የሰው ዘር ተአምራዊ ፈውስ የሚያገኝበት ጊዜ ቀርቧል
“እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አይተን አናውቅም።” እነዚህን ቃላት የተናገሩት ኢየሱስ ሽባ የነበረውን ሰው በቅጽበት በፈወሰ ጊዜ የተፈጸመውን ተአምር ይመለከቱ የነበሩ ሰዎች ናቸው። (ማርቆስ 2:12 የ1980 ትርጉም) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ዓይነ ስውራንን፣ ድዳዎችንና አንካሶችን ፈውሷል። ተከታዮቹም እንዲሁ አድርገዋል። ኢየሱስ ይፈውስ የነበረው በማን ኃይል ነበር? እምነትስ የነበረው ድርሻ ምን ነበር? እነዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸሙ ነገሮች በዛሬው ጊዜ ስለሚፈጸሙ ተአምራዊ ፈውሶች ምን የሚያስገነዝቡን ነገር አለ?— ማቴዎስ 15:30, 31
“እምነትሽ አድኖሻል”
በዛሬው ጊዜ ያሉ የእምነት ፈዋሾች ኢየሱስ ለ12 ዓመታት ደም እየፈሰሳት ትሠቃይ ለነበረችው አንዲት ሴት “እምነትሽ አድኖሻል” ብሎ የተናገረውን ቃል መጥቀስ ይቀናቸዋል። (ሉቃስ 8:43-48) የኢየሱስ አነጋገር የሴትዮዋ መዳን የተመካው በእምነቷ ላይ እንደነበር ያሳያል? በአሁኑ ጊዜ ለሚደረገው “የእምነት ፈውስ” እንደ ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላልን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን ታሪክ በጥንቃቄ በምናነብበት ጊዜ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ሕመምተኞችን ከመፈወሳቸው በፊት እምነት ያላቸው መሆኑን እንዲያሳዩ በአብዛኛው ይጠይቁ እንዳልነበር እንረዳለን። ከላይ የተገለጸችውም ሴት መጥታ ለኢየሱስ ምንም ዓይነት ቃል ሳትተነፍስ ቀስ ብላ ከበስተኋላው ልብሱን ስትነካ “የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ።” በሌላ ወቅትም ኢየሱስ ሊይዙት ከመጡት ሰዎች መካከል አንዱን ፈውሶታል። እንዲያውም የኢየሱስን ማንነት ፈጽሞ የማያውቀውን አንድ ሰው ፈውሷል።— ሉቃስ 22:50, 51፤ ዮሐንስ 5:5-9, 13፤ 9:24-34
ታዲያ እምነት የነበረው ድርሻ ምን ነበር? ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ጢሮስና ሲዶና አውራጃ በደረሱ ጊዜ አንዲት ከነናዊት ሴት መጥታ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች።” “ጌታ ሆይ . . . ማረኝ” ብላ ስትለምን ተሰምቷት የነበረውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ገምት! ኢየሱስም በሐዘን ስሜት “አንቺ ሴት፣ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደ ወደድሽ ይሁንልሽ አላት።” “ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች።” (ማቴዎስ 15:21-28) እርግጥ ነው፣ እዚህ ላይ እምነት ተጠቅሷል። ግን የማን እምነት? ኢየሱስ ያደነቀው የታመመችውን ልጅ እምነት ሳይሆን የእናትየዋን እምነት እንደነበር ልብ በል። በማን ላይ ያሳየችው እምነት? ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ” ብላ በመጥራቷ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን እንደምታምን በይፋ አረጋግጣለች። ይህ እንዲሁ ብቻ በአምላክ ላይ ማመንን ወይም ፈዋሹ ባለው ኃይል ላይ ማመንን የሚያሳይ አነጋገር አልነበረም። ኢየሱስ “እምነትሽ አድኖሻል” ብሎ ሲናገር መሲሕ መሆኑን ባያምኑ ኖሮ በመከራ የተጠቁ ሰዎች ለመፈወስ ወደ እርሱ አይመጡም ነበር ማለቱ ነው።
ኢየሱስ ያከናወነው ፈውስ በዛሬው ጊዜ ከሚታየው ወይም ከሚታመነው ፈውስ በጣም የተለየ እንደሆነ ከእነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች መገንዘብ እንችላለን። በሕዝቡ መካከል ጩኸት፣ እየጮኹ መዘመር፣ ልቅሶ፣ ራስን ስቶ መውደቅን የመሰሉ ኃይለኛ የስሜት ግንፋሎት አልታዩም። ኢየሱስም ቢሆን በስሜት እየተወራጨ ልዩ እንቅስቃሴ አላሳየም። በተጨማሪም ኢየሱስ እምነት ጎድሏችኋል ወይም የሰጣችሁት መዋጮ በቂ አይደለም የሚል ሰበብ በማቅረብ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ሳይፈውስ የቀረበት ጊዜ የለም።
በአምላክ ኃይል መፈወስ
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የፈጸሙት ፈውስ የተከናወነው እንዴት ነበር? “እርሱም እንዲፈውስ የጌታ [“የይሖዋ፣” NW] ኃይል ሆነለት” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ይሰጠናል። (ሉቃስ 5:17) አንድ ጊዜ ከፈወሰ በኋላ “ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ ተገረሙ” በማለት ሉቃስ 9:43 ይናገራል። ኢየሱስ በፈዋሽነት የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ አልሳበም። በአንድ ወቅት ከአጋንንት ጥቃት ነፃ ላወጣው ሰው “ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደማረህ አውራላቸው” በማለት ነግሮታል።— ማርቆስ 5:19
ኢየሱስና ሐዋርያቱ ያከናወኑት ፈውስ በአምላክ መንፈስ እስከሆነ ድረስ የሚፈወሰው ሰው ፈውስ እንዲያገኝ እምነት ማሳየቱ ሁልጊዜ አስፈላጊ ያልሆነው ለምን እንደሆነ ለመገንዘብ አያስቸግርም። ይሁን እንጂ ፈዋሹ ከፍተኛ እምነት ማሳየቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። እንዲያውም የኢየሱስ ተከታዮች በተለይ ኃይለኛ አጋንንት ማውጣት ባቃታቸው ጊዜ ኢየሱስ “ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው” በማለት ምክንያቱን ነግሯቸዋል።— ማቴዎስ 17:20
የተአምራዊ ፈውስ ዓላማ
ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ብዙ ፈውስ ያደረገ ቢሆንም ዋና ሥራው ‘የፈውስ አገልግሎት’ መስጠት አልነበረም። ኢየሱስ ሕዝቡን መዋጮ ወይም የእርዳታ ገንዘብ ሳይጠይቅ ያከናወነውን ተአምራዊ ፈውስ ቅድሚያ ሰጥቶ ያከናውን ከነበረው ‘የመንግሥት ምሥራች ስብከት’ በሁለተኛ ደረጃ ይመለከተው ነበር። (ማቴዎስ 9:35) በአንድ ወቅት “ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፣ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው” በማለት ዘገባው ይገልጻል። (ሉቃስ 9:11) በወንጌል ዘገባ ውስጥ ኢየሱስ “አስተማሪ” ተብሎ እንጂ “ፈዋሽ” ተብሎ በፍጹም አልተጠራም።
ታዲያ ኢየሱስ ተአምራዊ ፈውሶችን ያከናወነው ለምን ነበር? ዋናው ምክንያት ተስፋ የተደረገበት መሲሕ እርሱ መሆኑን ለይቶ ለማሳወቅ ነበር። አጥማቂው ዮሐንስ አለአግባብ ወኅኒ ቤት በነበረ ጊዜ አምላክ እንዲያከናውን የሰጠውን ሥራ ሙሉ በሙሉ የፈጸመው እርሱ መሆኑን ማረጋገጫ ማግኘት ፈልጎ ነበር። የራሱን ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ላከና “የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ብሎ ጠየቀ። ኢየሱስ ለዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ምን ብሎ እንደመለሰላቸው ልብ በል:- “ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፣ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፣ ሙታንም ይነሣሉ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል።”— ማቴዎስ 11:2-5
አዎን፣ ኢየሱስ ፈውስ ብቻ ሳይሆን በወንጌሎች ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ያከናወናቸው ሌሎች ተአምራትም “የሚመጣው” ማለትም ተስፋ የተደረገው መሲሕ እርሱ መሆኑን በማያሻማ መንገድ አረጋግጠዋል። ‘ሌላ ይመጣል ብሎ መጠበቅ’ አስፈላጊ አልነበረም።
ዛሬም ተአምራዊ ፈውሶች አሉ?
ታዲያ በዛሬው ጊዜ አምላክ ተአምራዊ ፈውስ በማድረግ ኃይሉን ያረጋግጣል ብለን መጠበቅ ይኖርብናል? በጭራሽ። ኢየሱስ በአምላክ ኃይል አማካኝነት ተአምራዊ ድርጊቶችን በማከናወን አምላክ ይመጣል ብሎ ተስፋ የሰጠው መሲሕ እርሱ መሆኑን በማያጠራጥር መንገድ አረጋግጧል። ኢየሱስ ያከናወናቸውን አስደናቂ ነገሮች ሁሉም ሰው እንዲያነባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበዋል። ስለዚህ አምላክ ለእያንዳንዱ ትውልድ እንዲህ ዓይነቱን ሥራ በማሳየት ኃይሉን ማረጋገጥ አያስፈልገውም።
የሚያስገርመው ፈውስም ሆነ ሌሎች ተአምራዊ ሥራዎች ማሳመን የሚችሉት እስከ ተወሰነ ደረጃ ድረስ ብቻ ነው። ኢየሱስ ተአምራት ሲፈጽም የተመለከቱ ሰዎች እንኳ የሰማያዊ አባቱ ድጋፍ እንዳለው አላመኑም። “ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ፤ . . . በእርሱ አላመኑም።” (ዮሐንስ 12:37) ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ክርስቲያን ጉባኤዎች ለሚገኙ ለተለያዩ አባላት አምላክ ትንቢትን፣ በልሳን መናገርን፣ ፈውስንና እንዲህ የመሰሉ ሌሎች የተለያዩ ተአምራዊ ስጦታዎችን እንደሰጠ ካብራራ በኋላ “ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፣ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል” ብሎ እንዲናገር በመንፈስ ተነሳስቶ ነበር።— 1 ቆሮንቶስ 12:28-31፤ 13:8-10
እርግጥ ነው ደህንነት እንድናገኝ በአምላክ ላይ ማመናችን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው እምነቱን በሐሰት ፈውሶች ላይ አንዲመሠረት ማድረጉ የኋላ ኋላ ሐዘን ላይ ይጥለዋል። ከዚህም በላይ የመጨረሻውን ጊዜ አስመልክቶ ኢየሱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፣ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።” (ማቴዎስ 24:24) ይህ ወቅት ከማጭበርበርና ከማታለል ባሻገር የአጋንንት ኃይል የሚገለጥበትም ጊዜ ነው። ስለዚህ እንግዳ የሆኑ ድርጊቶች ቢፈጸሙ ሊያስደንቀን አይገባም። እንዲሁም እነዚህ በአምላክ ላይ በትክክል ለማመን የሚያስችል መሠረት የሚጥሉ አለመሆናቸው የተረጋገጠ ነው።
በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ የፈጸመው ዓይነት ፈውስ መፈጸም የሚችል ሰው ባለመኖሩ ተበድለናልን? በጭራሽ። እንዲያውም ኢየሱስ የፈወሳቸው ሰዎች ውሎ አድሮ እንደገና ታመው ሊሆን ይችላል። ሁሉም አርጅተው ሞተዋል። በፈውስ አማካኝነት ያገኙት ጥቅም የቆየው በአንጻራዊ ሁኔታ ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ያከናወናቸው ፈውሶች በሚመጣው ዘመን ለሚኖሩት በረከቶች ጥላ ሆነው ስለሚያገለግሉ ዘላለማዊ ትርጉም ያዘሉ ናቸው።
ቀደም ሲል የተጠቀሱት አሌክሳንደር እና ቤነዲት የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ከመረመሩ በኋላ በዚህ ዘመን በሚከናወነው የእምነት ፈውስና መናፍስታዊ ፈውስ ላይ የነበራቸውን እምነት አቆሙ። ይሁን እንጂ ተአምራዊ ፈውሶች ባለፉት ጊዜያት ተፈጽመው ያበቃላቸው ነገሮች እንዳልሆኑ ተገንዝበዋል። ለምን? በዓለም ዙሪያ እንዳሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአምላክ መንግሥት ሥር ፈውስ የሚያመጣቸውን በረከቶች አሻግረው ይመለከታሉ።— ማቴዎስ 6:10
ሕመምና ሞት አይኖርም
ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የኢየሱስ አገልግሎት ዋና ዓላማ ሕመምተኞችን መፈወስና ሌሎች ተአምራትን ማድረግ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ዋና ሥራው ያደረገው የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክን ነበር። (ማቴዎስ 9:35፤ ሉቃስ 4:43፤ 8:1) አምላክ የሰው ዘር ተአምራዊ ፈውስ እንዲያገኝ በማድረግ ኃጢአትና አለፍጽምና በሰብዓዊ ቤተሰብ ላይ ያስከተሉትን ጉዳቶች ሙሉ በሙሉ የሚያስተካክለው በዚህ መንግሥት አማካኝነት ነው። ይህን የሚፈጽመው እንዴትና መቼ ነው?
ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አሻግሮ በማየት ለሐዋርያው ዮሐንስ ትንቢታዊ ራእይ አሳይቶት ነበር። “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፣ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።” (ራእይ 12:10) ከ1914 ጀምሮ ቀንደኛው የአምላክ ተቃዋሚ ሰይጣን ወደ ምድር አካባቢ እንደተጣለና የአምላክ መንግሥት እውን ሆኖ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ ማስረጃዎቹ ሁሉ ያሳያሉ! ኢየሱስ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ተሾሟል። አሁን በምድር ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ዝግጁ ነው።
በቅርቡ የኢየሱስ ሰማያዊ መስተዳድር “አዲስ ምድር” በሚሆነው ጻድቅ አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ላይ ይገዛል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በዚያን ጊዜ የሚኖሩት ሁኔታዎች ምን ይመስሉ ይሆን? ክብራማ የሆነው እይታ ይህን ይመስላል:- “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፣ ባሕርም ወደ ፊት የለም። እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”—ራእይ 21:1, 4
የሰው ዘሮች ተአምራዊ ፈውስ እውን በሚሆንበት ጊዜ ሕይወት ምን እንደሚመስል ልትገምት ትችላለህ? “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም፣ በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።” አዎን፣ አምላክ የእምነት ፈዋሾች ፈጽሞ ሊያደርጓቸው የማይችሏቸውን ነገሮች በሙሉ ይፈጽማል። “ሞትን ለዘላለም ይውጣል።” በእርግጥም “ጌታ እግዚአብሔር [“የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣” NW] ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”— ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር የሰው ዘር ተአምራዊ ፈውስ ያገኛል