መሠረታዊ ሥርዓትን መረዳት ጉልምስናን ያንጸባርቃል
ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። የዘራችሁትን ታጭዳላችሁ። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ገላትያ 6:7) እነዚህ አባባሎች በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ መሠረታዊ እውነትን ማለትም መሠረታዊ ሥርዓትን የሚያመለክቱ ምሳሌዎች ናቸው። እንዲሁም ሁለቱም ሕግ ሊረቀቁባቸው የሚችሉ መሠረቶች ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። ሆኖም ሕግ ዛሬ ተደንግጎ ነገ ሊሻር ይችላል። እንዲሁም ብዙውን ጊዜ ሕግ በቀጥታ አንድን ነገር በማስመልከት የሚሰጥ ነው። በሌላው በኩል ደግሞ መሠረታዊ ሥርዓት ሰፋ ባለ መንገድ የሚሠራና ለዘላለም ጸንቶ ሊኖር የሚችል ነው። በዚህም የተነሳ የአምላክ ቃል በተቻለ መጠን መሠረታዊ ሥርዓትን ተመርኩዘን እንድናስብ ያበረታታናል።
ዌብስተርስ ሰርድ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ መሠረታዊ ሥርዓትን “አጠቃላይ ወይም መሠረታዊ እውነት:- ሰፊና መሠረታዊ ሕግ፣ መሠረተ ትምህርት ወይም ለሌሎች ሐሳቦች መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ወይም ሌሎች ሐሳቦች የሚፈልቁበት መሠረታዊ ሐሳብ” በማለት ይፈታዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው “ምድጃውን እንዳትነካ” በማለት ለአንድ ሕፃን ሕግ ሊያወጣ ይችላል። ይሁን እንጂ ለአንድ ትልቅ ሰው “ምድጃው ትኩስ ነው” ብሎ መናገሩ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው አባባል ሰፋ ያለ መልእክት እንደሚያስተላልፍ ልብ በሉ። ምክንያቱም ይህ አነጋገር እንደ ማብሰል፣ መጋገር ወይም ምድጃውን ማጥፋት ባሉት አንድ ሰው ሊያደርጋቸው በሚችላቸው ነገሮች ላይ ለውጥ ያመጣል። በዚህም የተነሳ መሠረታዊ ሥርዓት ሆነ ማለት ነው።
እርግጥ ነው ለሕይወት መመሪያ ሆነው የሚያገለግሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች መንፈሳዊ ናቸው። ለአምላክ የምናቀርበውን አምልኮና ደስታችንን በቀጥታ ይነካሉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች በመሠረታዊ ሥርዓቶች ተመርኩዘው ለማሰብ ጥረት አያደርጉም። ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር ከፊታቸው በሚደቀንባቸው ጊዜ ሕግን በመጠቀም መወሰንን ይመርጣሉ። ይህ ጥበብ የጎደለውና በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ታማኝ ሰዎች ከተዉት ምሳሌ ጋር የሚቃረን ነው።—ሮሜ 15:4
አምላክ ባወጣው መሠረታዊ ሥርዓት ይመሩ የነበሩ ሰዎች
አቤል ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች መካከል አምላክ ባወጣው መሠረታዊ ሥርዓት ይመራ የነበረ የመጀመሪያው ሰው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ነው። አቤል ‘ዘሩን’ በሚመለከት የተሰጠውን ተስፋ በቁም ነገር ሳያስብበትና የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት የደም መሥዋዕት አስፈላጊ መሆኑን ሳይገነዘብ አልቀረም። (ዘፍጥረት 3:15) በዚህም የተነሳ ‘ከበጎቹ በኩራቱን’ ለአምላክ አቀረበ። “ከስቡ” የሚለው አባባል አቤል ለይሖዋ ምርጡን እንደሰጠ የሚያመለክት ነው። ሆኖም አምላክ መሥዋዕትን በሚመለከት መሟላት ያለባቸው ዝርዝር ሁኔታዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ የተናገረው አቤል ከሞተ ከሁለት ሺህ የሚበልጥ ዓመት ካለፈ በኋላ ነው። ፈሪሃ አምላክ ከነበረውና አምላክ ባወጣው መሠረታዊ ሥርዓት ይመራ ከነበረው ከአቤል በተለየ መንገድ ወንድሙ ቃየን ያቀረበው መሥዋዕት ለይስሙላ ያክል የተደረገ ነበር። ቃየል ተገቢ ያልሆነ ዝንባሌ የነበረው ከመሆኑም በላይ ያቀረበው መሥዋዕት በመሠረታዊ ሥርዓት የማይመራ ልብ እንደነበረው ያረጋግጥ ነበር።—ዘፍጥረት 4:3-5
ከዚህም በተጨማሪ ኖኅ አምላክ ባወጣው መሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ሰው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው አምላክ መርከብ እንዲሠራ በቀጥታ ትእዛዝ ሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ለሌሎች እንዲሰብክ የሚያዝ መመሪያ ተሰጥቶት እንደነበር የሚገልጽ ምንም ዓይነት የጽሑፍ ማስረጃ የለም። ያም ሆኖ ግን ኖኅ ‘የጽድቅ ሰባኪ’ ተብሎ ተጠርቷል። (2 ጴጥሮስ 2:5) ኖኅ እንዲሰብክ አምላክ መመሪያ ሰጥቶት ሊሆን ቢችልም እንኳን መሠረታዊ ሥርዓትን በሚመለከት ያለው እውቀትና ለጎረቤት ያለው ፍቅርም እንዲህ እንዲያደርግ ገፋፍቶት መሆን አለበት። የምንኖረው ከኖኅ ዘመን ጋር ተመሳሳይ በሆነ ጊዜ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን እኛም እርሱ ያሳየውን መልካም ዝንባሌና ምሳሌ የምንከተል እንሁን።
ኢየሱስ በዘመኑ ይኖሩ ከነበሩት ካህናት በተለየ መንገድ ሕዝቡ በመሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመርኩዘው እንዲያስቡ አስተምሯቸዋል። በተራራ ላይ ያቀረበው ስብከት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው። መላው ንግግሩ መሠረታዊ ሥርዓት የተንጸባረቀበት ነበር። (ማቴዎስ ምዕራፍ 5-7) ኢየሱስ ያስተማረው በዚህ መንገድ ነበር፤ ምክንያቱም ከእርሱ በፊት ይኖሩ እንደነበሩት እንደ አቤልና ኖኅ አምላክን በሚገባ ያውቅ ነበር። ገና በልጅነቱ “ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ” አይኖርም የሚለውን መሠረታዊ እውነት ከፍ አድርጎ ተመልክቷል። (ዘዳግም 8:3፤ ሉቃስ 2:41-47) አዎን፣ አምላክ ባወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመመራት የሚያስችለው ቁልፍ ነገር ይሖዋን፣ እርሱ የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች እንዲሁም ዓላማዎቹን ጠንቅቆ ማወቅ ነው። አምላክ ያወጣቸው እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሕይወታችንን እንዲቆጣጠሩ ስንፈቅድላቸው መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ሕያው ይሆናሉ።—ኤርምያስ 22:16፤ ዕብራውያን 4:12
መሠረታዊ ሥርዓቶችና ልብ
አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ቅጣት በመፍራት ብቻ ያለ ፍላጎት አንድን ሕግ መታዘዝ ይቻላል። ይሁን እንጂ መሠረታዊ ሥርዓትን መቀበል እንዲህ ያለውን ዝንባሌ ያስቀራል። ምክንያቱም አንድ ሰው በመሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ ከሆነ የሚታዘዘው ከልቡ ይሆናል። እንደ አቤልና ኖኅ፣ የሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን ከመሰጠቱ በፊት ይኖር የነበረውን ዮሴፍን እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። ዮሴፍ የጶጢፋራ ሚስት የጾታ ብልግና እንዲፈጽም ልታስተው በሞከረች ጊዜ “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” በማለት ተናግሯል። አዎን፣ ዮሴፍ ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” ናቸው የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት በሚገባ ያውቅ ነበር።—ዘፍጥረት 2:24፤ 39:9
በአሁኑ ጊዜ ያለው ዓለም የትኛውንም የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓት አይከተልም። በዓለም ያሉ ሰዎች ዓመፅንና የሥነ ምግባር ብልግናን እንደ ሆዳም ሰው ተስገብግበው ይመገቧቸዋል። አንድ ክርስቲያንም በፊልም፣ በቪድዮ ወይም በመጻሕፍት የሚቀርቡትን አሸር ባሸር ምግቦች በትንሽ በትንሹ ምናልባትም በድብቅ ለመቀማመስ ይፈተን ይሆናል። አምላክ ወደፊት ከሚመጣው “ታላቅ መከራ” የሚያድነው ታማኞቹን ብቻ መሆኑን በመገንዘብ እንደ ዮሴፍ በመሠረታዊ ሥርዓት እየተመሩ መጥፎ ነገሮችን መጸየፍ የሚያስመሰግን ነው። (ማቴዎስ 24:21) አዎን፣ በአንደኛ ደረጃ ውስጣዊ ማንነታችንን በትክክል የሚገልጠው በሰው ፊት ያለን አቋም ሳይሆን በግል የምናደርገው ነገር ነው።—መዝሙር 11:4፤ ምሳሌ 15:3
በዚህም የተነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምንመራ ከሆነ በአምላክ ሕግ ውስጥ ማምለጫ ቀዳዳ ፍለጋ አንገባም፤ እንዲሁም አንድን ሕግ ሳንጥስ ምን ያህል ርቀን መጓዝ እንደምንችል ለማየት አንሞክርም። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ እርባና ቢስ ነው። በመጨረሻም ጉዳት ላይ ይጥለናል።
ከሕጉ በስተጀርባ ያለውን ተመልከቱ
እርግጥ ነው፣ ሕግ በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ሕጎች እኛን ለመጠበቅ የሚረዱ እንደ ዘብ የቆሙ ጠባቂዎች ናቸው፤ በውስጣቸውም በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ያቀፉ ናቸው። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች አለመረዳት ተዛማጅ ለሆኑ ሕጎች ያለንን ፍቅር ያቀዘቅዝብናል። በጥንት የነበሩት እስራኤላውያን ይህ ሁኔታ ደርሶባቸው ነበር።
አምላክ ለእስራኤላውያን አሥርቱን ትእዛዛት ሰጥቷቸው ነበር። ከእነዚህ ትእዛዛት መካከል የመጀመሪያው ከይሖዋ በስተቀር ማንኛውንም ሌላ አምላክ እንዳያመልኩ የሚከለክል ነበር። ከዚህ ሕግ በስተጀርባ ያለው መሠረታዊ እውነት ይሖዋ ሁሉን ነገር ፈጥሯል የሚለው ነው። (ዘጸአት 20:3-5) ይሁን እንጂ ሕዝቡ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ጠብቀዋልን? ይሖዋ ራሱ መልስ ሲሰጥ “[እስራኤላውያን] ግንዱን:- አንተ አባቴ ነህ፤ ድንጋዩንም:- አንተ ወለድኸኝ [“እናቴ፣” የ1980 ትርጉም] ይላሉ፤ ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ” በማለት ይናገራል። (ኤርምያስ 2:27) የይሖዋን ልብ የሚያሳዝን እንዴት ያለ ልበ ደንዳናነትና ዓመፀኝነት ነበር!—መዝሙር 78:40, 41፤ ኢሳይያስ 63:9, 10
አምላክ ለክርስቲያኖችም ሕግ ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል ከጣዖት አምልኮ፣ ከጾታ ብልግናና ደምን አለአግባብ ከመጠቀም መራቅ አለባቸው። (ሥራ 15:28, 29) ይህን ስናስብ ከበስተጀርባ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማለትም አምላክ ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ልንሰጠው የሚገባ መሆኑን፣ ለትዳር ጓደኛችን ታማኝ መሆን እንዳለብንና ሕይወት ሰጪያችን ይሖዋ መሆኑን ልንገነዘብ እንችላለን። (ዘፍጥረት 2:24፤ ዘጸአት 20:5፤ መዝሙር 36:9) ከእነዚህ መመሪያዎች በስተጀርባ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ካስተዋልንና በሚገባ ከተገነዘብን ለእኛ ጥቅም ታስበው የተሰጡ እንደሆኑ እንረዳለን። (ኢሳይያስ 48:17) አምላክ ያወጣቸው ‘ትእዛዛት’ ለእኛ ‘ከባዶች አይደሉም።’—1 ዮሐንስ 5:3
በጥንት ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን የአምላክን ትእዛዛት ችላ ብለው የነበረ ሲሆን በኢየሱስ ዘመን የነበሩት “የሕጉ ዶክተሮች” ማለትም ጸሐፍት ደግሞ ወደ ሌላኛው ጽንፍ ሄደው ነበር። ንጹሑን አምልኮ የሚያዛቡና አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚያዳፍኑ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሕግጋትና ወጎች አውጥተው ነበር። (ማቴዎስ 23:2 ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ሰዎች ለውድቀት፣ ለተስፋ መቁረጥ ወይም ለግብዝነት ተዳረጉ። (ማቴዎስ 15:3-9) እንዲሁም ብዙዎቹ ሰው ሠራሽ ሕግጋት ሰብዓዊነት የጎደላቸው ነበሩ። ኢየሱስ የሰለለች እጅ የነበረችውን አንድ ሰው ሲፈውስ በአካባቢው የነበሩትን ፈሪሳውያን “በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን?” በማለት ጠየቃቸው። አንድም ቃል ሳይተነፍሱ ጸጥ ማለታቸው በነገሩ እንዳልተስማሙ የሚያሳይ ስለነበረ ኢየሱስ ‘ስለ ልባቸው ድንዛዜ እንዲያዝን’ አደረገው። (ማርቆስ 3:1-6) ፈሪሳውያን በሰንበት ቀን የባዘነችን ወይም የተጎዳችን አንዲት እንስሳ (ገንዘብ የወጣባትን) ይረዱ ይሆናል። ይሁን እንጂ የሞትና የሕይወት ጉዳይ እስካልሆነ ድረስ አንድ ሰው ወይም አንዲት ሴት ችግር ውስጥ ቢገቡ ምንም ዓይነት እርዳታ አያደርጉም። በሰብዓዊ ደንቦችና ኅልቆ መሳፍርት በሌላቸው ሕጎች የተተበተቡ ከመሆናቸው የተነሳ ሥዕል ላይ እንደሚሯሯጡ ጉንዳኖች የሥዕሉን የተሟላ ገጽታ ማለትም መለኮታዊውን መሠረታዊ ሥርዓት ሳያስተውሉ ቀርተዋል።—ማቴዎስ 23:23, 24
ይሁን እንጂ ወጣቶችም እንኳን ልባቸው ቅን ከሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ባላቸው እውቀት በመጠቀም ለይሖዋ ክብር ሊያመጡ ይችላሉ። የአሥራ ሦስት ዓመቷን ርብቃን የምታስተምር አንዲት አስተማሪ ከክፍል ተማሪዎች መካከል ቁማር የሚጫወት እንዳለ ጠየቀች። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች እንደማይጫወቱ ተናገሩ። ሆኖም የተለያዩ ሁኔታዎች በሚጠቀሱበት ጊዜ ከርብቃ በስተቀር ሁሉም በሆነ መንገድ ቁማር እንደሚጫወቱ አምነው ተናገሩ። አስተማሪዋም ከፍተኛ ዕጣ ያለው አንድ ሎተሪ በ20 ሳንቲም ትገዛ እንደሆነ ርብቃን ጠየቀቻት። ርብቃም እንደማትገዛ ተናገረችና ይህ ድርጊት አንዱ የቁማር ዓይነት መሆኑን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን እየጠቀሰች አስረዳች። ከዚያም አስተማሪዋ ለጠቅላላው ተማሪዎች ‘በእኔ አመለካከት እዚህ ካላችሁት መካከል በትክክለኛው የቃሉ ፍቺ መሠረት “በመሠረታዊ ሥርዓት” የምትመራ ናት ብዬ ልናገር የምችለው ርብቃን ብቻ ነው’ በማለት ተናገረች። አዎን፣ ርብቃ በአጭሩ “ሃይማኖቴ አይፈቅድልኝም” በማለት መልስ መስጠት ትችል ነበር። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ በጥልቀት አስባበታለች። በመሆኑም ቁማር ስህተት የሆነው ለምን እንደሆነና እርሷም ቁማር የማትጫወተው ለምን እንደሆነ በመግለጽ መልስ ሰጥታለች።
እንደ አቤል፣ ኖኅ፣ ዮሴፍና ኢየሱስ ያሉ ሰዎች የተዉት ምሳሌ ‘በማሰብ ችሎታችንና’ ‘በማመዛዘን ችሎታችን’ ተጠቅመን አምላክን ማምለካችን እንዴት ጥቅም ሊያስገኝልን እንደሚችል ያሳያል። (ምሳሌ 2:11፤ ሮሜ 12:1) ሽማግሌዎች “የእግዚአብሔርን መንጋ በርኅራኄ” በሚጠብቁበት ጊዜ ኢየሱስን መምሰላቸው ጠቃሚ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:2) በኢየሱስ ሁኔታ ላይ በግልጽ እንደታየው በልዑሉ ይሖዋ ከለላ ሥር የሚሆኑት የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚወዱ ሰዎች ብቻ ናቸው።—ኢሳይያስ 65:14