ለመረዳት ከልባችሁ የምትጥሩ ከሆነ የቤተሰባችሁ አንድነት ተጠብቆ መቀጠል እንዲችል ምን ማድረግ እንደምትችሉ ማስተዋል አያዳግታችሁም። ሌላው ትልቅ ሚና የሚጫወተው መመሪያ አድርጋችሁ የምትጠቀሙበት ነገር ነው። ብዙ ሰዎች የሥራ ጓደኞቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸው፣ የጋዜጣ አምድ አዘጋጆች ወይም ሌሎች ሰብዓዊ አማካሪዎች የሚሰጧቸውን ምክር ይከተላሉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች የአምላክ ቃል እነርሱ ስላሉበት ሁኔታ ምን እንደሚናገር በመመርመር ያገኙትን ትምህርት ሥራ ላይ አውለዋል። አንድ ቤተሰብ እንዲህ ማድረጉ ዘወትር በቤቱ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

      ባልሽ የተለየ እምነት ያለው ከሆነ

      በገጽ 130 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      የሌላውን ሰው አመለካከት ለመረዳት ጣሩ

      3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ እምነት ያለውን ሰው ማግባትን በተመለከተ ምን ምክር ይሰጣል? (ለ) አማኝ ያልሆነ የትዳር ጓደኛ ያለውን ሰው የሚመለከቱ አንዳንድ ዋና ዋና መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

      3 መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ ሃይማኖታዊ እምነት ያለውን ሰው እንዳናገባ አጥብቆ ይመክረናል። (ዘዳግም 7:​3, 4፤ 1 ቆሮንቶስ 7:​39) ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሰማሽው ካገባሽ በኋላ ሊሆን ይችላል፤ ባልሽ ደግሞ እውነትን አልተቀበለ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጊያለሽ? የጋብቻችሁ መሐላ በዚህ ጊዜም እንደጸና ይቀጥላል። (1 ቆሮንቶስ 7:​10) መጽሐፍ ቅዱስ የትዳር ማሰሪያን ዘላቂነት ጠበቅ አድርጎ የሚገልጽ ከመሆኑም በላይ የትዳር ጓደኛሞች በመካከላቸው አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ለችግሩ እልባት ለማግኘት መጣር እንጂ ከችግሩ መሸሽ እንደሌለባቸው ያሳስባል። (ኤፌሶን 5:​28-31፤ ቲቶ 2:​4, 5) ይሁን እንጂ ባልሽ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እምነት በመከተልሽ አጥብቆ ቢቃወምሽስ? ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች እንዳትሄጂ ሊከለክልሽ ይሞክር ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ከቤት ወደ ቤት እየሄድሽ ስለ ሃይማኖት እንድትሰብኪ አልፈልግም ይልሽ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጊያለሽ?

      4. አንዲት ሚስት ባሏ ከእሷ የተለየ እምነት ያለው ከሆነ ስሜቱን ልትጋራው የምትችለው በምን መንገድ ነው?

      4 ‘ባሌ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊያድርበት የቻለው ለምንድን ነው?’ ብለሽ ራስሽን ጠይቂ። (ምሳሌ 16:​20, 23) እያደረግሽ ያለውን ነገር በትክክል አልተረዳ ከሆነ ለአንቺ ደህንነት እያሰበ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ዘመዶቹ ከፍ አድርገው በሚመለከቷቸው አንዳንድ ባሕላዊ ልማዶች ላይ ባለመካፈልሽ ተጽዕኖ እያደረጉበት ይሆናል። “ቤት ውስጥ ብቻዬን ስቀር እንደተተውኩ ሆኖ ይሰማኛል” ሲል አንድ ባል ተናግሯል። ይህ ሰው ሃይማኖት ሚስቱን እንደነጠቀው ሆኖ ተሰምቶት ነበር። ሆኖም የነበረው ኩራት የተሰማውን የብቸኝነት ስሜት አውጥቶ እንዳይናገር አግዶት ነበር። ለይሖዋ ያለሽ ፍቅር ቀደም ሲል ለባልሽ የነበረሽን ፍቅር እንደማይቀንሰው ባልሽ እንዲገነዘብ ማድረግ ሊያስፈልግሽ ይችላል። ከባልሽ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይኖርብሻል።

      5. የተለየ እምነት የሚከተል ባል ያላት ሚስት ምን ዓይነት ሚዛን መጠበቅ አለባት?

      5 ይሁን እንጂ ሁኔታውን ጥበብ በተሞላበት መንገድ መቋቋም እንድትችይ ከዚህም ይበልጥ ልታስቢበት የሚገባ ነገር አለ። የአምላክ ቃል “በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ሲል ሚስቶችን አጥብቆ ያሳስባል። (ቆላስይስ 3:​18) በዚህ መንገድ ሚስቶች በራስ ከመመራት መንፈስ እንዲጠበቁ ያሳስባል። በተጨማሪም “በጌታ እንደሚገባ” የሚለው የዚህ ጥቅስ አነጋገር ሚስቶች ለባሎቻቸው በሚገዙበት ጊዜ ለጌታም መገዛት እንዳለባቸው መዘንጋት እንደማይኖርባቸው ያመለክታል። ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል።

      6. አንዲት ክርስቲያን ሚስት የትኞቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማስታወስ ይኖርባታል?

      6 አንድ ክርስቲያን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የመገኘትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እምነቱን ለሌሎች የመመሥከር ኃላፊነት አለበት፤ እነዚህ ነገሮች ችላ ሊላቸው የማይገቡ የእውነተኛው አምልኮ ዘርፎች ናቸው። (ሮሜ 10:​9, 10, 14፤ ዕብራውያን 10:​24, 25) እንግዲያው አንድ ሰው አምላክ ያዘዘውን ነገር እንዳታደርጊ በቀጥታ ቢያዝሽ ምን ታደርጊያለሽ? የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ሲሉ ገልጸዋል። (ሥራ 5:​29) እነዚህ ሐዋርያት የተዉት ምሳሌ በዛሬው ጊዜ በብዙ ሁኔታዎች ሊሠራ የሚችል ነው። ለይሖዋ ያለሽ ፍቅር ለእሱ የሚገባውን አምልኮ እንድታቀርቢ ይገፋፋሻልን? ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን ደግሞ፣ ለባልሽ ያለሽ ፍቅርና አክብሮት ይህን አምልኮ ባልሽን በማያስቆጣ መንገድ ለማቅረብ እንድትሞክሪ ያነሳሳሻልን?​—⁠ማቴዎስ 4:​10፤ 1 ዮሐንስ 5:​3

      7. አንዲት ክርስቲያን ሚስት ምን ዓይነት ቁርጥ ውሳኔ ሊኖራት ይገባል?

      7 ኢየሱስ እንዲህ ማድረግ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልክቷል። በእውነተኛው አምልኮ ላይ በሚሰነዘር ተቃውሞ ምክንያት አማኝ የሆኑ የአንዳንድ ቤተሰብ አባላት ከተቀሩት የቤተሰባቸው አባላት ጋር በሰይፍ የተለያዩ ያህል ሆነው እንደሚከፋፈሉ አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 10:​34-36) በጃፓን የምትኖር አንዲት ሴት ይህ ሁኔታ ደርሶባታል። ባሏ ለ11 ዓመታት ያህል ይቃወማት ነበር። በጣም ያሰቃያት የነበረ ከመሆኑም በላይ ብዙ ጊዜ ከቤት አስወጥቶ ይቆልፍባት ነበር። ሆኖም በአቋሟ ጸናች። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ጓደኞቿ አስፈላጊውን እርዳታ አደረጉላት። ያለማቋረጥ ወደ ይሖዋ ትጸለይ የነበረ ከመሆኑም በላይ 1 ጴጥሮስ 2:​20 ጥሩ ማበረታቻ ሆኖላታል። ይህች ክርስቲያን በአቋሟ ከጸናች፣ አንድ ቀን ባሏ ተለውጦ ከእሷ ጋር ይሖዋን ማገልገል እንደሚጀምር ጽኑ እምነት ነበራት። ያሰበችው አልቀረም፤ ከጊዜ በኋላ ይህ እምነቷ እውን ሆነ።

      8, 9. አንዲት ሚስት በባልዋ ፊት አላስፈላጊ እንቅፋቶች እንዳትፈጥር ምን ማድረግ ይኖርባታል?

      8 የትዳር ጓደኛሽን አመለካከት ለመለወጥ ውጤታማ የሆኑ ብዙ ነገሮች ማድረግ ትችያለሽ። ለምሳሌ ያህል ባልሽ ሃይማኖትሽን የሚቃወም ከሆነ በሌሎች መስኮች ስሞታ ለማቅረብ የሚያስችል ነገር እንዳያገኝ ጥረት አድርጊ። ቤቱን በንጽሕና ያዢ። ራስሽን ጠብቂ። ዘወትር ፍቅርሽንና አድናቆትሽን ግለጪለት። ከመተቸት ይልቅ ድጋፍ ስጭው። የእሱን የራስነት አመራር እንደምትፈልጊ አሳዪው። እንደበደለሽ ሆኖ ከተሰማሽ አጸፋውን ለመመለስ ማሰብ የለብሽም። (1 ጴጥሮስ 2:​21, 23) ያለበትን ሰብዓዊ አለፍጽምና ግምት ውስጥ አስገቢ፤ ጭቅጭቅ ከተፈጠረ ደግሞ በትሕትና ይቅርታ ለመጠየቅ ቀዳሚ ሁኚ።​—⁠ኤፌሶን 4:​26

      9 በስብሰባዎች ላይ መገኘትሽ የእራቱ ሰዓት እንዲዘገይበት ምክንያት መሆን የለበትም። በተጨማሪም አንዳንዴ ክርስቲያናዊ አገልግሎትሽን ባልሽ እቤት በማይኖርበት ጊዜ ማከናወን የተሻለ ሆኖ ልታገኚው ትችያለሽ። አንዲት ክርስቲያን ሴት ባሏ እንድትሰብክለት የማይፈልግ ከሆነ እንዲህ ከማድረግ መታቀብ ይኖርባታል። ከዚህ ይልቅ የሚከተለውን የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር ትከተላለች:- “እንዲሁም፣ እናንተ ሚስቶች ሆይ፣ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው።” (1 ጴጥሮስ 3:​1, 2) ክርስቲያን ሚስቶች የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች በማፍራት ይበልጥ በተሟላ መንገድ ይሠራሉ።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

      ሚስት የተለየ እምነት በሚኖራት ጊዜ

      10. አንድ አማኝ የሆነ ባል ሚስቱ ከእሱ የተለየ እምነት ያላት ከሆነች እንዴት ሊይዛት ይገባል?

      10 ባል ክርስቲያን ሆኖ ሚስት የተለየ እምነት ያላት በምትሆንበት ጊዜስ? መጽሐፍ ቅዱስ ለእንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች መመሪያ ይሰጣል። “ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፣ አይተዋት” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 7:​12) በተጨማሪም “ሚስቶቻችሁን ውደዱ” ሲል ባሎችን አጥብቆ ይመክራል።​—⁠ቆላስይስ 3:​19

      11. አንድ ባል ሚስቱ ክርስቲያን ካልሆነች አስተዋይ መሆንና የራስነት ሥልጣኑን በዘዴ መጠቀም የሚችለው እንዴት ነው?

      11 ሚስትህ ከአንተ የተለየ እምነት ያላት ከሆነች ለሚስትህ አክብሮት ለማሳየትና ለስሜቷ ትኩረት ለመስጠት ይበልጥ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። ዐዋቂ እንደ መሆኗ መጠን አንተ የማትስማማባቸው ቢሆኑም እንኳ ሃይማኖታዊ እምነቶቿን መፈጸም የምትችልበት የተወሰነ ነፃነት ሊኖራት ይገባል። ስለ እምነትህ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትነግራት ለብዙ ዓመታት አብረዋት የኖሩትን እምነቶች በአንድ ጊዜ እርግፍ አድርጋ በመተው አዲሱን እምነት ትቀበላለች ብለህ መጠበቅ የለብህም። እሷም ሆነች ቤተሰቧ ለረጅም ጊዜ ከፍ አድርገው ሲመለከቷቸው የቆዩት ልማዶች ሐሰት መሆናቸውን በቀጥታ ከመናገር ይልቅ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀስክ አሳማኝ በሆነ መንገድ በትዕግሥት ልታወያያት ሞክር። ለጉባኤ ሥራዎች ብዙ ጊዜ የምታውል ከሆነ ሚስትህ እንደተተወች ሆኖ ሊሰማት ይችላል። ይሖዋን ለማገልገል የምታደርገውን ጥረት ትቃወም ይሆናል፤ ከበስተጀርባ ያለው መልእክት ግን “ከእኔ ጋር የበለጠ ጊዜ እንድታሳልፍ እፈልጋለሁ!” የሚል ብቻ ሊሆን ይችላል። ታጋሽ ሁን። ለሚስትህ ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየትህ ከጊዜ በኋላ እውነተኛውን አምልኮ እንድትቀበል ሊረዳት ይችላል።​—⁠ቆላስይስ 3:​12-14፤ 1 ጴጥሮስ 3:​8, 9

      ልጆችን ማሠልጠን

      12. አንድ ባልና ሚስት እምነታቸው የተለያየ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ልጆችን በማሠልጠን ረገድ እንዴት ሊሠራባቸው ይገባል?

      12 በአምልኮ በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ለልጆቹ የሚሰጠውን ሃይማኖታዊ ትምህርት በተመለከተ አከራካሪ ጉዳይ ሊፈጠር ይችላል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ መዋል ያለባቸው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን የማስተማሩን ዋነኛ ኃላፊነት የሚሰጠው ለአባት ነው፤ ሆኖም እናትም በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሚና ትጫወታለች። (ምሳሌ 1:​8፤ ከዘፍጥረት 18:​19 እና ከ⁠ዘዳግም 11:​18, 19 ጋር አወዳድሩ።) አባትየው የክርስቶስን የራስነት ሥልጣን ባይቀበልም እንኳ የቤተሰቡ ራስ እሱ ነው።

      13, 14. አንዲት ሚስት ልጆቿን ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዛ እንዳትሄድ ወይም ደግሞ እንዳታስጠናቸው ባሏ ቢከለክላት ምን ማድረግ ትችላለች?

      13 አንዳንድ የማያምኑ አባቶች እናትየው ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ለልጆቿ ብታስተምር አይቃወሟትም። ሌሎቹ ግን ይቃወማሉ። ባልሽ ልጆቹን ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ይዘሻቸው እንዳትሄጂ አልፎ ተርፎም ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳታስጠኛቸው ቢከለክልሽስ? በዚህ ጊዜ የተለያዩ ግዴታዎችሽን ማለትም ለይሖዋ አምላክ፣ ለባልሽና ለውድ ልጆችሽ ያሉብሽን ግዴታዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት ይኖርብሻል። እነዚህን ነገሮች ማስታረቅ የምትችዪው እንዴት ነው?

      14 ስለ ጉዳዩ እንደምትጸልዪ የታወቀ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7፤ 1 ዮሐንስ 5:​14) ይሁን እንጂ በመጨረሻ የምትወስጂውን እርምጃ መወሰን ያለብሽ ራስሽ ነሽ። የባልሽን የራስነት ሥልጣን እየተቀናቀንሽ እንዳልሆነ ግልጽ በማድረግ በዘዴ ግዴታዎችሽን ለመወጣት ጥረት የምታደርጊ ከሆነ ከጊዜ በኋላ የባልሽ ተቃውሞ ሊረግብ ይችላል። ባልሽ ልጆችሽን ወደ ስብሰባዎች እንዳትወስጂያቸው ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳታስጠኚያቸው ቢከለክልሽ እንኳ እነሱን ማስተማር የምትቺይበት መንገድ አለ። በየዕለቱ ከልጆችሽ ጋር የምታደርጊውን የሐሳብ ልውውጥ መሣሪያ አድርገሽ በመጠቀምና ጥሩ ምሳሌ በመሆን በተወሰነ ደረጃ ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርባቸው፣ በቃሉ እንዲያምኑ፣ አባታቸውን ጨምሮ ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ፣ ለሌሎች ሰዎች ፍቅራዊ አሳቢነት እንዲኖራቸውና የሥራ ፍቅር እንዲያድርባቸው ለማድረግ ጣሪ። ከጊዜ በኋላ አባታቸው የተገኙትን ጥሩ ውጤቶች ሊመለከትና ያደረግሽው ጥረት ያስገኘውን ጥቅም ሊያደንቅ ይችላል።​—⁠ምሳሌ 23:​24

      15. ልጆችን በማስተማር ረገድ አማኝ የሆነ ባል ምን ኃላፊነት አለበት?

      15 አማኝ ያልሆነች ሚስት ያለህ ባል ከሆንክ ደግሞ ልጆችህን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” የማሳደጉን ኃላፊነት መሸከም አለብህ። (ኤፌሶን 6:​4) እርግጥ ይህን በምታደርግበት ጊዜ ከሚስትህ ጋር ባለህ ግንኙነት ደግ፣ አፍቃሪና ምክንያታዊ መሆን ይኖርብሃል።

      ሃይማኖትህ ከወላጆችህ እምነት የተለየ ከሆነ

      16, 17. ልጆች ከወላጆቻቸው የተለየ እምነት ከያዙ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ማስታወስ አለባቸው?

      16 ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች እንኳ ከወላጆቻቸው የተለዩ ሃይማኖታዊ አመለካከቶችን መቀበላቸው እንግዳ ነገር አይደለም። አንተም እንደዚህ አድርገሃልን? እንደዚህ አድርገህ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ለአንተም የሚሆን ምክር ይዟል።

      17 የአምላክ ቃል “ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፣ ይህ የሚገባ ነውና። . . . አባትህንና እናትህን አክብር” ይላል። (ኤፌሶን 6:​1, 2) ይህ ለወላጆች ጤናማ አክብሮት ማሳየት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ወላጆችን መታዘዝ አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ ይህ ታዛዥነት ለእውነተኛው አምላክ መሰጠት ያለበትን ቦታ የሚጋፋ መሆን የለበትም። አንድ ልጅ አድጎ የራሱን ውሳኔዎች ማድረግ ሲጀምር ለሚያደርጋቸው ነገሮች ያለበት ኃላፊነት ይጨምራል። ይህ በሰብዓዊ ሕግ ረገድ ብቻ ሳይሆን በመለኮታዊውም ሕግ ረገድ የበለጠ ይሠራል። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ሲል ይገልጻል።​—⁠ሮሜ 14:​12

      18, 19. ልጆች ሃይማኖታቸው ከወላጆቻቸው የተለየ ከሆነ ወላጆቻቸው እምነታቸውን ይበልጥ እንዲያውቁት ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

      18 እምነትህ በሕይወትህ ላይ ለውጥ ካመጣ የወላጆችህን አመለካከት ለመረዳት መጣር ይኖርብሃል። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በመማርህና በሥራ ላይ በማዋልህ ምክንያት ከበፊቱ ይበልጥ ወላጆችህን የምታከብር፣ የምትታዘዝና ያዘዙህን ነገር በትጋት የምታከናውን ከሆንክ ሊደሰቱ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ እምነትህ ወላጆችህ በግላቸው ከፍ አድርገው የሚመለከቷቸውን እምነቶችና ልማዶች እንድትተው የሚያደርግህ ከሆነ እነርሱ ሊያወርሱህ የሚፈልጉትን ቅርስ እንዳቃለልክ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። በተጨማሪም እያደረግክ ያለኸው ነገር በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ከሆነ ወይም ደግሞ ቁሳዊ ብልጽግና እንድታገኝ ሊረዱህ ይችላሉ ብለው በሚያስቧቸው ነገሮች ላይ እንዳታተኩር የሚያደርግህ ከሆነ ለደህንነትህ ሊሰጉ ይችላሉ። ኩራትም እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። በተዘዋዋሪ መንገድ እኔ ትክክል ነኝ፤ እናንተ ተሳስታችኋል እንዳልካቸው ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል።

      19 ስለዚህ በተቻለ መጠን ወላጆችህ በጉባኤህ ውስጥ ከሚገኙ አንዳንድ ሽማግሌዎች ወይም ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር ቶሎ እንዲገናኙ ለማድረግ ሞክር። ወላጆችህ ወደ መንግሥት አዳራሹ መጥተው እዚያ የሚሰጠውን ትምህርት ራሳቸው እንዲሰሙና የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ እንዲመለከቱ አበረታታቸው። ውሎ አድሮ የወላጆችህ አቋም ሊለዝብ ይችላል። ወላጆች በተቃውሟቸው ሲገፉ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ሲቀዳድዱና ልጆቻቸው ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዳይሄዱ ሲከለክሉ እንኳ ብዙውን ጊዜ በሌላ ቦታ ማንበብ፣ ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር መነጋገር እንዲሁም መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመስከርና ሌሎችን መርዳት የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። በተጨማሪም ወደ ይሖዋ መጸለይ ትችላለህ። አንዳንድ ወጣቶች የበለጠ መሥራት የሚችሉት ለአካለ መጠን ደርሰው ከቤተሰባቸው ውጪ ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ነው። ይሁን እንጂ ቤት ውስጥ ያለው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ‘አባትህንና እናትህን ማክበር’ እንዳለብህ አትዘንጋ። በቤታችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የበኩልህን አስተዋጽኦ አድርግ። (ሮሜ 12:​17, 18) ከሁሉ በላይ ደግሞ ምንጊዜም ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይኑርህ።

      የእንጀራ ወላጅ መሆን የሚያስከትለው ፈታኝ ሁኔታ

      20. ልጆች አባታቸው ወይም እናታቸው እንጀራ ወላጅ ከሆኑ ምን ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል?

      20 በብዙዎቹ ቤተሰቦች ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ፈታኝ ሁኔታ የሚፈጥረው ሃይማኖት ሳይሆን በቤተሰቡ ውስጥ የእንጀራ ወላጅ መኖሩ ነው። በአሁኑ ጊዜ በብዙዎቹ ቤተሰቦች ውስጥ አንደኛው ወይም ሁለቱም ወላጆች ከቀድሞ የትዳር ጓደኛቸው የወለዷቸው ልጆች ይኖራሉ። በእንዲህ ዓይነቱ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ልጆች የቅናት ስሜት ሊያድርባቸው፣ ቂም ሊይዙ ምናልባትም ደግሞ ለእንጀራ ወላጃቸው ታማኝ ሆኖ መገኘት ሊቸግራቸው ይችላል። በዚህም የተነሳ የእንጀራ ወላጆች ጥሩ አባት ወይም እናት ሆነው ለመገኘት ከልባቸው የሚያደርጉትን ጥረት ላይቀበሉት ይችላሉ። የእንጀራ ወላጅ ያለባቸው ቤተሰቦች የተሳካ ሕይወት መምራት እንዲችሉ ሊረዳቸው የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

      በገጽ 138 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      ሥጋዊ ወላጅም ሆናችሁ የእንጀራ ወላጅ መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ አድርጋችሁ ተጠቀሙበት

      21. የእንጀራ ወላጆች ምንም እንኳ ያሉበት ሁኔታ የተለየ ቢሆንም እርዳታ ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች መመልከት ያለባቸው ለምንድን ነው?

      21 ምንም እንኳ በእንዲህ ዓይነቶቹ ቤተሰቦች ውስጥ ያሉት ሁኔታዎች የተለዩ ቢሆኑም ሌሎቹን ቤተሰቦች የተሳካ ሕይወት መምራት እንዲችሉ የረዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እነዚህንም ቤተሰቦች ሊረዷቸው ይችላሉ። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ ማለቱ ለጊዜው ችግሩን የሚያቃልል መስሎ ሊታይ ቢችልም የኋላ ኋላ ግን የከፋ ሐዘን ማስከተሉ አይቀርም። (መዝሙር 127:​1፤ ምሳሌ 29:​15) ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኙትን አምላካዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ጥበብና የቤተሰባችሁ አባላት አንዳንድ ነገሮችን የሚናገሩትና የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችል ጥሩ የማስተዋል ችሎታ አዳብሩ። የሌላውን ሰው ስሜት መጋራትም በጣም አስፈላጊ ነው።​—⁠ምሳሌ 16:​21፤ 24:​3፤ 1 ጴጥሮስ 3:​8

      22. ልጆች የእንጀራ ወላጅን መቀበል ሊከብዳቸው የሚችለው ለምንድን ነው?

      22 የእንጀራ ወላጅ ከመሆናችሁ በፊት የቤተሰቡ ወዳጅ በነበራችሁበት ጊዜ ልጆቹ በጥሩ ሁኔታ ይቀበሏችሁ እንደነበረ ታስታውሱ ይሆናል። ሆኖም የእንጀራ ወላጃቸው ስትሆኑ አመለካከታቸው ሊለወጥ ይችላል። አብሯቸው የሌለውን ወላጅ በማስታወስና ምናልባትም ደግሞ ለእሱ ያላቸውን ፍቅር ለመንጠቅ እንደምትፈልጉ አድርገው በማሰብ ለእናንተ ታማኝነት ለማሳየት ሊቸገሩ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ አንተ አባቴ አይደለህም ወይም አንቺ እናቴ አይደለሽም ብለው ፊት ለፊት ሊናገሯችሁ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ አነጋገር በጣም ይጎዳል። ሆኖም “በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን።” (መክብብ 7:​9) የልጆቹን ስሜት ላለመጉዳት አስተዋይ መሆንና ስሜታቸውን መጋራት በጣም አስፈላጊ ነው።

      23. የእንጀራ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ተግሣጽ እንዴት ሊሰጥ ይችላል?

      23 አንድ ወላጅ ተግሣጽ በሚሰጥበት ጊዜ እነዚህን ባሕርያት ማሳየቱ በጣም ወሳኝ ነው። የምትሰጡት ተግሣጽ ተለዋዋጭ መሆን የለበትም። (ምሳሌ 6:​20፤ 13:​1) በተጨማሪም ሁሉም ልጆች አንድ ዓይነት ስላልሆኑ የሚሰጣቸው ተግሣጽ የተለያየ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ የእንጀራ ወላጆች ቢያንስ ቢያንስ መጀመሪያ ላይ ይህን ኃላፊነት ወላጅ እናት ወይም አባት ቢወጣው ይመርጣሉ። ሆኖም ተግሣጹን ሁለቱም ወላጆች ሊስማሙበትና ሊደግፉት ይገባል፤ ከአብራካቸው ለወጣ ልጃቸው ማድላት የለባቸውም። (ምሳሌ 24:​23) ልጆቻችሁ ታዛዥ መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነው፤ ሆኖም ያለባቸውን አለፍጽምና ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባችኋል። ከሚገባው በላይ ቁጡዎችና ኃይለኞች አትሁኑባቸው። በፍቅር ገሥጿቸው።​—⁠ቆላስይስ 3:​21

      24. የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ በሚገኙ ተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሥነ ምግባር ችግር እንዳይፈጠር ለመከላከል ሊረዳ የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

      24 በቤተሰብ ደረጃ መወያየት ችግሮችን ለማስወገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ቤተሰቡ በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ሊረዳው ይችላል። (ከፊልጵስዩስ 1:​9-11 ጋር አወዳድሩ።) በተጨማሪም እንዲህ ዓይነቱ ውይይት ቤተሰቡ ያወጣቸው ግቦች ላይ እንዲደርስ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል እንዴት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችል እንዲገነዘብ ይረዳዋል። ከዚህም በተጨማሪ ግልጽ የቤተሰብ ውይይት ማድረግ ሥነ ምግባራዊ ችግሮችን ሊያስወግድ ይችላል። ልጃገረዶች በእንጀራ አባታቸውና ከእንጀራ ወላጃቸው በተወለዱት ወንድሞቻቸው ፊት ምን ዓይነት አለባበስና ምግባር ሊኖራቸው እንደሚገባ ማወቅ አለባቸው፤ ወንዶች ልጆችም ለእንጀራ እናታቸውና ከእንጀራ ወላጃቸው ለተወለዱት እህቶቻቸው ትክክለኛ ሥነ ምግባር እንዲያሳዩ ምክር ሊሰጣቸው ይገባል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 4:​3-8

      25. የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ሊረዱ የሚችሉት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

      25 የእንጀራ ወላጅ መሆን የሚያስከትለውን ለየት ያለ ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም በምታደርጉት ጥረት ታጋሾች መሆን ይኖርባችኋል። አዲስ ዝምድና ለማዳበር ጊዜ ይጠይቃል። ከአብራካችሁ ያልወጡ ልጆችን ፍቅርና አክብሮት ለማትረፍ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ሊጠይቅባችሁ ይችላል። ሆኖም የማይቻል ነገር አይደለም። ይሖዋን ለማስደሰት ጠንካራ ፍላጎት ያለው ጥበበኛና አስተዋይ ልብ የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ቁልፍ ሚና ይጫወታል። (ምሳሌ 16:​20) እንዲህ ዓይነቶቹ ባሕርያት ሌሎች ሁኔታዎችንም እንድትቋቋሙ ሊረዷችሁ ይችላሉ።

      ቁሳዊ ነገሮች ለማግኘት የምታደርጉት ጥረት ቤተሰባችሁን ይከፋፍለዋልን?

      26. ከቁሳዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ ችግሮችና አመለካከቶች አንድን ቤተሰብ ሊከፋፍሉ የሚችሉት በምን መንገዶች ነው?

      26 ከቁሳዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ ችግሮችና አመለካከቶች ቤተሰቦችን በብዙ መንገዶች ሊከፋፍሏቸው ይችላሉ። የሚያሳዝነው፣ አንዳንድ ቤተሰቦች በገንዘብና ባለጸጋ ለመሆን ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮች ለማግኘት በመፈለግ የተነሳ በሚፈጠሩ ጭቅጭቆች ታምሰዋል። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ሰብዓዊ ሥራ ሲይዙና “በገዛ ገንዘቤ” መባባል ሲጀምሩ መከፋፈል ሊፈጠር ይችላል። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ሥራ በሚይዙበት ጊዜ ጭቅጭቅ ባይኖር እንኳን አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ ሊያጡ ይችላሉ። በአሁኑ ጊዜ አባቶች እቤት ሆነው ሊያገኙ ከሚችሉት የበለጠ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ለረጅም ጊዜ፣ ለወራት አልፎ ተርፎም ለዓመታት ከቤተሰባቸው ርቀው የሚሠሩበት ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ መጥቷል። ይህ በጣም የከፉ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።

      27. የገንዘብ ችግር ያለበትን ቤተሰብ ሊረዱ የሚችሉ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው?

      27 የተለያዩ ቤተሰቦች ያሉባቸው ተጽዕኖዎችና የሚያስፈልጓቸው ነገሮች የተለያዩ ስለሚሆኑ እነዚህን ሁኔታዎች መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ራሱን የቻለ ሕግ ማውጣት አይቻልም። ያም ሆኖ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሊጠቅም ይችላል። ለምሳሌ ያህል ‘አንድ ላይ ሆኖ በመማከር’ አላስፈላጊ የሆነን ትግል ማስቀረት እንደሚቻል ምሳሌ 13:​10 ይናገራል። ይህ የራስን አመለካከት መግለጽ ማለት ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምክር መጠየቅና ሌላው ሰው ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ማወቅ ይጠይቃል። በተጨማሪም ትክክለኛ የሆነ በጀት ማውጣት ቤተሰቡ የሚያደርገውን ጥረት ለማስተባበር ሊረዳ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ፣ በተለይ ደግሞ ልጆች ወይም በቤተሰቡ ሥር የሚተዳደሩ ሌሎች ሰዎች ካሉ ተጨማሪ ወጪዎችን ለመሸፈን፣ ለተወሰነ ጊዜ ሊሆን ይችላል፣ ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ሥራ መያዛቸው አስፈላጊ ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ባልየው በእንዲህ ዓይነቱ ወቅትም ቢሆን ከእሷ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ እንዳለው በመግለጽ ሚስቱን ሊያጽናናት ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ብቻዋን የምታከናውናቸውን አንዳንድ ሥራዎች ከልጆቹ ጋር ሆኖ በመሥራት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ሊረዳት ይችላል።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​1-4

      28. አንድ ቤተሰብ የትኞቹን ማሳሰቢያዎች ሥራ ላይ ማዋሉ አንድነት እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል?

      28 ይሁን እንጂ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ገንዘብ አስፈላጊ ነገር ቢሆንም እንኳ ደስታ እንደማያመጣ መዘንጋት የለባችሁም። ሕይወት ሊያስገኝ አይችልም። (መክብብ 7:​12) እንዲያውም ቁሳዊ ነገሮችን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርጎ መመልከት መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ውድቀት ሊያስከትል ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​9-12) ይሖዋ ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት የሚባርክልን በመሆኑ አስቀድመን የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን መፈለጋችን ምንኛ የተሻለ ነው! (ማቴዎስ 6:​25-33፤ ዕብራውያን 13:​5) መንፈሳዊ ነገሮችን የምታስቀድሙና ከሁሉ በፊት ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራችሁ የምትጥሩ ከሆነ ቤተሰባችሁ በአንዳንድ ሁኔታዎች የተከፋፈለ ቢሆን እንኳ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት መንገዶች አንድነት ያለው ይሆናል።

      የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች . . . የቤተሰብ አባላት በቤታቸው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ እንዲችሉ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

      ክርስቲያኖች ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያዳብራሉ።​—⁠ምሳሌ 16:​21፤ 24:​3

      አንድ ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ፍቅርና አክብሮት ማሳየት ያለባቸው አንድ ዓይነት ሃይማኖት ሲኖራቸው ብቻ አይደለም።​—⁠ኤፌሶን 5:​23, 25

      አንድ ክርስቲያን የአምላክን ሕግ ሆን ብሎ አይጥስም።​—⁠ሥራ 5:​29

      ክርስቲያኖች ሰላም ፈጣሪዎች ናቸው።​—⁠ሮሜ 12:​18

      ለመቆጣት አትቸኩሉ።​—⁠መክብብ 7:​9

      ትክክለኛ ጋብቻዎች ክብርና ሰላም ያስገኛሉ

      በዘመናችን ብዙ ወንዶችና ሴቶች በሕግ ሳይጋቡ እንደ ባልና ሚስት ሆነው አንድ ላይ ይኖራሉ። አንድ አዲስ አማኝ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ጥምረቱ በማኅበረሰቡ ወይም ደግሞ በጎሳው ልማድ ተቀባይነት ያገኘ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ሕጋዊ አይደለም። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት መሠረት አንድ ጋብቻ በትክክል ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ የተመዘገበ መሆን አለበት። (ቲቶ 3:​1፤ ዕብራውያን 13:​4) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በጋብቻ መጣመር የሚችሉት አንድ ባልና አንዲት ሚስት ብቻ መሆናቸውን ይደነግጋል። (1 ቆሮንቶስ 7:​2፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:​2, 12) በቤታችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን በመጀመሪያ ከዚህ መሥፈርት ጋር መስማማት ይኖርባችኋል። (መዝሙር 119:​165) ይሖዋ ያወጣቸው ብቃቶች ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ ወይም ደግሞ ሸክም አይደሉም። ይሖዋ የሚያስተምረን የሚበጀንን ነገር ነው።​—⁠ኢሳይያስ 48:​17, 18

  • ቤተሰብን የሚያናጉ ችግሮችን መቋቋም ትችላላችሁ
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
    • ምዕራፍ አሥራ ሁለት

      ቤተሰብን የሚያናጉ ችግሮችን መቋቋም ትችላላችሁ

      1. በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ምን ስውር ችግሮች አሉ?

      አሮጌዋ መኪና በደንብ ታጥባ ተወልውላለች። ከውጪ ለሚያያት በጣም የምታብረቀርቅ ከመሆኗም በላይ አዲስ መኪና ትመስላለች። ከውስጥ ግን በዝገት እየተበላች ነው። አንዳንድ ቤተሰቦች ያሉበት ሁኔታም ልክ እንደዚሁ ነው። ከውጪ ሲታዩ ምንም ችግር የሌለባቸው ይመስላሉ፤ በፊታቸው ላይ የሚነበበው ፈገግታ ያለባቸውን ፍርሃትና ሥቃይ ይሸፍነዋል። በጓዳቸው ውስጥ የሚፈጸሙ ጎጂ የሆኑ ነገሮች ግን የቤተሰቡን ሰላም እያናጉት ነው። ይህን መዘዝ ሊያስከትሉ የሚችሉት ሁለት አስቸጋሪ ሁኔታዎች የአልኮል ሱሰኝነትና በሌሎች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ናቸው።

      የአልኮል ሱሰኝነት የሚያስከትለው ጉዳት

      2. (ሀ) የአልኮል መጠጦችን መጠቀምን በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) የአልኮል ሱሰኝነት ምንድን ነው?

      2 መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጦችን ልከኛ በሆነ መንገድ መጠቀምን አያወግዝም፤ ስካርን ግን ያወግዛል። (ምሳሌ 23:​20, 21፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​23፤ ቲቶ 2:​2, 3) ይሁን እንጂ የአልኮል ሱሰኝነት ከስካርም የከፋ ነገር ነው፤ የአልኮል መጠጦች ተገዥ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ያለ ገደብ የመጠጣት ልማድ ያስከትላል። ዐዋቂዎች የአልኮል ሱሰኞች ሊሆኑ ይችላሉ። የሚያሳዝነው ደግሞ ወጣቶችም የአልኮል ሱሰኞች ሊሆኑ መቻላቸው ነው።

      3, 4. የአልኮል ሱስ በአልኮል ሱሰኛው የትዳር ጓደኛና በልጆቹ ላይ ምን ውጤቶች እንደሚያስከትል ግለጽ።

      3 መጽሐፍ ቅዱስ አልኮልን አላግባብ መጠቀም የቤተሰብን ሰላም ሊያደፈርስ እንደሚችል ያመለከተው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። (ዘዳግም 21:​18-21) የአልኮል ሱሰኝነት በመላው ቤተሰብ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ ያሳድራል። የትዳር ጓደኛው የአልኮል ሱሰኛውን ከሱሱ ለማላቀቅ ወይም ደግሞ ተለዋዋጭ ባሕሪውን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለች።a መጠጡን ትደብቅበታለች፣ ትጥልበታለች፣ ገንዘቡን ትሸሽግበታለች፣ እንዲሁም ለቤተሰቡ፣ ለሕይወቱና አልፎ ተርፎም ለአምላክ ሲል መጠጡን እንዲተው ትማጸነዋለች፤ የአልኮል ሱሰኛው ግን እንደዚያም ሆኖ መጠጡን አይተውም። የሚወስደውን መጠጥ ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት በተደጋጋሚ ሲከሽፍ በጣም ትበሳጫለች፤ ይህን የማድረግ ብቃት እንደሌላት ሆኖም ይሰማታል። ፍርሃት፣ ቁጣ፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ጭንቀትና የመረበሽ ስሜት ሊያድርባት እንዲሁም በራስ የመተማመን መንፈስ ሊጎድላት ይችላል።

      4 የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ያላቸው ልጆችም የአልኮል ሱሰኝነት ከሚያስከትለው ችግር ነፃ አይደሉም። አንዳንዶቹ አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ሌሎቹ ደግሞ በፆታ ተነውረዋል። ወላጃቸው የአልኮል ሱሰኛ የሆነው በእነሱ ምክንያት እንደሆነ በማሰብ ራሳቸውን ሊወቅሱ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ የአልኮል ሱሰኛው ተለዋዋጭ ጠባይ ሌሎችን እንዳያምኑ ያደርጋቸዋል። በቤት ውስጥ እየተፈጸመ ስላለው ነገር በነፃነት መናገር ስለማይችሉ ስሜታቸውን አፍነው የመያዝ ልማድ ያዳብራሉ፤ ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ አካላዊ ጉዳት ያስከትላል። (ምሳሌ 17:​22) እንዲህ ዓይነቶቹ ልጆች ካደጉም በኋላ በራሳቸው የማይተማመኑ ወይም ለራሳቸው አክብሮት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

      ቤተሰቡ ምን ሊያደርግ ይችላል?

      5. የአልኮል ሱስን መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው? ይህስ ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?

      5 ምንም እንኳ ብዙ ባለሙያዎች የአልኮል ሱስ ፈውስ የሌለው ችግር እንደሆነ ቢናገሩም ከአልኮል ሙሉ በሙሉ በመራቅ ከሱሱ መላቀቅ እንደሚቻል አብዛኞቹ ይስማሙበታል። (ከ⁠ማቴዎስ 5:​29 ጋር አወዳድሩ።) ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የአልኮል ሱሰኛው ችግር እንዳለበት አምኖ ስለማይቀበል ፈቃደኛ ሆኖ እርዳታ እንዲቀበል ማድረጉ እንዲህ እንደምናወራው ቀላል አይደለም። ሆኖም የቤተሰቡ አባላት የአልኮል ሱሱ በእነሱ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም አንዳንድ እርምጃዎችን ሲወስዱ የአልኮል ሱሰኛው ችግር እንዳለበት ሊገነዘብ ይችላል። የአልኮል ሱሰኞችንና ቤተሰቦቻቸውን የመርዳት ልምድ ያካበቱ አንድ ሐኪም እንዲህ ብለዋል:- “ቤተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በተቻለው መጠን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለማከናወን መጣሩ ይበልጥ ጠቃሚ ይመስለኛል። የአልኮል ሱሰኛው በእሱና በተቀረው ቤተሰቡ መካከል ምን ያህል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ እያደር ግልጽ እየሆነለት ይሄዳል።”

      6. የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ሰው ያለባቸው ቤተሰቦች ከሁሉ የተሻለ ምክር የሚያገኙት ከየት ነው?

      6 በቤተሰባችሁ ውስጥ የአልኮል ሱሰኛ ካለ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር ሕይወታችሁን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድትመሩ ሊረዳችሁ ይችላል። (ኢሳይያስ 48:​17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) የተለያዩ ቤተሰቦች የአልኮል ሱስን በተሳካ መንገድ መቋቋም እንዲችሉ የረዷቸውን አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመልከት።

      7. አንድ የቤተሰብ አባል የአልኮል ሱሰኛ ከሆነ ተጠያቂው ማን ነው?

      7 ጥፋቱን ሁሉ በራሳችሁ ላይ አታላኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ይሸከማል፤’ እንዲሁም “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ሲል ይናገራል። (ገላትያ 6:​5፤ ሮሜ 14:​12) የአልኮል ሱሰኛው ተጠያቂዎቹ የቤተሰቡ አባላት እንደሆኑ አድርጎ ለመናገር ይሞክር ይሆናል። ለምሳሌ ያህል “ባታበሳጩኝ አልጠጣም ነበር” ሊል ይችላል። ሌሎቹ በዚህ አባባሉ የሚስማሙ ሆነው ከተገኙ በጠጪነቱ እንዲገፋበት እያበረታቱት ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሁኔታዎች ለችግር ቢያጋልጡን ወይም ደግሞ ሌሎች ሰዎች አግባብ ያልሆነ ድርጊት ቢፈጽሙብን እንኳ የአልኮል ሱሰኞችን ጨምሮ ሁላችንም ለምናደርገው ነገር ተጠያቂዎች ነን።​—⁠ከፊልጵስዩስ 2:​12 ጋር አወዳድሩ።

      8. የአልኮል ሱሰኛው የራሱ ችግር ያስከተላቸውን መዘዞች ራሱ እንዲወጣ መርዳት የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

      8 የአልኮል ሱሰኛውን ሁልጊዜ ጠጪነቱ ከሚያስከትልበት መዘዝ መታደግ እንዳለባችሁ ሆኖ ሊሰማችሁ አይገባም። ስለ ቁጡ ሰው የተነገረ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ የአልኮል ሱሰኛ በሆነ ሰውም ላይ በእኩል ደረጃ ሊሠራ ይችላል:- “አንድ ጊዜ ከችግሩ ልታወጣው ብትሞክር፣ ሌላ ጊዜም እንዲሁ ማድረግህ አይቀርም።” (ምሳሌ 19:​19 የ1980 ትርጉም) የአልኮል ሱሰኛው ጠጪነቱ የሚያስከትለውን መዘዝ እንዲቀምስ አድርጉት። ያዝረከረከውን ነገር ሁሉ ራሱ ያስተካክል፤ ወይም ደግሞ ከጠጣ በኋላ በነጋታው ጠዋት ራሱ ለአሠሪው ይደውል።

      በገጽ 146 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      ክርስቲያን ሽማግሌዎች የቤተሰብን ችግሮች በመፍታት ረገድ ትልቅ የእርዳታ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ

      9, 10. የአልኮል ሱሰኛ ያለባቸው ቤተሰቦች እርዳታ ማግኘት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? በተለይ ደግሞ የማንን እርዳታ ለማግኘት መጣር አለባቸው?

      9 የሌሎችን እርዳታ ተቀበሉ። ምሳሌ 17:​17 “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” ሲል ይናገራል። በቤተሰባችሁ ውስጥ የአልኮል ሱሰኛ ካለ መከራ ይኖራል። እርዳታ ያስፈልጋችኋል። ‘ከእውነተኛ ወዳጆች’ እርዳታ ለማግኘት አታመንቱ። (ምሳሌ 18:​24) ችግሩን የሚረዱ ወይም ደግሞ ተመሳሳይ ሁኔታ የገጠማቸውን ሰዎች ማነጋገራችሁ ማድረግ ያለባችሁንና ማድረግ የሌለባችሁን ነገር በተመለከተ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮች እንድታገኙ ሊረዳችሁ ይችላል። ሆኖም ሚዛናዊ መሆን ይኖርባችኋል። ማነጋገር ያለባችሁ እምነት የምትጥሉባቸውንና ‘ምሥጢራችሁን’ የሚጠብቁ ሰዎችን ነው።​—⁠ምሳሌ 11:​13

      10 በክርስቲያን ሽማግሌዎች የመታመንን ልማድ አዳብሩ። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች ትልቅ የመጽናኛ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ የጎለመሱ ወንዶች የአምላክን ቃል በሚገባ የተማሩ ከመሆናቸውም በላይ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በሥራ በመተርጎም ረገድ ጥሩ ልምድ ያካበቱ ናቸው። “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ” ሆነው ሊገኙ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:​2) ክርስቲያን ሽማግሌዎች መላውን ጉባኤ ጎጂ ከሆኑ ተጽዕኖዎች የሚጠብቁ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ችግር ያለባቸውን ግለሰቦች ያጽናናሉ፣ ያነቃቃሉ፣ እንዲሁም በግል እርዳታ ይሰጣሉ። እነሱ በሚሰጡት እርዳታ ሙሉ በሙሉ ተጠቀሙ።

      11, 12. የአልኮል ሱሰኛ ላለባቸው ቤተሰቦች ከሁሉ የተሻለውን እርዳታ የሚሰጠው ማን ነው? ይህ እርዳታ የሚሰጠውስ እንዴት ነው?

      11 ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ይሖዋ ኃይል እንዲሰጣችሁ ጠይቁት። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” ሲል በጋለ ስሜት ያረጋግጥልናል። (መዝሙር 34:​18) የአልኮል ሱሰኛ ከሆነ የቤተሰብ አባል ጋር አብራችሁ መኖራችሁ በሚያሳድርባችሁ ተጽዕኖ የተነሳ ልባችሁ በሐዘን ቢደቆስ ወይም መንፈሳችሁ ቢጎዳ ‘ይሖዋ ቅርብ’ መሆኑን ማወቅ ይኖርባችኋል። ቤተሰባችሁ ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ያውቃል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​6, 7

      12 ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የተናገረውን ማመናችሁ ጭንቀትን ለመቋቋም ሊረዳችሁ ይችላል። (መዝሙር 130:​3, 4፤ ማቴዎስ 6:​25-34፤ 1 ዮሐንስ 3:​19, 20) የአምላክን ቃል ማጥናታችሁና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በሕይወታችሁ ውስጥ በሥራ ላይ ማዋላችሁ በየዕለቱ የሚያጋጥማችሁን ችግር እንድትቋቋሙ “ከወትሮው የላቀ ኃይል” ሊያስታጥቃችሁ የሚችለውን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እርዳታ እንድታገኙ ያስችላችኋል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​7 NWb

      13. ብዙ ቤተሰቦችን የሚያነጋው ሁለተኛው ችግር ምንድን ነው?

      13 አልኮልን አላግባብ መጠቀም ብዙ ቤተሰቦችን የሚያናጋ ሌላ ችግር ማለትም በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት መፈጸምን ሊያስከትል ይችላል።

      በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሚያስከትለው ጉዳት

      14. በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት መፈጸም የተጀመረው መቼ ነው? በዛሬው ጊዜ በዚህ ረገድ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

      14 በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የጥቃት እርምጃ የተፈጸመው የአንድ ቤተሰብ አባላት በሆኑት በሁለቱ ወንድማማቾች ማለትም በቃየልና በአቤል መካከል ነው። (ዘፍጥረት 4:​8) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ዘር፣ በቤተሰብ አባላት ላይ በሚፈጸም የተለያየ ዓይነት ጥቃት ሲሠቃይ ቆይቷል። ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ባሎች፣ በባሎቻቸው ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ሚስቶች፣ ትንንሽ ልጆቻቸውን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የሚደበድቡ ወላጆችና በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን የሚያንገላቱ ትልልቅ ልጆች አሉ።

      15. የቤተሰብ አባላት በሚፈጸምባቸው ጥቃት ስሜታቸው የሚጎዳው እንዴት ነው?

      15 በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸም ጥቃት አካላዊ ጠባሳ ብቻ ጥሎ የሚያልፍ አይደለም። አንዲት ባሏ ይደበድባት የነበረች ሚስት እንዲህ ብላለች:- “ልትቋቋሙት የሚገባ ከባድ የጸጸትና የውርደት ስሜት ይሰማችኋል። አብዛኛውን ጊዜ አስፈሪ ቅዠት ውስጥ እንደነበራችሁ አድርጋችሁ በማሰብ ጠዋት አልጋችሁ ውስጥ መቆየት ትፈልጋላችሁ።” በራሳቸው ላይ ጥቃት የተፈጸመባቸው ወይም ደግሞ በሌሎች የቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት ሲፈጸም ያዩ ልጆች ወደፊት ካደጉ በኋላ እነርሱም በራሳቸው ቤተሰብ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ሊፈጽሙ ይችላሉ።

      16, 17. በስሜት ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ምንድን ነው? የቤተሰብ አባላት በዚህ የሚነኩት እንዴት ነው?

      16 በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት የሚፈጸመው በመደብደብ ብቻ አይደለም። ብዙውን ጊዜ ጥቃቱ የሚሰነዘረው በቃላት ነው። ምሳሌ 12:​18 [የ1980 ትርጉም] “ያለ ጥንቃቄ የተነገረ ቃል እንደ ሰይፍ ያቆስላል” ሲል ይገልጻል። መሳደብና መጮኽ፣ እንዲሁም ሁልጊዜ መተቸት፣ ማዋረድና አካላዊ ጥቃት ለመሰንዘር መዛት በቤተሰብ አባላት ላይ ‘የሚያቆስል’ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው መንገዶች መካከል የሚደመሩ ናቸው። በስሜት ላይ የሚሰነዘር ጥቃት የሚያስከትለው ቁስል የማይታይ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ የሌሎችን ትኩረት ሳያገኝ ይቀራል።

      17 ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ልጆችን ዘወትር በመተቸት እንዲሁም ችሎታቸውን፣ እውቀታቸውን ወይም ደግሞ ዋጋማነታቸውን ዝቅ በማድረግ በስሜታቸው ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ነው። እንዲህ ዓይነቱ በቃላት የሚሰነዘር ጥቃት የአንድን ልጅ ቅስም ሊሰብረው ይችላል። ሁሉም ልጆች ተግሣጽ እንደሚያስፈልጋቸው አይካድም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” ሲል ለአባቶች ጥብቅ መመሪያ ይሰጣል።​—⁠ቆላስይስ 3:​21

      በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት ማስወገድ የሚቻልበት መንገድ

      በገጽ 151 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      እርስ በርስ የሚዋደዱና የሚከባበሩ ክርስቲያን ባልና ሚስት በመካከላቸው የሚፈጠረውን አለመግባባት ወዲያውኑ ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ

      18. በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት የመፈጸም ሐሳብ የሚጸነሰው የት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ድርጊት ለማቆም የሚያስችለው ነገር ምን እንደሆነ ይናገራል?

      18 በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት የመፈጸም ሐሳብ የሚጸነሰው በልብና በአእምሮ ውስጥ ነው፤ ወደ ድርጊት የሚያሸጋግረን በውስጣችን የምናስበው ነገር ነው። (ያዕቆብ 1:​14, 15) ጥቃቱን ማቆም እንዲቻል ጥቃቱን የሚሰነዝረው ግለሰብ አስተሳሰቡን መለወጥ አለበት። (ሮሜ 12:​2) እንዲህ ማድረግ ይቻላልን? አዎ፣ ይቻላል። የአምላክ ቃል ሰዎችን የመለወጥ ኃይል አለው። እንደ “ምሽግ” የጠነከሩ ጎጂ አስተሳሰቦችን መንግሎ ማውጣት ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 10:​4፤ ዕብራውያን 4:​12) ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንዲለወጡ ሊረዳቸው የሚችል በመሆኑ አዲስ ሰውነት እንደሚለብሱ ተገልጿል።​—⁠ኤፌሶን 4:​22-24፤ ቆላስይስ 3:​8-10

      19. አንድ ክርስቲያን የትዳር ጓደኛውን እንዴት መመልከትና መያዝ አለበት?

      19 ለትዳር ጓደኛችሁ ሊኖራችሁ የሚገባ አመለካከት። የአምላክ ቃል “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል” ይላል። (ኤፌሶን 5:​28) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ባል ሚስቱን “ልክ እንደ ተሰባሪ ዕቃ በክብር” ሊይዛት እንደሚገባ ይገልጻል። (1 ጴጥሮስ 3:​7 NW) ሚስቶች “ባሎቻቸውን የሚወዱ” እንዲሆኑና ለባሎቻቸው “ጥልቅ አክብሮት” እንዲኖራቸው ተመክረዋል። (ቲቶ 2:​4፤ ኤፌሶን 5:​33 NW) ፈሪሃ አምላክ ያለው የትኛውም ባል ሚስቱን እየደበደበም ሆነ በቃላት እያቆሰለ አከብራታለሁ ብሎ ሊናገር እንደማይችል የታወቀ ነው። በባሏ ላይ የምትጮኽ፣ ባሏን በአሽሙር የምትዘልፍ ወይም ዘወትር የምትነቅፍ ሚስት ባሏን እንደምትወድና እንደምታከብር ልትናገር አትችልም።

      20. ወላጆች ልጆቻቸውን በተመለከተ በማን ፊት ተጠያቂዎች ናቸው? ወላጆች ከልጆቻቸው ተገቢ ያልሆነ ነገር መጠበቅ የሌለባቸውስ ለምንድን ነው?

      20 ለልጆች ሊኖራችሁ የሚገባ ትክክለኛ አመለካከት። ልጆች የወላጆቻቸው ፍቅርና ትኩረት ያሻቸዋል። የአምላክ ቃል፣ ልጆች ‘የይሖዋ ስጦታና የእርሱ ዋጋ’ እንደሆኑ ይናገራል። (መዝሙር 127:​3) ወላጆች በይሖዋ ፊት ይህን ስጦታ በእንክብካቤ የመያዝ ኃላፊነት አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ‘ልጅነት ጠባይና’ ስለ ልጆች “ስንፍና” ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 13:​11፤ ምሳሌ 22:​15) ወላጆች ልጆቻቸው አስተዋይነት የጎደለው ድርጊት ሲፈጽሙ ቢመለከቱ ሊገረሙ አይገባም። ወጣቶች ዐዋቂዎች አይደሉም። ወላጆች አንድ ልጅ ዕድሜው፣ ያደገበት ቤተሰብ ሁኔታና ችሎታው ከሚፈቅድለት በላይ የሆነ ነገር ሊጠብቁበት አይገባም።​—⁠ዘፍጥረት 33:​12-14ን ተመልከቱ።

      21. ለአረጋውያን ወላጆች ሊኖረን የሚገባው አምላካዊ አመለካከትና አያያዝ ምንድን ነው?

      21 ለአረጋውያን ወላጆች ሊኖራችሁ የሚገባው አመለካከት። ዘሌዋውያን 19:​32 “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም አክብር” ይላል። በዚህ መንገድ የአምላክ ሕግ አረጋውያንን እንድናከብርና ከፍ አድርገን እንድንመለከት ያበረታታል። አረጋዊው ወላጅ በቀላሉ የማይረካ ሲሆን ወይም ደግሞ በሽተኛ ከሆነ፣ ከዚያም አልፎ ደግሞ የመንቀሳቀስም ሆነ የማሰብ ችሎታው ዘገምተኛ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ክብር መስጠት ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ግን ልጆች ‘ለወላጆቻቸው ብድራት መመለስ እንዳለባቸው’ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​4) ይህ አረጋውያን ወላጆችን በክብር መያዝ አልፎ ተርፎም በገንዘብ መደጎም ማለት ሊሆን ይችላል። አረጋውያን ወላጆችን በአካላዊ ሁኔታም ሆነ በሌላ መንገድ ማንገላታት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያዝዘን ነገር ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ ነው።

      22. በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማስወገድ ቁልፍ የሆነ ሚና የሚጫወተው ባሕርይ ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ማሳየት የሚቻለውስ እንዴት ነው?

      22 ራስን የመግዛት ባሕርይ አዳብሩ። ምሳሌ 29:​11 “ሰነፍ ሰው ቁጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል” ይላል። መንፈስህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው? ብስጭት በውስጣችሁ ሥር እንዲሰድ ከመፍቀድ ይልቅ በመካከላችሁ የተፈጠረውን አለመግባባት ወዲያውኑ ለመፍታት ጥረት አድርጉ። (ኤፌሶን 4:​26, 27) ራሳችሁን መቆጣጠር እንደተሳናችሁ ከተሰማችሁ ከአካባቢው ዞር ለማለት ሞክሩ። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድታፈሩ ይረዳችሁ ዘንድ ጸልዩ። (ገላትያ 5:​22, 23) ወጣ ብሎ በእግር መንሸራሸር ወይም ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት ስሜታችሁን ለመቆጣጠር ሊረዳችሁ ይችላል። (ምሳሌ 17:​14, 27) ‘ለቁጣ የዘገያችሁ’ ለመሆን ጥረት አድርጉ።​—⁠ምሳሌ 14:​29

      መለያየት ወይስ አብሮ መኖር?

      23. አንድ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ምንም የንስሐ ፍሬ ሳያሳይ የቤተሰብ አባላቱን መደብደብን ጨምሮ በተደጋጋሚ የቁጣ ውርጅብኝ የሚያወርድባቸው ከሆነ ምን እርምጃ ሊወሰድበት ይችላል?

      23 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሚያወግዛቸው ሥራዎች ብሎ ከፈረጃቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ‘ጥል፣ ክርክርና ቁጣ’ ሲሆኑ “እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት” እንደማይወርሱ ይገልጻል። (ገላትያ 5:​19-21) ስለዚህ ክርስቲያን ነኝ እያለ በሚያደርገው ነገር ምንም የጸጸት ስሜት ሳይሰማው በተደጋጋሚ ጊዜያት በትዳር ጓደኛውም ሆነ በልጆቹ ላይ የቁጣ ውርጅብኝ የሚያወርድ፣ ምናልባትም ደግሞ ከዚያም አልፎ የሚማታ ከክርስቲያን ጉባኤ ሊወገድ ይችላል። (ከ⁠2 ዮሐንስ 9, 10 ጋር አወዳድሩ።) በዚህ መንገድ ጉባኤው አግባብ ያልሆነ ድርጊት ከሚፈጽሙ ሰዎች የጠራ ይሆናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 5:​6, 7፤ ገላትያ 5:​9

      24. (ሀ) አግባብ ያልሆነ ድርጊት የሚፈጸምባቸው የትዳር ጓደኞች ምን ለማድረግ ሊመርጡ ይችላሉ? (ለ) አሳቢ የሆኑ ጓደኞችና ሽማግሌዎች አግባብ ያልሆነ ድርጊት የሚፈጸምበትን ባለ ትዳር እንዴት ሊረዱት ይችላሉ? ሆኖም ምን ማድረግ የለባቸውም?

      24 ምንም ዓይነት የመለወጥ ምልክት በማያሳይ ክፉ የትዳር ጓደኛ በየጊዜው እየተደበደቡ ያሉ ክርስቲያኖችስ ምን ማድረግ ይችላሉ? አንዳንዶቹ የራሳቸው የሆነ ምክንያት ስላላቸው አግባብ ያልሆነ ድርጊት ከሚፈጽምባቸው የትዳር ጓደኛቸው ጋር መቆየት መርጠዋል። ሌሎቹ ግን አካላዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ ጤንነታቸው አልፎ ተርፎም ሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ እንደወደቀ ስለተሰማቸው ከትዳር ጓደኛቸው መለየት መርጠዋል። በራሱ የቤተሰብ አባል ጥቃት የሚፈጸምበት ሰው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ወቅት የሚወስደው እርምጃ በይሖዋ ፊት የሚወስነው የራሱ የግል ውሳኔ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:​10, 11) አሳቢ የሆኑ ጓደኞች፣ ዘመዶች ወይም ደግሞ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እርዳታና ምክር ሊሰጡ ይችላሉ፤ ሆኖም ግለሰቡ ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ እንዲወስድ ሊጫኑት አይገባም። ይህ የራሱ ወይም የራሷ የግል ውሳኔ ነው።​—⁠ሮሜ 14:​4፤ ገላትያ 6:​5

      ጎጂ ችግሮች የሚወገዱበት ጊዜ

      25. ይሖዋ ለቤተሰብ ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

      25 ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን በጋብቻ ሲያጣምራቸው ቤተሰቦች በአልኮል ሱስ፣ በሌሎች ላይ በሚፈጸም ጥቃትና እነዚህን በመሳሰሉ ጎጂ ችግሮች እንዲፈራርሱ አስቦ አልነበረም። (ኤፌሶን 3:​14, 15) ቤተሰብ የተቋቋመው ፍቅርና ሰላም የሰፈነበትና እያንዳንዱ አባል አእምሯዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቹ የሚሟሉበት ቦታ እንዲሆን ታስቦ ነው። ኃጢአት ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ ግን የቤተሰብ ሕይወት በፍጥነት እየተበላሸ ሄዷል።​—⁠ከ⁠መክብብ 8:​9 ጋር አወዳድሩ።

      26. ይሖዋ ካወጣቸው ብቃቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚጥሩ ሁሉ ምን ዓይነት ጊዜ ይጠብቃቸዋል?

      26 የሚያስደስተው ግን ይሖዋ ለቤተሰብ ያለው ዓላማ ያልተለወጠ መሆኑ ነው። ሰዎች ‘የሚያስፈራቸው ሳይኖር ተዘልለው የሚቀመጡበት’ አዲስ ሰላማዊ ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል። (ሕዝቅኤል 34:​28) በዚያ ጊዜ የአልኮል ሱሰኝነት፣ በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸም ጥቃትና በአሁኑ ጊዜ ቤተሰቦችን እያፈራረሱ ያሉ ሌሎች ችግሮች የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ። ሰዎች ፍርሃታቸውንና ስቃያቸውን ለመደበቅ ብለው ሳይሆን በሚያገኙት ‘ብዙ ሰላም በመደሰት’ ፊታቸው በፈገግታ ይሞላል።​—⁠መዝሙር 37:​11

      a የአልኮል ሱሰኛውን በተባዕታይ ጾታ የገለጽነው ቢሆንም እዚህ ላይ የተጠቀሱት መሠረታዊ ሥርዓቶች የአልኮል ሱሰኛ በሆኑ ሴቶችም ላይ ይሠራሉ።

      b በአንዳንድ አገሮች ለአልኮል ሱሰኞችና ለቤተሰቦቻቸው የባለሙያ እርዳታ የሚሰጡ የሕክምና ማዕከሎች፣ ሆስፒታሎችና ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ የሚረዱ ፕሮግራሞች አሉ። በእንዲህ ዓይነቱ እርዳታ መጠቀም አለመጠቀሙ የግል ውሳኔ ነው። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተሻለው ሕክምና ይኼኛው ነው ብሎ ሐሳብ አያቀርብም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው እርዳታ ለማግኘት በሚጥርበት ጊዜ ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያስጥሱ ነገሮች እንዳይፈጽም መጠንቀቅ አለበት።

      የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች . . . ቤተሰቦች ከባድ ጉዳት የሚያስከትሉ ችግሮችን ማስወገድ እንዲችሉ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

      ይሖዋ አልኮልን አላግባብ መጠቀምን ያወግዛል።​—⁠ምሳሌ 23:​20, 21

      እያንዳንዱ ግለሰብ ለሚያደርገው ነገር ተጠያቂ ነው።—⁠ሮሜ 14:​12

      ራሳችንን መግዛት ሳንችል አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማገልገል አንችልም።​—⁠ምሳሌ 29:​11

      እውነተኛ ክርስቲያኖች አረጋውያን ወላጆቻቸውን ያከብራሉ።​—⁠ዘሌዋውያን 19:​32

  • ትዳር በቋፍ ላይ በሚሆንበት ጊዜ
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
    • ምዕራፍ አሥራ ሦስት

      ትዳር በቋፍ ላይ በሚሆንበት ጊዜ

      1, 2. ትዳር ውጥረት ውስጥ በሚገባበት ጊዜ የትኛውን ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልጋል?

      በ1988 ሉቺያ የምትባል አንዲት ጣሊያናዊት ሴት ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ወድቃ ነበር።a ለአሥር ዓመታት የቆየው ትዳሯ ሊፈርስ ነው። ከባሏ ጋር ለመታረቅ ብዙ ጊዜ ሞከረች፤ ሆኖም አልተሳካም። እርስ በርስ መጣጣም ባለመቻላቸው የተነሳ ከባሏ ጋር ስለ ተለያየች ሁለት ሴቶች ልጆቿን በራሷ የማሳደግ ኃላፊነት ወደቀባት። ሉቺያ በዚያን ጊዜ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብላ በማስታወስ “ትዳራችንን ከመፍረስ ሊያድነው የሚችል ምንም ነገር እንዳልነበረ እርግጠኛ ነበርኩ” ብላለች።

      2 እናንተም በትዳራችሁ ውስጥ ችግር ካለ የሉቺያን ስሜት መረዳት ላይከብዳችሁ ይችላል። ትዳራችሁ ችግር ላይ ወድቆ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም ከመፍረስ መዳኑ እያጠራጠራችሁ ይሆናል። ትዳራችሁ እንዲህ ዓይነት ችግር ላይ ከወደቀ የሚከተለውን ጥያቄ መመርመሩ ጠቃሚ ሆኖ ታገኙታላችሁ:- አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጠውን ትዳርን የተሳካ ለማድረግ የሚረዳ ጥሩ ምክር ሙሉ በሙሉ ሠርቼበታለሁን?​—⁠መዝሙር 119:​105

      3. ፍቺ በጣም የተስፋፋ ቢሆንም እንኳ ብዙ የተፋቱ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ምን እንደተሰማቸው ተዘግቧል?

      3 በባልና በሚስት መካከል ከፍተኛ ውጥረት በሚፈጠርበት ጊዜ ከሁሉ ይበልጥ ቀላል የሆነው እርምጃ ትዳሩን ማፍረስ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። በብዙ አገሮች የሚፈርሱት ትዳሮች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ቢሄድም እንኳ በቅርብ ጊዜ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተፋቱ ወንዶችና ሴቶች ትዳራቸው በመፍረሱ በጣም ተጸጽተዋል። ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ካልተፋቱት ሰዎች ይበልጥ ለአካላዊም ሆነ ለአእምሯዊ ሕመም ተጋልጠዋል። ልጆቹ ወላጆቻቸው በመፋታታቸው የሚሰማቸው የተመሰቃቀለ ስሜትና ሐዘን ብዙውን ጊዜ ለበርካታ ዓመታት አብሯቸው ይቆያል። የተፋቺዎቹ ወላጆችና ጓደኞችም ይጎዳሉ። የጋብቻ መሥራች የሆነው አምላክስ ሁኔታውን እንዴት ይመለከተዋል?

      4. በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን እንዴት መፍታት ይገባል?

      4 ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንደተገለጸው አምላክ ጋብቻን ያቋቋመው የዕድሜ ልክ ጥምረት እንዲሆን አስቦ ነው። (ዘፍጥረት 2:​24) ታዲያ ብዙ ትዳሮች የሚፈርሱት ለምንድን ነው? ይህ በቅጽበት የሚከሰት ነገር ላይሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ይታያሉ። በትዳር ውስጥ ትንንሽ የነበሩት ችግሮች ቀስ በቀስ እያደጉ ሄደው ፈጽሞ እልባት የማይገኝላቸው መስለው የሚታዩበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። ሆኖም እነዚህ ችግሮች በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ ወዲያውኑ ቢፈቱ ብዙ ትዳሮች ከመፍረስ ሊድኑ ይችላሉ።

      ከገሐዱ ዓለም ውጭ የሆነ ነገር አትጠብቁ

      5. በማንኛውም ትዳር ውስጥ የትኛውን እውነታ መቀበል ያስፈልጋል?

      5 አንዳንድ ጊዜ ችግር የሚፈጥረው ነገር አንደኛው ወይም ሁለቱም የትዳር ጓደኞች ከገሐዱ ዓለም ውጪ የሆኑ ነገሮች የሚጠብቁ መሆናቸው ነው። የፍቅር ታሪኮች፣ የታወቁ መጽሔቶች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ከገሐዱ ዓለም ውጪ የሆነ ተስፋና ሕልም ሊፈጥሩ ይችላሉ። እነዚህ ሕልሞች መና ሲቀሩ አንድ ሰው እንደተታለለ ሊሰማውና ሊበሳጭ አልፎ ተርፎም ክፉኛ ሊያማርር ይችላል። ይሁን እንጂ ፍጹም ያልሆኑ ሁለት ሰዎች በትዳራቸው መደሰት የሚችሉት እንዴት ነው? ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል።

      6. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻን በተመለከተ ምን ሚዛናዊ አመለካከት አለው? (ለ) በትዳር ውስጥ አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

      6 መጽሐፍ ቅዱስ እውነታውን ቁልጭ አድርጎ ይገልጻል። ትዳር ስለሚያስገኘው ደስታ በግልጽ ይናገራል፤ ሆኖም የሚያገቡ “በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል” የሚል ማስጠንቀቂያም ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 7:​28) ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ፍጹማን አይደሉም፤ የኃጢአት ዝንባሌ አላቸው። አስተሳሰባቸውም ሆነ ስሜታቸው እንዲሁም አስተዳደጋቸው የተለያየ ነው። አንዳንድ ጊዜ ባልና ሚስት በገንዘብ፣ በልጆቻቸውና በዘመዶቻቸው ሊጨቃጨቁ ይችላሉ። አንዳንድ ነገሮችን አብሮ ለመሥራት የሚያስችል በቂ ጊዜ ማጣትና ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ችግሮችም የግጭት መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ።b እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች ለመፍታት ጊዜ ይጠይቃል፤ ሆኖም ተስፋ አትቁረጡ! አብዛኞቹ የትዳር ጓደኛሞች እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች በመጋፈጥ በሁለቱም ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መፍትሔዎች ማግኘት ችለዋል።

      በመካከላችሁ አለመግባባት ሲፈጠር ተወያዩ

      በገጽ 154 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      በመካከላችሁ የሚፈጠሩትን ችግሮች ወዲያውኑ ለመፍታት ጥረት አድርጉ። በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ

      7, 8. የትዳር ጓደኛሞች ስሜታቸው በሚጎዳበት ወይም አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ መፍታት የሚቻልበት ቅዱስ ጽሑፋዊ መንገድ ምንድን ነው?

      7 ብዙዎች ስሜታቸው ተጎድቶ፣ አለመግባባት ተፈጥሮ፣ ወይም ስህተት ሠርተው በጉዳዩ ላይ በሚወያዩበት ጊዜ በተረጋጋ መንፈስ መነጋገር ይቸግራቸዋል። “በትክክል የተረዳሽኝ/ኸኝ አልመሰለኝም” ብለው በግልጽ ከመናገር ይልቅ ስሜታዊ ሊሆኑና ችግሩ ይባስ ሊጋነን ይችላል። ብዙዎቹ “ለራስሽ/ህ ብቻ ነው የምታስቢው/በው” ወይም ደግሞ “አትወጂኝም/ደኝም” ይላሉ። በዚህ ጊዜ እንዲህ የተባለው የትዳር ጓደኛ ከጭቅጭቅ ለመሸሽ ሲል ምንም ምላሽ ላይሰጥ ይችላል።

      8 ከዚህ ይልቅ የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተሉ የተሻለ ነው:- “ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ።” (ኤፌሶን 4:​26) አንድ ደስተኛ ባልና ሚስት የጋብቻቸውን 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲያከብሩ ለትዳራቸው ስኬት ቁልፉ ምን እንደሆነ ተጠይቀው ነበር። ባልየው “በመካከላችን ቀላል የሆነ አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ እንኳ ጉዳዩን ለነገ አናሳድረውም” ብሏል።

      9. (ሀ) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሐሳብ ልውውጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተገለጸው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ምንም እንኳ ድፍረትና ትሕትና የሚጠይቅ ቢሆንም የትዳር ጓደኛሞች ብዙውን ጊዜ ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?

      9 ባልና ሚስት በመካከላቸው አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ሁለቱም ‘ለመስማት የፈጠኑ፣ ለመናገርም የዘገዩ ለቁጣም የዘገዩ’ መሆን አለባቸው። (ያዕቆብ 1:​19) ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች በጥሞና ከተደማመጡ በኋላ ይቅርታ የመጠየቅን አስፈላጊነት ሊገነዘቡ ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:​16) “ስለጎዳሁሽ/ሁህ ይቅርታ” ብሎ ከልብ ምሕረት መጠየቅ ትሕትናና ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም የትዳር ጓደኛሞች በመካከላቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በዚህ መንገድ መፍታታቸው ለችግሮቻቸው እልባት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው ባለው ወዳጅነት ይበልጥ ደስታ የሚያስገኝላቸውን ፍቅርና የጠበቀ ዝምድና እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።

      ትዳር የሚጠይቀውን ግዴታ ማሟላት

      10. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጥበቃ እንዲሆናቸው ያቀረበው የትኛው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ ላለ ክርስቲያንም ሊሠራ ይችላል?

      10 ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ በጊዜው ‘ዝሙት በጣም ተስፋፍቶ ስለነበረ’ እንዲያገቡ ሐሳብ አቅርቦላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:​2) በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም ከጥንቷ ቆሮንቶስ ባላነሰ እንዲያውም በከፋ መጠን ተበላሽቷል። የዓለም ሰዎች በግልጽ የሚነጋገሩባቸው የብልግና ወሬዎች፣ አሳፋሪ አለባበሳቸው፣ በመጽሔቶች፣ በመጽሐፎች፣ በቴሌቪዥንና በፊልሞች የሚቀርቡ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ታሪኮች አንድ ላይ ተዳምረው ልቅ የጾታ ፍላጎት ይቀሰቅሳሉ። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን የቆሮንቶስ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ “በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላል” ብሏቸዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 7:​9

      11, 12. (ሀ) ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ምን የማድረግ ግዴታ አለባቸው? ይህንንስ በምን መንፈስ ሊያደርጉት ይገባል? (ለ) ለተወሰነ ጊዜ መከላከል ቢያስፈልግ ይህን ማድረግ የሚገባው እንዴት ነው?

      11 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የተጋቡ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል ያዝዛቸዋል:- “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፣ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ።” (1 ቆሮንቶስ 7:​3) ይበልጥ ትኩረት የተሰጠው መቀበሉ ሳይሆን መስጠቱ እንደሆነ ልብ በሉ። ሁለቱም የትዳር ጓደኞች አንዳቸው ለሌላው ጥቅም የሚያስቡ ከሆነ የፆታ ግንኙነት በትዳር ውስጥ እውነተኛ ደስታ ሊያስገኝ ይችላል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች ሚስቶቻቸውን “በማስተዋል” እንዲይዟቸው ያዝዛል። (1 ጴጥሮስ 3:​7) ይህ በተለይ ትዳር የሚጠይቀውን ግዴታ በመስጠትና በመቀበል ረገድ እንዲህ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። አንዲት ሚስት ፍቅርና አሳቢነት በተሞላበት መንገድ ካልተያዘች በዚህ የትዳር መስክ ደስታ ለማግኘት ልትቸገር ትችላለች።

      12 የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው የሚከላከሉባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ። ሚስትየዋ በወሩ ውስጥ በተወሰኑ ወቅቶች ላይ ወይም ደግሞ በጣም በሚደክማት ጊዜ እንዲህ ማድረጓ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። (ከዘሌዋውያን 18:​19 ጋር አወዳድሩ።) ባልየው በሥራ ቦታ ከባድ ችግር ሲያጋጥመውና ስሜቱ እንደተሟጠጠ ሲሰማው እንዲህ ሊያደርግ ይችላል። በእንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች ወቅት ሁለቱም በግልጽ እስከተወያዩበትና ‘እስከተስማሙበት’ ድረስ ለጊዜው መከላከላቸው ችግር አይፈጥርም። (1 ቆሮንቶስ 7:​5) ይህ ማንኛቸውም ቢሆኑ ተቻኩለው የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዳይደርሱ ይረዳቸዋል። ይሁን እንጂ ሚስትየው ሆን ብላ ባሏ የሚገባውን የምትነፍገው ከሆነ ወይም ደግሞ ባልየው ሆን ብሎ ሚስቱ የሚገባትን ነገር ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የማያደርግላት ከሆነ ተጽዕኖ የተደረገበት ወገን ለፈተና ሊጋለጥ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ በትዳር ውስጥ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ።

      13. ክርስቲያኖች አስተሳሰባቸውን ንጹሕ አድርገው መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው?

      13 እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ የተጋቡ የአምላክ አገልጋዮችም ወራዳና ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ወሲባዊ ፍላጎት ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ ጽሑፎችና ፊልሞች መራቅ አለባቸው። (ቆላስይስ 3:​5) በተጨማሪም ከማንኛውም ተቃራኒ ፆታ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት አስተሳሰባቸውንና ድርጊታቸውን መጠበቅ አለባቸው። ኢየሱስ “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 5:​28) ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት የሚሰጠውን ምክር ሥራ ላይ በማዋል ፈተና ውስጥ ከመውደቅና ምንዝር ከመፈጸም መጠበቅ መቻል ይኖርባቸዋል። የፆታ ግንኙነት የጋብቻ መሥራች ከሆነው ከይሖዋ የተገኘ ጤናማና ውድ ስጦታ እንደሆነ አድርገው በመመልከት በትዳራቸው ውስጥ አስደሳች የሆነ የጠበቀ ግንኙነት ይዘው መመላለስ ይችላሉ።​—⁠ምሳሌ 5:​15-19

      በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ለፍቺ የሚያበቃ ምክንያት

      14. አንዳንድ ጊዜ ምን አሳዛኝ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል? ለምንስ?

      14 የሚያስደስተው ነገር በክርስቲያናዊ ትዳሮች ውስጥ የሚፈጠሩት አብዛኞቹ ችግሮች እልባት ሊያገኙ የሚችሉ መሆናቸው ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን እንዲህ ማድረግ አይቻል ይሆናል። ሰዎች ፍጹማን ካለመሆናቸውም በላይ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ኃጢአተኛ ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩ አንዳንዶቹ ትዳሮች የመፍረስ አደጋ ያጠላባቸዋል። (1 ዮሐንስ 5:​19) ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነቱን ትዕግሥትን እጅግ የሚፈታተን ሁኔታ መቋቋም ያለባቸው እንዴት ነው?

      15. (ሀ) በቅዱስ ጽሑፋዊው መመሪያ መሠረት የትዳር ጓደኛን ፈትቶ ሌላ ማግባት የሚቻለው ምን ሲሆን ብቻ ነው? (ለ) አንዳንዶች የፆታ ብልግና የፈጸመውን የትዳር ጓደኛቸውን ላለመፍታት የወሰኑት ለምንድን ነው?

      15 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ላይ እንደተገለጸው በቅዱስ ጽሑፋዊው መመሪያ መሠረት የትዳር ጓደኛን ፈትቶ ሌላ ማግባት የሚቻለው ምንዝር ሲፈጸም ብቻ ነው።c (ማቴዎስ 19:​9) የትዳር ጓደኛችሁ ምንዝር እንደፈጸመ ወይም እንደፈጸመች በቂ ማስረጃ ካገኛችሁ ከባድ ውሳኔ ከፊታችሁ ይደቀናል። ትዳራችሁ እንዳለ እንዲቀጥል ታደርጋላችሁ ወይስ ትፋታላችሁ? እንዲህ አድርጉ የሚል ሕግ የለም። አንዳንድ ክርስቲያኖች ከልቡ ንስሐ የገባውን የትዳር ጓደኛቸውን ሙሉ በሙሉ ይቅር ብለው ትዳራቸው እንዳለ እንዲቀጥል አድርገዋል፤ እንዲህ ማድረጋቸውም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ሌሎቹ ደግሞ ለልጆቻቸው ሲሉ ላለመፋታት ወስነዋል።

      16. (ሀ) አንዳንዶች ኃጢአት የሠራውን የትዳር ጓደኛቸውን ለመፍታት የገፋፏቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ተበዳዩ የትዳር ጓደኛ ለመፍታትም ሆነ ላለመፍታት በሚወስንበት ጊዜ ሌሎች ውሳኔውን መተቸት የሌለባቸው ለምንድን ነው?

      16 በሌላ በኩል ደግሞ የተፈጸመው ኃጢአት እርግዝና ወይም ደግሞ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፍ በሽታ ሊያስከትል ይችላል። ምናልባትም ደግሞ ልጆቹን በፆታ ከሚያስነውር ወላጅ መጠበቅ ሊያስፈልግ ይችላል። አንድ ውሳኔ ላይ ከመድረስ በፊት በጥሞና ማሰብ እንደሚገባ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛችሁ የፆታ ብልግና እንደፈጸመ ብታውቁና ከዚያ በኋላ እንደ ወትሮው ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸማችሁን ብትቀጥሉ ይቅር እንዳላችሁትና ትዳራችሁ እንዳለ እንዲቀጥል እንደምትፈልጉ ያሳያል። ከዚህ በኋላ በቅዱስ ጽሑፋዊው መመሪያ መሠረት የትዳር ጓደኛችሁን ፈትታችሁ ሌላ ማግባት አትችሉም። ማንም ሰው በእናንተ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ በውሳኔያችሁ ላይ ተጽዕኖ ማድረግም ሆነ አንድ ውሳኔ ላይ ከደረሳችሁ በኋላ ውሳኔያችሁን መተቸት የለበትም። ውሳኔያችሁ ያስከተለውን ውጤት ተቀብላችሁ መኖር ይገባችኋል። “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።”​—⁠ገላትያ 6:​5

      ለመለያየት የሚያበቁ ምክንያቶች

      17. ቅዱሳን ጽሑፎች ዝሙት ተፈጽሞ ካልሆነ በስተቀር መለያየትን ወይም ፍቺን በተ​መለከተ ምን ገደቦች አስቀምጠዋል?

      17 አንድ የትዳር ጓደኛ ዝሙት ባይፈጽምም እንኳ ከዚህ የትዳር ጓደኛ ለመለየት ምናልባትም ደግሞ ለመፋታት በቂ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎች ይኖራሉን? አዎ፣ ሆኖም በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ አንድ ክርስቲያን እንደገና ለማግባት በማሰብ ከሌላ ሰው ጋር ግንኙነት መመሥረት አይችልም። (ማቴዎስ 5:​32) መጽሐፍ ቅዱስ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ መለያየትን የሚፈቅድ ቢሆንም እንኳ ለመለያየት የመረጠው ወገን ‘ሳያገባ መኖር ወይም ከትዳር ጓደኛው ጋር መታረቅ’ እንዳለበት ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 7:​11) መለያየት የተሻለ አማራጭ ሊሆን የሚችልባቸው አንዳንድ አስከፊ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

      18, 19. እንደገና ማግባት የማይቻል ቢሆንም እንኳ አንድ ባለ ትዳር በሕጋዊ መንገድ መለያየት ወይም መፋታት የተሻለ መሆን አለመሆኑን እንዲመረምር ሊገፋፉት የሚችሉት አንዳንድ አስከፊ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

      18 ቤተሰቡ በባልየው የለየለት ስንፍና እና መጥፎ ልማድ ሳቢያ ከፍተኛ ችግር ላይ ሊወድቅ ይችላል።d የቤተሰቡን ገቢ በቁማር ሊያጠፋው ወይም ደግሞ የአደንዛዥ ዕፅ ወይም የአልኮል ሱሱን ለማርካት ሊጠቀምበት ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) እንዲህ ዓይነቱ ሰው አካሄዱን ለመለወጥ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ አልፎ ተርፎም ሚስቱ ራስዋ ሠርታ የምታገኘውን ገንዘብ የራሱን መጥፎ ልማድ ለማርካት የሚጠቀምበት ከሆነ ሚስትየዋ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከባልዋ በመለያየት የራስዋንም ሆነ የልጆቿን ደህንነት ለመጠበቅ ልትወስን ትችላለች።

      19 አንድ ባለትዳር የትዳር ጓደኛው ላይ ከባድ ጥቃት የሚፈጽም ከሆነ ምናልባትም ደግሞ የትዳር ጓደኛውን በተደጋጋሚ በመደብደብ ጤናዋንም ሆነ ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ሕጋዊ እርምጃ ሊታሰብበት ይችላል። በተጨማሪም አንድ ባለትዳር የትዳር ጓደኛው የአምላክን ሕግ በሆነ መንገድ እንድትጥስ ዘወትር ሊያስገድዳት የሚሞክር ከሆነና በተለይ ሁኔታው መንፈሳዊ ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥልበት ደረጃ ላይ ከደረሰ ለመለያየት ልትመርጥ ትችላለች። ችግር ላይ የወደቀው ወገን ‘ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ’ በሕጋዊ መንገድ ከመለያየት ሌላ አማራጭ እንደሌለው ሆኖ ሊሰማው ይችላል።​—⁠ሥራ 5:​29

      20. (ሀ) ከቤተሰብ መፍረስ ጋር በተያያዘ የጎለመሱ ጓደኞችና ሽማግሌዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ምን ማድረግስ የለባቸውም? (ለ) ያገቡ ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለያየትና ስለ ፍቺ የሚሰጠውን ሐሳብ ምን ለማድረግ ሰበብ አድርገው ሊጠቀሙበት አይገባም?

      20 በትዳር ጓደኛ ላይ በሚፈጸም በማንኛውም ዓይነት ከባድ ጥቃት ወቅት ማንም ሰው ተበዳዩን የትዳር ጓደኛ እንዲለያይም ሆነ ከትዳር ጓደኛው ጋር አብሮ እንዲኖር መጫን የለበትም። የጎለመሱ ጓደኞችና ሽማግሌዎች እርዳታና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሊሰጡ ቢችሉም በባልየውና በሚስትየው መካከል ያለውን እያንዳንዱን ነገር ማወቅ አይችሉም። ይህን ማየት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። እርግጥ አንዲት ሚስት ሰንካላ በሆነ ምክንያት ከባሏ ብትለያይ አምላክ ላቋቋመው የጋብቻ ዝግጅት አክብሮት እንደሌላት ያሳያል። ሆኖም በጣም አደገኛ የሆነ ዘላቂ ሁኔታ ተፈጥሮ ከባሏ ለመለያየት ብትወስን ማንም ሊተቻት አይገባም። ለመለያየት የሚፈልግን ክርስቲያን ባልንም በተመለከተ ይኸው ሁኔታ ይሠራል። “ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን።”​—⁠ሮሜ 14:​10

      የፈረሰ ትዳር እንዴት ዳግመኛ እንደተገነባ

      21. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትዳር የሚሰጠው ምክር የሚሠራ መሆኑን የትኛው ተሞክሮ ያሳያል?

      21 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሉቺያ ከባሏ ከተለያየች ከሦስት ወራት በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘችና ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። “ችግሬን ሊፈቱ የሚችሉ ተግባራዊ ሐሳቦችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሳገኝ በጣም ተገረምኩ” ስትል ገልጻለች። “በመጀመሪያው ሳምንት ካጠናሁ በኋላ ወዲያውኑ ከባሌ ጋር ለመታረቅ ወሰንኩ። በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቁ ትዳሮችን እንዴት ከመፍረስ ማዳን እንደሚችል ያውቃል ማለት እችላለሁ፤ ምክንያቱም ትምህርቶቹ የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው እንዴት መከባበር እንደሚችሉ ያስተምሯቸዋል። አንዳንዶች እንደሚሉት የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦችን የሚከፋፈሉ አይደሉም። በእኔ ላይ የተፈጸመው ከዚህ ተቃራኒ የሆነው ነገር ነው።” ሉቺያ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሕይወቷ ውስጥ በሥራ ላይ ማዋል ተምራለች።

      22. ባለ ትዳሮች ሁሉ በምን ነገር ላይ ሙሉ እምነት ሊኖራቸው ይገባል?

      22 ይህ ሁኔታ የታየው በሉቺያ ሕይወት ላይ ብቻ አይደለም። ትዳር ሸክም ሳይሆን በረከት መሆን ይኖርበታል። ይህ እንዲሆን ይሖዋ ትዳርን አስመልክቶ እስከ ዛሬ ከተጻፉት ሁሉ የላቀ ምክር የሚገኝበትን ምንጭ ማለትም ውድ ቃሉን አዘጋጅቷል። መጽሐፍ ቅዱስ “ማስተዋል ለጎደላቸው ጥበብን” [የ1980 ትርጉም] ሊሰጥ ይችላል። (መዝሙር 19:​7-11) በቋፍ ላይ የነበሩ ብዙ ትዳሮችን አድኗል፤ ከባድ ችግር የነበረው ሌሎች ብዙ ትዳሮችም ችግራቸውን መፍታት እንዲችሉ ረድቷቸዋል። የትዳር ጓደኛሞች ሁሉ ይሖዋ አምላክ ትዳርን አስመልክቶ በሚሰጠው ምክር ላይ ሙሉ እምነት ይኖራቸው ዘንድ ምኞታችን ነው። ምክሩ ውጤታማ ነው!

      a ስሟን ለውጠነዋል።

      b ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

      c በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዝሙት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ምንዝርን፣ ግብረ ሰዶምን፣ ከእንስሳት ጋር የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነትና የፆታ ብልቶችን በመጠቀም ሆን ተብሎ የሚፈጸሙ ሌሎች ልቅ የፆታ ግንኙነቶችን ያጠቃልላል።

      d ይህ ሁኔታ አንድ ባል አሳቢ ሆኖ እያለ እንደ በሽታ ወይም ደግሞ ሥራ አጥነት በመሳሰሉ ከአቅሙ በላይ በሆኑ ችግሮች ሳቢያ ለቤተሰቡ የሚገባውን ማሟላት የማይችልባቸውን ሁኔታዎች አይጨምርም።

      የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች . . . አንድ ትዳር እንዳይፈርስ ለማድረግ ሊረዱ የሚችሉት እንዴት ነው?

      ትዳር ደስታም፣ መከራም ያስከትላል።​—⁠ምሳሌ 5:​18, 19፤ 1 ቆሮንቶስ 7:​28

      በመካከላችሁ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ወዲያውኑ መፍታት ይኖርባችኋል።​—⁠ኤፌሶን 4:​26

      ውይይት በሚደረግበት ጊዜ ማዳመጥ የመናገርን ያህል አስፈላጊ ነው።​—⁠ያዕቆብ 1:​19

      የትዳር ጓደኛሞች ያለባቸውን ግዴታ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነና አሳቢነት በተሞላበት መንፈስ መወጣት አለባቸው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 7:​3-5

  • በእርጅና ዘመንም ተደጋግፎ መኖር
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
    • ምዕራፍ አሥራ አራት

      በእርጅና ዘመንም ተደጋግፎ መኖር

      1, 2. (ሀ) ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ምን ለውጦች ይከሰታሉ? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሰዎች በእርጅና ዘመናቸው እርካታ ያገኙት እንዴት ነው?

      በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ ብዙ ለውጦች ይከሰታሉ። አካላችን እየደከመ ኃይላችን እየተሟጠጠ ይሄዳል። መልካችንን በመስታወት ስንመለከት ቆዳችን እየተሸበሸበ፣ ፀጉራችን እየሸበተ አልፎ ተርፎም እየሳሳ መሆኑን እናስተውላለን። አንዳንድ ነገር እየዘነጋን እንቸገር ይሆናል። ልጆች ሲያገቡና ከዚያም የልጅ ልጆች ሲመጡ አዳዲስ ዝምድናዎች ይፈጠራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ከሰብዓዊ ሥራቸው በጡረታ መገለላቸው የተለመደውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ይለውጠዋል።

      2 እውነቱን ለመናገር ከሆነ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ሁኔታዎች ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ። (መክብብ 12:​1-8) ያም ሆኖ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩትን የአምላክ አገልጋዮች ተመልከቱ። ምንም እንኳ በመጨረሻ ሞት ቢወስዳቸውም በእርጅና ዘመናቸው ትልቅ እርካታ ያመጣላቸውን ጥበብና ማስተዋል አግኝተዋል። (ዘፍጥረት 25:​8፤ 35:​29፤ ኢዮብ 12:​12፤ 42:​17) በእርጅና ዘመናቸውም ደስተኞች ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? ዛሬ እኛ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የምናገኛቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ በሥራ ላይ በማዋላቸው እንደሆነ ግልጽ ነው።​—⁠መዝሙር 119:​105፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

      3. ጳውሎስ በዕድሜ ለገፉ ወንዶችና ሴቶች ምን ምክር ሰጥቷል?

      3 ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ጥሩ መመሪያ ሰጥቷል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሽማግሌዎች ልከኞች፣ ጭምቶች፣ ራሳቸውን የሚገዙ፣ በእምነትና በፍቅር በመጽናትም ጤናሞች እንዲሆኑ ምከራቸው፤ እንዲሁም አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ፣ የማያሙ፣ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ፣ በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ።” (ቲቶ 2:​2, 3) ይህን ምክር መከተላችሁ በእርጅና ዘመን የሚያጋጥሟችሁን ፈታኝ ሁኔታዎች እንድትቋቋሙ ሊረዳችሁ ይችላል።

      ልጆቻችሁ ራሳቸውን ችለው ሲወጡ ከሚፈጠረው ሁኔታ ጋር ራሳችሁን አስማሙ

      4, 5. ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ምን ይሰማቸዋል? አንዳንዶች ከተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ያስማሙት እንዴት ነው?

      4 የኃላፊነት ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ ራስን ከተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ጋር ማላመድ አስፈላጊ ነው። ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆች ራሳቸውን ችለው ከቤት በሚወጡበትና በሚያገቡበት ጊዜ ይህን የማድረጉ አስፈላጊነት ጎልቶ ይታያል። ብዙ ወላጆች ዕድሜያቸው እየገፋ መሆኑን የሚያስታውሳቸው የመጀመሪያው ነገር ይህ ሁኔታ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው ለአካለ መጠን መድረሳቸው የሚያስደስታቸው ቢሆንም እንኳ ብዙውን ጊዜ ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ለመኖር የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አድርጌያለሁ ወይስ አላደረግኩም የሚለው ነገር ያስጨንቃቸዋል። ልጆቻቸውን ከአጠገባቸው ማጣታቸውም ቅር ያሰኛቸዋል።

      5 ወላጆች ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው ከቤት ከወጡም በኋላ ስለ ልጆቻቸው ደህንነት ማሰባቸው አይቀርም። “ብዙውን ጊዜ ደህንነታቸውን ከእነሱ መስማት መቻሌ ብቻ እንኳ ያስደስተኛል” ስትል አንዲት እናት ተናግራለች። አንድ አባት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ልጃችን ራሷን ችላ መኖር ስትጀምር በጣም ተረብሸን ነበር። ሁልጊዜ ማንኛውንም ነገር አብረን እንሠራ ስለነበር በጣም አጉድላናለች።” እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ከእነሱ መለየታቸው የፈጠረባቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ የተቋቋሙት እንዴት ነው? በአብዛኛው ይህን ማድረግ የቻሉት ለሌሎች ሰዎች አሳቢነት በማሳየትና በመርዳት ነው።

      6. በቤተሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት ለመያዝ ሊረዳ የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

      6 ልጆች ሲያገቡ የወላጆቹ የኃላፊነት ቦታ ይለወጣል። ዘፍጥረት 2:​24 “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ሲል ይገልጻል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ወላጆች ስለ ራስነት ሥልጣንና ስለ ሥርዓታማነት የሚገልጹትን አምላካዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ማክበራቸው ለተፈጠሩት ሁኔታዎች ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 11:​3፤ 14:​33, 40

      7. አንድ አባት ሴቶች ልጆቹ አግብተው መኖር ሲጀምሩ ምን ጥሩ አመለካከት አዳብሯል?

      7 አንድ ባልና ሚስት ሁለት ሴቶች ልጆቻቸው አግብተው ከቤት ከወጡ በኋላ የብቸኝነት ስሜት ተሰማቸው። መጀመሪያ ላይ ባልየው በልጆቹ ባሎች አልተደሰተም ነበር። ሆኖም ስለ ራስነት ሥልጣን በሚናገረው መሠረታዊ ሥርዓት ላይ በሚገባ ሲያሰላስል በአሁኑ ጊዜ በየቤተሰባቸው ላይ ሥልጣን ያላቸው የልጆቹ ባሎች እንደሆኑ ተገነዘበ። ስለዚህ ልጆቹ ምክር ሲጠይቁት ባሎቻቸው በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሐሳብ በመጠየቅ በተቻለ መጠን የእነሱን ሐሳብ ለመደገፍ መጣር ጀመረ። በአሁኑ ጊዜ የልጆቹ ባሎች እንደ ጓደኛቸው የሚመለከቱት ከመሆናቸውም በላይ የሚሰጣቸውን ምክር በደስታ ይቀበላሉ።

      8, 9. አንዳንድ ወላጆች ለአካለ መጠን የደረሱት ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው መኖር መጀመራቸው ካስከተለው ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ያስማሙት እንዴት ነው?

      8 አዲስ ተጋቢዎች ቅዱስ ጽሑፉን የሚቃረን ነገር ባያደርጉም እንኳ ወላጆቻቸው የተሻለ ነው ብለው የሚያስቡትን ነገር ሳያደርጉ ቢቀሩስ? “ሁልጊዜ ጉዳዩን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር እንዲመለከቱት እንረዳቸዋለን” ሲሉ ያገቡ ልጆች ያሏቸው አንድ ባልና ሚስት ገልጸዋል፤ “ሆኖም በወሰዱት ውሳኔ ባንስማማ እንኳ ውሳኔያቸውን ተቀብለን ድጋፍና ማበረታቻ እንሰጣቸዋለን።”

      9 በአንዳንድ የእስያ አገሮች አንዳንድ እናቶች ወንዶች ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው መኖራቸው አይዋጥላቸውም። ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊ ሥርዓትንና የራስነትን ሥልጣን የሚያከብሩ ከሆነ ከምራቶቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግጭት በጣም ይቀንሳል። አንዲት ክርስቲያን ሴት ወንዶች ልጆቿ ከቤተሰባቸው ተለይተው ራሳቸውን ችለው መኖር መጀመራቸው “ትልቅ የደስታ ምንጭ” ሆኖላታል። አዳዲስ ቤተሰቦቻቸውን የማስተዳደር ችሎታቸውን ማየቷ እጅግ አስደስቷታል። ይህ ደግሞ እሷም ሆነች ባሏ በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ ያለባቸው አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ሸክም እየቀለለላቸው እንዲሄድ ረድቷቸዋል።

      የትዳራችሁን ማሰሪያ እንደ አዲስ ማጠናከር

      በገጽ 166 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      በዕድሜ እየገፋችሁ ስትሄዱ አንዳችሁ ለሌላው ያላችሁን ፍቅር ግለጹ

      10, 11. ሰዎች በዕድሜ ጠና እያሉ ሲሄዱ ራሳቸውን ከአንዳንድ ወጥመዶች መጠበቅ እንዲችሉ የሚረዳቸው የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ነው?

      10 ሰዎች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የተለያዩ ነገሮችን ሲያደርጉ ይታያሉ። አንዳንዶቹ ወንዶች ወጣት መስለው ለመታየት ለየት ያለ አለባበስ ይለብሳሉ። ብዙ ሴቶች ማረጥ የሚያስከትላቸው ለውጦች ያስጨንቋቸዋል። የሚያሳዝነው አንዳንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ወንዶች ከወጣት ሴቶች ጋር በመቃበጥ የትዳር ጓደኞቻቸው ቅር እንዲሰኙና የቅናት ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጓቸዋል። ሆኖም ፊሪሃ አምላክ ያላቸው በዕድሜ የገፉ ወንዶች ትክክለኛ ያልሆኑ ፍላጎቶችን በመቆጣጠር “እንደ ባለ አእምሮ” ያስባሉ። (1 ጴጥሮስ 4:​7) የጎለመሱ ሴቶችም እንደዚሁ ለባሎቻቸው ባላቸው ፍቅርና ይሖዋን ለማስደሰት ባላቸው ፍላጎት ተገፋፍተው ትዳራቸው ጸንቶ እንዲቀጥል ጠንክረው ይሠራሉ።

      11 ንጉሥ ልሙኤል በመንፈስ አነሳሽነት ተገፋፍቶ ‘ዕድሜዋን ሙሉ ለባሏ ክፉ ሳይሆን መልካም ለምታደርገው ባለሙያ ሚስት’ የምስጋና ቃላት ጽፏል። አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱ ዕድሜዋ እየገፋ ሲሄድ የሚያጋጥማትን ማንኛውንም ዓይነት የስሜት መረበሽ ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት እንዲሁ በቸልታ አያልፍም። ለእሷ ያለው ፍቅር ‘እንዲያመሰግናት’ ይገፋፋዋል።​—⁠ምሳሌ 31:​10, 12, 28

      12. ባልና ሚስት ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ይበልጥ እየተቀራረቡ መሄድ የሚችሉት እንዴት ነው?

      12 ልጅ በማሳደግ ባሳለፋችኋቸው ውጥረት የበዛባቸው ዓመታት ሁለታችሁም ልጆቻችሁ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ስትሉ የግል ፍላጎቶቻችሁን በደስታ ወደ ጎን አድርጋችሁ ሊሆን ይችላል። ልጆቻችሁ ራሳቸውን ችለው መኖር ከጀመሩ በኋላ ግን እንደገና በራሳችሁ የትዳር ሕይወት ላይ ታተኩራላችሁ። አንድ ባል “ሴቶች ልጆቼ ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ከሚስቴ ጋር እንደ አዲስ መጠናናት ጀመርኩ” ሲል ተናግሯል። አንድ ሌላ ባል ደግሞ “አንዳችን ለሌላው ጤንነት የምናስብ ከመሆኑም በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግን አስፈላጊነት አንዳችን ለሌላው እናሳስባለን” ሲል ተናግሯል። እሱና ሚስቱ የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማቸው ለሌሎቹ የጉባኤው አባላት የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ያሳያሉ። አዎ፣ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት በረከት ያስገኛል። ከዚህም በላይ ይሖዋን ያስደስተዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​4፤ ዕብራውያን 13:​2, 16

      13. ባልና ሚስት በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ ግልጽነትና ሐቀኝነት ምን ሚና ይጫወታሉ?

      13 ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ በምታደርጉበት ጊዜ ምንም የምትደባበቁት ነገር መኖር የለበትም። በግልጽ ተነጋገሩ። (ምሳሌ 17:​27) “አንዳችን ሌላውን በመንከባከብና አሳቢ በመሆን በመካከላችን ያለውን ወዳጅነት አጠናክረነዋል” ሲል አንድ ባል ተናግሯል። ሚስቱ ከባሏ አባባል ጋር በመስማማት “ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ አብረን ሻይ የመጠጣት፣ የመጫወትና እርስ በርስ የመረዳዳት ልማድ አዳብረናል” ብላለች። ምንም ሳትደባበቁ በግልጽ መወያየታችሁ የትዳር ፀር የሆነው ሰይጣን የሚሰነዝራቸውን ጥቃቶች መቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ በመስጠት የትዳራችሁን ማሰሪያ እንድታጠብቁ ሊረዳችሁ ይችላል።

      በልጅ ልጆቻችሁ ተደሰቱ

      14. ጢሞቴዎስ ክርስቲያን ሆኖ እንዲያድግ በመርዳት ረገድ አያቱ ምን ሚና እንደተጫወተች ግልጽ ነው?

      14 የልጅ ልጆች የአረጋውያን “አክሊል” ናቸው። (ምሳሌ 17:⁠6) ከልጅ ልጆች ጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍ የሚያስደስትና መንፈስን የሚያድስ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከልጅዋ ከኤውንቄ ጋር ሆና የልጅ ልጅዋ ለሆነው ለጢሞቴዎስ እምነቷን ስላካፈለችው ሎይድ ስለተባለች አረጋዊት ሴት ይናገራል። ይህ ወጣት ገና ከልጅነቱ ጀምሮ እናቱና አያቱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ ሊገነዘብ ችሏል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 1:​5፤ 3:​14, 15

      15. የልጅ ልጆችን በተመለከተ አያቶች ምን ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ? ሆኖም ምን ከማድረግ መቆጠብ አለባቸው?

      15 ስለዚህ የልጅ ልጆች ያሏቸው ወላጆች በዚህ ረገድ እጅግ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። የልጅ ልጆች ያሏችሁ ወላጆች ቀደም ሲል ስለ ይሖዋ ዓላማዎች የሚገልጸውን እውቀት ለራሳችሁ ልጆች አካፍላችሁ ነበር። አሁን ደግሞ ለሌላ ትውልድ ይህንኑ ማድረግ ትችላላችሁ! ብዙ ትንንሽ ልጆች አያቶቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ሲተርኩላቸው መስማት ያስደስታቸዋል። እርግጥ ነው፣ አባትየው በልጆቹ አእምሮ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በመቅረጽ ረገድ ያለበትን ኃላፊነት ትወስዳላችሁ ማለት አይደለም። (ዘዳግም 6:​7) ከዚህ ይልቅ ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ ትረዱታላችሁ። የሚከተለው የመዝሙራዊው ጸሎት የእናንተም ጸሎት ይሁን:- “እስካረጅም እስክሸመግልም ድረስ፣ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኃይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፣ አቤቱ፣ አትተወኝ።”​—⁠መዝሙር 71:​18፤ 78:​5, 6

      16. አያቶች በቤተሰባቸው ውስጥ ለግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ ምን ከማድረግ መራቅ አለባቸው?

      16 የሚያሳዝነው አንዳንድ አያቶች የልጅ ልጆቻቸውን በጣም ስለሚያሞላቅቋቸው በእነሱና በራሳቸው ልጆች መካከል ግጭት ይፈጠራል። ይሁን እንጂ የልጅ ልጆቻችሁ ከልባችሁ የምታሳዩአቸው ደግነት አንዳንድ ጉዳዮችን ለወላጆቻቸው መግለጽ በሚከብዳቸው ጊዜ እናንተን ማማከር እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ሊፈጥርላቸው ይችላል። አያቶቻቸው የሚያሞላቅቋቸው ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በሚጋጩበት ጊዜ አያቶቻቸው ከእነሱ ጎን እንደሚቆሙ አድርገው ያስባሉ። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? ጥበብ በመጠቀም የልጅ ልጆቻችሁ ለወላጆቻቸው ግልጽ እንዲሆኑ አበረታቷቸው። ይህ ይሖዋን እንደሚያስደስተው ልትገልጹላቸው ትችላላችሁ። (ኤፌሶን 6:​1-3) አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ወላጆቻቸውን ቀርባችሁ በማነጋገር ለልጆቹ መንገዱን ልታመቻቹላቸው ትችላላችሁ። በሕይወት ባሳለፋችኋቸው በርካታ ዓመታት የተማራችሁትን ነገር ለልጅ ልጆቻችሁ በግልጽ ንገሯቸው። ሐቀኝነታችሁና ግልጽነታችሁ ሊጠቅማቸው ይችላል።

      ዕድሜያችሁ እየገፋ መሄዱ ከሚያስከትለው ሁኔታ ጋር ራሳችሁን አስማሙ

      17. በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች የትኛውን የመዝሙራዊውን ቁርጥ ውሳኔ መከተል ይኖርባቸዋል?

      17 ዕድሜያችሁ እየገፋ ሲሄድ ቀደም ሲል ታደርጓቸው የነበሩትን ወይም ደግሞ ልታደርጉ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ ማድረግ ይሳናችኋል። አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን የእርጅና ሂደት አምኖ መቀበልና መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው? በውስጣችሁ ገና የ30 ዓመት ሰው እንደሆናችሁ ይሰማችሁ ይሆናል፤ ሆኖም መልካችሁን በመስታወት ስትመለከቱ እውነታው ሌላ ሆኖ ታገኙታላችሁ። ተስፋ አትቁረጡ። መዝሙራዊው ይሖዋን እንዲህ ሲል ተማጽኗል:- “በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፣ ጉልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ።” የመዝሙራዊውን ዓይነት አቋም ለመውሰድ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። መዝሙራዊው “እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፣ በምስጋናህም ሁሉ ላይ እጨምራለሁ” ብሏል።​—⁠መዝሙር 71:​9, 14

      18. አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ጡረታ ሲወጣ ጊዜውን ጠቃሚ በሆነ መንገድ ሊጠቀምበት የሚችለው እንዴት ነው?

      18 ብዙዎች ከሰብዓዊ ሥራቸው በጡረታ ከተገለሉ በኋላ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን ምስጋና ከፍ ለማድረግ አስቀድመው ዝግጅት አድርገዋል። “ሴት ልጃችን ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ የማደርገውን ነገር አስቀድሜ አቅጄ ነበር” ሲል በአሁኑ ጊዜ ጡረታ የወጣ አንድ አባት ገልጿል። “በሙሉ ጊዜ የስብከት አገልግሎት ለመሳተፍ ወስኜ ነበር፤ ይሖዋን ይበልጥ ሙሉ በሙሉ ለማገልገል የሚያስችል ነፃነት ለማግኘት ስል የንግድ ድርጅቴን ሸጥኩ። አምላክ መመሪያ እንዲሰጠኝ ጸለይኩ።” ጡረታ ወደምትወጡበት ዕድሜ እየተቃረባችሁ ከሆነ በሚከተለው የታላቁ ፈጣሪያችን መግለጫ ልትጽናኑ ትችላላችሁ:- “እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፣ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ።”​—⁠ኢሳይያስ 46:​4

      19. በዕድሜ ለገፉት ምን ምክር ተሰጥቷል?

      19 ከሰብዓዊ ሥራ በጡረታ መገለል ከሚያስከትለው ሁኔታ ጋር ራስን ማስማማት ቀላል ላይሆን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዕድሜ የገፉ ወንዶች “ልከኞች” እንዲሆኑ መክሯል። ይህም የተንደላቀቀ ኑሮ የመኖርን ፍላጎት በመቆጣጠር በሁሉም ነገር ቁጥብ መሆን ይጠይቃል። ጡረታ ከወጣችሁ በኋላ ከበፊቱ ይበልጥ የተደራጃችሁ መሆንና ራሳችሁን መገሰጽ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። እንግዲያው ራሳችሁን በሥራ አስጠምዱ፤ “ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና . . . የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” (1 ቆሮንቶስ 15:​58) ሌሎችን መርዳት እንድትችሉ እንቅስቃሴያችሁን አስፉት። (2 ቆሮንቶስ 6:​13) ብዙ ክርስቲያኖች ዕድሜያቸው በሚፈቅድላቸው መጠን በምሥራቹ ስብከት በቅንዓት በመሳተፍ ይህን በማድረግ ላይ ናቸው። በዕድሜ እየገፋችሁ ስትሄዱ “በእምነትና በፍቅር በመጽናትም ጤናሞች” ሁኑ።​—⁠ቲቶ 2:​2

      የትዳር ጓደኛችሁን በሞት ማጣታችሁ የሚያስከትልባችሁን ሐዘን መቋቋም

      20, 21. (ሀ) በዚህ ባለንበት ሥርዓት ውስጥ ባልና ሚስት በመጨረሻ በምን መለያየታቸው አይቀርም? (ለ) ሐና የትዳር ጓደኛቸው በሞት ለተለያቸው ሰዎች ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው እንዴት ነው?

      20 ምንም እንኳ ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ቢሆንም በዚህ ባለንበት ሥርዓት ውስጥ የትዳር ጓደኛሞች በመጨረሻ በሞት መለያየታቸው አይቀርም። የትዳር ጓደኛቸው በሞት የተለያቸው ክርስቲያኖች የሚወዱት ጓደኛቸው በእንቅልፍ ላይ እንደሚገኝና ወደፊት ዳግመኛ እንደሚያገኙት እርግጠኞች ናቸው። (ዮሐንስ 11:​11, 25) ያም ሆኖ ግን የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣቱ ከባድ ሐዘን ያስከትላል። የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣው ሰው የደረሰበትን ሐዘን መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው?a

      21 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸች አንዲት ሴት ያደረገችውን ነገር ማስታወሱ ይረዳል። ሐና ባሏ በሞት የተለያት በተጋቡ በሰባት ዓመት ውስጥ ነበር፤ ስለ እሷ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በተጻፈ ጊዜ 84 ዓመት ሆኗት ነበር። ቧላን በሞት ስታጣ እጅግ እንዳዘነች ጥርጥር የለውም። ይህን ሐዘን የተቋቋመችው እንዴት ነው? ቀንና ሌሊት በቤተ መቅደሱ ለይሖዋ አምላክ ቅዱስ አገልግሎት ታቀርብ ነበር። (ሉቃስ 2:​36-38) ሐና ከልብ የመነጨ አገልግሎት በማቅረብ ያሳለፈችው ሕይወት መበለት መሆኗ ያስከተለባትን ሐዘንና የብቸኝነት ስሜት መቋቋም እንድትችል በጣም እንደረዳት ምንም አያጠራጥርም።

      22. የትዳር ጓደኞቻቸውን በሞት ያጡ አንዳንዶች የብቸኝነትን ስሜት የተቋቋሙት እንዴት ነው?

      22 “ከሁሉ ይበልጥ ፈታኝ ሆኖብኝ የነበረው ላጫውተው የምችል ጓደኛ ማጣቴ ነው” ስትል ከአሥር ዓመታት በፊት ባሏ በሞት የተለያት አንዲት የ72 ዓመት ሴት ገልጻለች። “ባሌ ጥሩ አዳማጭ ነበር። ስለ ጉባኤያችንና በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስለምናደርገው ተሳትፎ እንጫወት ነበር።” አንዲት ሌላ መበለት ደግሞ እንዲህ ብላለች:- “ጊዜ እያለፈ መሄዱ ራሱ ሐዘኑን የሚያቀል ቢሆንም እንኳ አንድ ሰው ከሐዘኑ መላቀቅ እንዲችል ይበልጥ የሚረዳው ነገር ባለው ጊዜ ተጠቅሞ የሚያደርገው ነገር ነው የሚል እምነት አለኝ። ያላችሁበት ሁኔታ ሌሎችን ለመርዳት የተሻለ አጋጣሚ ይፈጥርላችኋል።” ሚስቱን በሞት ያጣ አንድ የ67 ዓመት ሰው ከዚህ አባባል ጋር የሚስማማ ሐሳብ ሰጥቷል:- “ሌሎችን ማጽናናት የደረሰባችሁን ሐዘን መቋቋም እንድትችሉ የሚረዳ ጥሩ መንገድ ነው።”

      በእርጅና ዘመናችሁ አምላክ ከፍ አድርጎ ይመለከታችኋል

      23, 24. መጽሐፍ ቅዱስ በዕድሜ ለገፉት፣ በተለይ ደግሞ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ላጡ ምን ትልቅ መጽናኛ ይሰጣል?

      23 ሞት የምትወዱትን የትዳር ጓደኛ ሊነጥቃችሁ ቢችልም ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችሁ ነው። “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት” ሲል በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ንጉሥ ዳዊት ዘምሯል፤ “እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፣ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።”​—⁠መዝሙር 27:​4

      24 ሐዋርያው ጳውሎስ “በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​3) ከዚህ መመሪያ ቀጥሎ ያለው ምክር እንደሚጠቁመው የቅርብ ዘመዶች ለሌላቸውና የሚገባቸው ሆነው ለተገኙ መበለቶች ጉባኤው ቁሳዊ እርዳታ ማድረግ ሊያስፈልገው ይችላል። ሆኖም “አክብር” የሚለው መመሪያ ትርጉም እነዚህን መበለቶች ከፍ አድርጎ መመልከትንም ይጨምራል። የትዳር ጓደኞቻቸውን በሞት ያጡ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸውና እንደሚደግፋቸው ማወቃቸው በጣም ሊያጽናናቸው ይችላል!​—⁠ያዕቆብ 1:​27

      25. በዕድሜ የገፉ ሰዎች አሁንም ቢሆን ምን ግብ አላቸው?

      25 “የሽማግሌዎችም ጌጥ ሽበት ነው” ሲል በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ይናገራል። “በጽድቅ መንገድ ሲገኝ የውበት ዘውድ ነው።” (ምሳሌ 16:​31 NW፤ 20:​29) እንግዲያው ባለ ትዳሮችም ሆናችሁ ዳግመኛ ነጠላ የሆናችሁ የይሖዋን አገልግሎት በሕይወታችሁ ውስጥ ማስቀደማችሁን ቀጥሉ። በዚህ መንገድ በአምላክ ፊት ጥሩ ስም ታተርፋላችሁ፤ በተጨማሪም እርጅና የሚያስከትለው መከራ በማይኖርበት ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራችኋል።​—⁠መዝሙር 37:​3-5፤ ኢሳይያስ 65:​20

      a በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይበልጥ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የምትወዱት ሰው ሲሞት የተባለውን ብሮሹር ተመልከቱ።

      የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች . . . ባልና ሚስት በዕድሜ በሚገፉበት ጊዜ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

      የልጅ ልጆች ለአያቶቻቸው “አክሊል” ናቸው።​—⁠ምሳሌ 17:​6

      እርጅና ይሖዋን ለማገልገል ተጨማሪ አጋጣሚዎችን ሊያስገኝ ይችላል።​—⁠መዝሙር 71:​9, 14

      በዕድሜ የገፉ ሰዎች “ልከኞች” እንዲሆኑ ተመክረዋል።​—⁠ቲቶ 2:​2

      የትዳር ጓደኛቸው በሞት የተለያቸው ሰዎች ጥልቅ ሐዘን ቢደርስባቸውም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጽናኛ ሊያገኙ ይችላሉ።​—⁠ዮሐንስ 11:​11, 25

      ይሖዋ በዕድሜ የገፉ ታማኝ ሰዎችን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል።​—⁠ምሳሌ 16:​31 NW

  • አረጋውያን ወላጆቻችንን ማክበር
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
    • ምዕራፍ አሥራ አምስት

      አረጋውያን ወላጆቻችንን ማክበር

      1. ወላጆቻችን ምን ውለታ ውለውልናል? በመሆኑም ለወላጆቻችን ምን ዓይነት ስሜት ሊኖረንና ምን ልናደርግላቸው ይገባል?

      ከረጅም ዘመናት በፊት ይኖር የነበረው ጠቢቡ ሰው “የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ምሳሌ 23:​22) ‘ኧረ፣ እንዲህስ አላደርግም!’ ትሉ ይሆናል። አብዛኞቻችን እናቶቻችንንም ሆነ አባቶቻችንን ከመናቅ ይልቅ ከልብ እንወዳቸዋለን። ብዙ ውለታ እንደዋሉልን እናውቃለን። በመጀመሪያ ደረጃ ወላጆቻችን ሕይወት ሰጥተውናል። የሕይወት ምንጭ ይሖዋ ቢሆንም እንኳ ወላጆቻችን ባይኖሩ ኖሮ እኛም አንኖርም ነበር። ለወላጆቻችን የሕይወትን ያህል ውድ የሆነ ምንም ነገር ልንሰጣቸው አንችልም። አንድን ልጅ ከሕፃንነት ወደ ጉልምስና ማሸጋገር የሚጠይቀውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ፣ ከፍተኛ እንክብካቤ፣ ወጪና ፍቅራዊ አሳቢነት እስቲ ለአንድ አፍታ አስቡት። እንግዲያው የአምላክ ቃል “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር” የሚል ምክር መስጠቱ ምንኛ ምክንያታዊ ነው!​—⁠ኤፌሶን 6:​2, 3

      ስሜታዊ ፍላጎታቸውን መረዳት

      2. ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆች ‘ተገቢውን ብድራት’ መመለስ የሚችሉት እንዴት ነው?

      2 ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ልጆች ወይም የልጅ ልጆች . . . አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፣ ለወላጆቻቸውም [“ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸው፣” የ1980 ትርጉም] ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና።” (1 ጢሞቴዎስ 5:​4) ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆች ወላጆቻቸውና አያቶቻቸው ለብዙ ዓመታት ያሳዩአቸውን ፍቅር እንዲሁም የዋሉላቸውን ውለታና ያደረጉላቸውን እንክብካቤ በማድነቅ ይህን “ብድራት” ይመልሳሉ። ልጆች ይህን ማድረግ እንዲችሉ አንዱ የሚያስፈልጋቸው ነገር እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ በዕድሜ የገፉ ሰዎችም ፍቅርና ማጽናኛ የሚያሻቸው መሆኑን መረዳት ነው፤ እንዲያውም ይህ ብዙውን ጊዜ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች በጣም አንገብጋቢ ነገር ነው። እኛ ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጠን እንደምንፈልግ ሁሉ እነሱም በሌሎች ዘንድ ከፍ ተደርገው መታየት ይፈልጋሉ። ሕይወታቸው ዋጋማ እንደሆነ እንዲሰማቸው ማድረግ ያስፈልጋል።

      3. ወላጆቻችንንና አያቶቻችንን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?

      3 ስለዚህ ወላጆቻችንና አያቶቻችን እንደምናፈቅራቸው እንዲያውቁ በማድረግ ልናከብራቸው እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 16:​14) ወላጆቻችን አብረውን የማይኖሩ ከሆነ በሆነ መንገድ ስለ እኛ ደህንነት ማወቃቸው በጣም ያስደስታቸዋል። ደስ የሚል ደብዳቤ ብንጽፍላቸው፣ ስልክ ብንደውልላቸው ወይም ደግሞ ሄደን ብንጠይቃቸው እጅግ ይደሰታሉ። በጃፓን የምትኖረው ሚዮ የ82 ዓመት ሴት በነበረችበት ጊዜ የሚከተለውን ጽፋለች:- “ሴት ልጄ [ባሏ ተጓዥ አገልጋይ ነው] ‘እማዬ እባክሽ አብረሽን “ተጓዢ”’ ትለኛለች። በየሳምንቱ የሚሄዱበትን ቦታና በሚሄዱበት ቦታ የሚጠቀሙበትን ስልክ ቁጥር ትነግረኛለች። ስለዚህ ካርታዬን እዘረጋና ‘አሁን እዚህ አካባቢ ናቸው ማለት ነው!’ እላለሁ። ይሖዋ ይቺን የመሰለች ልጅ በመስጠት ስለባረከኝ ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ።”

      በቁሳዊ ነገሮች መርዳት

      4. የአይሁድ ሃይማኖታዊ ወግ ሰዎች በአረጋውያን ወላጆቻቸው ላይ ምን ዓይነት የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያበረታታ ነበር?

      4 ወላጆችን ማክበር በቁሳዊ ነገሮች መርዳትንም ሊጨምር ይችላልን? አዎ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረግንም ይጨምራል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም ንብረቱን “ለእግዚአብሔር መባ አድርጌ አቅርቤአለሁ” ካለ ወላጆቹን የመጦር ኃላፊነት የለበትም የሚል ወግ ነበራቸው። (ማቴዎስ 15:​3-6 የ1980 ትርጉም) እንዴት ያለ ጭካኔ ነው! እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች በተዘዋዋሪ መንገድ ሰዎች ወላጆቻቸውን ከማክበር ይልቅ በራስ ወዳድነት መንፈስ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በመንፈግ በንቀት እንዲመለከቷቸው እያበረታቱ ነበር። እኛ ግን እንዲህ የማድረግ ሐሳብ ፈጽሞ ወደ አእምሯችን ሊመጣ አይገባም!​—⁠ዘዳግም 27:​16

      5. በአንዳንድ አገሮች ምንም እንኳ መንግሥት አረጋውያንን ለመርዳት አንዳንድ ዝግጅቶች ያደረገ ቢሆንም ወላጆችን ማክበር አንዳንድ ጊዜ በቁሳዊ ነገሮችም መርዳትን የሚጨምረው ለምንድን ነው?

      5 በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ በመንግሥት የሚደጎሙ ማኅበራዊ ፕሮግራሞች እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ያሉ ለአረጋውያን የሚያስፈልጉ አንዳንድ ቁሳዊ እርዳታዎች ይሰጣሉ። ከዚህም በተጨማሪ አረጋውያኑ ራሳቸው ለእርጅና ዘመናቸው ብለው ያስቀመጡት ጥሪት ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም ይህ ጥሪታቸው ከተሟጠጠ ወይም በቂ ሆኖ ካልተገኘ ልጆች ወላጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ለወላጆቻቸው ያላቸውን አክብሮት ያሳያሉ። እንዲያውም በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መጦር ለአምላክ ያደሩ መሆንን፣ በሌላ አነጋገር አንድ ሰው የቤተሰብ ዝግጅት መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ያደረ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

      ፍቅርና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ

      6. አንዳንዶች ወላጆቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ሲሉ ምን ዓይነት ዝግጅቶች አድርገዋል?

      6 ለአካለ መጠን የደረሱ ብዙ ልጆች አቅመ ደካማ ለሆኑ ወላጆቻቸው ፍቅርና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በማሳየት ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። አንዳንዶቹ ወላጆቻቸውን ወደ ራሳቸው ቤት ወስደዋቸዋል፤ ወይም ደግሞ ቤታቸውን ቀይረው በአቅራቢያቸው መኖር ጀምረዋል። ሌሎቹ ደግሞ ቤታቸውን ለቅቀው ከወላጆቻቸው ጋር መኖር ጀምረዋል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹ ዝግጅቶች ለወላጆቹም ሆነ ለልጆቹ በረከት ሆነው ተገኝተዋል።

      7. አረጋውያን ወላጆችን በተመለከተ ለውሳኔ መቸኮል ጥሩ ያልሆነው ለምንድን ነው?

      7 ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹ እርምጃዎች ጥሩ ውጤት ሳያመጡ ይቀራሉ። ለምን? ምናልባት ውሳኔዎቹ የተወሰዱት በችኮላ ወይም ደግሞ በስሜታዊነት በመሆኑ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” ሲል ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (ምሳሌ 14:​15) ለምሳሌ ያህል አረጋዊት እናትህ ብቻዋን መኖር አልቻለች ይሆናል፤ በመሆኑም ከአንተ ጋር ብትኖር የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ተሰምቶህ ይሆናል። የምትወስዳቸውን እርምጃዎች ጥበብ በተሞላበት መንገድ በጥሞና በማሰብ የሚከተሉትን ጉዳዮች ትመረምር ይሆናል:- በእርግጥ የሚያስፈልጓት ነገሮች ምንድን ናቸው? ተቀባይነት ያለው አማራጭ መፍትሔ ሊያስገኙ የሚችሉ የግል ወይም የመንግሥት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይኖራሉን? እሷስ ከአንተ ጋር መኖር ትፈልጋለች? የምትፈልግ ከሆነ ይህ በሕይወቷ ላይ ምን ለውጦች ያመጣል? የምትለያቸው ጓደኞች ይኖራሉን? ይህ በስሜቷ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል? ስለ እነዚህ ጉዳዮች አነጋግረሃታልን? እናትህ ከአንተ ጋር መኖሯ በትዳር ጓደኛህና በልጆችህ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል? እናትህ ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋት ከሆነ ይህን እንክብካቤ የሚያደርግላት ማን ነው? ኃላፊነቱን መከፋፈል ይቻላልን? ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይተሃልን?

      8. አረጋውያን ወላጆቻችሁን መርዳት የምትችሉበትን መንገድ በተመለከተ ማንን ልታማክሩ ትችላላችሁ?

      8 እንክብካቤ የማድረጉ ኃላፊነት በቤተሰቡ ውስጥ ያሉትን ልጆች ሁሉ የሚመለከት በመሆኑ ሁሉም በሚወሰዱት ውሳኔዎች ላይ የበኩላቸውን ሐሳብ እንዲሰጡ ቤተሰቡ አንድ ላይ ተሰብስቦ ቢወያይ ጥሩ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌዎችን ወይም ተመሳሳይ ሁኔታ የገጠማቸውን ጓደኞች ማማከሩ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። “ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል፤ “መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል።”​—⁠ምሳሌ 15:​22

      የሌላውን ሰው ስሜት መጋራትና ችግሩን መረዳት

      በገጽ 179 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      አስቀድሞ ራሱን ወላጁን ሳያማክሩ እሱን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ማድረግ ተገቢ አይደለም

      9, 10. (ሀ) አረጋውያን ወላጆች ምንም እንኳ ዕድሜያቸው እየገፋ ቢሄድም ምን ዓይነት አሳቢነት ልናሳያቸው ይገባል? (ለ) ለአካለ መጠን የደረሰ ልጅ ለወላጆቹ ሲል ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ በሚወሰድበት ጊዜ ሁሉ ምን ሊያደርግ ይገባዋል?

      9 አረጋውያን ወላጆቻችንን ማክበር ስሜታቸውን መጋራትና ችግራቸውን መረዳት ይጠይቃል። በእርጅና ዘመን ላይ የሚገኙ ሰዎች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ መራመድ፣ መብላትና ማስታወስ እየተሳናቸው ይሄዳል። እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ ልጆች ለወላጆቻቸው ደህንነት ከሚገባው በላይ በማሰብ መመሪያ ሊሰጧቸው ይሞክራሉ። ሆኖም አረጋውያን የብዙ ዓመታት ጥበብና ልምድ ያካበቱ እንዲሁም ዕድሜ ልካቸውን ራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩና የራሳቸውን ውሳኔዎች ሲያደርጉ የኖሩ ዐዋቂ ሰዎች ናቸው። ወላጆችና ዐዋቂዎች መሆናቸው ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸውና በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲያዳብሩ አድርጓቸዋል። ሕይወታቸው በልጆቻቸው ቁጥጥር ሥር እንደወደቀ ሆኖ የሚሰማቸው ወላጆች የመንፈስ ጭንቀት ሊያድርባቸውና ሊበሳጩ ይችላሉ። አንዳንዶች ሲደረግ የሚያዩትን ነገር የራሳቸውን ሕይወት በራሳቸው የመምራት መብታቸውን ለመጋፋት የሚደረግ ሙከራ እንደሆነ አድርገው በመረዳት ቅር ሊሰኙና ተቃውሟቸውን ሊገልጹ ይችላሉ።

      10 እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች በቀላሉ መፍታት አይቻልም፤ ሆኖም አረጋውያን ወላጆች በተቻለ መጠን ራሳቸውን በራሳቸው እንዲረዱና የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያደርጉ መፍቀዱ የደግነት መግለጫ ነው። መጀመሪያ እነሱን ሳታማክሩ ለእነሱ የተሻለ ነው ብላችሁ ያሰባችሁትን ውሳኔ ባትወስኑ ጥሩ ነው። በእርጅና ሳቢያ ብዙ ነገሮች አጥተው ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ባላቸው ነገር እንዲጠቀሙ ፍቀዱላቸው። በተቻለ መጠን ነፃነት የምትሰጧቸው ከሆነ በመካከላችሁ የተሻለ ዝምድና ይኖራል። እነሱም ይደሰታሉ፤ እናንተም ትደሰታላችሁ። በአንዳንድ ጉዳዮች ለእነርሱ ጥቅም ስትሉ ግፊት ማሳደሩ አስፈላጊ ቢሆንም ለወላጆቻችሁ ያላችሁ አክብሮት የሚገባቸውን ቦታና ከፍ ያለ ግምት እንድትሰጧቸው ያደርጋችኋል። የአምላክ ቃል “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም አክብር” የሚል ምክር ይሰጣል።​—⁠ዘሌዋውያን 19:​32

      ትክክለኛ አመለካከት መያዝ

      11-13. ለአካለ መጠን የደረሰ አንድ ልጅ በልጅነት ዘመኑ ከወላጆቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበረው ባይሆን እንኳ ወላጆቹ በዕድሜ በገፉበት ዘመን እነርሱን በመጦር ረገድ የሚገጥመውን ፈታኝ ሁኔታ መወጣት የሚችለው እንዴት ነው?

      11 አንዳንድ ጊዜ ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆች በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን ማክበር የሚያስቸግራቸው ልጆች በነበሩበት ጊዜ ከወላጆቻቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ነው። ምናልባት አባታችሁ ወዳጃዊ ስሜትና ፍቅር ያልነበረው ይሆናል፤ እናታችሁ ደግሞ ኃይለኛና ጥብቅ የነበረች ልትሆን ትችላለች። ወላጆችህ አንተ የምትፈልገውን ዓይነት ስላልነበሩ አሁንም ድረስ ትበሳጭና ትናደድ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ በደል እንደፈጸሙብህ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱን ስሜት መቋቋም ትችላለህን?a

      12 በፊንላንድ ውስጥ ያደገው ባስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የእንጀራ አባቴ በናዚ ጀርመን ውስጥ የኤስ ኤስ መኮንን ነበር። ግልፍተኛ ነበር፤ ከዚያ በኋላ የሚያደርገውን አያውቅም። እናቴን ብዙ ጊዜ እፊቴ ደብድቧታል። አንድ ቀን በጣም ተናድዶ ቀበቶውን አውልቆ ሲገርፈኝ የቀበቶው ዘለበት ፊቴን መታኝ። ምቱ ኃይለኛ ስለነበር አልጋ ላይ ተዘረርኩ።”

      13 ሆኖም ለዚህ ባሕሪው አስተዋጽኦ ያደረጉ ነገሮች ነበሩ። ባስ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል:- “በሌላ በኩል ግን ተግቶ ይሠራ የነበረ ከመሆኑም በላይ ቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር በሚገባ ያሟላ ነበር። አባታዊ ፍቅሩን ገልጾልኝ የማያውቅ ቢሆንም የስሜት ጠባሳ እንደነበረው አውቅ ነበር። እናቱ ከቤት ያባረረችው ገና ትንሽ ልጅ እያለ ነው። እየተደባደበ ያደገ ከመሆኑም በላይ ወደ ጦርነት የገባው በጣም ወጣት እያለ ነው። ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ስለምረዳለት አልፈርድበትም። ትልቅ ሰው ከሆንኩ በኋላ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ እሱን ለመርዳት የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ጥሬያለሁ። ይህን ማድረጉ ቀላል አልነበረም፤ ቢሆንም የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ። እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ ጥሩ ልጅ ሆኜ ለመገኘት ሞክሬያለሁ፤ እሱም እንደዚህ እንደተሰማው አምናለሁ።”

      14. አረጋውያን ወላጆችን መጦርን በተመለከተ ያለውን ሁኔታ ጨምሮ በሁሉም ሁኔታዎች የሚሠራው የትኛው ጥቅስ ነው?

      14 የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሌሎች ጉዳዮች እንደሚሠራ ሁሉ በቤተሰብ ሁኔታም ይሠራል:- “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።”​—⁠ቆላስይስ 3:​12, 13

      ጧሪዎችም እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል

      15. ወላጆችን መጦር አንዳንድ ጊዜ በጣም የሚያስጨንቀው ለምንድን ነው?

      15 አቅመ ደካማ የሆኑ ወላጆችን መጦር ብዙ ኃላፊነት የሚያስከትልና ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ነው። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ይበልጥ የሚከብደው በስሜት ላይ የሚፈጥረው ጫና ነው። ወላጆቻችሁ ጤናቸውን፣ የማስታወስ ችሎታቸውንና ራሳቸውን በራሳቸው የመምራት ብቃታቸውን ሲያጡ መመልከቱ በጣም ይረብሻል። የፖርቶ ሪኮዋ ሳንዲ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “እናቴ የቤተሰባችን ምሰሶ ነበረች። ስትሰቃይ እያዩ እሷን ማስታመሙ በጣም ከባድ ነበር። በመጀመሪያ ማነከስ ጀመረች፤ ከዚያም ከዘራ መጠቀም ጀመረች፤ በኋላ ምርኩዝ አስፈለጋት፤ ቀጥሎ ደግሞ ተሽከርካሪ ወንበር ለመጠቀም ተገደደች። ከዚህ በኋላ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ በጣም እየባሰባት ሄዶ ነበር። የአጥንት ካንሠር ይዟት ስለነበር ሌት ተቀን ማስታመም ያስፈልግ ነበር። እናጥባታለን፣ እናበላታለን እንዲሁም እናነብላታለን። ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር፤ በተለይ በስሜታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። እናቴን በጣም እወዳት ስለነበር ልትሞት በምታጣጥርበት ጊዜ አለቀስኩ።”

      16, 17. ወላጁን የሚያስታምም አንድ ሰው ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው የትኛው ምክር ሊረዳው ይችላል?

      16 እናንተም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ካላችሁ ችግሩን ለመቋቋም ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ አማካኝነት ይሖዋን መስማትና በጸሎት አማካኝነት ማነጋገር በጣም ይረዳል። (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7) ተመጣጣኝ ምግብ መመገብና በቂ እንቅልፍ መተኛት ይኖርባችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ የታመመውን ወላጃችሁን ለማስታመም በስሜታዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ የተሻለ ብቃት ይኖራችኋል። ምናልባት አልፎ አልፎ ከተለመደው የዕለት ተዕለት ተግባራችሁ ማረፍ የምትችሉበት ዝግጅት ማድረግ ትችሉ ይሆናል። ረዘም ያለ ዕረፍት መውሰድ የምትችሉበት ሁኔታ ባይኖር እንኳ ለጥቂት ጊዜ መዝናናት የምትችሉበት ፕሮግራም ማውጣታችሁ ጠቃሚ ነው። ዕረፍት ማድረግ የምትችሉበት ጊዜ እንድታገኙ የታመመውን ወላጃችሁን በቅርብ ሆኖ የሚረዳ ሰው ልታዘጋጁ ትችሉ ይሆናል።

      17 ወላጆቻቸውን የሚጦሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ምክንያታዊ ያልሆኑ ነገሮችን ከራሳቸው ይጠብቃሉ። ሆኖም ማድረግ ባልቻላችሁት ነገር የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማችሁ አይገባም። በአንዳንድ ሁኔታዎች ወላጅህን ለአንድ እንክብካቤ መስጫ ተቋም መስጠት ሊያስፈልግህ ይችላል። ወላጅህን የምታስታምም ከሆንክ ከራስህ ምክንያታዊ ያልሆኑ ነገሮች አትጠብቅ። የወላጆችህን ብቻ ሳይሆን የልጆችህን፣ የባለቤትህንና የራስህንም ፍላጎቶች ማሟላት አለብህ።

      ከወትሮው የላቀ ብርታት

      18, 19. ይሖዋ ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል? ይህን ቃሉን እንደሚጠብቅስ የትኛው ተሞክሮ ያሳያል?

      18 ይሖዋ በዕድሜ የገፉ ወላጆቹን የሚጦርን ሰው በእጅጉ ሊረዳ የሚችል መመሪያ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ይሰጣል፤ ሆኖም ይሖዋ የሚሰጠው እርዳታ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም። “እግዚአብሔር . . . ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው” ሲል መዝሙራዊው በመንፈስ አነሳሽነት ተገፋፍቶ ጽፏል። “ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም።” ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች በሚገጥሟቸው ጊዜ እንኳ ሳይቀር ያድናቸዋል ወይም ይጠብቃቸዋል።​—⁠መዝሙር 145:​18, 19

      19 በፊሊፒንስ የምትኖረው ሚርና በአንጎል ውስጥ በሚከሰት የደም መፍሰስ ችግር ሳቢያ ሽባ የሆነችውን እናቷን በምታስታምምበት ጊዜ ይህን ልትገነዘብ ችላለች። “የምትወዱት ሰው የት ቦታ እንደሚያመው መናገር እንኳ ተስኖት ሲሰቃይ ከማየት የበለጠ የሚያስጨንቅ ነገር የለም” ስትል ሚርና ጽፋለች። “ሁኔታው፣ ቀስ በቀስ ውኃ ውስጥ ስትሰጥም እያየሁ ምንም ማድረግ እንዳልቻልኩ ያህል ነበር ማለት ይቻላል። ኃይሌ ምን ያህል እንደተሟጠጠ በመግለጽ ብዙ ጊዜ ተንበርክኬ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር። እንባውን በአቁማዳ ውስጥ እንዲያጠራቅምለትና እንዲያስታውሰው በመለመን ይሖዋን እንደተማጸነው እንደ ዳዊት ጮኼያለሁ። ይሖዋም ቃል በገባው መሠረት የሚያስፈልገኝን ብርታት ሰጥቶኛል። ‘ይሖዋ ደገፋዬ ሆነ።’”​—⁠መዝሙር 18:​18 NW

      20. ወላጆቻቸውን ሲያስታምሙ የነበሩ ሰዎች ሲያስታምሙት የነበረው ሰው ቢሞት እንኳ የወደፊቱን ጊዜ በሙሉ ትምክህት እንዲጠባበቁ የሚያደርጓቸው የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ናቸው?

      20 በዕድሜ የገፉ ወላጆችን ማስታመም “አሳዛኝ ፍጻሜ ያለው ታሪክ ነው” የሚል አባባል አለ። አስታማሚው ምንም ያህል ቢጥር በዕድሜ የገፉ ሰዎች ልክ እንደ ሚርና እናት ሊሞቱ ይችላሉ። ሆኖም በይሖዋ የሚታመኑ ሁሉ ሞት የታሪኩ መደምደሚያ እንዳልሆነ ያውቃሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” ብሏል። (ሥራ 24:​15) አረጋውያን ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሁሉ አምላክ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋና ‘ሞት የማይኖርበት’ አስደሳች አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ በገባው ቃል ሊጽናኑ ይችላሉ።​—⁠ራእይ 21:​4

      21. አረጋውያን ወላጆችን ማክበር ምን ጥሩ ውጤቶች ያስገኛል?

      21 የአምላክ አገልጋዮች ለወላጆቻቸው ጥልቅ አክብሮት አላቸው። ወላጆቻቸው በዕድሜ ከገፉ በኋላም ቢሆን ለእነሱ ያላቸው አክብሮት አይቀንስም። (ምሳሌ 23:​22-24) ለወላጆቻቸው ከፍ ያለ ግምት አላቸው። እንዲህ በማድረጋቸውም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የሚከተለው ምሳሌ በእነሱም ላይ ይፈጸማል:- “አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፣ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት።” (ምሳሌ 23:​25) ከሁሉ በላይ ደግሞ አረጋውያን ወላጆቻቸውን የሚያከብሩ ሰዎች ይሖዋ አምላክንም ደስ የሚያሰኙ ከመሆኑም በላይ ለእሱ ያላቸውን አክብሮት ያሳያሉ።

      a እንዲህ ስንል ወላጆች ሥልጣናቸውን ወይም የተጣለባቸውን አደራ አላግባብ በመጠቀም በወንጀለኛነት ሊያስጠይቅ የሚችል ድርጊት ስለፈጸሙባቸው ሁኔታዎች መናገራችን አይደለም።

      የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች . . .አረጋውያን ወላጆቻችንን እንድናከብር ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?

      ለወላጆቻችንና ለአያቶቻችን የሚገባቸውን ብድራት መመለስ ይኖርብናል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 5:​4

      የምናደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ በፍቅር ማድረግ አለብን።​—⁠1 ቆሮንቶስ 16:​14

      ከባድ ውሳኔዎችን በችኮላ መወሰን አይገባም።​—⁠ምሳሌ 14:​15

      አረጋውያን ወላጆች ቢታመሙና አቅማቸው እየደከመ ቢሄድም እንኳ መከበር አለባቸው።​—⁠ዘሌዋውያን 19:​32

      እርጅናና ሞት ዘላለም አብረውን የሚኖሩ ነገሮች አይደሉም።​—⁠ራእይ 21:​4

  • ቤተሰባችሁ ዘላቂ ተስፋ እንዲጨብጥ አድርጉ
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
    • ምዕራፍ አሥራ ስድስት

      ቤተሰባችሁ ዘላቂ ተስፋ እንዲጨብጥ አድርጉ

      1. ይሖዋ ቤተሰብን ሲመሠርት ዓላማው ምን ነበር?

      ይሖዋ አዳምና ሔዋንን በጋብቻ ባጣመራቸው ጊዜ አዳም በጥንታዊነቱ ቀደምት ሥፍራ የያዘውን የዕብራይስጥ ግጥም በመግጠም ደስታውን ገልጿል። (ዘፍጥረት 2:​22, 23) ይሁን እንጂ ፈጣሪ ጋብቻን ሲመሠርት ዓላማው ሰብዓዊ ልጆቹን ማስደሰት ብቻ አልነበረም። የትዳር ጓደኛሞችና ቤተሰቦች ፈቃዱን እንዲያደርጉ ይፈልግ ነበር። የመጀመሪያዎቹን ጥንዶች እንዲህ አላቸው:- “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” (ዘፍጥረት 1:​28) ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ሥራ ነበር! አዳምና ሔዋን የይሖዋን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ፈጽመው ቢሆን ኖሮ እነርሱም ሆኑ የሚወልዷቸው ልጆች ምንኛ ደስተኞች በሆኑ ነበር!

      2, 3. በዛሬው ጊዜ ቤተሰቦች ከሁሉ የላቀውን ደስታ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

      2 በዛሬው ጊዜም ቢሆን ቤተሰቦች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ተባብረው ሲሠሩ እጅግ ደስተኞች ይሆናሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔርን መምሰል [“ለአምላክ ያደሩ መሆን፣” NW] ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፣ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​8) ለአምላክ ያደረና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የይሖዋ መመሪያ የሚከተል ቤተሰብ ‘በአሁኑ ሕይወት’ ደስታ ያገኛል። (መዝሙር 1:​1-3፤ 119:​105፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16) መላው የቤተሰቡ አባላት ይቅርና አንዱ የቤተሰቡ አባል ብቻ እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ቢያውል የተሻሉ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ።

      3 ለቤተሰብ ደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተብራርተዋል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በመጽሐፉ ውስጥ በተደጋጋሚ እንደተጠቀሱ አስተውላችሁ ይሆናል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በተለያዩ የቤተሰብ ሕይወት ዘርፎች ለሁሉም የሚጠቅሙ ጠንካራ እውነታዎችን የሚወክሉ በመሆናቸው ነው። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ለማዋል የሚጥር ቤተሰብ ለአምላክ ማደር በእርግጥም ‘ለአሁኑ ሕይወት ተስፋ እንዳለው’ ይገነዘባል። ከእነዚህ ዋና ዋና መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አራቱን እስቲ ደግመን እንመልከት።

      ራስን መግዛት የሚያስገኘው ጥቅም

      4. በትዳር ውስጥ ራስን መግዛት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      4 ንጉሥ ሰሎሞን “ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፣ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው” ሲል ተናግሯል። (ምሳሌ 25:​28፤ 29:​11) ትዳራቸው አስደሳች እንዲሆን የሚፈልጉ ሁሉ ‘መንፈሳቸውን መከልከላቸው’ ማለትም ራሳቸውን መግዛታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። እንደ ንዴት ወይም የፆታ ብልግና የመፈጸም ፍላጎትን ለመሰሉ ጎጂ ስሜቶች እጅ መስጠት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመጠገን ብዙ ዓመታት ሊወስድ ይችላል፤ ለዚያውም ሊጠገን ከቻለ።

      5. ፍጹም ያልሆነ ሰው ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው? ይህስ ምን ጥቅም ያስገኝለታል?

      5 እርግጥ ነው፣ የትኛውም የአዳም ዘር ፍጹም ያልሆነውን ሥጋውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አይችልም። (ሮሜ 7:​21, 22) ያም ሆኖ ግን ራስን መግዛት የመንፈስ ፍሬ ነው። (ገላትያ 5:​22, 23) ስለዚህ ይህን ባሕርይ ለማግኘት የምንጸልይ ከሆነ፣ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛ ምክር ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ፣ እንዲሁም ይህን ባሕርይ ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር የምንወዳጅና ይህን ባሕርይ ከማያሳዩ ሰዎች ደግሞ የምንርቅ ከሆነ የአምላክ መንፈስ በውስጣችን ራስን የመግዛት ባሕርይ ያፈራል። (መዝሙር 119:​100, 101, 130፤ ምሳሌ 13:​20፤ 1 ጴጥሮስ 4:​7) እንዲህ ማድረጋችን ዝሙት እንድንፈጽም በምንፈተንበት ጊዜም እንኳ ‘ከዝሙት እንድንሸሽ’ ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 6:​18) በሌሎች ላይ ጥቃት ከመፈጸም እንቆጠባለን፤ የአልኮል ሱስንም እናስወግዳለን ወይም ድል እናደርገዋለን። የሚያናድዱና አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይበልጥ በተረጋጋ መንፈስ ችግሩን ለመፍታት እንጥራለን። ልጆችን ጨምሮ ሁላችንም ይህን እጅግ አስፈላጊ የሆነ የመንፈስ ፍሬ እንኮትኩት።​—⁠መዝሙር 119:​1, 2

      የራስነትን ሥልጣን በተመለከተ ተገቢ አመለካከት መያዝ

      6. (ሀ) መለኮታዊው የራስነት ሥልጣን ተዋረድ ምንድን ነው? (ለ) አንድ ወንድ የራስነት ሥልጣኑ ለቤተሰቡ ደስታ እንዲያስገኝ ከፈለገ ምን ማስታወስ ይኖርበታል?

      6 በጣም አስፈላጊ የሆነው ሁለተኛው መሠረታዊ ሥርዓት ለራስነት ሥልጣን እውቅና መስጠት ነው። ጳውሎስ ትክክለኛውን የሥልጣን ተዋረድ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 11:​3) ይህ ማለት አንድ ወንድ ቤተሰቡን በግንባር ቀደምትነት ይመራል፣ ሚስቱ በታማኝነት ትደግፈዋለች፣ ልጆች ደግሞ ለወላጆቻቸው ይታዘዛሉ ማለት ነው። (ኤፌሶን 5:​22-25, 28-33፤ 6:​1-4) ሆኖም የራስነት ሥልጣን ደስታ ሊያስገኝ የሚችለው በተገቢው መንገድ ሲሠራበት ብቻ እንደሆነ ልብ በሉ። ለአምላክ ያደሩ ባሎች የራስነት ሥልጣን አምባገነናዊነት እንዳልሆነ ያውቃሉ። የእነርሱ ራስ የሆነውን ኢየሱስን ይኮርጃሉ። ኢየሱስ ‘ከሁሉ በላይ ራስ’ የሚሆን ቢሆንም እንኳ ወደ ምድር የመጣው ‘ሊያገለግል እንጂ እንዲያገለግሉት አይደለም።’ (ኤፌሶን 1:​22፤ ማቴዎስ 20:​28) በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን ወንድ የራስነት ሥልጣኑን ለራሱ ጥቅም ሳይሆን ሚስቱና ልጆቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ይጠቀምበታል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​4, 5

      7. አንዲት ሚስት በቤተሰብ ውስጥ አምላክ የሰጣትን ድርሻ መወጣት እንድትችል የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይረዷታል?

      7 ለአምላክ ያደረች ሚስት ደግሞ ባሏን አትቀናቀንም ወይም ለመግዛት አትጥርም። ባሏን መደገፍና ከእሱ ጋር ተባብራ መሥራት ያስደስታታል። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ ሚስት የባሏ “ንብረት” እንደሆነች አድርጎ ይገልጻል፤ ይህም ባሏ የእሷ ራስ መሆኑን በማያሻማ መንገድ የሚያሳይ ነው። (ዘፍጥረት 20:​3 NW) በጋብቻ አማካኝነት ‘በባልዋ ሕግ’ ታስራለች። (ሮሜ 7:​2) ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “ረዳት” እና “ማሟያ” ብሎ ይጠራታል። (ዘፍጥረት 2:​20 NW) ባሏ የሚጎድሉትን ባሕርያትና ችሎታዎች ታሟላለች፤ የሚያስፈልገውንም እርዳታ ትሰጠዋለች። (ምሳሌ 31:​10-31) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሚስት ከባሏ ጎን ሆና የምትሠራ “ባልንጀራ” እንደሆነች ይገልጻል። (ሚልክያስ 2:​14) እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ባልና ሚስት የየራሳቸውን ቦታ ለይተው እንዲያውቁና አንዳቸው ለሌላው ተገቢ አክብሮት እንዲያሳዩ ይረዷቸዋል።

      ‘ለመስማት የፈጠናችሁ ሁኑ’

      8, 9. በቤተሰብ ውስጥ ያሉ ሁሉ የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ የሚረዷቸውን አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግለጹ።

      8 የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ አስፈላጊነት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ለምን? ሰዎች እርስ በርስ ሲነጋገሩና ሲደማመጡ ችግሮችን በተሻለ ሁኔታ መፍታት የሚቻል በመሆኑ ነው። የሐሳብ ልውውጥ ለመሄጃም ለመመለሻም እንደሚያገለግል መንገድ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ . . . ይሁን” ሲል ገልጾታል።​—⁠ያዕቆብ 1:​19

      9 እንዴት መናገር እንዳለብን ማሰቡም በጣም አስፈላጊ ነው። ያልታሰበባቸውና ንትርክ ሊፈጥሩ የሚችሉ ቃላት መሰንዘር ወይም ክፉኛ መተቸት ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ አያስችልም። (ምሳሌ 15:​1፤ 21:​9፤ 29:​11, 20) የምንናገረው ነገር ትክክል በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ርኅራኄ በጎደለው፣ በኩራት መንፈስ ወይም አሳቢነት በሌለው መንገድ የምንናገር ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። አነጋገራችን ጣዕም ያለው ማለትም ‘በጨው የተቀመመ’ መሆን አለበት። (ቆላስይስ 4:​6) የምንናገረው ነገር ‘በብር ፃሕል ላይ እንዳለ የወርቅ እንኮይ’ መሆን አለበት። (ምሳሌ 25:​11) በጥሩ ሁኔታ የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ልማድ ያዳበሩ ቤተሰቦች ደስታ ማግኘት የሚችሉበትን ትልቅ እርምጃ ወስደዋል ማለት ይቻላል።

      ፍቅር የሚጫወተው ትልቅ ሚና

      10. በትዳር ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆነው የፍቅር ዓይነት የትኛው ነው?

      10 “ፍቅር” የሚለው ቃል በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። በዋነኛነት የተጠቀሰው የፍቅር ዓይነት የቱ እንደሆነ ታስታውሳላችሁ? ፆታዊ ፍቅር (በግሪክኛ ኤሮስ) በትዳር ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው እሙን ነው፤ በተጨማሪም ስኬታማ በሆኑ ትዳሮች ውስጥ በባልና ሚስት መካከል የጠበቀ ፍቅርና ወዳጅነት (በግሪክኛ ፊሊያ) እየዳበረ ይሄዳል። ሆኖም ከእነዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው አጋፔ በተባለው የግሪክኛ ቃል የተወከለው የፍቅር ዓይነት ነው። ይህ ፍቅር ለይሖዋ፣ ለኢየሱስና ለሰዎች የምናዳብረው ፍቅር ነው። (ማቴዎስ 22:​37-39) ይሖዋ ለሰው ልጆች ያሳየው ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 3:​16) ለትዳር ጓደኛችንና ለልጆቻችን ይህን ፍቅር ማሳየት መቻላችን ምንኛ የሚያስደስት ነው!​—⁠1 ዮሐንስ 4:​19

      11. ፍቅር ለትዳር ጠቃሚ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?

      11 ይህ የላቀ የፍቅር ዓይነት በትዳር ውስጥ በእርግጥም “ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ” ነው። (ቆላስይስ 3:​14 NW) ባልና ሚስትን በአንድነት የሚያጣምር ከመሆኑም በላይ አንዳቸው ለሌላው እንዲሁም ለልጆቻቸው የሚጠቅመውን ነገር የማድረግ ፍላጎት ያሳድርባቸዋል። ቤተሰቦች ከባድ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው ፍቅር ችግሮቹን በአንድነት ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። ባልና ሚስት በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ ፍቅር እርስ በርሳቸው እንዲደጋገፉና አንዳቸው ሌላውን ከፍ አድርገው መመልከታቸውን እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል። “ፍቅር . . . የራሱንም አይፈልግም፣ . . . ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​4-8

      12. ባለ ትዳሮች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ትዳራቸውን የሚያጠነክረው ለምንድን ነው?

      12 የትዳር አንድነት በትዳር ጓደኛሞቹ መካከል ባለው ፍቅር ብቻ ሳይሆን በይበልጥ ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ሲጠብቅ በጣም ጠንካራ ይሆናል። (መክብብ 4:​9-12) ለምን? ሐዋርያው ዮሐንስ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:​3) ስለዚህ አንድ ባልና ሚስት ልጆቻቸው ለአምላክ ያደሩ እንዲሆኑ ማሰልጠን ያለባቸው ስለሚወዷቸው ብቻ ሳይሆን የይሖዋም ትእዛዝ በመሆኑ ጭምር መሆን አለበት። (ዘዳግም 6:⁠6, 7) ከፆታ ብልግና መራቅ ያለባቸው እርስ በርሳቸው ስለሚዋደዱ ብቻ ሳይሆን በይበልጥ ይህን ማድረግ ያለባቸው ‘በሴሰኞችና በአመንዝሮች ላይ ለሚፈርደው’ ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር መሆን አለበት። (ዕብራውያን 13:​4) አንደኛው የትዳር ጓደኛ በትዳር ውስጥ ከባድ ችግሮች በሚፈጥርበት ጊዜ እንኳ ሌላኛው የትዳር ጓደኛ ለይሖዋ ያለው ፍቅር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተሉን እንዲቀጥል ሊገፋፋው ይገባል። በመካከላቸው ያለው ፍቅር ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር እንዲጠናከር ያደረጉ ቤተሰቦች በእርግጥም ደስተኞች ናቸው!

      የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ቤተሰብ

      13. እያንዳንዱ ግለሰብ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚወስደው ቁርጥ ውሳኔ ዓይኑ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር የሚረዳው እንዴት ነው?

      13 አንድ ክርስቲያን መላ ሕይወቱ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው። (መዝሙር 143:​10) ለአምላክ ያደሩ መሆን ማለት ደግሞ ይህ ነው። ቤተሰቦች የአምላክን ፈቃድ ማድረጋቸው ዓይናቸው ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ይረዳቸዋል። (ፊልጵስዩስ 1:​9, 10) ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “ሰውን ከአባቱ፣ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፣ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል።” (ማቴዎስ 10:​35, 36) ኢየሱስ በተናገረው ማስጠንቀቂያ መሠረት ብዙ ተከታዮቹ በቤተሰባቸው አባሎች ስደት ደርሶባቸዋል። እንዴት ያለ አሳዛኝና መንፈስን የሚረብሽ ሁኔታ ነው! ሆኖም የቤተሰብ ዝምድና ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ካለን ፍቅር ሊበልጥብን አይገባም። (ማቴዎስ 10:​37-39) አንድ ሰው ከቤተሰቡ የሚሰነዘርበትን ተቃውሞ በጽናት ከተቋቋመ ተቃዋሚዎቹ ለአምላክ ያደሩ መሆን የሚያስገኛቸውን ጥሩ ውጤቶች በመመልከት ሊለወጡ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:​12-16፤ 1 ጴጥሮስ 3:​1, 2) ይህ ባይሆን እንኳ በተቃውሞ ሳቢያ አምላክን ከማገልገል በመታቀብ የሚገኝ ምንም ዘላቂ ጥቅም የለም።

      14. ወላጆች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት ለልጆቻቸው የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ ነገር እንዲያደርጉ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

      14 የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ወላጆች ትክክለኛ ውሳኔዎች ማድረግ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ መዋዕለ ንዋይ አድርገው ይመለከቷቸዋል፤ እናም በእርጅና ዘመናቸው እንደሚጦሯቸው ይተማመናሉ። ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆች በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን መጦራቸው ተገቢና ትክክል ቢሆንም ወላጆች ይህን በአእምሯቸው በመያዝ ልጆቻቸው የፍቅረ ነዋይ ጎዳና እንዲከተሉ ተጽዕኖ ሊያደርጉባቸው አይገባም። ወላጆች ልጆቻቸውን ከመንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ ለቁሳዊ ንብረት የበለጠ ቦታ እንዲሰጡ አድርገው የሚያሳድጓቸው ከሆነ ምንም የሚያስገኙላቸው ጥቅም የለም።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​9

      15. የጢሞቴዎስ እናት ኤውንቄ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሆና ልትጠቀስ የምትችለው እንዴት ነው?

      15 በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው የጳውሎስ ጓደኛ የነበረው የወጣቱ ጢሞቴዎስ እናት የሆነችው ኤውንቄ ናት። (2 ጢሞቴዎስ 1:​5) ምንም እንኳ ኤውንቄ የማያምን ባል የነበራት ቢሆንም ከጢሞቴዎስ አያት ከሎይድ ጋር ሆና ጢሞቴዎስ ለአምላክ ያደረ እንዲሆን በጥሩ ሁኔታ አሳድጋዋለች። (2 ጢሞቴዎስ 3:​14, 15) ጢሞቴዎስ ለአካለ መጠን ሲደርስ ከቤተሰቡ ተለይቶ የጳውሎስ ሚስዮናዊ ጓደኛ በመሆን በመንግሥቱ የስብከት ሥራ እንዲሳተፍ ፈቅዳለታለች። (ሥራ 16:​1-5) ልጅዋ የተዋጣለት ሚስዮናዊ ሲሆን ምንኛ ተደስታ ይሆን! በዐዋቂነት ዕድሜው ለአምላክ ያደረ መሆኑ በልጅነቱ ጥሩ ማሠልጠኛ እንዳገኘ በሚገባ ይመሠክራል። ኤውንቄ ምንም እንኳ ልጅዋ አብሯት ባለመኖሩ ቅር ልትሰኝ ብትችልም የጢሞቴዎስን የታማኝነት አገልግሎት በተመለከተ በምትሰማቸው ሪፖርቶች እንደተደሰተችና እንደረካች ጥርጥር የለውም።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​19, 20

      ቤተሰብና የወደፊት ዕጣችሁ

      16. ኢየሱስ ከአንድ ልጅ የሚጠበቅ ምን ተገቢ አሳቢነት አሳይቷል? ሆኖም ዋነኛ ዓላማው ምን ነበር?

      16 ኢየሱስ ያደገው ፈሪሃ አምላክ በነበረው ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ ለአካለ መጠን ከደረሰ በኋላም አንድ ልጅ ለእናቱ ሊኖረው የሚገባውን አሳቢነት አሳይቷል። (ሉቃስ 2:​51, 52፤ ዮሐንስ 19:​26) ይሁን እንጂ ዋነኛ ዓላማው የአምላክን ፈቃድ ማሟላት ነበር፤ ይህ ደግሞ ለሰው ልጆች የዘላለም ሕይወትን በር መክፈትንም ይጠይቅበት ነበር። ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ለኃጢአተኛው የሰው ዘር ቤዛ አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ይህን ፈጽሟል።​—⁠ማርቆስ 10:​45፤ ዮሐንስ 5:​28, 29

      17. የኢየሱስ የታማኝነት አካሄድ የአምላክን ፈቃድ ለሚያደርጉ ሰዎች ምን ታላላቅ ተስፋዎች አስገኝቷል?

      17 ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ይሖዋ ከሞት በማስነሣት ሰማያዊ ሕይወት የሰጠው ከመሆኑም በላይ ውሎ አድሮ በሰማያዊው መንግሥት ላይ ንጉሥ አድርጎ በመሾም ታላቅ ሥልጣን አጎናጽፎታል። (ማቴዎስ 28:​18፤ ሮሜ 14:​9፤ ራእይ 11:​15) የኢየሱስ መሥዋዕት የተወሰኑ ሰዎች ከእሱ ጋር በዚያ መንግሥት ላይ የመግዛት መብት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። የተቀሩት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችም ዳግመኛ ወደ ገነትነት በምትለወጠው ምድር ላይ ፍጹም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን በር ከፍቷል። (ራእይ 5:​9, 10፤ 14:​1, 4፤ 21:​3-5፤ 22:​1-4) በዛሬው ጊዜ ይህን እጅግ አስደሳች የሆነ ምሥራች ለሰዎች የመንገር ታላቅ መብት አግኝተናል።​—⁠ማቴዎስ 24:​14

      18. ለቤተሰቦችም ሆነ ለግለሰቦች ምን ማሳሰቢያና ማበረታቻ ተሰጥቷል?

      18 ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳመለከተው ለአምላክ ያደሩ መሆን በ“ሚመጣው” ሕይወት እነዚህን በረከቶች የመውረስ ተስፋ ያስገኛል። ደስታ ማግኘት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ይህ እንደሆነ ምንም አያጠያይቅም! ‘ዓለምና ምኞቱ እንደሚያልፉ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም እንደሚኖር’ አስታውሱ። (1 ዮሐንስ 2:​17) ስለዚህ ልጅም ሆናችሁ ወላጅ፣ ባልም ሆናችሁ ሚስት፣ ልጆች ያላችሁ ነጠላዎችም ሆናችሁ የሌላችሁ፣ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ጣሩ። ከባድ ተጽዕኖ ሥር በምትወድቁበትና አስከፊ ችግሮች በሚያጋጥሟችሁ ጊዜም እንኳ የሕያው አምላክ አገልጋዮች መሆናችሁን ፈጽሞ አትዘንጉ። በመሆኑም የምታደርጓቸው ነገሮች ይሖዋን ደስ የሚያሰኙ ይሁኑ። (ምሳሌ 27:​11) ምግባራችሁ በአሁኑ ጊዜ ደስታ በመጪው አዲስ ዓለም ደግሞ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላችሁ እንዲሆን እንመኛለን!

      የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች . . .ቤተሰባችሁ ደስተኛ እንዲሆን ሊረዱት የሚችሉት እንዴት ነው?

      ራስን የመግዛት ባሕርይን ማዳበር ይቻላል።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

      ባልም ሆነ ሚስት ለራስነት ሥልጣን ተገቢ አመለካከት በመያዝ ለቤተሰባቸው ይበልጥ የሚጠቅመውን ነገር ያደርጋሉ።—⁠ኤፌሶን 5:​22-25, 28-33፤ 6:​4

      የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ማዳመጥንም ይጨምራል።—⁠ያዕቆብ 1:​19

      ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅር ትዳራችሁን ያጠነክረዋል።​—⁠1 ዮሐንስ 5:​3

      የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ለአንድ ቤተሰብ ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ግብ ነው።​—⁠መዝሙር 143:​10፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​8

      የነጠላነት ስጦታ

      የሚያገቡት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። በተጨማሪም ያገቡ ሁሉ ልጆች መውለድ ይፈልጋሉ ማለት አይደለም። ኢየሱስ ነጠላ ነበር፤ “ስለ መንግሥተ ሰማያት” ብሎ ነጠላ መሆን ስጦታ እንደሆነም ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:​11, 12) ሐዋርያው ጳውሎስም ሳያገባ መኖርን መርጧል። ነጠላ መሆንም ሆነ ትዳር ይዞ መኖር “ስጦታ” እንደሆነ ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 7:​7, 8, 25-28) ስለዚህ ምንም እንኳ ይህ መጽሐፍ በአብዛኛው ከጋብቻና ልጆችን ከማሳደግ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች የሚያብራራ ቢሆንም ነጠላ መሆንም ሆነ አግብቶ ልጅ አለመውለድ ሊያስገኟቸው የሚችሉትን በረከቶችና ወሮታዎች መዘንጋት የለብንም።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ