ሁልጊዜ ሠራዊት ያስፈልገናልን?
ሠራዊቶች፣ የሰው ልጅ በቀላሉ የማይገመት ጥሪቱን እንዲያሟጥጥ ከማድረጋቸውም ሌላ ደስታውንም ነጥቀውታል። በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች ‘የሰው ልጅ ሠራዊት የማያስፈልገው ዓለም አቀፍ ደህንነት ማስፈን ይችል ይሆን?’ ብለው ያስባሉ። ሰዎችን በጅምላ የሚያረግፉ የጦር መሣሪያዎች ሕይወት የሚባል ነገር እንዳይኖር ማድረግ የሚቻልበት ደረጃ ላይ በደረሱበት በዛሬው ጊዜ ይህ ጥያቄ ይበልጥ አንገብጋቢ ሆኗል። ሠራዊት የሌለበት ዓለም ይመጣል ብሎ ተስፋ ማድረግ ምን ያህል እውን ሊሆን የሚችል ነገር ነው?
ጥሩ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች የሚያስገኙት የእርስ በርስ መተማመን በተወሰነ መጠን የጦር መሣሪያ ቅነሳ ወደ ማድረግ እንደሚያደርስ ካሁን ቀደም የተከናወኑት ነገሮች ያስረዳሉ። ለምሳሌ ያህል በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ወዳጃዊ ግንኙነት በመኖሩ ምክንያት ሁለቱን አገሮች የሚያዋስነው የ5,000 ኪሎ ሜትር ድንበር ከአንድ መቶ ዓመት ተኩል ለሚበልጥ ጊዜ በሠራዊት ተጠብቆ አያወቅም። እንደሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ ኖርዌይና ስዊድንም ተመሳሳይ ስምምነት ላይ መድረስ ችለዋል። በሁሉም መንግሥታት መካከል ስምምነት ቢደረስ ሠራዊት የማያስፈልግበት ዓለም ለማምጣት ያስችላልን? አንደኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለው አሰቃቂ ሁኔታ ይህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል።
በ1918 ሰላም በወረደ ጊዜ የቨርሳይለስ የሰላም ስምምነት አንደኛው ዓላማ “መንግሥታት የሚኖራቸውን የጦር መሣሪያ መጠን ለመገደብ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር” ነበር። በቀጣዮቹ ዓመታት ፓስፊስዝም (ሰላም ወዳድነት) የሚለው መርኅ እየገነነ መጣ። ይህን መርኅ የሚያራምዱ አንዳንድ ሰዎች ጦርነት አንድ መንግሥት ሊገጥመው ከሚችለው ነገር ሁሉ የከፋ ነው፤ ከሽንፈትም ሳይቀር ይከፋል የሚል ሐሳብ ማስፋፋት ጀመሩ። ይህን መርኅ የሚቃረኑ ሰዎች ደግሞ ባለፉት መቶ ዘመናት የተከናወኑትን የሚከተሉትን ምሳሌዎች በመጥቀስ ይህን ሐሳብ ተቃውመዋል። አይሁዳውያን ጠላቶቻቸውን ለመከላከል ያደረጉት የትጥቅ እንቅስቃሴ ባይኖርም እነርሱን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚደረገው ጭካኔ የተሞላበት ጥረት ቀጥሎ ነበር። አፍሪካውያን ለባርነት ወደ አሜሪካ ይጭኗቸው የነበሩትን ሰዎች ለመከላከል የሚያስችል አቅም ባይኖራቸውም ለበርካታ መቶ ዘመናት የጭካኔ ድርጊት ሲፈጸምባቸው ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ ጦርነትን የሚቃወሙት ወገኖች፣ አገራት የራሳቸው የመከላከያ ኃይል ሊኖራቸው ይገባል በሚለው ሐሳብ ተስማምተዋል። በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሲቋቋም ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነገር የጦር መሣሪያ ቅነሳ ሳይሆን ጠብ አጫሪነትን ለመከላከል ዓለም አቀፋዊ ትብብር እንዲሰፍን ለማድረጉ ጉዳይ ነበር። አባል አገራቱ በዚህ መንገድ የሚፈጠረው ከስጋት ነፃ የሆነ ሁኔታ መንግሥታት የጦር መሣሪያዎቻቸውን እንዲቀንሱ ያነሳሳቸዋል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር።
ይሁንና ሌላ ችግር በጉልህ መታየት ጀመረ። ብዙውን ጊዜ አንዱ መንግሥት አቋሙን አስተማማኝ ለማድረግ ሲጥር ለጎረቤቱ ስጋት የሚፈጥር እየሆነ መጣ። ይህ ሁኔታ ወደ ጦር መሣሪያ እሽቅድድም አመራ። ይሁን እንጂ በቅርቡ በታላላቅ መንግሥታት መካከል የተፈጠረው የተሻለ ግንኙነት የጦር መሣሪያ ቅነሳ የማድረጉ ተስፋ እንዲለመልም አድርጓል። ይሁን እንጂ ከዚያ ወዲህም የባሕረ ሰላጤው ጦርነትና በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተቀሰቀሰው ችግር ብዙዎች የጦር መሣሪያ ቅነሳን በሚመለከት የነበራቸው ተስፋ እንዲጨልም አድርጓል። ታይም መጽሔት ከአምስት ዓመታት ገደማ በፊት “ቀዝቃዛው ጦርነት ቢያበቃም ዓለም አደገኛ ቦታ የመሆኗ ስጋት ጨመረ እንጂ አልቀነሰም” ሲል አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር።
ዓለም አቀፍ “ጠባቂ” እንዲኖር መመኘት
ብዙ ታዛቢዎች የሰው ልጅ እያንዳንዱን ወገን ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል ያለው ብቸኛ ምድር አቀፍ አስተዳደር ያስፈልገዋል ብለው ደምድመዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ታላላቆቹ የዓለም ወታደራዊ ኃይሎች ይህን ማድረግ ሳይችሉ በመቅረታቸው አንዳንዶች ለወደፊቱ ጊዜ ያለው ተስፋ የተመናመነ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የምትቀበል ከሆነ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ለዚህ አንገብጋቢ ጥያቄ መፍትሔ ይሰጥ ይሆን ብለህ ታስብ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ “የፍቅርና የሰላምም አምላክ” ሲል የሚጠራው አምላክ ፍትሕን ለማስፈን ወታደራዊ ኃይል ይጠቀም ይሆን? ከሆነስ የትኛውን ሠራዊት? ዛሬ ያሉት ብዙዎቹ ሠራዊቶች አምላክ ይደግፈናል ብለው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በእርግጥ የአምላክን ፈቃድ እየፈጸሙ ነውን? ወይስ አምላክ እጁን ጣልቃ አስገብቶ ሰላምና መረጋጋት የሚያሰፍንበት ሌላ መንገድ አለው?—2 ቆሮንቶስ 13:11
ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አዳምና ሔዋንን ከገነት በማስወጣትና ተመልሰው እንዳይገቡ ኪሩቤሎችን በማቆም መጀመሪያ ለተነሳው ዓመፅ ምላሽ ሰጥቷል። ከዚህም በላይ በሉዓላዊነቱ ላይ የተነሣውን ዓመፅ በሙሉ ለማጥፋት ዓላማ እንዳለው ተናግሯል። (ዘፍጥረት 3:15) ይህ ነገር አምላክ ሠራዊት እንዲጠቀም የሚጠይቅ ይሆን?
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ፍርዱን ለማስፈጸም በሠራዊት የተጠቀመባቸው ጊዜያት እንዳሉ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል በከነዓን ምድር የነበሩት መንግሥታት ከእንስሳት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ይፈጽሙ፣ ልጆቻውን መሥዋዕት ያደርጉና ጭካኔ የተሞላባቸውን ውጊያዎች ያካሂዱ ነበር። አምላክ እነዚህ መንግሥታት ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ ከወሰነ በኋላ ይህንኑ ፍርድ ለማስፈጸም የኢያሱን ሠራዊት ተጠቅሟል። (ዘዳግም 7:1, 2) በተመሳሳይም የንጉሥ ዳዊት ሠራዊት አምላክ በፍልስጤማውያን ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ያስፈጸመ ሲሆን ይህ በመጨረሻው የፍርድ ቀን አምላክ ክፋትን ሁሉ እንዴት እንደሚያስወግድ የሚያሳይ ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል።
እነዚህ ክስተቶች ትምህርት ሰጭ ነበሩ። ይሖዋ ሰዎች ተረጋግተው እንዲኖሩ ለማድረግ በሠራዊቶች ሊጠቀም እንደሚችል አሳይተዋል። በእርግጥም ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ደረጃ በአገዛዙ ላይ ለተነሳው ዓመፅ እልባት የሚሰጥበት ልዩ ሠራዊት አለው።
“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር”
መጽሐፍ ቅዱስ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” የሚለውን መግለጫ ከ250 ጊዜ በላይ ይጠቀምበታል። ይህ መግለጫ በዋነኛነት የሚያመለክተው አምላክ እጅግ ግዙፍ የሆነው የመላእክት ሠራዊት አዛዥ መሆኑን ነው። በአንድ ወቅት ነቢዩ ሚክያስ ለነገሥታቱ ለአክዓብና ለኢዮሳፍጥ “እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ” ብሏቸዋል። (1 ነገሥት 22:19) እዚህ ላይ የተጠቀሰው የመላእክት ሠራዊት ነው። ይሖዋ ሕዝቡን ለመጠበቅ በዚህ ሠራዊት ተጠቅሟል። የዶታይን ከተማ በተከበበች ጊዜ የኤልሳዕ ሎሌ ተስፋው ተሟጥጦ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ በተዓምራዊ ሁኔታ የመንፈሳዊ ፍጥረታቱን ሠራዊት እንዲያይ በማድረግ አረጋጋው። “እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ገለጠ፤ አየም፤ እነሆም . . . የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር።”—2 ነገሥት 6:15-17
እነዚህ ነገሮች አምላክ ዛሬ ያሉትን ሠራዊቶች እንደሚደግፍ ያሳያሉን? አንዳንዶቹ የሕዝበ ክርስትና ሠራዊት የአምላክ ሠራዊት ነን ይሉ ይሆናል። ብዙዎቹም ቀሳውስት እንዲባርኳቸው ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ የሕዝበ ክርስትና ሠራዊቶች ብዙውን ጊዜ እርስ በርሳቸው የሚፋጁና ሌላውን ወንድማቸውን የሚዋጉ ናቸው። በዚህ መቶ ዘመን የተከናወኑት ሁለት የዓለም ጦርነቶች የተጀመሩት ክርስቲያን ነን በሚሉ ሠራዊቶች መካከል ነው። ይህ ደግሞ የአምላክ ሥራ ሊሆን አይችልም። (1 ዮሐንስ 4:20) እንደነዚህ ያሉት ወታደራዊ ሠራዊቶች ለሰላም እንደሚዋደቁ ይናገሩ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲህ ዓይነት ሠራዊቶችን አቋቁመው የዓለም ሰላም እንዳይደፈርስ ይጠብቁ ዘንድ አዝዟልን?
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ ይጸልይበት ወደ ነበረው የአትክልት ሥፍራ የታጠቁ ሰዎች መጥተው እጃቸውን በጫኑበት ጊዜ ሰላም የሚያደፈርስ ትልቅ ነገር ተከስቶ ነበር። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ከሰዎቹ መካከል የአንዱን ጆሮ በሰይፍ ቆረጠው። ኢየሱስ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ አንድ ትልቅ መሠረታዊ ሥርዓት አስተማራቸው። እንዲህ አለ:- “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ። ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን?” ኢየሱስ በእርሱ ትእዛዝ ሥር ያለ ግዙፍ ሠራዊት ነበረው፤ ይሁን እንጂ ጴጥሮስ የዚህ ሠራዊት አባል አልነበረም። የዚህ ሠራዊት ክፍል የሆነ አንድም ሰው የለም። ከዚህ ይልቅ ጴጥሮስም ሆነ ሌሎቹ የኢየሱስ ተከታዮች የተጠሩት “ሰዎችን አጥማጆች” እንዲሆኑ ነበር። (ማቴዎስ 4:19፤ 26:47-53) ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ኢየሱስ ጉዳዩን ለጲላጦስ ግልጽ አድርጎ አስረድቶታል። እንዲህ አለ:- “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፣ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም።” (ዮሐንስ 18:36) ከምድራዊው የንጉሥ ዳዊት መንግሥት በተለየ መልኩ አምላክ ለኢየሱስ የሰጠው መንግሥት ሰማያዊ ሲሆን በምድር ላይ ሰላምን ያሰፍናል።
የአምላክ ሠራዊት ለጦርነት ይከትታል
በቅርቡ የአምላክ ሠራዊት እርምጃ ይወስዳል። የራእይ መጽሐፍ ወደፊት የሚከናወነውን ጦርነት አስመልክቶ ሲገልጽ ኢየሱስን “የእግዚአብሔር ቃል” በማለት ይጠራዋል። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል።” መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ጦርነት “የምድር ነገሥታትና ጭፍራዎቻቸው [ሠራዊቶቻቸው]” የሚደመሰሱበት እንደሆነ ይገልጻል። ለአምላክ ታማኝ ሳይሆኑ የሚቀሩትን ሌሎች ሰዎች በሚመለከት ትንቢቱ “የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ” ይላል። ሰይጣን ዲያብሎስ ጭምር ከእንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆን ይደረጋል። ይህ በእርግጥም ሠራዊት የማያስፈልገው ሰላም የሰፈነበት ዓለም እንዲመጣ የሚያስችል እርምጃ ነው።—ራእይ 19:11-21፤ 20:1-3
ጦርነት የሌለበት ዓለም
ሠራዊት የማያስፈልግበትና መረጋጋት የሰፈነበት ዓለም ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙር እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔርን ሥራ፣ በምድር ያደረገውንም ተአምራት እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል።”—መዝሙር 46:8, 9
ይህ እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል! እስቲ አስበው፣ የሰው ልጅ ኅብረተሰብ ጠፍሮ ከያዘው ለየሠራዊቱና ለመሣሪያዎቻቸው ከሚከፈለው ቀረጥ ነፃ ይወጣል! ሰዎች የእያንዳንዱን ሰው የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል፣ ምድርን ለማጽዳትና እንደገና ለመገንባት ኃይላቸውን አስተባብረው ይሠራሉ። ለሰው ልጅ እውነተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን አዳዲስ ነገሮች ለመፍጠር የሚያስችል አጋጣሚ ይኖራል።
“ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፣ በዳርቻሽም ውስጥ ጉስቁልናና ቅጥቃጤ አይሰማም” የሚለው ትንቢት በምድር ዙሪያ ፍጻሜውን ያገኛል። (ኢሳይያስ 60:18) ከዚያ በኋላ ቤት ንብረታቸውን ጥለው በመጠለያ ካምፖች ውስጥ የመከራ ኑሮ ለመግፋት ከጦርነት ቀጣናዎች የሚሰደዱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች አይኖሩም። ከዚያ በኋላ በመንግሥታት መካከል በሚነሳ ግጭት ምክንያት የሚወዷቸው ሰዎች ስለተገደሉባቸው ወይም የአካል ጉዳት ስለደረሰባቸው የሚያዝኑና የሚያለቅሱ ሰዎች አይኖሩም። የይሖዋ ሰማያዊ ንጉሥ ዘላቂ የሆነ የዓለም ሰላም ያሰፍናል። “በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፣ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል።”—መዝሙር 72:7, 14
ጥላቻን ሳይሆን አምላካዊ በሆነ መንገድ ማፍቀርን በተማሩት ሰዎች መካከል የሚኖረው ሕይወት ደግሞ ከዚህ ይበልጥ አስደሳች ይሆናል። የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ይተነብያል:- “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።” ይሖዋን በሚያውቁና በሚወዱ ሰዎች መካከል መኖር ምን ይመስል ይሆን? ይኸው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “የጽድቅም ሥራ ሰላም፣ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል። ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።”—ኢሳይያስ 11:9፤ 32:17, 18
እምነታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ የመሠረቱ ሰዎች የአምላክ ሠራዊት ምድርን የሰላም ጠላት ከሆኑ ወገኖች ሁሉ ለማጽዳት እንደተዘጋጁ ያስተውላሉ። ይህን ነገር ማወቃቸው መጽሐፍ ቅዱስ “በዘመኑ ፍጻሜ” ይሆናል ሲል የሚናገርለትን ነገር እንዲያከናውኑ ትምክህት ይሰጣቸዋል። ይኸውም “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።”—ኢሳይያስ 2:2-4
ከብዙ ብሔራት እየተውጣጡ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ሰዎች አሁንም ቢሆን ‘ጦርነትን ከመማር’ ታቅበዋል። የአምላክ ሰማያዊ ሠራዊት ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ይተማመናሉ። አንተም ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ተመሳሳይ ትምክህት ልታዳብር ትችላለህ።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
U.S. National Archives photo