የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ገጽ 13-ገጽ 16 አን. 5
  • “እንዴት እንደምታዳምጡ በጥንቃቄ አስቡ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “እንዴት እንደምታዳምጡ በጥንቃቄ አስቡ”
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ልብህን አዘጋጅ
  • ሐሳብህን ሰብስብ
  • ንግግር ሲሰጥ ማዳመጥ
  • ውይይት ሲደረግ ማዳመጥ
  • በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ማዳመጥ
  • ልጆች እንዲያዳምጡ ማሰልጠን
  • ጥሩ አዳማጭ ሁን
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ጥሩ አዳማጭ ሁኑ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
  • ይሖዋ እየመራን ያለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ‘በማዳመጥ ተጨማሪ ትምህርት ቅሰሙ’
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ገጽ 13-ገጽ 16 አን. 5

“እንዴት እንደምታዳምጡ በጥንቃቄ አስቡ”

ማዳመጥ ትምህርት በመቅሰም ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። አንድ ሰው ሕይወቱን እንዲያተርፍ ወይም እንዲያጣ ምክንያት ሊሆንም ይችላል። ይሖዋ ሕዝቡን ከግብጽ ባርነት ነፃ የሚያወጣበት ጊዜ ሲደርስ ለሙሴ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። የበኩር ልጆችን እንዲገድል ከተላከው መልአክ ልጆቻቸውን መታደግ ይችሉ ዘንድ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሙሴ ለእስራኤል ሽማግሌዎች ነግሯቸዋል። (ዘጸ. 12:​21-23) ከዚያም ሽማግሌዎቹ የተነገራቸውን መመሪያ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ አስተላልፈዋል። መልእክቱን ያስተላለፉት በቃል ነበር። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ የሚነገራቸውን ነገር በጥሞና ማዳመጥ ነበረባቸው። ከዚያስ ምን ምላሽ ሰጡ? መጽሐፍ ቅዱስ “የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ” በማለት ይነግረናል። (ዘጸ. 12:28, 50, 51) ከዚህም የተነሣ እስራኤላውያን የአምላክን አስደናቂ የማዳን ኃይል ለማየት በቅተዋል።

ዛሬም ይሖዋ እኛን ከዚያ ለላቀ የማዳን ቀን እያዘጋጀን ነው። በመሆኑም የሚሰጠንን መመሪያ በትኩረት ልንከታተል ይገባል። እንዲህ ያለውን መመሪያ የምናገኘው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ነው። ከእነዚህ ስብሰባዎች ሙሉ ጥቅም እያገኘህ ነውን? ከስብሰባዎቹ የምታገኘው ጥቅም በእጅጉ የተመካው በምታዳምጥበት ሁኔታ ላይ ነው።

በስብሰባዎች ላይ የሚሰጡትን ትምህርቶች ዋና ዋና ነጥብ ማስታወስ ትችላለህ? ትምህርቶቹን በየጊዜው በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ የማድረግ ወይም ለሌሎች የመንገር ልማድ አለህ?

ልብህን አዘጋጅ

በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ከሚሰጠው ትምህርት በሚገባ ለመጠቀም ልባችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል። የይሁዳ ንጉሥ በነበረው በኢዮሣፍጥ የግዛት ዘመን የተከናወነው ነገር የዚህን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ኢዮሣፍጥ እውነተኛውን አምልኮ በመደገፍ ቆራጥ እርምጃ ወስዷል። ‘የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ ዐፀዱን ከይሁዳ ከማስወገዱም’ ሌላ በሁሉም የይሁዳ ከተሞች ለሚኖረው ሕዝብ የይሖዋን ሕግ የሚያስተምሩ መሳፍንት፣ ሌዋውያንና ካህናት ሾሟል። ያም ሆኖ ‘የኮረብታው መስገጃዎች ጨርሶ አልተወገዱም’ ነበር። (2 ዜና 17:6-9፤ 20:33) በአረማውያኑ የኮረብታ መስገጃዎች ላይ የሚቀርበው የሐሰት አምልኮና በይሖዋ ስም የሚካሄደው ተቀባይነት የሌለው አምልኮ ሥር የሰደደ ከመሆኑ የተነሣ ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ አልቻለም።

ኢዮሣፍጥ ባደረገው ዝግጅት አማካኝነት ለሕዝቡ የተሰጠው ትምህርት ዘላቂ ለውጥ ሳያመጣ የቀረው ለምንድን ነው? ዘገባው በመቀጠል “ሕዝቡም ገና ልባቸውን ወደ አባቶቻቸው አምላክ አላዘጋጁም ነበር” በማለት ይገልጻል። መስማት ሰምተዋል፤ ነገር ግን በሰሙት መሠረት እርምጃ አልወሰዱም። ምናልባት መሥዋዕት ለማቅረብ ብለው ኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ድረስ መጓዝ አድካሚ እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ከልብ እንዲነሳሱ የሚያደርግ እምነት አልነበራቸውም።

በሰይጣን ዓለም ተሸንፈን እንዳንወሰድ ይሖዋ ዛሬ የሚሰጠንን ትምህርት ለመቀበል ልባችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል። ልባችንን የምናዘጋጀው እንዴት ነው? አንደኛው ዋና መንገድ ጸሎት ነው። ከአምላክ የምናገኘውን ትምህርት በአመስጋኝነት መቀበል እንድንችል መጸለይ ይኖርብናል። (መዝ. 27:​4፤ 95:​2) አመስጋኞች ከሆንን የማስተማር ኃላፊነት የተጣለባቸው ወንድሞቻችን የሚያደርጉትን ጥረት እናደንቃለን። እነዚህ ወንድሞች ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ይሖዋ ሕዝቡን ለማስተማር እንዲጠቀምባቸው ራሳቸውን አቅርበዋል። በተጨማሪም አዲስ ነገር ስንማር ብቻ ሳይሆን በፊት ለምናውቀው ትምህርት ያለንን አድናቆት የሚያሳድግ አጋጣሚ ስናገኝም ይሖዋን እንድናመሰግነው ይገፋፋናል። የአምላክን ፈቃድ በተሟላ መንገድ ለመፈጸም ስለምንፈልግ ‘አቤቱ ይሖዋ፣ መንገድህን አስተምረኝ ስምህን ለመፍራት ልቤን አንድ አድርግልኝ’ ብለን እንጸልያለን።​—⁠መዝ. 86:​11

ሐሳብህን ሰብስብ

በጥሞና እንዳናዳምጥ እንቅፋት የሚሆኑብን ብዙ ነገሮች አሉ። በአእምሮአችን ውስጥ የሚጉላላ ብዙ ሐሳብ ይኖር ይሆናል። በአድማጮች መካከልም ሆነ ከስብሰባው ቦታ ውጭ የሚፈጠር ድምፅ ወይም የሚደረግ እንቅስቃሴ ሐሳባችንን ሊሰርቅብን ይችላል። ምቾታችንን የሚነፍጉ ሁኔታዎች ሐሳባችንን ሰብስበን እንዳንከታተል እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ። ሕፃናት ልጆች ያሏቸው ብዙውን ጊዜ ሐሳባቸው ይከፋፈላል። ፕሮግራሙን በትኩረት እንድንከታተል ምን ሊረዳን ይችላል?

ብዙውን ጊዜ ትኩረታችን የሚያርፈው ዓይናችን ባረፈበት ነገር ላይ ነው። ዓይኖችህ ተናጋሪው ላይ እንዲያርፉ ካደረግህ ሐሳብህን ሰብስበህ ማዳመጥ ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሲጠቅስ ጥቅሱን የምታውቀው ቢሆንም እንኳ አውጥተህ ተከታተል። ድምፅ በተሰማ ወይም አንድ ነገር ውልብ ባለ ቁጥር ወደዚያ ዞረህ እንዳታይ ራስህን መግታት ይኖርብሃል። ዓይንህ እዚህም እዚያም እያማተረ ሐሳብህ የሚከፋፈል ከሆነ ከሚተላለፈው ትምህርት አብዛኛው ያመልጥሃል።

‘በውስጥህ የሚያስጨንቅህ’ ነገር ኖሮ ሐሳብህን ሰብስበህ ፕሮግራሙን መከታተል ከተቸገርህ ይሖዋ በጥሞና ለመከታተል የሚያስችል የአእምሮና የልብ መረጋጋት እንዲሰጥህ ጸልይ። (መዝ. 94:​19 አ.መ.ት ፤ ፊልጵ. 4:​6, 7) ካስፈለገም ደጋግመህ ጸልይ። (ማቴ. 7:​7, 8) የጉባኤ ስብሰባዎች ይሖዋ ለእኛ ያደረገልን ዝግጅቶች ስለሆኑ ከእነዚህ ስብሰባዎች እንድትጠቀም እንደሚፈልግ አትጠራጠር።​—⁠1 ዮሐ. 5:​14, 15

ንግግር ሲሰጥ ማዳመጥ

እስከ ዛሬ ከሰማሃቸው የተለያዩ ንግግሮች ውስጥ የምታስታውሳቸው ደስ የሚሉህ ነጥቦች እንደሚኖሩ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከአንድ ንግግር የማረኩህን ነጥቦች ስላስታወስህ ብቻ ጥሩ አዳምጠሃል ማለት አይቻልም። ንግግር ከረጅም ጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በመንገድህ ላይ ደስ የሚሉ ነገሮች ልታይ ብትችልም ዋናው የጉዞህ ዓላማ ያሰብክበት ቦታ መድረስ ነው። ተናጋሪውም አድማጮቹ ወደ አንድ መደምደሚያ እንዲደርሱ ለመርዳት ወይም አንድ እርምጃ እንዲወስዱ ለማነሳሳት እየሞከረ ይሆናል።

በኢያሱ 24:​1-15 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ኢያሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ንግግር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የንግግሩ ዓላማ ሕዝቡ በዙሪያቸው ከነበሩት ብሔራት የጣዖት አምልኮ ሙሉ በሙሉ ርቀው ከእውነተኛው አምልኮ ጎን እንዲሰለፉ ማነሳሳት ነበር። ይህ ጉዳይ ያንን ያህል አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? የሐሰት አምልኮ መስፋፋት ብሔሩ ከይሖዋ ጋር የነበረውን ጥሩ ዝምድና አደጋ ላይ የሚጥል ስለነበረ ነው። ሕዝቡም “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ . . . እግዚአብሔርን እናመልካለን” በማለት ለኢያሱ ንግግር ምላሽ ሰጥተዋል። ደግሞም እንዳሉት አድርገዋል!​—⁠ኢያሱ 24:16, 18, 31

አንድን ንግግር ስታዳምጥ የንግግሩን ዓላማ ለመረዳት ሞክር። ተናጋሪው የሚዘረዝራቸው ነጥቦች የንግግሩን ዓላማ ዳር ለማድረስ የሚያበረክቱት ድርሻ ምን እንደሆነ አስብ። ይህ ትምህርት ምን እንዳደርግ ይጠይቅብኛል? እያልክ ራስህን ጠይቅ።

ውይይት ሲደረግ ማዳመጥ

የመጠበቂያ ግንብ ጥናትና የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት የሚመራው እንዲሁም አንዳንድ የአገልግሎት ስብሰባ ክፍሎች የሚቀርቡት በጥያቄና መልስ ነው።

በጥያቄና መልስ የሚደረግን ውይይት ማዳመጥ ከሰዎች ጋር ከመወያየት ጋር የሚመሳሰልበት ሁኔታ አለ። ሙሉ ጥቅም ማግኘት እንድትችል በጥሞና አዳምጥ። የውይይቱ አካሄድ እንዴት እንደሆነ አስተውል። የጥናቱ መሪ ጭብጡና ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። ጥያቄ ሲጠይቅ መልሱ ምን እንደሆነ አስብ። ሌሎች ነጥቡን ሲያብራሩና እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ሲገልጹ አዳምጥ። ነጥቡን እንዴት እንደተረዱት ማስተዋልህ በፊት ስለምታውቀው ርዕሰ ጉዳይም ቢሆን አዲስ ግንዛቤ ይጨምርልሃል። አንተም እምነትህን የሚገልጽ ሐሳብ በመስጠት ውይይቱ ይበልጥ እንዲዳብር የበኩልህን አስተዋጽኦ ማድረግ ትችላለህ።​—⁠ሮሜ 1:​12

ትምህርቱን አስቀድመህ መዘጋጀትህ ውይይቱን በጥሞና ለመከታተልና ሌሎች የሚሰጡትንም አስተያየት ከልብ ለማዳመጥ ይረዳሃል። የሚጠናውን ጽሑፍ ቀደም ብለህ በጥልቀት ለመዘጋጀት ባይመችህ እንኳ ከስብሰባው በፊት ቢያንስ የትምህርቱን አጠቃላይ ይዘት በአጭሩ ለማየት ሞክር። ይህን ማድረግህ ከውይይቱ የተሻለ ጥቅም እንድታገኝ ያስችልሃል።

በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ማዳመጥ

ከጉባኤ ስብሰባዎች ይልቅ በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ብዙ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮች ይኖራሉ። ይህም በጥሞና ማዳመጥን ይበልጥ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል። ይህን ችግር ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?

ሌሊት ጥሩ እንቅልፍ መተኛት በጣም ወሳኝ ነው። በእያንዳንዱ ዕለት ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ስለ ጭብጡ አስብ። የእያንዳንዱን ንግግር ርዕስ እያየህ በዚያ ንግግር አማካኝነት ምን ትምህርት ሊቀርብ እንደሚችል ለመገመት ሞክር። ጥቅስ ሲነበብ መጽሐፍ ቅዱስህን እያወጣህ ተከታተል። ብዙዎች ዋና ዋና ነጥቦችን በአጭሩ በማስታወሻ ማስፈር ፕሮግራሙን በትኩረት እንዲከታተሉ እንደሚረዳቸው ይናገራሉ። በግል ሕይወትህም ይሁን በአገልግሎትህ ልትሠራባቸው የምትፈልጋቸውን ነጥቦች በማስታወሻህ ያዝ። በየዕለቱ ወደ ስብሰባው ቦታ ስትሄድና ወደ ቤትህ ስትመለስ አንዳንድ ነጥቦችን አንስተህ ከሌሎች ጋር ተወያይ። ይህም ትምህርቱን እንዳትረሳው ይረዳሃል።

ልጆች እንዲያዳምጡ ማሰልጠን

ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን፣ ሕፃናት የሆኑትን እንኳ ሳይቀር በጉባኤ ስብሰባና በተለያዩ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ አብረዋቸው እንዲገኙ በማድረግ ‘መዳን የሚገኝበትን ጥበብ’ እንዲቀስሙ ሊያግዟቸው ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:​15) ልጆች ዝንባሌያቸውም ሆነ አንድን ነገር በትኩረት የመከታተል ችሎታቸው ስለሚለያይ እነርሱን በጥሞና እንዲያዳምጡ መርዳት ማስተዋል ይጠይቃል። ቀጥሎ የቀረቡት ሐሳቦች በዚህ ረገድ ሊረዱህ ይችላሉ።

ቤትህ በምትሆንበት ጊዜ ትናንሽ ልጆችህ በፀጥታ ተቀምጠው እንዲያነቡ ወይም በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ የሚገኙትን ሥዕሎች እንዲመለከቱ አድርግ። በስብሰባዎች ላይ ልጆች አርፈው እንዲቀመጡ ብለህ በአሻንጉሊቶች እንዲጫወቱ ማድረግ የለብህም። ጥንት በእስራኤል ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ልጆች ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ‘እንዲሰሙና እንዲማሩ’ ነው። (ዘዳ. 31:12) አንዳንድ ወላጆች ሕፃናት ልጆቻቸው ሳይቀሩ የሚጠናው ጽሑፍ የግል ቅጂ እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። ልጆቹ ትንሽ ከፍ እያሉ ሲሄዱ ደግሞ በጉባኤ መሳተፍ የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርጉ እርዳቸው።

ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋን ማዳመጥና እርሱን መታዘዝ የተሳሰሩ ነገሮች መሆናቸውን ይገልጻሉ። ሙሴ ለእስራኤል ብሔር ከተናገራቸው ቃላት ይህንን መረዳት ይቻላል። ‘በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን አስቀምጫለሁ። ሕይወትን ምረጥ። አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።’ (ዘዳ. 30:19, 20) የአምላክን ሞገስና የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው ዛሬ ይሖዋ የሚሰጠውን ትምህርት በማዳመጣችንና በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረጋችን ላይ ነው። እንግዲያው ኢየሱስ “እንዴት እንደምታዳምጡ በጥንቃቄ አስቡ” ሲል የሰጠውን ምክር ልብ ማለታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!​—⁠ሉቃስ 8:​18 NW 

በጥሞና ለማዳመጥ የሚረዱ ነጥቦች

  • ሐሳብህን ሰብስበህ ፕሮግራሙን መከታተል እንድትችል ጸልይ

  • ተናጋሪውን ተመልከት

  • ጥቅሶች ሲጠቀሱ መጽሐፍ ቅዱስህን አውጥተህ ተከታተል

  • የንግግሩ ዓላማ ምን እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር

  • ጥያቄ ሲጠየቅ መልሱ ምን እንደሆነ አስብ፤ ሌሎች የሚሰጡትንም መልስ በጥሞና አዳምጥ

  • አጠር አጠር ያሉ ሐሳቦችን በማስታወሻ ያዝ

  • በግልህ ልትሠራባቸው የምትፈልጋቸውን ነጥቦች ማስታወሻህ ላይ አስፍር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ