‘በማዳመጥ ተጨማሪ ትምህርት ቅሰሙ’
1 የምሳሌ መጽሐፍ ጥበብ የሚከተለውን ጥሪ እንደምታሰማ ይገልጻል:- “የከበረች ነገርን እናገራለሁና ስሙ፤ ከንፈሮቼም ቅን ነገርን ለመናገር ይከፈታሉ። ምክርና መልካም ጥበብ የእኔ ነው፤ . . . ስሙኝ፤ መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው። እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና፣ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛልና።” (ምሳሌ 8:6, 14, 32, 35) እነዚህ ቃላት “የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የሚጠብቀንን ትምህርት ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ።
2 የአውራጃ ስብሰባው የተዘጋጀው የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር የሚያስፈልገው ነገር ተገምግሞ ይህንኑ ፍላጎት ለማሟላት በሚያስችል መንገድ ነው። የሚቀርበው መንፈሳዊ ትምህርትና የሚሰጡት ተግባራዊ ሐሳቦች በሥራ የምንተረጉማቸው ከሆነ ደስተኞች እንድንሆን፣ ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ጥሩ ወዳጅነት ጠብቀን እንድንኖርና ወደ ሕይወት በሚያመራው መንገድ ጸንተን እንድንኖር ሊረዱን ይችላሉ። በእርግጥም ‘የምናዳምጥበትና ተጨማሪ ትምህርት የምንቀስምበት’ በቂ ምክንያት አለን።—ምሳሌ 1:5
3 ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት:- ከሚቀርበው ትምህርት ሙሉ ጥቅም ለማግኘት እንዲቻል ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ቦታችን ላይ መገኘትና ለሚቀርበው ትምህርት አእምሮአችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል። ይህ በጥሩ ሁኔታ መደራጀትን የሚጠይቅ ነው። ይህን ለማድረግ ቁልፉ በማለዳ መነሳት ነው። በዋዜማው ማታ ቶሎ ተኙ። አብረዋችሁ የሚሄዱት በሙሉ ለመዘጋጀትና ለመመገብ በቂ ጊዜ ማግኘት እንዲችሉ በማለዳ ተነሱ። መቀመጫ እንድታገኙና ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማጠናቀቅ እንድትችሉ የአውራጃ ስብሰባው ወደሚደረግበት ቦታ ቀደም ብላችሁ ድረሱ። በር የሚከፈተው 2:00 ላይ ሲሆን ፕሮግራሙ በእያንዳንዱ ዕለት 3:30 ላይ ይጀመራል።
4 የምንሰበሰብበት ዋነኛ ዓላማ ይሖዋን ‘በማኅበር መካከል’ ማወደስ ስለሆነ እያንዳንዱ የፕሮግራሙ ክፍለ ጊዜ አምላካችንን ከፍ ከፍ በሚያደርግ መንገድ መጀመር ይኖርበታል። (መዝ. 26:12) ይህን ለማድረግ ሲባል የመክፈቻው መዝሙር ከመጀመሩ በፊት ሁሉም መቀመጫቸውን እንዲይዙ ይጠየቃሉ። እንዲህ የሚደረገው “ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን” ከሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማሳሰቢያ ጋር ለመስማማት ነው። (1 ቆሮ. 14:40) ይህ ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም አለው? ሙዚቃው ጀምሮ ሊቀ መንበሩ መድረክ ላይ ተቀምጦ ስታዩ ፈጥናችሁ ወንበራችሁን ያዙ። እንዲህ ማድረጋችሁ በእያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ መጀመሪያ ላይ የሚዘመረውን መዝሙር ከልብ በመዘመር ይሖዋን ለማወደስ ያስችላችኋል።—መዝ. 149:1
5 ፕሮግራሙ ከጀመረ በኋላ:- ዕዝራ “የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ . . . ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።” (ዕዝራ 7:10) ይሖዋ ያዘጋጀልንን ትምህርት ለመቅሰም ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? በሚታደላችሁ ፕሮግራም ላይ የተዘረዘሩትን የተለያዩ የንግግር ርዕሶች ስትመለከቱ ‘ይሖዋ በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት ምን እየነገረኝ ነው? በማገኘው እውቀት ራሴንም ሆነ ቤተሰቤን መጥቀም የምችለው እንዴት ነው?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። (ኢሳ. 30:21፤ ኤፌ. 5:17) የአውራጃው ስብሰባ እስኪጠናቀቅ ድረስ ራሳችሁን እነዚህን ጥያቄዎች ጠይቁ። ልትሠሩባቸው ያሰባችኋቸውን ነጥቦች በማስታወሻችሁ ላይ አስፍሩ። ነጥቦቹን የእያንዳንዱ ዕለት ስብሰባ ካበቃ በኋላ ተወያዩባቸው። እንዲህ ማድረጋችሁ እውቀቱን በውስጣችሁ ለመቅረጽና በሥራ ለማዋል ይረዳችኋል።
6 አንዳንድ ጊዜ ለረጅም ሰዓት ትኩረትን መሰብሰብ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። አእምሯችን እንዳይባዝን ለመከላከል ምን ሊረዳን ይችላል? ዓይን ያለውን ችሎታ በጥሩ ሁኔታ ተጠቀሙበት። በአብዛኛው ትኩረታችንን የሚቆጣጠረው ዓይናችን ያረፈበት ነገር ነው። (ማቴ. 6:22) ስለዚህ ድምፅ ወደሰማችሁበት ወይም የሚንቀሳቀስ ነገር ወዳለበት ዞር እንድትሉ የሚገጥማችሁን ፈተና ተቋቋሙ። ዓይናችሁ በተናገሪው ላይ እንዲያተኩር አድርጉ። ጥቅስ በሚነበብበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን አውጥታችሁ ተከታተሉ፤ እንዲሁም ጥቅሱ በሚብራራበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን እንደገለጣችሁ ቆዩ።
7 ክርስቲያናዊ ፍቅር ስብሰባው እየተካሄደ ሌሎችን የሚረብሽ ነገር ከማድረግ እንድንቆጠብ ይገፋፋናል። (1 ቆሮ. 13:5) ይህ ‘ዝም ብለን የምናዳምጥበት ጊዜ’ ነው። (መክ. 3:7) ስለሆነም የማያስፈልግ ወሬና እንቅስቃሴ ከማድረግ ተቆጠቡ። አስቀድማችሁ በመጠናቀቅ ወደ መጸዳጃ ቤት የምትመላለሱበትን ጊዜ ቀንሱ። ከባድ የጤና ችግር ከሌለባችሁ በቀር ለመብላት የተመደበው ጊዜ እስኪደርስ ስብሰባው እየተካሄደ ምንም ነገር አትብሉ ወይም አትጠጡ። ሞባይል ቴሌፎን፣ ፔጀር፣ የቪዲዮ መቅረጫ እንዲሁም ካሜራ ይዘው የሚመጡ ወንድሞችና እህቶች የሌሎችን ትኩረት በሚከፋፍል መልኩ እነዚህን መሣሪያዎች መጠቀም አይገባቸውም። ወላጆች በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆቻቸውን ጨምሮ ከመላው ቤተሰባቸው ጋር ለመቀመጥ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው። ይህም ልጆቻቸውን በተገቢው ሁኔታ ለመቆጣጠር ያስችላቸዋል።—ምሳሌ 29:15
8 ለብዙ አሥርተ ዓመታት በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የተገኘ አንድ ሽማግሌ ባለፈው ዓመት ያስተዋለውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ይህንን የአውራጃ ስብሰባ ልዩ ያደረገው አንድ ነገር እንዳለ ይሰማኛል። ትናንሽ ልጆችን ጨምሮ እያንዳንዱ ሰው ማለት ይቻላል ማስታወሻ ይይዝ ነበር። ይህን ማየት በጣም የሚያስደስት ነበር። ተናጋሪዎች ጥቅስ ሲጠቅሱ አውጥተው በመከታተል መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በጥሩ ሁኔታ ይጠቀሙባቸው ነበር።” እንዲህ ያለው በጥሞና የማዳመጥ ልማድ በእርግጥ የሚያስመሰግን ነው። እኛንም ሆነ በአውራጃ ስብሰባው ላይ የተገኙትን የሚጠቅም ከመሆኑም ሌላ ታላቁ አስተማሪያችን የሆነውን ይሖዋ አምላክን ያስከብራል።—ኢሳ. 30:20